በበጀት አመቱ በዘጠኝ ወራት ወደ ውጭ በብዛት ከተላኩት ሲዳማ ቡና 32.1% በመያዝ ትልቁን ድርሻ ይዟል

በዘጠኝ ወሩ ወደ ውጭ ከተላከ የቡና ፣የቅመማቅመምና የሻይ ቅጠል ምርቶች 560 ሚሊየን ዶላር ማግኘት ተችሏል


በበጀት  አመቱ  ዘጠኝ   ወራት    ከቡና ፣ከቅመማ ቅመምና   ከሻይ  ቅጠል  ምርቶች  148 ሺ 227 ነጥብ  2  ቶን ተልኮ  560 ሚሊየን  ዶላር  ማግኘት  መቻሉን  የኢትዮጵያ   ቡናና  ሻይ  ልማትና   ግብይት   ባለስልጣን አስታወቀ፡፡ 
የባለስልጣኑ  የገበያ   ልማትና   ፕሮሞሽን    ዳይሬክተር   አቶ   ዳሳ ዳኒሶ   ለኢዜአ  እንደተናገሩት  ባለስልጣኑ  17 ሺ 354 ነጥብ 72  ቶን  በመላክ  649 ሚሊየን   ዶላር  ለማግኝት አቅዶ ነበር፡፡
ባለስልጣኑ ካቀደው   በመጠን 85.55  በመቶው ከገቢ ደግሞ 86.3 በመቶውን  ማሳካት  ችሏል፡፡
አፈጻጸሙ   ከባለፈው  አመት   ተመሳሳይ  ወቅት   ጋር   ሲነጻጸር   በመጠን  4.5%  በገቢ 15%  ጭማሪ   ማሳየቱም  ተገልጿል፡፡ 
ወደ  ውጭ   ከተላከ   139 ሺ 887  ቶን   የቡና  ምርት  ብቻ  545 ሚሊየን    ዶላር  ገቢ  ማግኘት   መቻሉን  የገለጹት  ዳይሬክተሩ  የእቅዱን   በመጠን  88.12 % ና  በገቢ 87.91 %  መሳካት  መቻሉን   ተናግረዋል፡፡
በበጀት   አመቱ   በዘጠኝ   ወራት  ወደ ውጭ   በብዛት ከተላኩት ሲዳማ ቡና 32.1% በመያዝ ትልቁን ድርሻ ሲይዝ  በመቀጠል የነቀምት ፣፣ የጅማ፣ የሀረር፣ የይርጋ ጨፌና  እና  የሊሙ ቡና በየደረጃቸው መላካቸውን   ከባለስልጣኑ ያገኘነው  መረጃ ያመለክታል፡፡
የኢትዮጵያ  ቡና  መዳረሻ  ሀገራት  59  ሲሆኑ   ሳውዳረቢያ 17.72 % ጀርመን  17.41፣ ጃፓን 10.25፣  ቤልጂየም 8.44%ና አሜሪካ 7.62%  በመያዝ  ቀዳሚውን  ቦታ  የያዙ እንደነበርም  ታዉቋል፡፡
ዘንድሮ ከባለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር   የተሻለ  ምርት   የተገኘበት  ሲሆን   ለገበያ  የቀረበውም በተመሳሳይ  የተሻለ ነው ተብሏል ፡፡ 
የዘጠኝ  ወሩን  እቅድ   ለምን   መቶ  በመቶ  ማሳካት  አልተቻለም   በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ  በአንደኛና  በሁለተኛ ሩብ  አመት  ለገበያ የሚቀርበው  የባለፈው   አመት  ምርት  በመሆኑና  በሚፈለገው መጠንም ማግኘት ባለመቻሉ ነው ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡ 
ባለስልጣኑ  በበጀት   አመቱ   241  ሺ  ቶን  ቡና  ወደ  ውጭ   በመላክ  941 ሚሊየን  የአሜሪካን  ዶላር  አቅዶ  እየሰራ መሆኑም   ታውቋል፡፡
በቀሪዎቹ  ሶስት ወራት  የቡና ምርት  ለገበያ   የተሻለ  የሚቀርብበት በመሆኑ  የአመቱን  እቅድ    ለማሳካት እንደሚቻልም  ተመላክቷል፡፡
ምንጭ፦ ኢዜኣ

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር