በየመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጥቃት ተፈጸመበት

በየመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጥቃት ተፈጸመበትበየመን ዋና ከተማ ሰነዓ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ መጋቢት 24 ቀን 2007 ዓ.ም. በጦር መሣሪያ ድብደባ ጥቃት ተፈጸመበት፡፡ ጥቃቱ በኤምባሲው ሠራተኞች ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት አለማድረሱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ 
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሆነው በቅርቡ የተሾሙት አቶ ተወልደ ሙሉጌታ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በኤምባሲው ላይ ጥቃት የተፈጸመው በየትኛው ተፋላሚ ወገን መሆኑ ለጊዜው አልታወቀም፡፡ የደረሰው አደጋ ከፍተኛ አለመሆኑንም ገልጸዋል፡፡ 
ከደረሰው የጦር መሣሪያ ጥቃት በኋላም ኤምባሲው መደበኛ ሥራውን የቀጠለ መሆኑን፣ በንብረት ላይ የደረሰውን አደጋ በዕለቱ መገመት እንደሚያስቸግርና ገና ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ቃል አቀባዩ ጨምረው አስረድተዋል፡፡ 
በየመን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሐሰን አብደላና የሥራ ባልደረቦቻቸው ከኢትዮጵያውያን በፊት የመንን ለቀው ባለመውጣታቸውና ወገኖቻቸውን ለመርዳት  ሲሉ እዚያ በመቆየታቸው፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ምሥጋና አቅርበውላቸዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኤምባሲው ከመንግሥት ጋር በመሆን በየመን በተቀሰቀሰው ውጊያ ምክንያት የታገቱ ኢትዮጵያውያንን የማውጣት ሥራ ተጠናክሮ እንደቀጠለ አቶ ተወልደ ጠቁመዋል፡፡ ከቀናት በፊት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በየመን የሚገኙ ከ2,000 በላይ ኢትዮጵያውያንን በመመዝገብ ወደ አገራቸው በሰላም እንዲመለሱ አንድ ግብረ ኃይል ማቋቋሙን ገልጿል፡፡ 
ከውጭ ጉይ ሚኒስቴር በተገኘው መረጃ መሠረት እስከ መጋቢት 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ 11 ሕፃናትና 12 ሴቶችን ጨምሮ 30 ኢትዮጵያውያንን ወደ ጂቡቲ እንዲጓዙ ተደርጓል፡፡
ነገር ግን በየመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ በመሆኑና ከአካባቢው አስቸጋሪነት አንፃር፣ ኢትዮጵያውያኑን የመታደግ ሥራ አስቸጋሪ መሆኑን የሚገልጹም አሉ፡፡ 
አቶ ተወልደ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ እስካሁን ከ2,000 በላይ ኢትዮጵያውያን በኤምባሲው አማካይነት ተመዝግበዋል፡፡ ‹‹በአስቸጋሪ ሁኔታም ቢሆን ነፍስ የማዳኑን ሥራ እንቀጥልበታለን፤›› ብለዋል፡፡ አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ 10,000 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በአንድ ወር ውስጥ ወደ የመን የሚጓጓዙ ሲሆን፣ አብዛኞቹ በየመን አቋርጠው ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ የሚሄዱ ናቸው፡፡ 
በየመን በመንግሥትና በአማፂው የሁቲ ታጣቂዎች መካከል ለወራት የቀጠለው ጦርነት መልኩን ቀይሮ በሳዑዲ ዓረቢያ የሚመራ የዓረብ አገሮች ጣልቃ ገብነት በየመን የተፈጠረውን ቀውስ እንዳባባሰው ይነገራል፡፡ በዚህም ምክንያት በርካታ አገሮች ዜጎቻቸውን ለማውጣት በመሯሯጥ ላይ ናቸው፡፡ 
በኢራን ይደገፋሉ የተባሉት የሁቲ ታጣቂዎች በውጊያ የአገሪቱን ፕሬዚዳንት ከሥልጣን አስወግደው ሰነዓን ከተቆጣጠሩ በኋላ፣ የመን ጠቅላላ ጦርነት ውስጥ ገብታለች፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያና የተወሰኑ የባህረ ሰላጤው አገሮች ኢራንን እየኮነኑ ናቸው፡፡
በተጠናቀቀው ሳምንት ብቻ ከ200 በላይ የሚሆኑ የቻይና ዜጎች በጂቡቲ አድርገው ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ሲሆን፣ ከሰዓታት በኋላ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቤጂንግ እንዲጓጓዙ ተደርጓል፡፡ 
የተለያዩ ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት ቻይናን ጨምሮ የህንድና የአፍሪካ አገሮች ዜጎች ወደ ጂቡቲ እንዲሸሹ እየተደረጉ ናቸው፡፡ ለበርካታ ዓመታት ሰላም ርቋት ወደነበረችው ሶማሊያም የሚፈልሱ የተለያዩ አገር ዜጎች እንዳሉ እየተነገረ ነው፡፡ 
http://www.ethiopianreporter.com/index.php/news/item/9355-%E1%89%A0%E1%8B%A8%E1%88%98%E1%8A%95-%E1%8B%A8%E1%8A%A2%E1%89%B5%E1%8B%AE%E1%8C%B5%E1%8B%AB-%E1%8A%A4%E1%88%9D%E1%89%A3%E1%88%B2-%E1%8C%A5%E1%89%83%E1%89%B5-%E1%89%B0%E1%8D%88%E1%8C%B8%E1%88%98%E1%89%A0%E1%89%B5

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር