ጉዞ ወደ ጥበበኞቹ አገር

በዘንድሮው በዓል አዛውንቶች (አያንቱዎች) የበዓሉ ድምቀት ሆነው ሰንብተዋል፤

በአንድ አገር ውስጥ ማህበረሰባዊ የተቋም ሽግግር እንዲመጣ፣ የህዝቦች የጋራ እሴት እንዲጎለብት እና የትውልድ ቅብብሎሽ መኖር መሰረታዊ ስለመሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም። ሀገር ያለ ሰው አይደምቅም። ሰውም ያለ ሀገር አይፈጠርም። ለሀገር ዘመን ተሻጋሪ ድርና ማጉ ህዝብ ነው። የአንድ ህዝብ ታሪክ መሰረቱ የተከታታይ ትውልዶች ሥራ ነው።
እያንዳንዱ ትውልድ ማህበራዊ አንድነቱንና አብሮ የመኖር ህልውናው አረጋግጦ ለሚቀጥለው ትውልድ የሚያስተላልፈው እሴት የዛ ህዝብ የማንነት መገለጫ ነው። የአንድ ህዝብ አገር በቀል እውቀት፣ ልምድ፣ ትውፊታዊ እምነት፣ ወግና ስርዓት፣ ያለፉትን ተከታታይ ትውልዶች ከዛሬው ከወደፊቱ ትውልዶች ጋር የሚያገናኝ፣ የሚያስተዋውቅና የሚያስተሳስር ሰንሰለት ነው። ያ ህዝብ የራሱን የኑሮ ዘይቤ በመደንገግና በመቅረፅ ሥርዓት ባለው መልኩ ህይወቱን ለመምራት ያደረጋቸው የለውጥ ሂደቶች የስብዕናው መገለጫዎችም ሆነው ይስተዋላሉ።
ጉዞአችን በደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ ነው። የሲዳማ ህዝብ በደቡብ ክልል ከሚገኙ ብሄር ብሄረሰቦች ህዝቦች መካከል አንዱ ነው። ዞኑ በሰሜን ምስራቅና በደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ ክልል እንዲሁም በስተምዕራብ የወላይታ ዞን ያዋስኑታል። የሲዳማ ህዝብ የራሱ የሆነ ቋንቋ ፣ የዘመን አቆጣጠር፣ ባህል፣ ስርዓት፣ ትውፊት፣ ወግና ሥርዓት ያለው ነው። ቋንቋው ሲዳምኛ ነው።
የሲዳማ ብሄር የማንነቱ መለያና መገለጫ የሆኑ የበርካታ ባህላዊ ፣ታሪካዊና ማህበራዊ የአኗኗር ዘይቤ እሴቶች ባለቤት ነው። ከእነዚህ መካከል የፊቼ ጨምበላላ በዓል ዋና እና ቀዳሚው ከሆኑ ባህላዊ እሴቶች ይመደባል። የሲዳማ ዘመን መለወጫ ፊቼ ጨምበላላ የሚውልበት ዕለትና ለበዓሉ የሚሰጠው ቦታና ትርጉም እንዲሁም ከህይወቱና ከማንነቱ ጋር ካለው ቁርኝት የተነሳ የብሄሩ ተወላጆች በዓሉን ሲያከብሩ የሚጠበቅባቸውን ሥነ ሥርዓትና ሥነ ምግባር የተመልካቹን ቀልብ ከሚገዙ ትዕይንቶች መካከል ተጠቃሽ ነው።
የሲዳማ ህዝብ በአብዛኛው ልዩ ቃና ባለው ቡና አምራችነቱ ይታወቃል። የሲዳማን ብሄር ከሌላው ልዩ የሚያደርገው ህዝቡ ከጥንት ጀምሮ ሲመራባቸውና ሲተዳደርባቸው የነበሩ ክዋኔዎችና እሴቶችን ጠብቆ ያቆየበት መንገድ ነው። እኔም በዝና ብቻ ለማውቃትና « የተመለከቷት ተመልሰው ለመምጣት ይቸገራሉ» ወደ ተባለላት የሲዳማ ዞንን ለማየት በጣም ጓጉቼአለሁ። ለዚህም ነው በጠዋት የጉዞ አቅጣጫዬን ወደ እዚያው ያስተካከልኩት። የጉዞአችን ዋነኛ ዓላማም የዘንድሮውን የሲዳማ ዘመን መለወጫ በዓል ጨምበላላን ለመታደም ነው።
