ሚዲያና የኢትዮጵያ ምርጫ

ሚዲያና የኢትዮጵያ ምርጫየኢትዮጵያ ምርጫዎችን ውጤት በመወሰን ረገድ የሚዲያ ተቋማት ሚና ምን ያህል ነው ለሚለው ጥያቄ ወጥ ምላሽ ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ አብዛኛው ከሚዲያ ተቋማቱ ባለቤትነት ጋር ይያያዛል፡፡
የሰፊው ሕዝብ የመረጃ ምንጭ የሆነው የብሮድካስት ሚዲያ በተለይ በመንግሥት ቁጥር ሥር ያለና ሞኖፖሊ ሊባል በሚችል ደረጃ በሥልጣን ላይ ያለውን ኃይል የሚያገለግል ተቋም እንዲሆን አድርጎታል በሚል የሚከራከሩ አካላት፣ የግል የኅትመት የሚዲያ ተቋማት በመረጃ ምንጭነት የሚያገለግሉት ጥቂት ሺሕ የከተማ ልሂቃንን ብቻ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ሚዲያ ከባለቤትነት ተፅዕኖ ይልቅ በሙያው ተቀባይነት ባለው መርህ መሠረት ነፃና ገለልተኛ በመሆን አለማገልገሉን እንደ ትልቅ ስንክሳር የሚወስዱም አሉ፡፡ ለአብነት ያህል የአገሪቱ የበላይ ሕግ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 29(5) ላይ ‹‹በመንግሥት ገንዘብ የሚካሄድ ወይም በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለ መገናኛ ብዙኃን የተለያዩ አስተያየቶችን ለማስተናገድ በሚያስችለው ሁኔታ እንዲመራ ይደረጋል፤›› ተብሎ መደንገጉን ያስታውሳሉ፡፡ በተጨማሪም እንደ ሸገርና ዛሚ ያሉ የሬዲዮ ጣቢያዎች በመንግሥት ቁጥጥር ናቸው ሊባሉ እንደማይችሉ ይከራከራሉ፡፡ የግሉ የኅትመት ዘርፍም በመንግሥት ተፅዕኖ አይታማ እንጂ፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከሌሎች አካላት ተፅዕኖ ራሱን ያላፀዳ መሆኑ በእንቅስቃሴው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደፈጠረበት ያወሳሉ፡፡ 
መጋቢት 26 ቀን 2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋኩልቲ የእሸቱ ጮሌ አዳራሽ ‹‹ሚዲያና ምርጫ የኢትዮጵያ ልምድና ለ2007 ምርጫ ያሉት አንድምታዎች›› በሚል ርዕስ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን ትምህርት ቤት፣ ከዩኒቨርሲቲው የፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ጋር ለመተባበር ባዘጋጀው የአንድ ቀን ዓውደ ጥናት ተሳታፊዎቹ በእነዚሁ አንኳር የሚዲያው ችግሮች ላይ ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡፡
የምርጫና የሚዲያ ቁርኝት
የኅትመትና የዌብ የትምህርት ክፍል አስተባባሪ የሆኑት አቶ ዳግም አፈወርቅ፣ ትርጉም ያለው ምርጫ ለማድረግ የሚዲያ ሚና ጉልህ እንደሆነ ባደረጉት የመግቢያ ንግግር አመልክተዋል፡፡ ‹‹ምርጫ በቂ የፖለቲካ ዕውቀት ያለውና በመረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ መስጠት  ወይም መምረጥ የሚችል ዜጋ የሚያስፈልገው ሒደት ነው፡፡ ይህ ዓይነት ዜጋ የሚፈጠረው በዋናነት በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት ነው፡፡ ዜጎች ትክክለኛ ውሳኔና ምርጫ ማካሄድ እንዲችሉ መገናኛ ብዙኃን ኃላፊነት በተሞላበትና የሙያ ሥነ ምግባሩን በጠበቀ ሁኔታ የፖለቲካ ተወዳዳሪዎችን ሙሉ ምሥል ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፤›› ብለዋል፡፡ የሚዲያ ተቋማቱና ጋዜጠኞች ከምርጫ ጋር የተገናኙ ዜናዎችን ከማቅረብ ባለፈ፣ የክርክርና የውይይት መድረኮችን በመፍጠር ዜጎች የተለያዩ ሐሳቦችን ማንሸራሸር እንዲችሉ የማድረግ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸውም አክለዋል፡፡
በተለይ በኢትዮጵያ አማራጭ ሚዲያና ኢንተርኔት ካለመስፋፋቱ ጋር ተያይዞ ይህ ዓይነት ትልቅ ኃላፊነት በአገር አቀፍ ጋዜጦች፣ መጽሔቶች፣ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ላይ እንደሚወድቅ አቶ ዳግም አስገንዝበዋል፡፡ ይሁንና እነዚህ የሚዲያ ተቋማት እየተጫወቱት ያለው ሚና መሆን ከሚጠበቅበት የራቀ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ‹‹የሚዲያ ተቋማት አንዳንድ ጊዜ ራሳቸውን ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመለጠፋቸው እውነተኛና ያልተዛባ መረጃና ትንተና ማቅረብ አይችሉም፡፡ ሌሎች የሚዲያ ተቋማት ደግሞ አገልግሎታቸውን ሁሉ ከገዥው መደብ ጋር በማድረግ ዴሞክራሲያዊ ባህል እንዳይዳብር የራሳቸውን ድርሻ ያበረክታሉ፤›› ብለዋል፡፡ አቶ ዳግም የምርጫ ሒደቱን፣ ዕጩዎችንና የፓርቲዎቹን የፖለቲካ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፕሮግራሞችን በተመለከተ መረጃና ትንተና ለመስጠት መገናኛ ብዙኃን ነፃና ገለልተኛ መሆናቸው እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በአፅንኦት በመግለጽ ሐሳባቸውን ደምድመዋል፡፡
የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ትምህርት ቤት ኃላፊ ዶ/ር አብዲሳ ዘርዓይ፣ ‹‹Media and Democracy in Ethiopia: Challenges and Opportunities›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት የውይይት መነሻ ጽሑፍ እንደ አቶ ዳግም ሁሉ ትልቁ የሚዲያ አስተዋጽኦ ሐሳብን በነፃነት በማንሸራሸር እንደሚገለጽ አስገንዝበዋል፡፡ ይህ የሚዲያ ዋና ዓላማ ደግሞ የዴሞከራሲም ሆነ የምርጫ መገለጫ ጭምር በመሆኑ፣ ዴሞክራሲንና ምርጫን ሐሳብን በነፃነት ከመግለጽ መብት ለይቶ ማየት አዳጋች መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ‹‹ዴሞክራሲ የተለያዩ አመለካከቶችና አስተሳሰቦች ያላቸው ክፍሎች ወጥተው የኅብረተሰቡን ይሁንታ ለማግኘት የሚደረግ ትግል ነው፤›› ብለዋል፡፡
ዶ/ር አብዲሳ፣ ‹‹እውነትን በሞኖፖሊ የያዘ የኅብረተሰብ ክፍል የለም፤›› በማለትም በሐሳብ የነፃ ገበያ እውነትን ለማግኘት በሚደረገው ጥረት ትክክለኛ እውነት ለማግኘት፣ ሐሳቦች በነፃ መንሸራሸራቸውና እንደ ልብ መገኘታቸው አስፈላጊ እንደሆነ አስምረውበታል፡፡
ኢትዮጵያ ለዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሥርዓትም ሆነ ሐሳብን በነፃነት ለመግለጽ መብት የነበራት እንግድነት በ1983 ዓ.ም. መደምደሙን ያስታወሱት ዶ/ር አብዲሳ፣ ለእነዚህ መሠረታዊ መብቶች አፈጻጸምና ዕድገት የሚስማማ የፖለቲካ ባህል አለመፈጠሩን ጠቁመዋል፡፡ ለዚህ አስተዋጽኦ ያደረጉት ሁለቱ ምክንያቶች ከ1983 ዓ.ም. በፊት የነበረው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህልና ከግራ ፖለቲካ ያልፀዳው የኢሕአዴግ የፖለቲካ ባህል እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡
ከ1984 ዓ.ም. እስከ 1988 ዓ.ም. ባሉት ጊዜያት ከ200 በላይ ጋዜጦችና መጽሔቶች በአዲሱ የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ጎዳና አማካይነት ወደ ገበያ መግባታቸውን ያስታወሱት ዶ/ር አብዲሳ፣ በኃላፊነት ስሜት እንዳያገለግሉ የነበረው የፖለቲካ ባህል እንቅፋት እንደሆነባቸው ገልጸዋል፡፡ በወቅቱ የነበረው የሚዲያ ባህል ፅንፈኛ፣ ጦረኛና ፕሮፓጋንዲስት እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ የነበረው አሠራር በትክክል በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ከመሆን ይልቅ አማፂ፣ መንግሥትን ተገዳዳሪና አፍራሽ ሚዲያ ገበያውን እንዳጥለቀለቀው አውስተዋል፡፡ ይህ አቀራረብ የጋዜጠኝነት ሙያ እንዳያድግ መከላከሉንም ገልጸዋል፡፡ የግሉ ሚዲያ አሁንም ከዚያ ችግር ሙሉ በሙሉ አገግሟል ብለው እንደማያምኑም ጠቁመዋል፡፡ 
ከ1988 ዓ.ም. እስከ 1992 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ መንግሥት በሚዲያ እንቅስቃሴ ውስጥ በስፋት ጣልቃ በመግባት በርካታ የሚዲያ ተቋማትን ለመዝጋት የራሳቸው የተቋማቱ ጥፋት ገፋፊ ምክንያት ቢሆንም፣ የመንግሥት አምባገነናዊ ባህል አለመቀየሩና የገዥው ፓርቲ ግራ ዘመም ርዕዮተ ዓለማዊ ቅኝት አስተዋጽኦ ማድረጉንም አብራርተዋል፡፡ በሽግግሩ ጊዜ መንግሥት የተቀበለው የዴሞክራሲ ማሻሻያ ከውስጣዊ እምነት ይልቅ ከዓለም አቀፋዊ ኃይሎች ተፅዕኖ መምጣቱ አፈጻጸሙ ላይ መንግሥት ቁርጠኛ እንዳይሆን ማድረጉን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ሚዲያ የተለያዩ ግቦችን የሚያሳካበት መሣሪያ እንጂ፣ እንደ አንድ ነፃ ተቋም በራሱ አስፈላጊ እንደሆነ ዕውቅና እንደማይሰጥም ተችተዋል፡፡ መንግሥት ማርክሲስታዊ የሚዲያ መዋቅራዊ ትንታኔን የሚከተል በመሆኑ፣ ሚዲያ የገዥው መደብ ጉዳይ አስፈጻሚ አድርጎ እንደሚያይም አስገንዝበዋል፡፡ በእነዚህ ሁለት አካላት ተፅዕኖ የተነሳ ሰለባ የሆኑት ዴሞክራሲ፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና የዜጎች የማወቅ መብት እንደሆኑም አመልክተዋል፡፡
የብሮድካስት ሚዲያና የኢትዮጵያ ምርጫ
‹‹What Roles Have the Broadcast Media Played During the 2005 and 2010 General Elections?›› በሚል ርዕስ የውይይት መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወልዱ ይመስል፣ ከግሉ የኅትመት ሚዲያ በተቃራኒ የብሮድካስት ሚዲያው የኢትዮጵያ የምርጫ ባህል ላይ አዎንታዊ ሚና መጫወቱን ተከራክረዋል፡፡
በተለይ የምርጫ 97 ስኬት ከብሮድካስት ሚዲያው ጋር የተያያዘ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከምርጫው ጊዜ እጅግ ቀደም ብለው የምርጫ ቅስቀሳ እንዲጀመር በማድረግ ኢብኮ (የያኔው ኢቲቪ) እና ሌሎች የብሮድካስት ሚዲያ ተቋማት ሰው ሁሉ በየቤቱ ስለምርጫው የሚያወራበትን ዕድል በመፍጠር ሰፊ ንቅናቄ እንዲካሄድ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡ በወቅቱ በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚ ፓርቲዎች የተደረጉ ሠልፎችን የብሮድካስት ሚዲያው እኩል ሽፋን ይሰጥ እንደነበርም አውስተዋል፡፡
ምርጫ 97ትን አስመልክቶ ብሮድካስት ሚዲያውና የግሉ የኅትመት ሚዲያ ተፃራሪ አቋም እንደነበራቸው ጠቁመዋል፡፡ ‹‹በአጠቃላይ የብሮድካስት ሚዲያው ፍላጎት ምርጫውን በሰላም ማጠናቀቅ ነበር፡፡ የግሉ የኅትመት ሚዲያ ደግሞ ምርጫውን ለሌላ ግብ የመጠቀም ፍላጎት ነበረው፡፡ ይኼንን ስሜት ለማረጋጋት ብሮድካስት ሚዲያው ሙከራ አድርጓል፡፡ በግሉ ፕሬስ የታየው ብሮድካስት ሚዲያው ላይ ቢገለጽ ኖሮ እዚያች አገር በጣም ከፍተኛ ችግር ይፈጠር ነበር፡፡ ብሮድካስት ሚዲያው ሚዛናዊ የሆነ ሚና ተጫውቷል፡፡ ጥናቶችም ይህን ነው የሚያሳዩት፤›› በማለትም አብራርተዋል፡፡
ይህ በምርጫ 97 ዕለትና ከዚያ በፊት በቅድመ ምርጫው የታየው ሰፊ የሕዝብ ተሳትፎ በድኅረ ምርጫው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የፈጠረ ቢሆንም፣ ሒደቱ በአበረታች ውጤቶች መጠናቀቁን ግን አቶ ወልዱ አመልክተዋል፡፡ የዚህ አንዱ መገለጫ በፓርላማው 176 ወንበሮች በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች መያዙ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡
የሁለት ተፃራሪ ወገኖች ግጭት ያስከተለው ጉዳት የሒደቱ አሉታዊ ተፅዕኖ ቢሆንም፣ የችግሩ ምንጭ ተቃዋሚዎች እንደሆኑ ግን ተከራክረዋል፡፡ ‹‹ችግሩ የተከሰተው ሙሉ በሙሉ ሥልጣን ካልተቆጣጠርን ባሉ አካላት ነው፡፡ በምርጫና በሕዝብ ፈቃድ ሳይሆን በአቋራጭ ሥልጣን ማግኛ ሥልት የሚነድፈውን የዶ/ር ነገዴ ጎበዜን መንገድ በመከተላቸው የተከሰተ ጉዳት ነበር፤›› ብለዋል፡፡
የምርጫ 2002 ሒደት ግን ከጅምሩ የምርጫ 97ን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቅረፍ ጥረት በማድረግ የተጀመረ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ምርጫ 2002 የተሻለ እንዲሆን በወቅቱ የፀደቁት የመገናኛ ብዙኃን አጠቃቀም መመርያውና የፖለቲካ ፓርቲዎች የሥነ ምግባር አዋጅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳደረጉም አስገንዝበዋል፡፡ በምርጫ 97 ከኢትዮጵያ ባህል ያፈነገጡ ቃላት በፓርቲዎች ክርክር ላይ ጥቅም ላይ መዋላቸውን አስታውሰው፣ እነዚህ መመርያዎች ግን ተመሳሳይ ነገር እንዳይደገም ማድረጋቸውን አመልክተዋል፡፡
በምርጫ 97 ተቃዋሚዎች ያሸነፉዋቸው ወንበሮች ባለመውሰዳቸው ሕዝቡ ምርጫ ትርጉም የለውም በሚል ተስፋ ሊቆርጥ ይችላል የሚል ሥጋት እንደነበርም አቶ ወልዱ አስታውሰዋል፡፡ ይህ ሥጋት እውን እንዳይሆንና ሕዝቡ በምርጫ ሒደት ላይ እምነት እንዲያጠናክር በማድረግ ብሮድካስት ሚዲያው ከፍተኛ ሚና መጫወቱንም ጠቅሰዋል፡፡ በዚህም በምርጫ 97 ከነበረው 27 ሚሊዮን የመራጭ ቁጥር በምርጫ 2002 ግን 32 ሚሊዮን እንዲደርስ የብሮድካስት ሚዲያ ጉልህ ሚና መጫወቱን ገልጸዋል፡፡ ይሁንና ሕዝቡ በተቃዋሚዎች ላይ የነበረው እምነት በመቀነሱ ያገኙት ድምፅ ዝቅተኛ ነበር ብለዋል፡፡
አቶ ወልዱ በአጠቃላይ በሁለቱ ጠቅላላ ምርጫዎች የብሮድካስት ሚዲያ በሰጠው ሰፊ ሽፋን አማካይነት በምርጫ ላይ የሕዝቡ ግንዛቤ በከፍተኛ ደረጃ ማደጉን ገልጸዋል፡፡ ሥራቸውም በኤድቶሪያል ነፃነት የታጀበ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ የብሮድካስት ሚዲያው ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ አስተዋጽኦ ማበርከቱንና የተወዳዳሪ ፓርቲዎችን የፖሊሲ አማራጭና የቅስቀሳ ሥራ በብቃት በማቅረብ ተመጣጣኝ ዕድል መፍጠሩ እንደ ጥንካሬ የሚወስድ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
ይሁንና የብሮድካስት ሚዲያው ጥልቀት ያለው ትንታኔ የማቅረብ ክፍተት እንደነበረበት ግን አምነዋል፡፡ ምክንያታዊና ሚዛናዊ የሆነ አስተሳሰብ፣ ምሁራንን ያሳተፈ ፖሊሲ ተኮር ክርክር እንዲደረግ ሁኔታዎች የተመቻቹ እንዳልነበሩም አመልክተዋል፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ አሁን ጥረት እየተደረገ ቢሆንም፣ የምርጫ ሒደቱን ከመዘገብ በላቀ ሁኔታ ወሳኝ ሚና መጫወት የሚችሉ የምርጫ ኤክስፐርት ጋዜጠኞችን ማፍራት የሚቀር እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡ የፓርቲዎቹን የተለያዩ አማራጮች በዘርፉ ባለሙያዎች ማስተቸትም ተጠናክሮ ሊካሄድ እንደሚገባው ጠቁመዋል፡፡
የኅትመት ሚዲያውና የኢትዮጵያ ምርጫ
‹‹የኅትመት መገናኛ ብዙኃን ሚና በቀደምት ሁለት ምርጫዎች ምርጫ 97 እና ምርጫ 2002›› በሚል ርዕስ የውይይት መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት አቶ ተሻገር ሽፈራው፣ በድኅረ 1983 የተቋቋሙ የግል የኅትመት ሚዲያ ተቋማት በጋዜጠኝነት ሙያ ጉድለትና በጋዜጠኞቹ የፖለቲካ አቋም የተነሳ ከተቃዋሚነት ባለፈ የተዋጊ ጋዜጠኝነት ዝንባሌ ጎልቶ ይታይባቸው እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡ ለዚህ አስተዋጽኦ ያደረገው አንዱ ምክንያት የግል ጋዜጦችን በማቋቋም ሥራ ከጀመሩት መካከል ከደርግ መወገድ ጋር ተያይዞ ከልዩ ልዩ የሥራ መስኮች የተፈናቀሉ ሰዎች መገኘታቸው እንደሆነም አመልክተዋል፡፡
ያሉባቸው ፈተናዎችና የራሳቸው ችግሮች እንደተጠበቁ ሆነው ብዙ ጋዜጦች ከይፋዊና መንግሥታዊ የፖለቲካ አቋሞች የተለዩና ተፃራሪ የሆኑ ዘገባዎችና ሐሳቦችን ለሕዝብ በማቅረብ፣ የአማራጭ ይዘት አቅራቢነት ሚናቸውን በስፋት እንደተወጡ ግን አቶ ሽመልስ ቦንሳ የተባሉ ተመራማሪን በመጥቀስ ተከራክረዋል፡፡
የተለያዩ በወቅቱ መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች ላይ የተሠሩ ጥናቶች በምርጫ 97 ዘጠና ልዩ ልዩ ጋዜጦች በኅትመት ላይ እንደነበሩ እንደሚጠቀሙ የገለጹት አቶ ተሻገር፣ በዘገባዎቹ ውስጥ አራት አበይት የዘገባ ቅርጾች እንደነበሩ አመልክተዋል፡፡ እነዚህም የትግል ዘይቤ፣ ግለሰብ አግናኝ ዘይቤ፣ የተከታታይ ታሪክ ዘይቤና ጭብጥ ተኮር አቀራረብ እንደነበሩ ጠቅሰዋል፡፡
የትግል ዘይቤ ተከትለው ይሠሩ የነበሩ የኅትመት መገናኛ ብዙኃን የምርጫ ፉክክሮችን በግጥሚያ ዘይቤ የሚያቀርቡና የፍልሚያ ትዕይንት ፈጥረው የመራጩን ሕዝብ ስሜት የመሳብ፣ የመቀስቀስና የመጎንተል ጠባይ የሚታይባቸው እንደነበሩ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ይህ የምርጫ ዜና አቀራረብ ቅርጽ በመንግሥትም ሆነ በግል የኅትመት መገናኛ ብዙኃን ጎልቶ የታየ ከመሆኑም በላይ፣ ምርጫን በፍልሚያና በጦርነት መስሎ የማቅረቡ ዝንባሌ ግን በመገናኛ ብዙኃን ብቻ ይታይ የነበረ ሳይሆን፣ በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና በገዥው ፓርቲ መሪዎች ንግግሮችም ውስጥ የሚታይ ነበር፤›› ብለዋል፡፡ ለአብነት ያህልም ‹‹በዝረራ››፣ ‹‹አንገት ላንገት ተናንቀው››፣ ‹‹ኢንተርሃምዌ›› የሚሉትን ቃላት ይጠቀሙ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡ 
ግለሰብ አግናኝ ዘይቤ ይከተሉ የነበሩ የኅትመት መገናኛ ብዙኃን ተወዳዳሪውን ከዓውዱ የመነጠል ዝንባሌ ይታይባቸው እንደነበር አቶ ተሻገር አስረድተዋል፡፡ ‹‹ይህ የዘገባ አቀራረብ ግለሰቡ ከሚወክለው የፖለቲካ ፓርቲ ይልቅ በግለሰቡ ልዩ ጠባይ፣ ክህሎት፣ ዕውቀትና ልምድ ላይ ያተኩራል፡፡ የተለዩ ትረካዎችን በመፍጠር ሰዎች ለመስማት የሚጓጉላቸውን  ዘገባዎች ያቀርባል፡፡ የግለሰቦችን ገጽታ ጉልህ ያደርጋል፤›› ሲሉም አብራርተዋል፡፡
የተከታታይ ታሪክ ዘይቤ በክዋኔዎችና ሁነቶች ተከታታይነት ላይ እንደሚያተኩር የገለጹት አቶ ተሻገር፣ ጭብጥ ተኮር አቀራረብ በጉዳዩ ጭብጥ ላይ ስለሚያተኩር በክዋኔዎችና ሁነቶች ገለጻ ላይ ጊዜ እንደማያባክን ጠቁመዋል፡፡ በአጠቃላይ ምርጫ 97 ከጋዜጠኝነት አንፃር ሲታይ ለዴሞክራሲ መታገል ተቀባይነት ያለው ቢሆንም፣ ‘ተዋጊ ጋዜጠኝነት’ ግን አዋጭ እንዳልሆነ የታየበት አጋጣሚ እንደነበር አቶ ተሻገር ጠቅሰዋል፡፡
‹‹ምርጫ 2002 ፍፁም የሰከነ ነበር›› ያሉት አቶ ተሻገር፣ የኅትመት መገናኛ ብዙኃን እንደ ምርጫ 97 የሞቀና የደራ ድባብ ባይፈጥሩም ቀደም ሲል በነበረው የአዘጋገብ ፈሊጥ መቀጠላቸውን ግን አመልክተዋል፡፡
ከተሳታፊዎቹ የተወረወሩ ጥያቄዎች
ወደ መድረኩ በቅድሚያ የተረወረው ጥያቄ ነፃና ገለልተኛ ሚዲያ በኢትዮጵያ ለመፍጠር አመቺ ሁኔታዎች አሉ ወይ? የሚል ነበር፡፡ አቶ ወልዱ ከኢኮኖሚያዊና ከፖለቲካዊ ፍላጎት የፀዳ የሚዲያ ተቋም ስለሌለ ነፃ ሚዲያ አለ ብለው እንደማያምኑ ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር አብዲሳ ግን ጋዜጠኛው የማኅበረሰቡ አባል በመሆኑ የራሱ ፍላጎትና እምነት ቢኖረውም፣ እሱ በያዘው አቋም የተነሳ ሌሎች እስካልተጠቁ ድረስና እውነታዎች ተዛብተው እስካልቀረቡ ድረስ ነፃና ገለልተኛ ሆኖ ከመሥራት የሚያግደው ነገር እንደሌለ ተከራክረዋል፡፡ 
ሬዲዮ ፋና በምርጫ ላይ በማተኮር የሚሠራውን ፕሮግራም በተለይ ‹‹ሞጋችን›› እንደሚያመሰግኑ የገለጹ አንድ ተሳታፊ፣ ተቃዋሚዎችን በሚሞግትበት መጠን ለገዥው ፓርቲ አባላት በተመሳሳይ ለምን አይሠራም? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ አቶ ወልዱ ፋና እንደማንኛውም ሚዲያ የራሱ ኤዲቶሪያል ፖሊሲና የሚያስፋፋው እምነትና እሴት እንዳለው ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ይሁንና ለሁሉም ፍትሐዊ የሆነ አጠያየቅ መከተል እንዳለብን ስለምንቀበል ትችቱን እንቀበላለን፤›› ብለዋል፡፡
በቴሌቪዥን የሚቀርቡ የፓርቲዎች ክርክሮች ላይ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተወካዮች በተለያዩ አጀንዳንዎችም ላይ ተመሳሳይ መሆናቸውንና ዝግጅታቸውና አቀራረባቸው በጣም ደካማ እንደሆነ በመግለጽ የተቹት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር፣ ከጥናት አቅራቢዎቹና ከፓርቲዎቹ ተወካዮች ምላሽ አግኝተዋል፡፡ ‹‹እኔና እናንተ ስንደበቅ ደፍረው አደባባይ የወጡትን ተቃዋሚዎች አበረታታለሁ፡፡ የጥራት ጥያቄ እንዳለ፣ የአቋም ልዩነት እንዳለ ግልጽ ነው፡፡ ይህን ለማሻሻል እኛ ምን ያህል አስተዋጽኦ አድርገናል?›› በማለት ዶ/ር አብዲሳ ምላሽ የሰጡ ሲሆን፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎቹን የወከሉ ግለሰቦችም ተመሳሳይ ምላሽ በመስጠት ከዳር ሆነው የሚተቹ አካላት ትግሉን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ በምርጫ 97 የብሮድካስት ሚዲያው ለተቃዋሚዎች ክፍት የነበረው በመንግሥትና በገዥው ፓርቲ በጎ ፈቃድ ወይስ በሚዲያ ተቋማቱ ፍላጎት ነው? በሚል ጠይቀው ነበር፡፡ አቶ ወልዱ በአንፃራዊነት የሚዲያ ተቋማቱ ውሳኔን ለመስጠት ነፃነቱ እንደነበራቸው ተከራክረዋል፡፡ ‹‹የፖለቲካ ኢኮኖሚው ሥርዓት የራሱ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ ነፃነቱን ለማጠናከር የተሻለ አቅም ማዳበር ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን የሚዲያ ተቋማቱ አሁንም ሚና አላቸው፤›› ብለዋል፡፡ 
ምርጫ 97 እና የምርጫ 2002 የመራጮች ቁጥርን ብቻ መግለጽ የሚደብቃቸው ከጥራት ጋር የተገናኙ እውነታዎች እንዳሉ በመቃወም የተናገሩት የኢኮኖሚክስ መምህሩ ሲሆኑ፣ ለአብነት ያህልም በምርጫ 97 ዕድሜያቸው 18 ዓመት ያልሞላቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናት በምርጫ 2002 የመራጩን ቁጥር በተፈጥሮ እንደሚጨምሩ አመልክተዋል፡፡ በተጨማሪም በተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች በምርጫ 97 የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊ የነበሩ ግለሰቦች በምርጫ 2002 ገዥው ፓርቲን መምረጣቸው መዘንጋት እንደሌለበት ጠቁመዋል፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር