POWr Social Media Icons

Thursday, August 27, 2015

(ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያና ሳዑዲ አረብያ የኢትዮጵያውያን ሠራተኞችን መብት የሚያስጠብቀውን የሰራተኞች ቅጥር ስምምነት በመጪው መስከረም ሊፈርሙ ነው።
ኢትዮጵያና ሳዑዲ አረብያ የሠራተኞች ቅጥር ስምምነት ሊፈራረሙ ነውስምምነቱ የሳዑዲ አረብያ መንግሥት ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች ክፍያቸውን በወቅቱ እንዲያገኙ፣ ከማንኛውም አካላዊ ትንኮሳ የመጠበቅና ደህንነታቸው እንደተጠበቀ ወደ አገራቸው የመመለስ ኃላፊነት እንዳለበት ያስቀምጣል።
በሳዑዲ አረብያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጉዳይ አስፈፃሚ አቶ ተመስገን ዑመር እንደገለጹት፥ ስምምነቱ በሳዑዲ ዓረቢያ ተቀጥረው የሚሰሩ ኢትዮጵያውያንን የክፍያና የሥራ ሁኔታን የሚቀይር ነው።
በአሰሪዎቻቸው ከሚደርስባቸው ጭቆና የመጠበቅና የመኖሪያ ፈቃድ የማግኘት መብትንም ያስገኝላቸዋል ብለዋል።
ስምምነቱ የሳዑዲ መንግሥት ኢትዮጵያውያን በአሰሪዎቻቸውና በኤጀንሲዎች ለሚደርሰባቸው ማንኛውም የመብት ጥሰት ኃላፊነትን እንዲጋራ የሚጠይቅ ነው።
በዓረብ አገራት ተቀጥረው የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን በአሰሪዎቻቸው በተደጋጋሚ ደመወዝ መከልከልን ጨምሮ የተለያዩ የመብት ጥሰቶች እየተፈጸመባቸው መሆኑን ይናገራሉ።
ይህን ተከትሎም የኢትዮጵያ መንግሥት ለችግሩ እልባት እስኪያገኝለት ድረስ ዜጎቹ ሥራ ፍለጋ ወደ ዓረብ አገራት የሚያደርጉትን ጉዞ ከጥቅምት 2006 ዓ.ም ጀምሮ አግዷል።
ይህን ተከትሎ ከሳዑዲ አረብያና ከሌሎች የዓረብ አገራት ጋር የሠራተኞቹን መብትና ጥቅም ሊያስጠብቅ የሚችል የሠራተኛ ቅጥር ስምምነት መፈረም የሚያስችሉ በርካታ ድርድሮች ሲካሄድ ቆይቷል።
በኢትዮጵያና ሳዑዲ ዓረቢያ መካከል ሲደረግ በቆየው ድርድር መሰረት ስምምነቱ በመጪው መስከረም እንደሚፈረም ይጠበቃል።
በሳዑዲ ዓረቢያ ይኖራሉ ተብሎ ከሚገመተው 500 ሺህ ኢትዮጵያውያን መካከል 200 ሺህ የሚሆኑት ህጋዊ አለመሆናቸውም መብታቸውን ለማስጠበቅ የሚደረገውን ጥረት ውስብስብ አድርጎታል።  
የሳዑዲ አረብያ መንግሥት በዚህ ዓመት መጀመሪያ ከ120 ሺህ የሚበልጡ ኢትዮጵያውያንን ከአገሩ ማስወጣቱ የሚታወስ ነው።

0 comments :