ሲዳማዎች የራሳቸው የዘመን አቆጣጠር መርህ አላቸው። እንዴት ከተባለም፣ በእጅ የያዙት ወርቅ ሆኖብን እንጂ የሲዳማዎቹ አያንቱዎች ጥበብ በመሬት አካል ዙሪያና ከዛ ውጪ የሚገኙ ክስተቶችን የሚያጠና ጥንታዊ ሳይንሶች ክፍል የሚመደበው ሥነ ፈለክ ( አስትሮኖሚ ) ሊቅ ናቸው ማለት ይቻላል። ሲዳማዎች ከዚህ አኳያ ሲቃኙም የከዋክብትና የጨረቃዎችን ጥናት ተክነዋል ቢባልም አይደንቅም። ሲዳማዎች የወቅቶችን ዑደት ምስጢር ከራሷ ከተፈጥሮ ገፀ በረከት በመነሳት የሚያውቁበትና ዘመናት የተገለገሉበት ልዩ ክህሎት አላቸው።
የሲዳማ ብሄር ከዘረጋቸው ባህላዊ እሴቶች መካከል የጊዜ፣ የቀናት፣ የወራት፣ የዓመታትንና የወቅቶችን ዑደት ምስጢር ከራሷ ከተፈጥሮ ገፀ ባህሪ በመነሳት የጊዜን ምስጢር ማወቅ የቅድመ አባቶች አበይት ተግባር በመሆኑ ነው። ሲዳማዎች ዓለም እንደዛሬው በቴክኖሎጂ ሳይንበሸበሽ የአየር ትንበያ መሳሪያቸውም ሳይፈጠሩ፣ ዘመናዊ የእጅና የግድግዳ ሰዓቶች ሳይመረቱ በፊት ገና ያኔ ጥንት ቀናትን የሚቆጥሩበት ለህይወት ትርጉም የሚሰጡበት የዘመን አቆጣጠር ሂደት በቅድመ ጥናት አባቶች ምርምር በማድረግ ህይወትን በጊዜ ስሌት ያጣጥማሉ።
ወደ እዚህ ምድር በመምጣትና መኖር ብቻውን ለሲዳማዎች የኑሮ ግብ አይደለም። ይልቁንም በምድር የመኖር ትልቅ ገፀ በረከት ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ብቻ ሳይሆን ቀናት ቀናትን እየወለዱ የሚፈጠሩ ወራት ተንትነው የሚፈራረቁትን ወቅቶች በባህሪያትና ልዩነት ጭምር በማጤን በሁሉም ወቅቶች ራሳቸውን እንዴት እንደሚያኖሩ በመረዳት ውጤታማ ህይወት መምራት መቻላቸው ነው። ስለሆነም በብሄሩ ባህላዊ እሴቶች፣ መካከል የጊዜ፣ የቀናትን፣ የወራት፣ የዓመታትንና የወቅቶችን ዑደት ምስጢር ከሯሷ ከተፈጥሮ ገፀ በረከቶች በመነሳት የጊዜ ቀመሮችን ማወቃቸው የቅድመ አባቶች አበይት ተግባር ነው።
ለሲዳማዎች የስልጣኔ ጅማሬ ህይወትን ከዘመን አኳያ ትርጉም መስጠት አንዱ በመሆኑ አካባ ቢያቸውን ለማወቅ መመራመር ጀመሩ። ጅማሬያቸውም አንገታቸውን ወደ ሰማይ ቀና ሲያደርጉ የሚያዩት ውብ ሰማይ በቀንና በምሽት ዑደት ውስጥ የሚታይበት የመንጋትና የመምሸት፣ የመብራትና የመጨለም ተለዋዋጭ ሂደት የጊዜ ምስጢር መነሻ መሆኑን በማወቅ እንደዋዛ በሚመሸውና በሚነጋው ዓለም ውስጥ አንድ ምስጢር እንዳለ ተገነዘቡ።
በማለዳ የምትወጣው ፀሐይ በምሽት የምትፈንዳው ጨረቃ ውበትን ቀና በማለትና አንጋጠው በመመለከት በተፈጥሯዊ ትዕይንት ከመደሰት በዘለለ አንዳች ምስጢርን መፈለግ የሲዳማ አዋቂዎች ወይም በቋንቋቸው (አያንቱዎች ) ዓይነተኛ የጥበብ ጀማሬ ነው። በተለይ በምሽቱ ውስጥ አልፎ አልፎ የጨረቃዋ ክስተት አንዳንዴ ደግሞ ብርሃኗን የምትነፍገው ጨረቃ የሲዳማን አያንቱዎች አስተሳሰብ ሰርቆታል። በተለይ በሰማዩ ላይ የሚስተዋለው ምሽታዊ ትዕይንት ረጃጅም ሌሊቶችን በደጅ በማደር ለመረዳት ከመሞከር በላይ በየምሽቱ የምትወጣው ጨረቃ በከዋክብት መታጀቧ ይበልጥ በትዕይንቱ እንዲሳቡ አድርጓል።
ጨረቃዋ እንደ ፈንዲሻ በሚፈኩ ከዋክብት ታጅባ ስትታይ ከዋክብት ለጨረቃዋ የሚሰግዱ ይመስላል። በዚህም የጨረቃና ከዋክብት ቁርኝት እንዳለው በመረዳት በሰው ልጅ ችሎታ ውስጥ ለብዙዎቹ የማይታሰበውን የኮከብ ቆጠራ ጥበብ ከሲዳማዎች አባቶች ለሁሉም ሳይሆን ለጥቂቶቹ የተሰጠ የጥበብ ምስጢር ነው።
ጨረቃ የምትወጣበትንና የማትወጣበትን ቀናት በመቁጠር ጭምር የቀናትንና የወራትን ብሎም የዘመናትን አቆጣጠር ሂደት የባህላቸው መሰረት ሆነ። ይህ ሁኔታ መምሸትና መንጋት የቀናት መፈጠር ውጤት ሲሆን፤ ቀናት ደግሞ ለወራት መፈጠር ብሎም የወራት መፈጠር ለወቅቶች መፈራረቅና ዓመታት መቆጠር ትልቅ ምስጢር መሆኑን ደረሱበት።
ሁሉም አያንቱዎች በያሉበት ሥፍራ የጨረቃን መውጣትና መግባት ወይም የብርሃንና ጨለማ ሂደት ተከትሎ የህብረ ከዋክብት አቅጣጫ ከጨረቃ አቀማመጥ ጋር በማገናዘብና በመቀመር የሲዳማን ባህላዊ የዘመን አቆጣጠር ይቆጥራሉ። ከዋክብቶቹን መቁጠር ጥልቅ የትኩረት ተመስጦንና ክፍት ልቦናን ይጠይቃል። ይህም ብቻ አይደልም፣ ከከዋክብት መቁጠር እስከ ሌሊት ድረስ ሊሆን ስለሚችል በብርዳማ ሌሊት በቀዝቃዛው ንጋት ሳይታክቱ የህብረ ከዋክብትን ሂደት መከታትልና መቁጠር ታላቅ ሰብዓዊ ጥንካሬንና አለመታከትንና መስዋዕትነትን ይጠይቃል።
ከዋክብቶችን በሌሊት መቁጠር በብዙ ተፈጥሯዊ ተግዳሮቶች የተሞላ መሆኑን የኮኮብ ቆጣሪነትን ሌላኛው ገፅታ ነው። የሰማዩ ሙሉ ገፅታ እይታ አድማስ እንደ ልብ ለማየት ሲያዳግትም ቆጠራውን ከቤት ውጪ በደጅ በማደር የሚከናወን ይሆናል። በዚህም ከሌሊት አራዊት ጋር ግብ ግብ መፍጠርም ሊኖር ይችላል።
በዚህ መልኩ በያሉበት ሆነው ቆጠራውን የሚያከናውኑት አዋቂዎች (አያንቱዎች) በአቅራቢያ ቸው ካሉ አያንቱዎች ጋር በመሆኑ ሲንጎ (ስብሰባ) በማድረግ ሁሉም የራሱ የቀመር ስሌት ለጨሜሳዎች ስብሰባ ያቀርባል። « ዩኒክ ኢትዮጵያ የሲዳማ ባህላዊ እሴቶችና ቱሩፋቶች » በሚል ከታተመው ብሮሸር ከሰፈረው መረጃ መረዳት እንደቻልኩት፤ አያንቱዎቹ ስለ ቆጠራቸው ሪፖርት የሚያደርጉት፣ ሁሉም በትክክል ቆጠራውን ማከናወናቸውን ለመገምገም ሲሆን፤ በዚህ ኡደት አብዛኛው ተመሳሳይ ነው።
ከዚያም በየአካባቢያቸው ወይም በየወረዳቸው ተሰብስበው የቆጠራውን ውጤት ካወቁ በኋላ በሌላ ወረዳ ላሉት ውጤታቸውን መልዕክት በመላክ የቆጠራውን ስሌት በመላ ሲዳማ ተመሳሳይ መሆኑን ያረጋግጣሉ። ብዙውን ጊዜ በዚህ ሁኔታ የሚፈፀሙ ሂደቶች ገዘፍ ላሉ ማህበራዊ መስተጋብር ሲሆን በዋነኝነት የዘመን መለወጫ በዓል ፊቼ ጨምበላላ የሚውልበትን ቀን ለማወቅ በጥቅም ላይ ይውላል።
የሲዳማ ብሄር የዘመን መለወጫ የፊቼ ጨምበላላ በዓልን ለማክበር ሲዘጋጅ ከምንም በላይ ቀልብ ይገዛል። የፊቼ ጨምበላላ በዓል ለብሄሩ የማንነቱ መገለጫ ከመሆኑም ባሻገር የልማት፣ የመከባበር፣ የመቻቻልና የአብሮነት ተምሳሌት ተደርጎም ይቆጠራል። የዘንድሮው የፊቼ ጨምበላላ በዓልም ሐምሌ 7 በሃዋሳ ሲዳሞ ባህል አዳራሽ በድምቀት ተከናውኗል። አይዴ ጨምበላላ!!


Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር