ምክር ቤቱ ከነገ ጀምሮ የሶስት ቀናት ብሄራዊ የሀዘን ቀን ያውጃል

ምክር ቤቱ ከነገ ጀምሮ የሶስት ቀናት ብሄራዊ የሀዘን ቀን ያውጃል
(ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት በአይ ኤስ በግፍ የተገደሉትን ኢትዮጵያዊያንን ለማሰብ ነገ የሶስት ቀናት ብሄራዊ የሀዘን ቀን እንደሚያውጅ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
በሊቢያና በደቡብ አፍሪካ በግፍ የተገደሉትን ዜጎች ለማሳብ በመላው ሀገሪቱ እና በአለም ዙሪያ በሚገኙ የኢትዮጵያ ኢምባሲዎች ባንዲራዎች ዝቅ ብለው እንዲውለበለቡ ያደርጋል ነው ያለው ጽህፈት ቤቱ በመግለጫው።
መንግስት ትናንት በአክራሪ ቡድኑ የተገደሉት 28 ዜጎች ሁሉም ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን ማረጋገጡንም ገልጿል።
የኢፌዴሪ መንግስት በንጹሃን ዜጎቻችችን ላይ በደረሰው ጉዳት እጅጉን ማዘኑን በመግለጽ ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን ተመኝቷል።
ዜጎችን ከሊቢያ፣ የመን እና ደቡብ አፍሪካ ወደ ሀገራችው ለመመለስም የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
በቀጣይ በመንግስት የሚወሰዱ እርምጃዎች የሚገለፁ ሲሆን በንጹሃን ዜጎች ላይ የደረሰው አደጋ መንግስት የተያያዘውን የጸረ ሽብር እርምጃ ለአፍታ ያህል እንደማያቋርጠው ነው ያስታወቀው።
“በዚህ አጋጣሚ መላው የሀገራችን ዜጎች በፀረ ሽብር ላይ የከፈትነውን ዘመቻ አጠናክረን እንድንቀጥልበት መንግስት ጥሪውን ያቀርባል” ይላል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ያወጣው መግለጫ።
በሀገራችን ሰርቶ የመለወጥ ዕድል እየሰፋ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ምንም አይነት ጥበቃ ሊያገኙ በማይችሉበት አቅጣጫ በመሄድ አደጋ ላይ ከሚጥላቸው ህገወጥ ስደት እንዲታቀቡ የሃይማኖት ተቋማትና ቤተሰቦች በዚሁ ላይ ጠንክረው እንዲሰሩም አሳስቧል።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር