የቡና ዘርፍ ችግሮችን ለመፍታት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የውሳኔ ሐሳብ ቀረበ

Image result for ቡናበቡና ልማትና ግብይት ዘርፍ የተንሰራፋውን ችግር ለመፍታት መሠረታዊ የመዋቅር ለውጥ ያመጣል የተባለ የውሳኔ ሐሳብ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀረበ፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበለትን የውሳኔ ሐሳብ መነሻ በማድረግ ዕርምጃዎች መውሰድ መጀመሩ ታውቋል፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከወሰዳቸው ዕርምጃዎች መካከል የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የተቋቋመበትን ካፒታል አሳድጓል፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣን ተጠሪነቱ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ወደ ንግድ ሚኒስቴር እንዲዛወርም አድርጓል፡፡
የፌዴራል መንግሥት አገሪቱ ከውጭ ንግድ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ ዕቅዶች ቢያወጣም፣ አገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘው ገቢ ግን እየቀነሰ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በተለይ ከአንድ መቶ ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያስገኙ ዘርፎች ላይ የተጋረጠውን እንቅፋት የማስወገድ ኃላፊነት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ለሚገኘው የኢኮኖሚ ዕቅድ ውጤታማነት ክፍል ተሰጥቷል፡፡
የኢኮኖሚ ዕቅድ ውጤታማነት ዘርፍ አስተባባሪ አርከበ ዕቁባይ (ዶ/ር) ከመቶ ሚሊዮን ዶላር ዓመታዊ ገቢ የሚያስገኙ ስድስት የኤክስፖርት ዘርፎችን በመለየት ለእያንዳንዳቸው ከመንግሥት፣ ከግልና ከማኅበራት የተውጣጡ 20 አባላት ያሉት ኮሚቴ በማቋቋም ጥናት እንዲካሄድ በማድረግ፣ በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ግብይት ባለሥልጣን አማካይነት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የውሳኔ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡  
የመጀመሪያው ትኩረት ያገኘው ዘርፍ አገሪቱ ከምታስገባው የውጭ ምንዛሪ 26 በመቶ ድርሻ ያለውና በብዙ መሰናክሎች ውስጥ የሚገኘው ቡና ነው፡፡
በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለሥልጣን ባለቤትነት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የኢኮኖሚ ዕቅድ ውጤታማነት ክፍል አስተባባሪነት የተዘጋጀው ዝርዝር የውሳኔ ሐሳብ ሰሞኑን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡
የውሳኔ ሐሳቡ ሰነድ በዋናነት ያቀረበውን ትንታኔ እንደሚያብራራው፣ የቡና ዘርፍ የግብይት ሥርዓቱ እጅግ የተንዛዛና ብዙ ተዋንያን በጥቂት ምርት ላይ የሚርመሰመሱበት፣ የግብይት ሒደቱ ለከፍተኛ ወጪና ረዥም ጊዜ ለሚወስድ አሠራር የተጋለጠ፣ በዓለም እያደገ የመጣውን የምርት ጥራት ማረጋገጥ ያልቻለ፣ የምርት ዱካና ምርቱን በቀጣይነት የማግኘት ዕድል የዘጋ፣ የተሻለ ዋጋ የሚከፍሉ ገበያዎችን መጠቀም ያልቻለ፣ በግብይት ተዋንያን ዘንድ መተማመን እንዳይኖር ያደረገ፣ ለሕገወጥ ንግድ ተጋላጭ የሆነ፣ በዚህም ሳቢያ አገሪቱ ማግኘት ያለባትን የውጭ ምንዛሪ እንዳታገኝ ያደረገ ነው፡፡  
ሰነዱ ጨምሮ የቡና ምርትና ምርታማነት ዕድገት ዘገምተኛ መሆኑን፣ የአገልግሎት የጥራት ችግር ያለበት መሆኑንም አብራርቷል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ምርት ገበያ፣ የመጋዘን አገልግሎት ድርጅቶችና የምርት ገበያ ባለሥልጣን ጠንካራና ጎናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በውጤታማነት፣ በቅልጥፍና፣ በግልጽነት መርህ ላይ ተመሥርተው የደንበኞችን ተጠቃሚነትና እርካታ እያረጋገጡ በኤክስፖርት ዕድገትና በሚያስገኘው የውጭ ምንዛሪ ግኝት እየተቃኙ መመራት አልቻሉም፤›› ሲል ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ሰነድ ገልጿል፡፡ እነዚህ ማነቆዎች እንዲፈጠሩ፣ ዘርፉ በተበታተኑና ያልተቀናጁ አደረጃጀትና አሠራር ሲመራ መቆየቱ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ ማድረጉን ሰነዱ ጨምሮ አብራርቷል፡፡
ከቀረቡት ማሻሻያ ሐሳቦች መካከል የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በአገናኝ አባላት አማካይነት መገበያየት ግዴታ ማድረጉ አግባብ ባለመሆኑ እንዲሻሻል ተደርጓል፡፡ በዚህም መሠረት አቅም ያላቸው አቅራቢዎችም ሆኑ ላኪዎች የራሳቸውን ቡና ራሳቸው እንዲገበያዩ ማድረግ፣ ምርት ገበያ የአገናኝ አባላትን አገልግሎት አሠራሩን ለሚፈልጉ ብቻ ማመቻቸት እንደሚኖርበት የውሳኔ ሐሳብ ቀርቧል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በምርት ገበያ የአቅርቦት ቡና የጥራት ደረጃ ከአንድ እስከ ዘጠኝ የነበረው አሠራር እንዲሻሻልና ደረጃውም ከአንድ እስከ አምስት ብቻ እንዲሆን ሐሳብ ቀርቧል፡፡ በመጋዘን አገልግሎት ድርጅት የምርት አያያዝ ችግር ያለበት በመሆኑ ይኼንን ችግር ለማስወገድ የጥራት ደረጃ አሠጣጥ በሰርቪላንስ ካሜራ እንዲታገዝና በመኪና ላይ ሽያጭ እንዲካሄድ ሐሳብም ቀርቧል፡፡ ይህም በማራገፍና በመጫን፣ ከመጋዘን አያያዝ ጋር የሚያያዙ የጥራት ችግሮችን ማስወገድ እንደሚያስችል ታምኖበታል፡፡ በአደረጃጀት በኩል ያለውን ችግር ለመፍታት ራሱን የቻለ ሥልጣን የነበረው የመጋዘን አገልግሎት ድርጅት ከምርት ገበያ ጋር እንዲዋሀድ የውሳኔ ሐሳብ ቀርቧል፡፡
የተለይ በገበያ አገናኝ አባላት ሆን ብለው የቡና አቅርቦት እንዲዛባ እያደረጉ በመሆኑ፣ በምርት ገበያው የአገናኝ አባላት ተፅዕኖ ለመቀነስ አቅም ያላቸው ነባርና አዲስ ላኪዎችና አቅራቢዎች በራሳቸው እንዲገበያዩ ማድረግ፣ አቅም ያላቸውን አቅራቢዎች ወደ ላኪነት ማሸጋገር፣ አቅራቢዎች ከላኪዎች ጋር በትስስር እንዲሠሩ የሚፈቅድ አሠራር ቀደም ሲል ያልነበረ በመሆኑ በአዲሱ የውሳኔ ሐሳብ ሰነድ ላይ እንዲፈቀድ ሐሳብ ቀርቧል፡፡
በምርምር በኩል ያለውን ችግር ለመፍታት ጅማ የሚገኘው ምርምር ማዕከል የቡና፣ የሻይና የቅመማ ቅመም የምርምር ሥራዎችን አካትቶ እንዲሠራና ‹‹የኢትዮጵያ የቡና ምርምር ኢንስቲትዩት›› ሆኖ እንዲደራጅ፣ ተጠሪነቱም ለኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለሥልጣን እንዲሆን የውሳኔ ሐሳብ ቀርቧል፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበለትን የውሳኔ ሐሳብ እየተመለከተ ዕርምጃ መወሰድ ጀምሯል፡፡ በቅርቡ ተሰብስቦ የምርት ገበያ ባለሥልጣን ተጠሪነቱ ለንግድ ሚኒስቴር እንዲሆን፣ የተቀሩት በቡና ዘርፍ ከምርት እስከ ግብይት ድረስ የሚሠሩ መንግሥታዊ ተቋማት በቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለሥልጣን ሥር እንዲሆኑ ወስኗል፡፡  በዚህ ጉዳይ ላይ ሪፖርተር የምርት ገበያ ባለሥልጣንና የቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለሥልጣንን አስተያየት ለማካተት ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡  

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር