POWr Social Media Icons

Tuesday, August 18, 2015

ሀዋሳ 5ኛውን የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ታዘጋጃለችግንባታው እየተጠናቀቀ ያለውና 40 ሺ ሰዎችን መያዝ የሚችለው የሀዋሳ ስታዲየም የውድድሩ ድምቀት እንደሚሆን ይጠበቃል፤

8ኛው የፌዴራል ስፖርት ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ከትናንት በስቲያ በተጠናቀቀበት ወቅት በ2008ዓም የሚካሄደውን የ5ኛውን መላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች እቅድ ሰነድ አጽድቋል። ውድድሩን የሀዋሳ ከተማ ታስተናግዳለች።
ጉባኤው ሰነዱን ያጸደቀው ከትናንት በስቲያ በተናቀቀበት ወቅት ነው። በ1999ዓም የተጀመረውና ሁሉንም ክልሎች ባሳተፈ መልኩ የሚካሄደው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች የኦሎምፒክን ጽንሰ ሃሳብን ይከተላል። በየሁለት ዓመቱ የሚዘጋጀው ይህ ውድድር ብዛት ባለው የስፖርት ዓይነት ብዛት ያላቸውን ስፖርተኞች በማሳተፍም ይታወቃል። በ2008.ም የሚካሄደው የ5ኛው መላ ኢትዮጵያ ጨዋታም በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል በሃዋሳ ከተማ የሚዘጋጅ ይሆናል።
የጨዋታው እቅድ ሰነድም በፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን የስፖርት ተሳትፎና ውድድር ፌስቲቫል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ በቀለ ቀርቧል። በዕቅዱም ላይ በሃዋሳ ከተማ በሚዘጋጀው ውድድር ተጫዋቾችን፣ አሰልጣኞችን፣ የቡድን መሪዎችንና ሌሎችንም ጨምሮ 4150 የሚሆኑ የልኡካን ቡድን አባላት ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል። በዚህም መሰረት ከጥር1እስከ መጋቢት 30 ቀን 2008 .ም ድረስ ክልሎች ዝግጅታቸውንና የተጫዋቾች መረጣቸውን እንደሚጨርሱ በእቅዱ ላይ ተገልጿል።
በዚህም መሰረት የክልሉ መንግስት ባለፈው ዓመት አዘጋጅ ከነበረው የኦሮሚያ ክልል መልካም ተሞክሮዎችን እንዳገኘ ተገልጿል። ክልሉ ለውድድሩ ማካሄጃ የሚያውላቸው የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ዝግጅት ከወዲሁ ተጀምሯል። አዲሱ የሃዋሳ ከተማ ስታዲየም፣ የደቡብ ክልል ፖሊስ ሜዳ እንዲሁም የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሜዳ ለዚህ ውድድር የተዘጋጁ ሲሆን፤ ለቤት ውስጥ ጨዋታዎች ማስተናገጃ የተለያዩ አዳራሾች እንዲሁም የኦሎምፒክ ደረጃውን የጠበቀ የመዋኛ ገንዳ ደግሞ በግንባታ ላይ ይገኛል።
በእቅዱ ላይ 4ኛው መላ አፍሪካ ጨዋታዎች ላይ የታዩ ደካማ ጎኖች ተጠቁመዋል። በውድድሩ ወቅት በተለይ ጎልተው ሲታዩ የቆዩት የስፖርተኞች የስነምግባር እንዲሁም የአድሎና ወገንተኝነት ችግሮች በ5ኛው መላ አፍሪካ ጨዋታዎች ላይ እንዳይደገሙ መሰራት እንዳለበት የምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል።
 ምንጭ፦ ኢዜኣ
በዘንድሮው በዓል አዛውንቶች (አያንቱዎች) የበዓሉ ድምቀት ሆነው ሰንብተዋል፤

በአንድ አገር ውስጥ ማህበረሰባዊ የተቋም ሽግግር እንዲመጣ፣ የህዝቦች የጋራ እሴት እንዲጎለብት እና የትውልድ ቅብብሎሽ መኖር መሰረታዊ ስለመሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም። ሀገር ያለ ሰው አይደምቅም። ሰውም ያለ ሀገር አይፈጠርም። ለሀገር ዘመን ተሻጋሪ ድርና ማጉ ህዝብ ነው። የአንድ ህዝብ ታሪክ መሰረቱ የተከታታይ ትውልዶች ሥራ ነው።
እያንዳንዱ ትውልድ ማህበራዊ አንድነቱንና አብሮ የመኖር ህልውናው አረጋግጦ ለሚቀጥለው ትውልድ የሚያስተላልፈው እሴት የዛ ህዝብ የማንነት መገለጫ ነው። የአንድ ህዝብ አገር በቀል እውቀት፣ ልምድ፣ ትውፊታዊ እምነት፣ ወግና ስርዓት፣ ያለፉትን ተከታታይ ትውልዶች ከዛሬው ከወደፊቱ ትውልዶች ጋር የሚያገናኝ፣ የሚያስተዋውቅና የሚያስተሳስር ሰንሰለት ነው። ያ ህዝብ የራሱን የኑሮ ዘይቤ በመደንገግና በመቅረፅ ሥርዓት ባለው መልኩ ህይወቱን ለመምራት ያደረጋቸው የለውጥ ሂደቶች የስብዕናው መገለጫዎችም ሆነው ይስተዋላሉ።
ጉዞአችን በደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ ነው። የሲዳማ ህዝብ በደቡብ ክልል ከሚገኙ ብሄር ብሄረሰቦች ህዝቦች መካከል አንዱ ነው። ዞኑ በሰሜን ምስራቅና በደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ ክልል እንዲሁም በስተምዕራብ የወላይታ ዞን ያዋስኑታል። የሲዳማ ህዝብ የራሱ የሆነ ቋንቋ ፣ የዘመን አቆጣጠር፣ ባህል፣ ስርዓት፣ ትውፊት፣ ወግና ሥርዓት ያለው ነው። ቋንቋው ሲዳምኛ ነው።
የሲዳማ ብሄር የማንነቱ መለያና መገለጫ የሆኑ የበርካታ ባህላዊ ፣ታሪካዊና ማህበራዊ የአኗኗር ዘይቤ እሴቶች ባለቤት ነው። ከእነዚህ መካከል የፊቼ ጨምበላላ በዓል ዋና እና ቀዳሚው ከሆኑ ባህላዊ እሴቶች ይመደባል። የሲዳማ ዘመን መለወጫ ፊቼ ጨምበላላ የሚውልበት ዕለትና ለበዓሉ የሚሰጠው ቦታና ትርጉም እንዲሁም ከህይወቱና ከማንነቱ ጋር ካለው ቁርኝት የተነሳ የብሄሩ ተወላጆች በዓሉን ሲያከብሩ የሚጠበቅባቸውን ሥነ ሥርዓትና ሥነ ምግባር የተመልካቹን ቀልብ ከሚገዙ ትዕይንቶች መካከል ተጠቃሽ ነው።
የሲዳማ ህዝብ በአብዛኛው ልዩ ቃና ባለው ቡና አምራችነቱ ይታወቃል። የሲዳማን ብሄር ከሌላው ልዩ የሚያደርገው ህዝቡ ከጥንት ጀምሮ ሲመራባቸውና ሲተዳደርባቸው የነበሩ ክዋኔዎችና እሴቶችን ጠብቆ ያቆየበት መንገድ ነው። እኔም በዝና ብቻ ለማውቃትና « የተመለከቷት ተመልሰው ለመምጣት ይቸገራሉ» ወደ ተባለላት የሲዳማ ዞንን ለማየት በጣም ጓጉቼአለሁ። ለዚህም ነው በጠዋት የጉዞ አቅጣጫዬን ወደ እዚያው ያስተካከልኩት። የጉዞአችን ዋነኛ ዓላማም የዘንድሮውን የሲዳማ ዘመን መለወጫ በዓል ጨምበላላን ለመታደም ነው።
ሲዳማዎች የራሳቸው የዘመን አቆጣጠር መርህ አላቸው። እንዴት ከተባለም፣ በእጅ የያዙት ወርቅ ሆኖብን እንጂ የሲዳማዎቹ አያንቱዎች ጥበብ በመሬት አካል ዙሪያና ከዛ ውጪ የሚገኙ ክስተቶችን የሚያጠና ጥንታዊ ሳይንሶች ክፍል የሚመደበው ሥነ ፈለክ ( አስትሮኖሚ ) ሊቅ ናቸው ማለት ይቻላል። ሲዳማዎች ከዚህ አኳያ ሲቃኙም የከዋክብትና የጨረቃዎችን ጥናት ተክነዋል ቢባልም አይደንቅም። ሲዳማዎች የወቅቶችን ዑደት ምስጢር ከራሷ ከተፈጥሮ ገፀ በረከት በመነሳት የሚያውቁበትና ዘመናት የተገለገሉበት ልዩ ክህሎት አላቸው።
የሲዳማ ብሄር ከዘረጋቸው ባህላዊ እሴቶች መካከል የጊዜ፣ የቀናት፣ የወራት፣ የዓመታትንና የወቅቶችን ዑደት ምስጢር ከራሷ ከተፈጥሮ ገፀ ባህሪ በመነሳት የጊዜን ምስጢር ማወቅ የቅድመ አባቶች አበይት ተግባር በመሆኑ ነው። ሲዳማዎች ዓለም እንደዛሬው በቴክኖሎጂ ሳይንበሸበሽ የአየር ትንበያ መሳሪያቸውም ሳይፈጠሩ፣ ዘመናዊ የእጅና የግድግዳ ሰዓቶች ሳይመረቱ በፊት ገና ያኔ ጥንት ቀናትን የሚቆጥሩበት ለህይወት ትርጉም የሚሰጡበት የዘመን አቆጣጠር ሂደት በቅድመ ጥናት አባቶች ምርምር በማድረግ ህይወትን በጊዜ ስሌት ያጣጥማሉ።
ወደ እዚህ ምድር በመምጣትና መኖር ብቻውን ለሲዳማዎች የኑሮ ግብ አይደለም። ይልቁንም በምድር የመኖር ትልቅ ገፀ በረከት ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ብቻ ሳይሆን ቀናት ቀናትን እየወለዱ የሚፈጠሩ ወራት ተንትነው የሚፈራረቁትን ወቅቶች በባህሪያትና ልዩነት ጭምር በማጤን በሁሉም ወቅቶች ራሳቸውን እንዴት እንደሚያኖሩ በመረዳት ውጤታማ ህይወት መምራት መቻላቸው ነው። ስለሆነም በብሄሩ ባህላዊ እሴቶች፣ መካከል የጊዜ፣ የቀናትን፣ የወራት፣ የዓመታትንና የወቅቶችን ዑደት ምስጢር ከሯሷ ከተፈጥሮ ገፀ በረከቶች በመነሳት የጊዜ ቀመሮችን ማወቃቸው የቅድመ አባቶች አበይት ተግባር ነው።
ለሲዳማዎች የስልጣኔ ጅማሬ ህይወትን ከዘመን አኳያ ትርጉም መስጠት አንዱ በመሆኑ አካባ ቢያቸውን ለማወቅ መመራመር ጀመሩ። ጅማሬያቸውም አንገታቸውን ወደ ሰማይ ቀና ሲያደርጉ የሚያዩት ውብ ሰማይ በቀንና በምሽት ዑደት ውስጥ የሚታይበት የመንጋትና የመምሸት፣ የመብራትና የመጨለም ተለዋዋጭ ሂደት የጊዜ ምስጢር መነሻ መሆኑን በማወቅ እንደዋዛ በሚመሸውና በሚነጋው ዓለም ውስጥ አንድ ምስጢር እንዳለ ተገነዘቡ።
በማለዳ የምትወጣው ፀሐይ በምሽት የምትፈንዳው ጨረቃ ውበትን ቀና በማለትና አንጋጠው በመመለከት በተፈጥሯዊ ትዕይንት ከመደሰት በዘለለ አንዳች ምስጢርን መፈለግ የሲዳማ አዋቂዎች ወይም በቋንቋቸው (አያንቱዎች ) ዓይነተኛ የጥበብ ጀማሬ ነው። በተለይ በምሽቱ ውስጥ አልፎ አልፎ የጨረቃዋ ክስተት አንዳንዴ ደግሞ ብርሃኗን የምትነፍገው ጨረቃ የሲዳማን አያንቱዎች አስተሳሰብ ሰርቆታል። በተለይ በሰማዩ ላይ የሚስተዋለው ምሽታዊ ትዕይንት ረጃጅም ሌሊቶችን በደጅ በማደር ለመረዳት ከመሞከር በላይ በየምሽቱ የምትወጣው ጨረቃ በከዋክብት መታጀቧ ይበልጥ በትዕይንቱ እንዲሳቡ አድርጓል።
ጨረቃዋ እንደ ፈንዲሻ በሚፈኩ ከዋክብት ታጅባ ስትታይ ከዋክብት ለጨረቃዋ የሚሰግዱ ይመስላል። በዚህም የጨረቃና ከዋክብት ቁርኝት እንዳለው በመረዳት በሰው ልጅ ችሎታ ውስጥ ለብዙዎቹ የማይታሰበውን የኮከብ ቆጠራ ጥበብ ከሲዳማዎች አባቶች ለሁሉም ሳይሆን ለጥቂቶቹ የተሰጠ የጥበብ ምስጢር ነው።
ጨረቃ የምትወጣበትንና የማትወጣበትን ቀናት በመቁጠር ጭምር የቀናትንና የወራትን ብሎም የዘመናትን አቆጣጠር ሂደት የባህላቸው መሰረት ሆነ። ይህ ሁኔታ መምሸትና መንጋት የቀናት መፈጠር ውጤት ሲሆን፤ ቀናት ደግሞ ለወራት መፈጠር ብሎም የወራት መፈጠር ለወቅቶች መፈራረቅና ዓመታት መቆጠር ትልቅ ምስጢር መሆኑን ደረሱበት።
ሁሉም አያንቱዎች በያሉበት ሥፍራ የጨረቃን መውጣትና መግባት ወይም የብርሃንና ጨለማ ሂደት ተከትሎ የህብረ ከዋክብት አቅጣጫ ከጨረቃ አቀማመጥ ጋር በማገናዘብና በመቀመር የሲዳማን ባህላዊ የዘመን አቆጣጠር ይቆጥራሉ። ከዋክብቶቹን መቁጠር ጥልቅ የትኩረት ተመስጦንና ክፍት ልቦናን ይጠይቃል። ይህም ብቻ አይደልም፣ ከከዋክብት መቁጠር እስከ ሌሊት ድረስ ሊሆን ስለሚችል በብርዳማ ሌሊት በቀዝቃዛው ንጋት ሳይታክቱ የህብረ ከዋክብትን ሂደት መከታትልና መቁጠር ታላቅ ሰብዓዊ ጥንካሬንና አለመታከትንና መስዋዕትነትን ይጠይቃል።
ከዋክብቶችን በሌሊት መቁጠር በብዙ ተፈጥሯዊ ተግዳሮቶች የተሞላ መሆኑን የኮኮብ ቆጣሪነትን ሌላኛው ገፅታ ነው። የሰማዩ ሙሉ ገፅታ እይታ አድማስ እንደ ልብ ለማየት ሲያዳግትም ቆጠራውን ከቤት ውጪ በደጅ በማደር የሚከናወን ይሆናል። በዚህም ከሌሊት አራዊት ጋር ግብ ግብ መፍጠርም ሊኖር ይችላል።
በዚህ መልኩ በያሉበት ሆነው ቆጠራውን የሚያከናውኑት አዋቂዎች (አያንቱዎች) በአቅራቢያ ቸው ካሉ አያንቱዎች ጋር በመሆኑ ሲንጎ (ስብሰባ) በማድረግ ሁሉም የራሱ የቀመር ስሌት ለጨሜሳዎች ስብሰባ ያቀርባል። « ዩኒክ ኢትዮጵያ የሲዳማ ባህላዊ እሴቶችና ቱሩፋቶች » በሚል ከታተመው ብሮሸር ከሰፈረው መረጃ መረዳት እንደቻልኩት፤ አያንቱዎቹ ስለ ቆጠራቸው ሪፖርት የሚያደርጉት፣ ሁሉም በትክክል ቆጠራውን ማከናወናቸውን ለመገምገም ሲሆን፤ በዚህ ኡደት አብዛኛው ተመሳሳይ ነው።
ከዚያም በየአካባቢያቸው ወይም በየወረዳቸው ተሰብስበው የቆጠራውን ውጤት ካወቁ በኋላ በሌላ ወረዳ ላሉት ውጤታቸውን መልዕክት በመላክ የቆጠራውን ስሌት በመላ ሲዳማ ተመሳሳይ መሆኑን ያረጋግጣሉ። ብዙውን ጊዜ በዚህ ሁኔታ የሚፈፀሙ ሂደቶች ገዘፍ ላሉ ማህበራዊ መስተጋብር ሲሆን በዋነኝነት የዘመን መለወጫ በዓል ፊቼ ጨምበላላ የሚውልበትን ቀን ለማወቅ በጥቅም ላይ ይውላል።
የሲዳማ ብሄር የዘመን መለወጫ የፊቼ ጨምበላላ በዓልን ለማክበር ሲዘጋጅ ከምንም በላይ ቀልብ ይገዛል። የፊቼ ጨምበላላ በዓል ለብሄሩ የማንነቱ መገለጫ ከመሆኑም ባሻገር የልማት፣ የመከባበር፣ የመቻቻልና የአብሮነት ተምሳሌት ተደርጎም ይቆጠራል። የዘንድሮው የፊቼ ጨምበላላ በዓልም ሐምሌ 7 በሃዋሳ ሲዳሞ ባህል አዳራሽ በድምቀት ተከናውኗል። አይዴ ጨምበላላ!!
በሰኔና ሐምሌ ዝናብ ባልዘነበባቸውና ለድርቅ አደጋ በተጋለጡ አፋርና ወሎ እንዲሁም ሃረርና ድሬደዋ አካባቢ ሰሞኑን ዝናብ መዝነብ እንደጀመረ ምንጮቻችን ገልፀዋል፡፡
በድርቅ አደጋ በቀን እስከ 100 የቤት እንስሳት እየሞቱ በነበረበት የአፋር ክልል በአሁን ወቅት አስቸኳይ እርዳታና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን የጠቆሙት ምንጮቹ፤ በተለይ ከሎጊያ እስከ ክልሉ ዋና መቀመጫ ሠመራና አካባቢው ተደጋጋሚ ዝናብ እንደዘነበ ተናግረዋል፡፡
ድርቅ ተከስቶባቸው ከነበሩ ቦታዎች አንዱ የድሬደዋና ሀረር ቆላማ አካባቢ ከባለፈው ሠኞ ጀምሮ መጠነኛ ዝናብ እየዘነበ ሲሆን በድሬደዋ ከተማ ጠንከር ያለ ዝናብ መዝነቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በድሬደዋ ገጠራማ አካባቢዎች ግን አሁንም የዝናቡ ሁኔታ የሚጠበቀውን ያህል አለመሆኑን ምንጮች ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡
ከሰሜኑ የአገሪቱ ክፍሎች አንዱ በሆነውና ከፍተኛ የድርቅ ስጋት አንዣቦበት የነበረው ከሸዋሮቢት እስከ ወሎ ባለው መስመር በሣምንቱ ተደጋጋሚ ዝናብ መዝነቡን በአካባቢው የሚገኙ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
በምስራቅ ስምጥ ሸለቆ አካባቢ ተብሎ በሚታወቀው ከአዳማ እስከ መተሃራ ባለው አካባቢም በሳምንቱ የሚጠበቀውን ያህል ባይሆንም ዝናብ መዝነብ መቻሉን በአካባቢው የሚመላለሱ ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡
የብሄራዊ ሜትሪዎሎጂ አገልግሎት ማክሰኞ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በሰኔና በሐምሌ ወር በሰሜን ምስራቅ፣ በመካከለኛው እንዲሁም በመካከለኛው ምስራቅ ስምጥ ሸለቆ አካባቢዎችና በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍሎች ከመደበኛ በታች ዝናብ መዝነቡን ጠቅሶ በነሐሴ ወር በነዚህ አካባቢዎች የዝናቡ መጠን ሊጨምር እንደሚችል ተንብይዋል፡፡
በዘንድሮ ክረምት የተፈጠረው የዝናብ እጥረት የኤሊኒኖ ክስተት ውጤት መሆኑን የአየር ትንበያ ባለሙያው ዶ/ር ድሪባ ቆሪቻ ጠቅሰው፣ በፓስፊክ ውቅያኖስ አካባቢ የተፈጠረውን ሙቀት መጨመር ተከትሎ የዝናብ እጥረቱ መፈጠሩን ገልፀዋል። በነሐሴ ወር የዝናቡ ሁኔታ በሚፈለገው መጠን እንደሚዘንብና ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ብሄራዊ ሜትሪዎሎጂ በመግለጫው ጠቁሟል፡፡

ተቋሙ ከኢትዮጵያ ጋር መስራቴን  ሙሉ ለሙሉ አቋርጫለሁ ብሏል

አለማቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ሂዩማን ራይትስ ዎች ለኢትዮጵያ የመረጃ ጠለፋ ቴክኖሎጂዎችን ሸጧል፤ ለደህንነት ባለሙያዎች ስልጠና በመስጠት የዜጎች መብቶች እንዲጣሱ እገዛ አድርጓል ያለውን “ሃኪንግ ቲም” የተባለ የጣሊያን ተቋም በጉዳዩ ዙሪያ በቂ ምላሽ አልሰጠም፣ የመብቶች ጥሰቶችን ለማስቆምም እርምጃ አልወሰደም ሲል ከሰሰ፡፡
ሃኪንግ ቲም ለተለያዩ አገራት መንግስታት የመረጃ መጥለፊያ ቴክኖሎጂዎችን በመሸጥና ለባለሙያዎች ስልጠና በመስጠት፣ መንግስታት የዜጎችን ሰብአዊ መብቶች እንዲጥሱ እገዛ ያደርጋል ያለው ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ በኢትዮጵያ ሲከናወን የቆየውን የመረጃ ጠለፋና የመብቶች ጥሰት በተመለከተ ምላሽ እንዲሰጠው ቢጠይቅም በቂ ምላሽ ሊሰጠው እንዳልቻለ ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ተቋሙ ጉዳዩን በተመለከተ ምርመራ ለማድረግም ሆነ የኢትዮጵያ መንግስት ቴክኖሎጂውን በመጠቀም በዜጎቹ ላይ የሚያደርሰውን የመብቶች ጥሰት ለማስቆም ምንም አይነት ተጨባጭ እርምጃ አልወሰደም ሲል የከሰሰው ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ ሃኪንግ ቲም ለኢትዮጵያ የደህንነት ባለሙያዎች የግለሰቦችን ኮምፒውተሮች ሰብረው መግባት የሚችሉበትን ስልጠና መስጠቱን እንደቀጠለና ቀጣይ ስምምነቶችን ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀምሮ እንደነበር የሚያረጋግጡ መረጃዎችን በሃምሌ ወር እንዳገኘ አስታውቋል፡፡
ሃኪንግ ቲም ለኢትዮጵያ መንግስት የሸጣቸው የመረጃ መጥለፊያ ቴክኖሎጂዎች ከቫይረስ መከላከያ ፕሮግራሞች አቅም በላይ እንደሆኑና በቀላሉ ወደ ግለሰቦች ኮምፒውተሮች በመግባት መረጃዎችን እንደሚወስዱ የጠቆመው ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ ከተቋሙ ኢሜይል አፈትልከው የወጡ መረጃዎችም ተቋሙ በሚያዝያ ወር ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ከ700 ሺህ ዶላር በላይ የሚገመት አዲስ የቴክኖሎጂና የስልጠና ስምምነት ለመፈጸም ሲያደርጉት የነበረው እንቅስቃሴ ሳይሳካ መቅረቱን ያመለክታሉ ብሏል፡፡
ሃኪንግ ቲም ጉዳዩን በተመለከተ ምላሹን እንዲሰጥ ባለፈው ሃምሌ ወር ላይ ከሂውማን ራይትስ ዎች ለቀረበለት ጥያቄ በሰጠው ምላሽም፣ የሚያመርታቸው ሶፍትዌሮች የሚንቀሳቀሱት በእሱ ሳይሆን በገዙት ደንበኞቹ መሆኑን ጠቁሞ፣ ቴክኖሎጂው ለስለላ ተግባር ስለመዋሉ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ገልጾልኛል ያለው ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ ከተቋሙ አፈትልከው የወጡ መረጃዎች ግን የኢትዮጵያ መንግስት የስለላ ተግባራት የሰብአዊ መብቶችን የሚጥሱ መሆን አለመሆናቸውን ለማጣራት በርካታ አጋጣሚዎች እንደነበሩት የሚያመለክቱ ናቸው ብሏል፡፡
ተቋሙ በዚሁ ምላሹ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ያለውን ግንኙነት በ2015 የመጀመሪያዎቹ ወራት ሙሉ ለሙሉ አቋርጫለሁ ማለቱንም ሂውማን ራይትስ ዎች ጠቁሟል፡፡

 
Sidamigobba, or Sidama country, extends along the Great Rift Valley from Lake Hawassa in the north to the town of Dilla in the south and from Mount Garamba in the east to the Bilaatte River in the west. The Sidama are one of the original ...

Read more at: Link