የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ፕሮፋይል ሊዘጋጅ ነው

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ፕሮፋይል (ገጽ ታሪክ) በ2008 ዓ.ም. ለማዘጋጀት መታቀዱን ምንጮች ገለጹ፡፡የፕሮፋይል ዝግጅቱ ዋና ዓላማ ለማንነት ጥያቄዎች የመጀመርያ ምላሽ መስጠት የሚያስችል እንደሆነ
የገለጹት ምንጮች፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ብሔር የቱ እንደሆነ፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚባሉት የትኞቹ እንደሆኑ ለመለየት የሚያስችል እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ለሌሎች ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መረጃዎች እንደ ምንጭነት ሊያገለግል እንደሚችልም አስረድተዋል፡፡
የፕሮፋይል ዝግጅቱን ተግባራዊ ለማድረግ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መለያ መሥፈርት ተረቆ፣ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በቀጣዩ ዓመት መጀመርያ ላይ እንደሚቀርብና እንደሚፀድቅ ገልጸዋል፡፡
ይህ የመለያ መሥፈርት በአሁኑ ወቅት በዝግጅት ላይ እንደሆነም ምንጮች ተናግረዋል፡፡ ይኼንን ተከትሎም የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፕሮፋይል ዝግጅቱን በበላይነት የሚመራ ቦርድና ጽሕፈት ቤት ያቋቁማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የሚቋቋመው ቦርድና ጽሕፈት ቤት በፌዴሬሽን ምክር ቤት በሚፀድቀው የመለያ መሥፈርት መሠረት የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ፕሮፋይል የሚያጠና ኩባንያ በጨረታ እንደሚቀጠር ለማወቅ ተችሏል፡፡
በሥራ ላይ የሚገኘው ሕገ መንግሥት ከመፅደቁ ከሃያ ዓመት በፊት በሽግግር መንግሥቱ ፀድቆ የነበረው ብሔራዊ ክልላዊ የሽግግር መስተዳድሮች ማቋቋሚያ አዋጅ በሚሰጠው ትርጓሜ መሠረት ‹‹ብሔር›› ወይም ‹‹ብሔረሰብ›› ማለት በአንድ ኩታ ገጠም መልክዓ ምድር የሚኖር፣ አንድ የመግባቢያ ቋንቋና የአንድነት ሥነ ልቦና ያለው ሕዝብ ማለት እንደሆነ ይገልጻል፡፡ በማስከተልም በኢትዮጵያ ውስጥ 64 ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መኖራቸውን ያስቀምጣል፡፡
በ1987 ዓ.ም. ፀድቆ ሥራ ላይ በዋለው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 39(5) መሠረት ደግሞ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ ማለት ሰፋ ያለ የጋራ ጠባይ የሚያንፀባርቁ፣ ባህል ወይም ተመሳሳይ ልምዶች ያላቸው፣ ሊግባቡበት የሚችሉበት የጋራ ቋንቋ  ያላቸው፣ የጋራ ወይም የተዛመደ ህልውና አለን ብለው የሚያምኑ፣ የሥነ ልቦና አንድነት ያላቸውና በአብዛኛው በተያያዘ መልክዓ ምድር የሚኖሩ እንደሆኑ ይደነግጋል፡፡ 
ይሁን እንጂ እስካሁን ድረስ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ የተባሉትን የሚለይ ሕግ በአገሪቱ የለም፡፡ በመሆኑም በፌዴሬሽን ምክር ቤት የበላይነት የሚመራው ፕሮጀክት በአገሪቱ ውስጥ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ የሚባሉትን የሚለይና ፕሮፋይላቸውን የሚያስቀምጥ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር