የሐዋሳ ምዕራፍ ሁለትና የሌሎች ፓርኮች ግንባታ በስድስት ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል ተባለ

ሙሉ ዜናውን ከሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ያንቡ

በሐዋሳ ከተማ በ300 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የተንጣለለው የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ለማምረቻ የተገነቡት 37 የማምረቻ ሼዶች ሙሉ በሙሉ በውጭና በአገር ውስጥ ባለሀብቶች መያዛቸው ተገለጸ፡፡ ከቀናት በኋላም በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ተመርቆ በይፋ ሥራ እንደሚጀምር ታውቋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ያልቃል ተብሎ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ከክረምቱ ወራት በፊት ሊጠናቀቅ ቀናት ቀርተውታል፡፡ በመሆኑም ሰኔ 23 ቀን 2008 ዓ.ም. የግንባታ ሥራው ሙሉ ለሙሉ እንደሚጠናቀቅ ዶ/ር አርከበ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ፍጹም አረጋ በበኩላቸው እንደገለጹት፣ ከውጭ ከመጡት አሥር ዋና ዋና ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በተጨማሪ ስምንት የአገር ውስጥ ኩባንያዎች በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የማምረቻ ሼዶችን ተረክበዋል፡፡ እስካሁን ስድስት ያህል እንደነበሩ ሲገለጽ ቢቆይም፣ አቶ ፍጹም ግን ስምንት እንደደረሱና በጠቅላላው በአገሪቱ እየተገነቡ በሚገኙት ፓርኮች ውስጥ የማምረቻ ቦታ ለመከራየት የሚጠባበቁት የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ቁጥር 22 መድረሱን ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በአምራችነት ለመሳተፍ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የማምረቻ ቦታ የተከራየው የአሜሪካው ግዙፍ የአልባሳት አምራች ፒቪኤች (ዘ ፊሊፕ ቫን ሂውዝን ኮርፖሬሽን) ከሌላኛው የአሜሪካ ቪኤች (ቫኒቲ ፌር ኮርፖሬሽን) ከስዊድኑ ኤችኤንድኤም (ሔንስ ኤንድ ማውሪትዝ ኤቢ) ኩባንያዎች ከመንግሥት ጋር በመተባበር ባዘጋጁት ጉባዔ ላይ 35 ያህል የውጭ ኢንቨስተሮች በሐዋሳና በሌሎች የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ለመሳተፍ ፍላጎት አሳይተዋል  ተብሏል፡፡ ዶ/ር አርከበ እንዳብራሩት፣ ለጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ወሳኝ የሆኑት አክሰሰሪዎች የሚያመርቱ ኩባንያዎች ታድመዋል፡፡
አቶ ፍጹም ስለኩባንያዎቹ እንዳብራሩት፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋት ታዋቂ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪዎች ወደ አገር ውስጥ መምጣት፣ በተለይ ለአልባሳት አምራቾች እንደ ቁልፍ (አዝራር)፣ ዚፕና መሰል ግብዓቶችን፣ የስፌት ክሮችንና መሰል ግብዓቶችን የሚያመርቱ ኩባንያዎች መምጣታቸው ከትልልቆቹ መምጣት ጋር የሚያያዝ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በመሆኑም የልብስ አምራቾችን የፋሽንና የሞዴል ምርጫ ተንተርሰው ወደ አገር ውስጥ ለመምጣት ከወሰኑት መካከል የፈረንሣዩ ሻርጀስና የደቡብ አፍሪካው አይቲኤል የሚጠቀሱ ሆነዋል፡፡
በሌላ በኩል የመቐሌና የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ እየተካሄደ ሲሆን፣ የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ከሰሞኑ እንደሚጀመር፣ የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክም ከሁለት ሳምንት በኋላ ግንባታው እንደሚጀመር የገለጹት ዶ/ር አርከበ፣ የጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታም ከሁለት ሳምንት በኋላ እንደሚጀመር አስታውቀዋል፡፡ ከእነዚህ ባሻገር ሞጆ ከተማ አጠገብ፣ አረርቲ ምንጃር በተባለው አካባቢም የግንባታ፣ የቤትና የቢሮ ዕቃዎች ማምረቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ እየተጀመረ እንደሚገኝና የመሬት ርክክብ መካሔዱን ዶ/ር አርከበ ገልጸዋል፡፡ በድሬዳዋም በአንድ ሼሕ ሔክታር መሬት ላይ የሚያርፍና በተለያዩ ማሽነሪዎችና መሣሪያዎች ላይ ያተኮረ የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ በሐምሌ ወር እንደሚጀመርም ጠቅሰዋል፡፡
ይህም ሆኖ በጨርቃ ጨርቅ አልባሳት ዘርፍ ተሰማርተው የሚገኙ ትልልቅ አምራቾች ፈተና ውስጥ መውደቃቸው ታውቋል፡፡ የቱርኮቹ ሳይገንዲማ እንዲሁም አይካ አዲስ በኪሳራና ህልውና ጥያቄ ውስጥ መውደቃቸውን ሰሞኑን ለፓርላማ ከቀረበ ሪፖርት ለመረዳት መቻሉን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ይህንን በሚመለከት ዶ/ር አርከበ እንደገለጹት፣ ‹‹አይካ አዲስ በአገሪቱ ውስጥ የጨርቃ ጨርቅ ምርቶችን ኤክስፖርት እያደረጉ ካሉ ድርጅቶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ እነዚህ ድርጅቶች ከፓርክ ውጭ የሚሠሩ በመሆናቸው በርካታ ያልተመቻቹላቸው ነገሮች አሉ፡፡ የኃይል መቆራረጥ ያጋጥማቸዋል፡፡ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትና ሌሎች የተለያዩ ችግሮች ያግጥሟቸዋል፡፡ እነዚህን መንግሥት ደግፎ መፍታት አለበት፡፡ በመንግሥት መፈታት  ያለባቸው ጉዳዮች አሁንም እንዳልተፈቱላቸው መገንዘብ አለብን፤›› ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል የ250 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት የጠየቀው የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ላይ የተሳተፉት፣ ቻይናዊው የፓርኩ ፕሮጀክት ማናጀር ከሥራቸው ገበታቸው ቢባረሩም ይቅርታ ጠይቀው መመለሳቸው ታውቋል፡፡ የፕሮጀክት ማናጀሩ ዡ ሊ (ጆን) በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለኢትዮጵያውያን ሠራተኞች አግባብ ያለው የንጽህናና የመጸዳጃ አቅርቦት እንዲኖር ካለማድረጋቸውም በላይ ባሳዩት ያልተገባ ባህርይ በዶ/ር አርከበ እንዲባረሩ ምክንያት ሆኖ እንደነበር ቢሰማም፣ ይቅርታ በመጠየቅ ወደ ሥራ ምድባቸው መመለሳቸውን የሪፖርተር ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር