POWr Social Media Icons

Saturday, April 18, 2015

‹‹ቅጽ አራት ከተሞላ በኋላ ራስን ማግለል አይቻልም›› ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በወላይታ ዞን በቦሎሶሶሬ 2 የምርጫ ክልል ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር ለውድድር ከቀረቡት ዕጩ ተወዳዳሪዎች መካከል፣
የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ)ን ወክለው ለውድድር ቀርበው የነበሩት አቶ ተስፋዬ ኃይሌ ራሳቸውን ከምርጫው ማግለላቸውን ለሪፖርተር አስታወቁ፡፡
‹‹ከምርጫው ራሴን ለማግለል ስወስን ምንም ዓይነት ተፅዕኖ አልደረሰብኝም፤›› ያሉት አቶ ተስፋዬ፣ በገጠሙዋቸው አንዳንድ የግል ጉዳዮችና የገንዘብ እጥረት ምክንያት ከምርጫው ራሳቸውን እንዳገለሉ ገልጸዋል፡፡ 
የመድረክ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጥላሁን እንደሻው በበኩላቸው፣ ‹‹አባላችን ራሳቸውን ከምርጫ ያገለሉት በገጠማቸው ማስፈራርያና ማባበያ ምክንያት ነው፤›› በማለት በደረሰባቸው ጫና ከምርጫው ራሳቸውን እንዳገለሉ አመልክተዋል፡፡ 
ከዚህ ቀደም በየካቲት ወር እኚሁ ዕጩ ተወዳዳሪ ለእስር ተዳርገው እንደነበር ያስታወሱት አቶ ጥላሁን፣ ነገር ግን መድረክ ባቀረበው ተደጋጋሚ አቤቱታ ከእስር እንደተፈቱ ገልጸዋል፡፡ 
አቶ ተስፋዬ ከእስር ከተፈቱ በኋላ ከምርጫው ውድድር ራሳቸውን ማግለላቸውን ለፓርቲው አሳውቀው፣ ከፓርቲው ጋር የነበራቸውን ግንኙነት እንዳቋረጡ ገልጸዋል፡፡ 
ዕጩ ተወዳዳሪው ራሳቸውን ከምርጫው ማግለላቸውን ለመድረክ ከማሳወቅ በዘለለ ያቀረቡት ምንም ዓይነት ምክንያት እንደሌለ የገለጹት አቶ ጥላሁን፣ ግለሰቡ ከዕጩነት እንጂ ከፓርቲው ራሳቸውን ማግለል አለማግለላቸው እስካሁን ድረስ እንደማይታወቅ ጠቁመዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ለሪፖርተር ማብራሪያ የሰጡት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደምሰው በንቲ በበኩላቸው፣ ‹‹ግለሰቡ አሁንም ቢሆን ተወዳዳሪ ነው፡፡ በስሙ የመወዳደሪያ መልዕክቶችን እያዘጋጀና እየለጠፈ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ ራሱን አገለለ የሚባል ተወዳዳሪ የለም፤›› ብለው፣ ‹‹ዕጩ ተመዝጋቢው የመወዳደር ፍላጐት ባይኖረው እንኳን ቅጽ አራት ተሞልቶ ወደ ኅትመት ከገባን በኋላ ራሱን ማግለል አይችልም፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
‹‹ይህ የሕግ አግባብ መከበር አለበት፤›› ያሉት አቶ ደምሰው፣ ለምርጫ ክልሉም ሆነ ለቦርዱ በጉዳዩ ላይ የቀረበ ምንም ዓይነት ደብዳቤ እንደሌለ አስታውቀዋል፡፡
አምስተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ የፊታችን ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. የሚካሄድ ሲሆን፣ ከገዥው ፓርቲ በመቀጠል በርካታ ዕጩዎችን ያስመዘገበው መድረክ ነው፡፡ መድረክ በአሁኑ ጊዜ አራት ፓርቲዎችን በአባልነት ታቅፈውበታል፡፡ እነዚህ አራት ፓርቲዎችም የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን)፣ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ አረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉዓላዊነት (ዓረና) እና የኢትዮጵያ ማኅበረ ዴሞክራሲያዊ-ደቡብ ኅብረት አንድነት ናቸው፡፡
4ኛው የጣና ፎረም በባህር ዳር ተጀምሯል(ኤፍ.ቢ.ሲ) አራተኛው የጣና ፎረም በባህርዳር ከተማ ተጀምሯል።
ጉባኤው “ሴኩላሪዝም እና ፖለቲካ ጠቀስ የሃይማኖት እንቅስቃሴ” በሚል መሪ ቃል ነው እየተካሄደ ያለው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ የማሊ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ እና ሩዋንዳ መሪዎችን ጨምሮ የታንዛኒያና ቦትስዋና የቀድሞ ፕሬዚዳንቶችና ሌሎች እንግዶች የጉባኤው ተሳታፊዎች ናቸው። 
ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም በፎረሙ ላይ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል።
የተለያዩ ሀገራት ምሁራንም በእምነት ላይ በተመሰረቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ ጥናታዊ ጽሁፎች እየቀረቡ ነው።
በጉባኤው የመላው አለም የሰላም እና ፀጥታ ፈተና የሆነው አክራሪነት ዋና መወያያ ርእስ ይሆናል።
የሴኩላሪዝም ብያኔ፣ ሴኩላሪዝም መከባበርንና ህበረ ብሄራዊነትን ከማስተናገድ አንፃር ያለው ሚና፣ የውጭ ሃይሎች የፖለቲካ ሽፋን ያለው የሃይማኖት እንቅስቃሴን የማራገብ ሁኔታ በጉባኤው ይዳሰሳሉ።
ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት በሚዘልቀው ፎረም የዜጎች የሃገር ፍቅር ግንባታ እና ማህበራዊ ለውጥ በአፍሪካም ይገመገማል።
(ኤፍ.ቢ.ሲ) 19ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ እና ነገ በሚደረጉ ጨዋታዎች  ይቀጥላል።
መከላከያ ከአዳማ  ዛሬ ይጫወታሉ።
ነገ የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጰያ ቡና 10 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚያደርጉት የሸገር ደርቢም ትልቅ ግምት አግኝቷል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ኔይደር ዶስ ሳንቶስን፤ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ጥላሁን መንገሻን በተመሳሳይ የውጤት ማጣት ምክንያት ማሰናበታቸው ይታወሳል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስን ምክትል አሰልጣኝ በነበሩት ፋሲል ተካልኝ እና ዘሪሁን ሸንገታ እየተመራ ታላቁን ድርቢ የሚያደርግ ይሆናል፡፡ 
ኢትዮጵያ ቡናም በተመሳሳይ ምክትል አሰልጣኝ በነበረው አንዋር ያሲን መሪነት ጊዮርጊስን ይገጥማል፡፡ 
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ18 ጨዋታዎች 35 ነጥብ በመያዝ በሊጉ አናት ላይ ተቀምጧል፡፡
ቡና ደግሞ ከተመሳሳይ 18 ጨዋታዎች በ7 ነጥብ ዝቅ ብሎ በሊጉ አራተኛ ደረጃ ይገኛል፡፡
ፕሪሚየር ሊጉን በሁለተኝነት እየተከተለ ያለው ሲዳማ ቡናም ደደቢትን በይርጋለም ይገጥማል።
የወራጅ ስጋት ያለባቸው ዳሽን እና ሙገር ሲሚንቶ ደግሞ ነገ በአሰላ 9 ሰዓት ላይ የሚገናኙ ይሆናል።
የፊታችን ሰኞ ኤሌክትሪክ በወራጅ ቀጠና ከሚገኘው ወልዲያ ከነማ ሲጫወት፤ ወላይታ ዲቻ ሀዋሳ ከነማን ያስተናግዳል።

ህንድ በርበሬ የሚረጭ “አድማ በታኝ ድሮን” ልትጠቀም ነው
 “በርበሬን የመረጥነው የከፋ ጉዳት ስለማያደርስ ነው” - የአገሪቱ ፖሊስ
   በሰሜናዊ ህንድ የምትገኘው ኡታር ፕራዴሽ ግዛት ዋና ከተማ የሆነችው የላክኖው ፖሊስ፣ ከአየር ላይ በርበሬ የሚረጩ አነስተኛ አድማ በታኝ ድሮኖችን በስራ ላይ ማዋል ሊጀምር ነው ሲል ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ዘ ኢንዲያን ኤክስፕረስ ጋዜጣን ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ የግዛቷ ፖሊስ ህገወጥ ተቃውሞ የሚያደርጉ ዜጎችን ለመበተን የሚያስችሉና እያንዳንዳቸው 2 ኪሎ ግራም በርበሬ የመጫን አቅም ያላቸው አምስት አነስተኛ ድሮኖችን በስራ ላይ ለማዋል ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡
“ህገወጥ አመጽ የሚያካሂዱ ዜጎችን በርበሬ እየረጨን እንበትናለን፡፡ ይህን ያልተለመደ የአድማ ብተና መሳሪያ ለመጠቀም የመረጥነው፣ በአመጹ ተሳታፊዎች ላይ የከፋ ጉዳት የማያደርስ በመሆኑ ነው፡፡ ህገወጥ ተቃውሞዎችንና የጎዳና ላይ አመጾችን በቁጥጥር ውስጥ በማዋል ረገድ ውጤታማ እንደሚሆንም ተስፋ አለን” ብለዋል ያሻዝቪ ያዳይ የተባሉት የግዛቲቱ ከፍተኛ የፖሊስ ባለስልጣን፡፡
የግዛቲቱ አስተዳደር ባለፈው አመት ባደረገው ሙከራ፤ በርበሬ የሚረጩ ድሮኖች አድማን በመበተን ረገድ ውጤታማነታቸውን በማረጋገጡ፣ ለእያንዳንዳቸው 10ሺህ ዶላር የከፈለባቸውን ድሮኖች በስራ ላይ ለማዋል መወሰኑንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
ህንድ በርበሬ የሚረጩ አድማ በታኝ ድሮኖችን በመጠቀም ከዓለማችን አገራት ቀዳሚዋ እንደሆነችም ዘገባው አክሎ ገልጿል።
ኣዲስ ኣድማስ
 የ1997 ዓ.ም የኮንዶሚኒየም ቤት ፈላጊዎች ምዝገባ ሂደት የተወሳሰቡ ችግሮች የነበሩበት በመሆኑ ለተመዝጋቢዎች የመረጃ ሰነድ መጥፋትና አሁን ድረስ ለዘለቁ በርካታ ቅሬታዎች መነሻ ሆኗል ተባለ፡፡ 
በወቅቱ ምዝገባው በአዲስ አበባ አስሩም ክፍለከተሞችና በሌሎች ተቋማት የተከናወነ ሲሆን ሁሉም ወገን የምዝገባ ተራ ቁጥሮችን ከ001 የጀመሩ በመሆናቸው መረጃዎቹ ወደ አንድ ማዕከል ሲሰባሰቡ የመደበላለቅ ችግር ፈጥሯል ያሉት የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ሥራ አሥኪያጅ አቶ መስፍን መንግስቱ፤ አንድ ግለሰብ በተለያዩ መዝጋቢ ተቋማት ሶስትና አራት ጊዜ የተመዘገበበት አጋጣሚ እንዳለም ገልፀዋል፡፡ 
የምዝገባ ማረጋገጫ የነበረውን ቢጫ ካርድ ተመሳሳይ ቁጥር እስከ 15 የሚደርሱ ግለሰቦች ይዘው ወደ ማዕከሉ እንደሚቀርቡ ያስረዱት አቶ መስፍን፤ “ሁሉም መረጃዎች በአንድ ማዕከል ተሰባስበው ከተራ ቁጥር 001 እስከ 453ሺህ ድረስ በመቀመጡ፣ እነሱ ቁጥራችን የሚሉትና ሲስተሙ የሚያውቀው የምዝገባ ቁጥር የተለያዩ ናቸው” ብለዋል፡፡ 
ለወቅቱ ቤት ፈላጊዎች ምዝገባ እንደ ችግር የተጠቀሰው ሌላው ጉዳይ የ97 ምርጫን ተከትሎ የተፈጠረው ግርግር መረጃን በተገቢው መንገድ ለማደራጀት አለማስቻሉ ነው ይላሉ አቶ መስፍን። በወቅቱ ከተማዋን እንዲያስተዳድር አደራ የተሰጠው የባለአደራ አስተዳደር ስራውን ተላምዶ ወደ ተግባር እስኪገባ ድረስ መረጃዎቹ በተገቢው መንገድ ተይዘው ነበር ለማለት አያስደፍርም ብለዋል - ሃላፊው፡፡ 
በወቅቱ የተበላሸውን ለማስተካከል በርካታ ስራዎች መሠራታቸውን የጠቀሱት ሃላፊው፤ በ2005 ዓ.ም በተደረገው ምዝገባ፤ “መረጃን ጠፍቶብናል” ያሉ ቤት ፈላጊዎች በነባር የምዝገባ ስርአት ውስጥ ተካተው እንዲስተናገዱ መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ 
የጋራ መኖሪያ ቤቶች መሠረተልማት ሳይሟላላቸው ለተጠቃሚዎች ይተላለፋሉ በማለት የቤት ባለቤቶች ቅሬታ የሚያቀርቡ ሲሆን የገላን ሶስት ኮንደሚኒየም ነዋሪዎች እስካሁን ድረስ የመብራት አገልግሎት እንደሌላቸው፣ በሌላው የገላን ሳይት ደግሞ የግቢው መንገድ በተገቢው መንገድ ባለመስተካከሉ ለአደጋ የተጋለጡ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ሃላፊው በበኩላቸው፤ የነዚህ ቅሬታዎች መነሻ ከመሠረተ ልማት ጋር ተያይዞ የነበሩ ክፍተቶች ናቸው ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የቤቶቹ ግንባታ 80 በመቶ ሲደርስ እድለኞች እንዲረከቡ ይደረግ እንደነበር የጠቆሙት ሃላፊው፤ በአሁን ወቅት ግን መቶ በመቶ ተጠናቀውና መሠረተ ልማት ተሟልቶላቸው እንደሚተላለፉ ገልፀዋል። በፊት ለነዋሪዎች መሠረተ ልማት ሳይሟላላቸው የተላለፉትም በአሁን ወቅት ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተሟላላቸው እንደሆነ ሃላፊው ጨምረው ገልፀዋል፡፡ “አካባቢውን ለኑሮ የሚመች ማድረግ ግን የነዋሪው ሃላፊነት ነው” ብለዋል ሃላፊው፡፡ 
በስም አሊያም በሌላ የማጭበርበር ዘዴ በህገወጥ መንገድ የኮንዶሚኒየም ቤት ተጠቃሚ የሆኑ ግለሰቦች ካሉ ህብረተሰቡ በጥቆማ ማጋለጥ እንደሚገባው ያሳሰቡት አቶ መስፍን፤ እንዲህ ያሉ ችግሮች በተደጋጋሚ  እንደሚያጋጥሙ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡  
ኣዲስ ኣድማስ