ትኩረት ለእንሰት !

ትኩረት ለእንሰት !እንሰት በአብዛኛው የደቡብ ክልል ዞኖችና በተወሰኑ የኦሮሚያ  አከባቢዎች የሚመረት ተወዳጅ የምግብ ተክል ከመሆኑም ባሻገር የህብረተሰቡ የክብር መገለጫም ተደርጎ ይወሰዳል።
የጉራጌ፣ ስልጤ፣ ሃዲያ፣ ከንባታ፣ ወላይታና ሲዳማ ዞኖች ለረጅም ዘመናት እንሰትን በማምረት የሚጠቀሱ ናቸው።
በአሁኑ ጊዜ በእንሰት አምራችነቱ የሚታወቀው የሃዲያ ህዝብ ኑሮ ለረጅም ዓመታት በእንስሳት እርባታ ላይ የተመሰረተ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።
ነገር ግን በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ በተከሰተው በሽታ የእንስሳት ሃብቱ በማለቃቸውና  የሸዋ ወራሪ ሃይል አካባቢው መቆጣጣሩን ተከትሎ የግብርና ምርቶችን በግብር መልክ እንዲያቀርብ በመገደዱ ምክንያት የእርሻ ስራ እንዲላመድ በር መክፈቱን አቶ አለባቸው ኬዕምሶ እና አቶ ሳሙኤል ሃንዳሞ የተባሉ የታሪክ ምሁራን ያስረዳሉ።
በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ እና በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ በአካባቢው ከታወቁ የእርሻ ምርቶች መካካል የእንሰት ተክል በዋናነት ይጠቀሳል። እንሰት በአከባቢው ቀድሞ የታዋወቀው ለዞኑ አጎራባች በሆኑት የጉራጌና የከምባታ ዞኖች መሆኑ ይነገራል።
በተለይም ከ1900 እስከ 1970 ዓ.ም ድረስ በነበረው ጊዜ ውስጥ የአከባቢው ህብረተሰብ የተክሉ ጠቃሜታዎች በስፋት በመረዳቱ በከፍተኛ ደረጃ ያመርተው  እንደነበር መረጃዎች ያመላክታሉ።
ዘውዳዊ አገዛዙን መገርሰሱን ተከትሎ የመንግስትነት ስልጣን የተቆናጠጠው ወታደራዊው የደርግ ስርዓት በ1974 ዓ.ም የአከባቢውን ህዝብ በሰፈራና በመንደር ማሰባሰብ ሰበብ ህዝቡ ተረጋግቶ ይኖርበት ከነበረው አከባቢ ያለፈላጎቱ ከቀየው እንዲፈናቀልና መንግስት የሚፈልጋቸውን የስንዴና የበቆሎ ምርቶች ብቻ እንዲያመርት በመገደዱ ምክንያት የእንሰት ምርት ስራ ተቀዛቅዞ ነበር።
ሆኖም በ1983 ዓ.ም የደርግን የአገዛዝ ስርዓት በማክተሙ ዜጎች ያለ ፍላጎታቸው ተገድደው የመሰረቱት የመንደር እና የሰፈራ ፕሮግራም በመተው በፈለጉትና በመረጡት ቦታ የመኖር እድል በማግኘታቸው እንሰት የማምረትን ስራ አጠናክረው ቀጥለውበታል ።
የሃዲያ ህዝብ እንሰትን በማልማት  ለምግብነት መጠቀም ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የተክሉ ጠቀሜታ ጎልቶ እየታየው በመምጣቱ በልዩ ፍቅር ያመርተዋል ። ይንከባከበዋል ።እንሰት ከምግብነቱ ባሻገር ለእንስሳት መኖም ተመራጭ እንደሆነ ነዋሪዎቹ ይመሰክራሉ ።
ከእንሰት ምርት ከ10 በላይ የምግብ አይነቶችን ማዘጋጀት የሚቻል ሲሆን ተረፈ ምርቱን ዘርፈ ብዙ አገልግሎት አለው ይላሉ ።
ለአብነትም ከእንሰት ተረፈ ምርት የተለያዩ የቤት ውስጥ መገልገያ እቃዎችን ማዘጋጀት ይቻላል ።አንዳንድ የተክሉ ዝርያዎች ደግሞ ለሰውና ለእንስሳት መድሃኒተነት ያገለግላሉ ።
እንሰት እድገቱን ለመጨረስ በአማካይ ከአምስት እስከ ስድስት ዓመታት የሚጠይቅ ሲሆን ተከሉ ምንም አይነት ዘመናዊ ማዳበሪያዎችን ሳይፈልግ በተፈጥሯዊ ብስባሾች ብቻ የሚያድግ በመሆኑ አዋጭነቱ የላቀ ያደርገዋል።
ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተከሰተው የእንሰት አጠውልግ በሽታ ተክሉ እንዲመናመን አድርጎታል ። ከዚህ የተነሳም አንዳንድ አርሶ አደሮች ተክሉን ማምረት እንዲያቆሙ እየተገደዱ ነው።
አካባቢው ስንዴ፣ ጤፍ፣ ባቄላ፣ በቆሎ የመሳሳሉ አዝዕርቶችንና  የተለያዩ አትክልቶችንና ፍራፍሬዎችን የሚያበቅል ቢሆንም ሰብሎቹን ለገበያ ለማቅረብ እንጂ ለቤት ውስጥ ፍጆታ በስፋት የሚጠቀሙት እንሰትን ነው ።
በሃዲያ ዞን ሌሞ ወረዳ የቦቢቾ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ አለሙ ሱለንቆ የ9 ልጆች አባት ሲሆኑ ኑሯቸው በዋናናት በእንሰት ምርት ላይ የተመሰረተ ነው።
በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ እንሰትን በመትከል ለምግብነት ከመጠቀም ባሻገር ለገበያ በማቅረብ ሌሎች ለቤቱ አስፈላጊ የሆኑትን ነገር በመሸመት የቤተሰባቸውን ኑሮ ይመሩ ነበር።
ታዲያ አቶ አለሙ እንደሚናገሩት ካለፉት አራት አመታት ወዲህ በተከሰተው የእንሰት አጠውልግ በሽታ ምክንያት የነበራቸውን የእንሰት ሃብት ሙሉ በሙሉ ማጣታቸውን ይናገራሉ።
በበሽታው ምክንያት በጠፋው የእንሰት ተክል ምትክ መሬታቸውን በሌሎች ሰብሎች ለማምረት  ቢገደዱም ገቢቸውንም ሆነ የቀለብ ፍጆቻቸው የእንሰትን ያክል ሊሆንላቸው አልቻለም ።
በዞኑ የሚሻ ወረዳ ኗዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ካሾ አርሲዶ ያለአባት የሚያሳድጉዋቸው የአምስት ልጆች  እናት ናቸው ። ከቅድመ አያታቸው ጀምሮ ኑሯቸው በዋናነት በእንሰት ተክል ላይ የተመሰረተ እንደነበር ያስታውሳሉ ።
በአሁኑ ወቅት ግን የእንሰት አጠውልግ በሽታ በኑሮአቸው ላይ ትልቅ ፈተና ሆነባቸዋል ። በምግብ ዋስትና መረጋገጥ ላይ ጋሬጣ ሆኗል ። በመሆኑም መንግስት ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የምርምር ማእከላት ልዩ ትኩረት ሰጥተው መፍትሔ እንዲፈልጉለት ጠይቀዋል ።
የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ታምራት በየነ እንደገለፁት በሃዲያ ከሚገኙ ከ11 ወረዳዎች መካከል 7ቱ እንሰት አብቃይ ናቸው ። ከአጠቃላይ የዞኑ ህዝብ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው  ኑሮው በእንሰት ምርት ላይ የተመሰረተ ነው።
በአብዛኞቹ እንሰት አብቃይ አከባቢዎች በሽታው በመከሰቱ ምክንያት በእንሰት ምርትና ምርታማነት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ እየጨመረ መጥቷል ። የተጠናከረ የበሽታ መከላከልና የኤክስቴንሽን ስራ አለመካሔዱ ደግሞ ችግሩ እንዲባባስ አድርጎቷል ።ይህ ደግሞ የተክሉ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ በወጉ ካለመረዳት የሚመነጭ ነው ብለዋል ።
አሁን ግን የዞኑ ግብርና መምሪያ፣ በእንሰት አብቃይ ወረዳዎች የሚገኙ የግብርና ቢሮዎችና የተለያዩ መንግስታዊና መንግታዊ ያልሆኑ የጥናትና ምርምር ተቋማት ችግሩን በአፋጣኝ ለመቅረፍ በሽታ የሚቋቋሙ የእንሰት ዝሪያዎች ለአርሶአደሩ እንዲደርስ በማድረግ ላይ ናቸው ። ዘመናዊ የእንሰት አመራረት ዘዴዎችን የተመለከተ ስልጠናውም ለተግሉ ተጠቃሚዎች እየተሰጠ መሆኑን አስረድተዋል ።
በተለይም በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ለተክሉ ልዩ ትኩረት በመስጠት የአካባቢው አርሶ አደሮች በስፋት እና በጥራት በማምረት ከአከባቢው ፍጆታ በሻገር ለአገር አቀፍ ገበያ ማቅረብ እንዲችሉ ርብርብ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
ዋቸሞ ዩንቨርሲቲ፣ አፍሪካ ራይዝንግ የተባለ የምርምር ተቋም፣ አረካ ፣ እና ወረቤ ምርምር ተቋማት በተክሉ ላይ ሰፊ ጥናት ምርምር በማካሄድ ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል ።
የአፍሪካ ራይዝንግ ድርጅት የሆሳዕና ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ወርቅነሀ ዱባለ እንደሚናገሩት እንሰት ለምግብነት ካለው ጠቃሜታ ባሻገር ዘመናዊ የመድሃኒት ፋብሪካዎችም በስፋት የሚፈልጉት ነው ይላሉ ። የእንሰት ንጥረ ነገር የሆነውን ቡዕላ ማጣበቂያዎችን ለመስሪያነት እንደሚያገለግልም አስረድተዋል ። ሆኖም ግን የእንሰት አጠውልግ በሽታው ምርቱን እንዲያሽቆለቁል አድርጎታል ባይ ናቸው ።
ድርጅታቸው ችግሩን አሳሳቢ በመሆኑ ከሌሎች የምርምር ተቋማት ጋር በመተባበር ላለፉት ሁለት ዓመታት የበሽታውን ዋና መንስኤ የመለየትና ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ለማፈላለግ ጥናት ሲያካሄድ መቆየቱን ያወሳሉ።
በጥናቱ መሰረትም የበሽታው ዋና መንስኤ ባክቴሪያ መሆኑ ተረጋግጧል ። ባክቴሪያው በአፈር ውስጥ ከአንድ እንሰት ወደ ሌላው እንደሚዛመት ነው የሚናገሩት። በእንሰት መቁረጫ መሳሪያዎች ጭምር በቀላሉ የሚተላለፍም ነው ብለዋል ።
አቶ ወርቅነህ እንደሚናገሩት ጥናቱ መሰረት በማድረግ በዞኑ ውስጥ በሁለት ቀበሌዎች በሚገኙ 27 አርሶ አደሮቸ ማሳ ላይ በሽታውን መከላከል የሚችሉ የእንሰት ዝሪያዎችን የማባዛት ስራ እየተካሄደ ይገኛል።
ጥናቱ በሚቀጥሉ አራት ዓመታት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለአርሶ አደሩ ይፋ የሚሆን ሲሆን  ዝሪያዎቹ በሽታ የሚቋቋሙ ስለመሆናቸው  ለህዝቡ በማሳወቅ በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግና በዝሪያዎቹ ላይ የዘረ መል ትንታኔ በማካሄድ ዝሪያዎቹ በሽታ የሚቋቋሙ ስለመሆናቸው እውቅና እና ስያሜ የመስጠት ስራ ይሰራል።
ምርምር ማካሄድ አስፈላጊ መሆኑን አያጠያይቅም ። ዋናው ቁም ነገር ግን የምርምር ግኝቶችን በማላመድ ለአርሶ አደሮች በፍጥነት ደርሰው በምርትና ምርታማነት ላይ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ማድረጉ ላይ ነው ።ተመራማሪዎቻችን በዚህ ዙሪያ በርቱልን እንላለን ። ቸር እንሰንብት !።
- See more at: http://www.ena.gov.et/index.php/component/k2/item/8076-2015-09-27-21-37-23#sthash.0MQ1EQhX.dpuf

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር