POWr Social Media Icons

Tuesday, July 26, 2016

ከጢልቴ ዱሜ ግርጌ
በእንዳለ ደበላ ሀዋሳ ኢዜአ
“ተረግዞ ለመወለድ ያለ ተጨማሪ ቀናት ዘጠኝ ድፍን ወራት ብቻ የፈጀበት በርካቶችን ያስደመመ ልጅ  በሀዋሳ ተወልዷል”  አሉኝ አንድ በእድሜ የገፉ አዛውንት፡፡
እንዴ ታዲያ እርግዝና እኮ ዘጠኝ ወር ነው የሚፈጀው በዘጠኝ ወር መወለድ ያስደመመበት ምክንያት አልገባኝም አልኳቸው፡፡
“አይ ልጄ አሉኝ በቅዱስ መጽሀፉ የሰፈረውን እንኳን ብናይ ማርያም እየሱስ ክርስቶስን የወለደችው ከዘጠኝ ወር ከዘጠኝ ቀናት እርግዝና በኋላ ነው” አሉኝ፡፡
“እናቶችን ብትጠይቅ ልጆቻቸውን ለመውለድ ከዘጠኝ ድፍን ወራት ተጨማሪ ቢያንስ ዘጠኝ ቀናት ይኖራል ፡፡ ይህ ልጅ ግን ዘጠኝ ድፍን ወር ብቻ የተረገዘ ነው ፡፡ ያለ ተጨማሪ ቀናት ተወለደ ”፡፡
 በቅርቡ ወንድ ልጅ ያስታቀፈችኝ ውዷ ባለቤቴ ልጁን የተገላገለችው አስር ወር ከሰባት ቀን መሆኑን ትውስ አለኝና የአዛውንቱን ወግ ማድመጥ ቀጠልኩ፡፡
አቶ ታደሰ ባላ ከሀዋሳ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኝ የሸበዲኖ ወረዳ ማዕከል በሆነችው ለኩ እንደተወለዱና በተለምዶ እርሻ ጣቢያ እየተባለ በሚጠራው የመንግስት እርሻ ድርጅት ተቀጥረው ሲሰሩ ቆይተው ጡረታ ከወጡ 12 ዓመት እንደሆናቸው አወጉኝ፡፡
“ዛሬ በዘጠኝ ወሩ የተወለደውን ልጅ ለማየት መጣሁ እናም በእድሜዬ እንደዛሬው ተደምሜ አላውቅም” ባይ ናቸው ፡፡
“እንዲህ ፈጥኖ ይሆናል ብዬ በፍጹም አልጠበቅሁም ነበር ፡፡ ግን ሆኖ ሳየው አስደመመኝ ፡፡ በዚች ከተማ ባልወለድባትም የስራን ሀሁ የጀመርኩባት ናት”፡፡
“ከ40 አመት በላይ የኖርኩባት በመሆኑ በዚህ መልክ በአጭር ጊዜ የሆነ ታምር ገጥሞኝ አያውቅም” ብለው ከታሪክ ያወቁትን የሀዋሳን አመሰራረት አጫወቱኝ፡፡
እሳቸው ያወጉኝን በከተማዋ ታሪክ ዙሪያ በዘለቀ ከበደና ሰርካለም አለማየሁ ‘History of Awassa’ በሚል ርዕስ ሀምሌ 1999 ዓ/ም ከታተመው መጽሀፍ ያገኘሁትን የሀዋሳ ከተማን አመሰራረት በጥቂቱ ላውጋችሁ፡፡ 
በ1949 ዓ/ም የሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት ገዥ የነበሩት ራስ መንገሻ ስዩም በአካባቢው ከተማ እንዲመሰርቱ በንጉሰ ነገስቱ ታዘዙ፡፡
ራስ መንገሻ ስዩም ትዕዛዙን ተቀብለው በጣሊያን መሀንዲሶች የሚመራ ሰባት ባለሙያዎች ያሉት ከተማዋ የምትመሰረትበትን ማስተር ፕላን የሚያዘጋጅ አንድ ቡድን አቋቋሙ፡፡
ሰፋፊ የእርሻ ቦታዎች ያሏት የቱሪስትና ኢንደስትሪ ማዕከል(በተለይ የአግሮ ኢንደስትሪ) የምትሆን ከተማ ለመመስረት ታቅዶ የማስተር ፕላን ስራ ተጀመረ፡፡
ከማስተር ፕላን ስራው ጎን ለጎን ከከተማዋ በስድስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሎቄ ቀበሌ ለመዝናኛና ጊዜያዊ ማረፊያ እንዲሆናቸው ቤተ መንግስት ተገንብቶ በ1951 ዓ/ም ተመረቀ፡፡
በ1952 ዓ/ም የከተማዋ ማስተር ፕላን ስራ ተጠናቀቀ  ፡፡ ይህን ተከትሎ የሀዋሳ ከተማ እንድትመሰረትና የአቤላ ወረዳ ጽህፈት ቤት ወደ ሀዋሳ እንዲዛወር ተደርጎ  ከተማዋ በ48 ጋሻ መሬት ላይ ተመሰረተች፡፡
ቀጣዩ ስራ ነዋሪዎችን ማስፈር በመሆኑ በወቅቱ የማህበረሰብ ልማት ሚኒስትር የነበሩት ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ አዲሷን ከተማ የሚመሰርቱ ነዋሪዎችን የማስፈር ኃላፊነት ተሰጣቸው፡፡
ጄኔራሉም  ከ1928 እስከ 1933 ዓ/ም በጣሊያን ወረራ ወቅት ሲፋለሙ የነበሩ 404 አባት ጡረተኞችን ከአዲስ አበባ ሐረር ፣ውቅሮና ኮረም መልምለው ወደ ስፍራው አመጡ፡፡
በወር 20 ብር የጡረታ አበል ተቆርጦላቸውና ለእርሻና ለመኖሪያ ቤት መስሪያ 1 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ተሰጥቷቸው የመጀመሪያዎቹ የሀዋሳ ከተማ 28 የቆርቆሮ ቤቶች በ1953 ዓ/ም በአባት ጡረተኞቹ ተገነቡ፡፡
እነዛ አባት ጡረተኞች የመሰረቷቸው የከተማዋ አራት መንደሮች መጠሪያ ስማቸውን ከመጡበት ስፍራ ወርሰው ውቅሮ አዲስ አበባ ኮረምና ሐረር ቀበሌ እየተባሉ እስከ ዛሬ ድረስ ይጠሩበታል፡፡ 
ይህን ተከትሎ ለንግድ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት በሀይቁ ዳርቻ ጊዜያዊ ማረፊያ በመስራት ቆይታ ያደርጉ የነበሩ ነጋዴዎች ቋሚ መኖሪያና ንግድ ቤት መስራት ቻሉ፡፡
የመንግስትና የግል የእርሻ ድርጅቶች፣ የዕምነት፣ የትምህርትና የጤና ተቋማት ተገንብተው ስራ ጀመሩ፡፡
ቀስ በቀስ እንቁላል…. እንዲሉ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በርካታ ሰዎች እየመጡ ኑሯቸውን በከተማዋ መሰረቱ፡፡
 እየጨመረ የመጣውን የነዋሪ ቁጥር ያስተዋሉ በዲላ ከተማ በንግድ ስራ ተሰማርተው የነበሩ አረቦች ወደ ሀዋሳ በመምጣት ንግድ ቤቶችን ከፈቱ ፡፡ የዛሬው አረብ ሰፈር ስያሜውን ያገኘውም ከዚህ ነው ፡፡
በዚህ መልኩ የተመሰረተችው የሀዋሳ ከተማ በዋናነት የኢንደስትሪ መንደር እንድትሆን ታስቦ ብትቆረቆርም ከበቆሎ እርሻነት ባለፈ አንድ የጨርቃ ጨርቅ አንድ ሴራሚክና አንድ ዱቄት ፋብሪካ ውጪ ምንም ሳይኖራት ለአመታት ቆይታለች፡፡
ዛሬ ይህ ታሪክ የሆነበትና በከተማዋ ነዋሪዎች ዘንድ ይሆናል ተብሎ ያልታሰበ ግርምትን ያጫረ ትልቅ የኢንደስትሪ ፓርክ ባለቤት መሆን ችላለች፡፡
ይህ የኢንደስትሪ ፓርክ ግንባታ ለመጠናቀቅ የወሰደበት ጊዜ ድፍን ዘጠኝ ወር ብቻ መሆኑ ነበር አቶ ታደሰን ያስደመመው፡፡
“አንዲት እናት ልጅ ለመውለድ ከዘጠኝ ድፍን ወራት ባለፈ ቢያንስ ዘጠኝ ተጨማሪ ቀናት የእርግዝና ጊዜያት ያስፈልጓታል ፡፡ይህ ልጅ ግን ዘጠኝ ወር ብቻ መፍጀቱ አስደምሞኛል” ያሉት ለዚህ ነበር፡፡
ከቻይናው የግንባታ ተቋራጭ በርካታ ልንማራቸው የሚገቡ ጉዳዮች መኖራቸውን አቶ ታደሰ ይናገራሉ፡፡
በሀገራችን ተቋራጮች በርካታ የመንገድና ሌሎች ተቋማት ግንባታዎች እየተከናወኑ ነው  ነገርግን በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ሲጠናቀቁ አይስተዋልም ፡፡ አብዛኞቹ ተጀምረው ለአመታት ባሉበት ቆመው ይታያሉ ነው ያሉት ፡፡
ይህ የሀዋሳ ኢንደስትሪ ፓርክ ከሌሎቹ ልዩ የሚያደርገው በርካታ ነገሮች አሉት ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ከብክለት ነጻ በሆነ መልኩ የተገነባው የፍሳሽ ማጣሪያ አንዱ ነው፡፡
ማጣሪያ ከኢንደስትሪዎቹ የሚወጣውን ፍሳሽ ቆሻሻ በማጣራት ተመልሶ ጥቅም ላይ የሚያውል በመሆኑ በአካባቢ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት የለም፡፡
ቆሻሻውን ውሀ ወደ ማጣሪያ የተጣራውን ደግሞ ወደ እያንዳንዱ ፋብሪካ የሚያመላልስ 32 ሺህ 700 ሜትር ስኩየር ርዝመት ያለው የውሃ መስመር ተዘርግቷል፡፡
ቀደም ሲል በከተማዋ የተገነቡ አብዛኞቹ ፋብሪካዎች የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ የሌላቸው በመሆኑ ከነዋሪው ለጤና ችግር ተጋለጥን አቤቱታ ሲሰማባቸው ቆይተዋል፡፡
በሀዋሳ ኢንደስትሪ ፓርክ ግን ይህ እንደ ችግር አይታይም ምክንያቱም ፍሳሽ ቆሻሻ ብሎ ነገር የሌለበት በመሆኑ በሰው ጤና ላይም ሆነ በአካባቢ ላይ የሚያደርሰው አሉታዊ ተጽዕኖ የለም፡፡
ፓርኩ ሌላ ልዩ የሚያደርገው ነገር የእሳት አደጋ መከላከያ ዘዴው ነው ፡፡ይህ ፓርክ በእያንዳንዱ ሼዶች ያለውን የሙቀት መጠን እየተቆጣጠረ መጠኑ ከፍ ሲል የሚያሳውቅ ልዩ መሳሪያ የተገጠመለት ነው፡፡
18 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ ፣21 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የኤሌክትሪክ መስመር ፣16 ኪሎ ሜትር የቴሌኮም መስመርና 23 ኪሎ ሜትር የውሃ መስመር ዝርጋታ ከግንባታው ጋር አብሮ ተከናውኗል፡፡
በአሁኑ ሰዓት 15 የውጪና 6 የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኩ ስራ ለመጀመር ዝግጅታቸውን እያጠናቀቁ ሲሆን በሁለት ፈረቃ 60 ሺህ ሰዎች የስራ እድል ባለቤት ማድረጉ ከበርካታ ልዩነቶቹ መካከል  ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ከ56 ዓመት በፊት ንጉሰ ነገስቱ በሎቄ ቀበሌ ያስገነቡትን ቤተ መንግስት ሲመርቁ በጢልቴ ዱሜ ተራራ ላይ ወጥተው ሀይቁንንና ዙሪያውን ከተመለከቱ በኋላ ይህ ተራራ የእስራኤሉን ታቦር ተራራ መሰለኝ ብለው በመናገራቸው ከዛች ቀን ጀምሮ መጠሪያውን ታቦር ተራራ አደረገ፡፡
ጢልቴ በሲዳማ ብሔረሰብ ዘንድ ባህላዊ የምግብ ማቅረቢያና መመገቢያ ዕቃ ሲሆን ዱሜ ማለት ቀይ ማለት ነው፡፡
የዛሬው ታቦር ተራራ ያኔ ይጠራበት የነበረውን ጢልቴ ዱሜ የሚለውን ስም የወረሰው የተራራው አቀማመጥ የመመገቢያ ዕቃውን ቅርስ መያዙና ቀይ አፈር ያለው በመሆኑ እንደነበር ይነገራል፡፡
ከአመታት በፊት ከጢልቴ ዱሜ ግርጌ ስር የከተመችው የሀዋሳ ከተማ ስትመሰረት ለኢንደስትሪ ከተማነት ታስባ ቢሆንም ሳይሳካላት ቆይታ እንሆ ዛሬ በከተማዋ ትልቅ ከተማ ተመስርቶላታል፡፡
ከጤልቴ ዱሜ ግርጌ የተንጣለለችው ሀዋሳ ከተማ ዛሬ በከተማዋ ውስጥ የተመሰረተው የኢንደስትሪ ፓርክ በከተማ ውስጥ ሌላ ከተማ ሆኖላታል፡፡
                                                                       ቸር እንሰንብት!፡፡
ምንጭ ኢዜኣ

0 comments :