ባለስልጣኑ ሃዋሳን ጨምሮ የስምጥ ሸለቆ ሀይቆችን ከደለልና ከብክለት ለመከላከል እየሰራ ነው

ባለስልጣኑ የስምጥ ሸለቆ ሀይቆችን ከደለልና ከብክለት ለመከላከል እየሰራ ነውሀዋሳ ሰኔ 12/2007 የስምጥ ሸለቆ ሀይቆችን ከደለልና ከብክለት ለመከላከል ማህበረሰብ አቀፍ የተፈጥሮ ሀብትና የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን በውሀ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የስምጥ ሸለቆ ሀይቆች ተፋሰስ ባለስልጣን አስታወቀ ።
በባለስልጣኑ የስምጥ ሸለቆ ሀይቆች የተቀናጀ የተፋሰስ ልማትና እንክብካቤ ፕሮጀክት የ2007 የበጀት አመት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማና አውደ ጥናት  በሃዋሳ ከተማ ተካሂዷል፡፡
ፕሮጀክቱ በ2004 በደቡብና ኦሮሚያ ክልሎች በሚገኙ  ዘጠኝ ዞኖችና 21 ወረዳዎች የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ስራን በማጠናከር በስምጥ ሸለቆ ሀይቆች ላይ እያንዣበበ ያለውን አደጋ ለመከላከል ወደ ስራ መገባቱ ተገልጧል ።
በዚህም በክልሎቹ ያሉ ሐይቆች፣ ወንዞችና ለተለያዩ አገልግሎቶች የተገነቡ ሰው ሰራሽ ግድቦችን ከደለል በመጠበቅ ዘላቂነት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን የባለስልጣኑ ዳይሬክተር ዶክተር ከበደ ካንቹላ አስታውቀዋል ።
ፕሮጀክቱ ተግባራዊ ከተደረገበት ጊዜ አንስቶ በጎርፍ እየታጠበ ወደ ሀይቆቹ የሚገባውን የደለል አፈር በመከላከል ረገድ የየአካባቢው ህብረተሰብ እያደረገ ያለው ተሳትፎም  ውጤት  እያስገኘ ነው ብለዋል ።
በተለይ የሃዋሳን ሀይቅ ከብክለት ለመከላከል በተያዘው ጥረት ከከተማውና በዙሪያው ካሉ አካባቢዎች በጎርፍ ታጥቦ የሚመጣውን ኬሚካልና ደረቅ ቆሻሻ አጣርተው የሚያስቀሩ ሁለት ሰው ሰራሽ ኩሬዎችን በመገንባት እየተካሄደ ያለው የሙከራ ስራ አበረታች መሆኑ ተገልጧል ።
በተጨማሪም ባለስልጣኑ በሀይቆቹ የሚገኙ ለምግብነት ያለደረሱ አሳዎችን ከጥፋት ለመታደግ በአሳ ማስገር ስራ ላይ ለተሰማሩ ማህበራት አባላት ስልጠና  በመስጠት በሃላፊነት መንፈስ እንዲንቀሳቀሱ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል ።
በዝዋይና በአባያ ሀይቅ ላይ እንደ ስጋት እየታየ ያለውን በመጤ አረም የመወረር አደጋ ለመከላከልና  ከጣና ሀይቅ የተገኘውን ተሞክሮ በሀይቆች ላይ ተግባራዊ እንደሚደረግ ጠቁመዋል  ፡፡
የስምጥ ሸለቆ ሀይቆች የተቀናጀ የተፋሰስ ልማትና እንክብካቤ ፕሮጀክት አስተባባሪ ኢንጂኜር ሽፈራው ካኔቦ በበኩላቸው በሀይቆቹ ተፋሰስ ስር በሚገኙ 21 ወረዳዎች ጉዳት የደረሰበትን 1ሚሊዮን ሄክታር መሬትን መልሶ በማልማት የተጠናከረ ስራ እየተካሄደ ነው ብለዋል ።
ከ2004  ጀምሮ ከ2 ሚሊዮን የሚበልጡ በተፋሰሶቹ አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎችን በማህበረሰብ አቀፍ የተፈጥሮ ሀብትና አካባቢ ጥበቃ ስራዎች ላይ በማሳተፍ  ከ122 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት ማልማት ተችሏል ።
ከተፋሰስ ልማት ስራው ጎን ለጎን ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበትን 10ሺህ ሄክታር መሬት ከሰውና እንስሳት ንክኪ በመከለል መልሶ እንዲያገግም ማድረግ  መቻሉንም  ጠቁመዋል፡፡
ቦረቦር የበዛባቸውን አካባቢዎች በጋቢዮን ድንጋይ በመሙላትና ተራሮችን በማልማት እንዲሁም የተለያዩ የውሃ ማስረጊያ ትሬንቾችና እርከኖችን በመስራት በጎርፍ እየታጠበ ወደ ሀይቁ የሚገባውን አፈር በመቀነስ በሀይቆቹ የውሀ መጠን ላይ ለውጥ ማምጣት እንደተቻለ አቶ ሽፈራው አስረድተዋል፡፡
በተፋሰስ ልማት ስራው መልሰው ባገገሙ አካባቢዎች በተለይ ወጣቶችና ሴቶች በማህበር ተደራጅተው በንብ ማነብ ስራ ተሰማርተው ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን ማሳደግ እንደቻሉ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በአውደ ጥናቱ ላይ ከተሳተፉ ባለሙያዎች ውስጥ የአዳሚ ቱሉ ጅዶ ኮምቦልቻ ወረዳ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ አብርሀም ዋለልኝ በበኩላቸው እንዳሉት በወረዳው በተፈጥሮ ሀብት ላይ የሚደርሰው ጉዳት በዝዋይ ሀይቅ ላይ የሚያስከትለውን  አደጋ ለማሰቀረት የተፋሰስ ልማት ስራዎች አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጠዋል ።
በፕሮጀክቱ የታቀፉ ወረዳዎች በበጀት ዓመቱ ያከናወኗቸውን ተግባራት በመገምገም የቀጣዩን  ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎችን በመለየት ወደ ተግባር እንደሚገባ በግምገማው ማጠናቀቂያ ላይ መገለጡን ኢዜአ በዘገባው አመልክቷል ።
- See more at: http://www.ena.gov.et/index.php/economy/item/5631-2015-06-19-19-29-07#sthash.AWfLaGPh.dpuf

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር