በዘጠኝ ወራት ተገንብቶ የተጠናቀቀው የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የውጭ ኩባንያዎች ሊያስተዳድሩት ነው

ፎቶ ከሪፖርተር ጋዜጣ
በታሰበለት ጊዜ መጠናቀቁ ዶ/ር አርከበ ዕቁባይን አስወድሷቸዋል ዘጠኝ ወራት የግንባታ ጊዜ ወስዶ ባለፈው ሳምንት የተመረቀው የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለማስተዳደርና እንቅስቃሴውን በአግባቡ ለማስቀጠል፣ ለህንድና ለቻይና ኩባንያዎች ኮንትራት መሰጠቱ ተገለጸ፡፡ ግንባታውን በታሰበለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ በማስቻልና በጥራት እንዲከናወን በማድረግ፣ በበላይነት በመምራትና በማስተካከል ባደረጉት አስተዋጽኦ ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ ከመንግሥትና ከባለሀብቶች ውዳሴ ጎርፎላቸዋል፡፡ በ250 ሚሊዮን ዶላር በቻይናው ተቋራጭ (ሲሲኢሲሲ) ኩባንያ የተገነባው የኢንዱስትሪ መንደር ዓለም አቀፍ መሥፈርቶች ያሟላና ከብክለት ነፃ የሚያደርግ ቴክኖሎጂ የተገጠመለት ሲሆን፣ በዓመት አንድ ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ እንደሚያስገኝም ተገልጿል፡፡ የፓርኩ አሠራር ውስብስብና ከፍተኛ የማስተዳደር ክህሎት የሚጠይቅና በአገር ውስጥ ባለሙያዎች ለማስተዳደር የሚያስቸግር በመሆኑ፣ በውጭ ኩባንያዎች ለሦስት ዓመታት እንዲተዳደር በመንግሥት መወሰኑን ዶ/ር አርከበ በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ወቅት አስታውቀዋል፡፡ የፓርኩን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴን ጨምሮ አጠቃላይ አስተዳደራዊ ሥራና የጥገና አገልግሎቶችን እንዲያስተዳድር ተቋራጩ ሲሲኢሲሲና የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማስተዳደር ዝና አለው የተባለው ኩን ሻን ኩባንያ በጋራ ኃላፊነቱን ወስደዋል፡፡ እንዲሁም ፓርኩ ከብክለት ነፃ እንዲሆን ፍሳሽ አልባ ቴክኖሎጂ (Zero Liquid Discharge) የተከለው የህንዱ አርቪን ኩባንያ ይህንን ኃላፊነት መውሰዱን ዶ/ር አርከበ ገልጸዋል፡፡ በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ሚኒስትር አቶ ሲሳይ ገመቹ፣ ሦስቱ ኩባንያዎች ፓርኩን ለሦስት ዓመት እንደሚያስተዳድሩትና ከኮንትራት ውሉ ከተጠናቀቀ በኋላ ባሉት ዓመታት ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን እንደሚተዳደር ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም ለሦስቱ ኩባንያዎች በዓመት እስከ ሦስት ሚሊዮን ዶላር ለእያንዳንዳቸው እንደሚከፈልም አቶ ሲሳይ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡ ሃያ ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ የጨርቃ ጨርቅና የአልባሳት አምራች ፋብሪካዎችን የያዘው ይኼው ፓርክ 1.3 ሚሊዮን ካሬ ሜትር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፣ በውስጡ ያሉት የፋብሪካዎቹ መጠለያ ብቻ በ300 ሺሕ ካሬ ሜትር መሬት ላይ ተገንብተዋል፡፡ እንዲሁም በግቢው ውስጥ 18 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገዶች ሲኖሩ፣ 21.5 ኪሎ ሜትር የኤሌክትሪክ መስመር፣ 16 ኪሎ ሜትር የስልክ መስመሮችና 23 ኪሎ ሜትር የንፁህ ውኃ ማስተላለፊያ ቧንቧዎች ተዘርግተውለታል፡፡ በተጨማሪም በፓርኩ ውስጥ የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ የንግድ ሱቆችና የተለያዩ አገልግሎቶች ለሚሰጡ ተቋማት የሚውሉ ቢሮዎችም ተገንብተዋል፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኩ ለአምራቾች የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲሰጡ የታሰቡ የአንድ መስኮት አገልግሎቶች የተሟሉለት ሲሆን፣ ዋና ዋናዎቹም የኤሌክትሪክ፣ የውኃ፣ የስልክ፣ የሎጂስቲክስ፣ የጉምሩክ፣ እንዲሁም የቪዛ አገልግሎትን እንደሚያካትቱ ዶ/ር አርከበ ገልጸዋል፡፡ ባለፈው ረቡዕ ሐምሌ 6 ቀን 2008 ዓ.ም. በተካሄደው የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች፣ የውጭ አምራቾችና ዲፕሎማቶች የፓርኩን የተለያዩ ክፍሎች ጎብኝተዋል፡፡ በወቅቱ ጎብኝዎቹ በፓርኩ ግንባታ፣ በግዙፍነቱና በያዛቸው ውስብስብና ዘመናዊ አገልግሎት መስጫዎች መደነቃቸውን ገልጸዋል፡፡ በተለይም ግንባታውን በማስተባበር፣ በመምራት፣ አመራር በመስጠትና በመከታተል ረገድ በግል ለዶ/ር አርከበ እቁባይ አድናቆት ተችሯቸዋል፡፡ በፓርክ ውስጥ የሚሳተፉ የውጭ አገሮች ኩባንያዎች፣ የተቋራጭ ኩባንያው ኃላፊዎች ግንባታው ከመጀመሩ በፊትም ሆነ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ዶ/ር አርከበ ላሳዩት ትብብርም ሆነ ኃላፊነት በተደጋጋሚ ሲያደንቋቸው ተስተውሏል፡፡ እንዲሁም በዕለቱ ፓርኩን ለመክፈት በክብር እንግድነት የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝም ዶ/ር አርከበን በተለየ ሁኔታ አሞግሰዋቸዋል፡፡ ‹‹ምንም እንኳ ግለሰቦችን ነጥሎ ማመስገን የድርጅታችንም ሆነ የመንግሥታችን ባህል ባይሆንም፣ ዶ/ር አርከበ ለዚህ ሥራ የሰጠው ትኩረትና ኃላፊነትን ሳልጠቅስ ማለፍ አግባብ አይመስለኝም፡፡ እንቅልፍ ነስቶን ለዚህ ትልቅ ስኬት እንድንደርስ አድርጎናል፤›› ሲሉ በክብር እንግዶች ፊት አወድሰዋቸዋል፡፡ በዘርፉ ዓለም አቀፍ ዝና ያላቸው 14 የጨርቃ ጨርቅ አምራቾች ምርታቸውን በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ማምረት ይጀምራሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥም የ130 ዓመታት ልምድ እንዳለው የሚነገርለት የአሜሪካው ፒቪኤች ይገኝበታል፡፡ በተለይም ፒቪኤች ካልቪን ክሌይ፣ ቶሚ ሂል ፊገርና በመሳሰሉት አልባሳት መለያዎች (ብራንዶች) ይታወቃል፡፡ እንዲሁም የቻይናው ውሺ ጂንማኦ፣ የህንዱ አርቪንድ የመሳሰሉትን ጨምሮ የሆንግ ኮንግ፣ የቤልጂየም፣ የሲሪላንካና የአሜሪካ ኩባንያዎች ይገኙበታል፡፡ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ስድስት ሲሆኑ፣ አቅማቸውንና ተሳትፎአቸውን ለማሳደግ ከመንግሥት ልዩ ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም ዶ/ር አርከበ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በተለይም በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ ገብተው ለሚሳተፉ ባለሀብቶች መንግሥት እስከ 85 በመቶ የሚደርስ የባንክ ብድር እንደሚያመቻችም ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ከሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በተጨማሪም የመቐለና የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታም መጀመሩን አውስተዋል፡፡ በተጨማሪም በ300 ሚሊዮን ዶላር የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክም በመጪው መስከረም ወር ግንባታው እንደሚጀምርም ተገልጿል፡፡ እንዲሁም በቂሊንጦ፣ በድሬዳዋ፣ በደብረ ብርሃን፣ በጂማ፣ በባህር ዳርና በአረርቲ ምንጃር የኢንዱስትሪያል ፓርኮችም በሚቀጥለው ዓመት ግንባታ ይጀመራል ተብለው ከሚጠበቁ አሥር ፓርኮች ውስጥ እንደሚጠቀሱ አስታውቀዋል፡፡ የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ አሁን ባለበት ደረጃ ለ60 ሺሕ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር፣ ከሁለት ወራት በኋላ የሚጀመረው ሁለተኛው የማስፋፊያ ምዕራፍ ግንባታ ሲጠናቀቅ ለ84 ሺሕ ያህል ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጠር ተገልጿል፡፡ ከዚህኛው በተጨማሪ ሌላ የኢንዱስትሪ ፓርክ እንደሚገነባ አቶ አርከበ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡ የአሁኑ ፓርክ ከግዙፉ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጎን የተገነባ ሲሆን፣ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፎሰር ዮሴፍ ማሞ የሳይንስ ተማሪዎችን ያለባቸውን የሥራ ላይ ልምምድ ችግር እንደሚቀርፍ ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲውም በፓርኩ ውስጥ ተቀጥረው ለሚሠሩ ሠራተኞች የአጭርና የረጅም ጊዜ ሥልጠና እንደሚያዘጋጅ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
Source

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር