አይ ኤስ በሊቢያ በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ላይ የፈፀመውን አሰቃቂ ግድያ በማውገዝ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ነገ ሰልፍ ያካሂዳሉ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 13፣ 2007(ኤፍ.ቢ.ሲ) አይ ኤስ በሊቢያ በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ላይ የፈፀመውን አሰቃቂ ግድያ በማውገዝ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ነገ ሰልፍ ያካሂዳሉ።
በደቡብ አፍሪካ በወገኖቻችንና ሌሎች አፍሪካ ሃገራት ስደተኞች ላይ የተፈፀመውን ግፍና በሊቢያ አይ ኤስ አይ ኤስ የተባለው አሸባሪ ቡድን በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ የፈፀመውን የጅምላ ግድያ የሚያወግዝ ታላቅ ሃገራዊ የተቋውሞ ሰልፍ ነው ብሏል ሰልፉን ያስተባበረዉ የአዲስ አበባ ወጣቶች ፌዴሬሽን።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተደደርም ድርጊቱ በሰው ልጅ ላይ የተፈጸመ አስነዋሪና አረመኔያዊ ድርጊት በመሆኑ መላው የከተማችን ነዋሪ በተደራጀ መልኩ ነገ ከጠዋቱ 3 ሰአት በመስቀል አደባባይ በመገኘት ድርጊቱን አምርረን እናውግዝ በማለት ጥሪ አስተላልፏል።
በሰልፉ ላይ መንግስትና የከተማው ነዋሪ በተደራጀ መልኩ አስቀድሞ የጀመረውን የፀረ ሽብር ትግል አጠናክሮ እንደሚቀጥልበት ለሁሉም አሸባሪዎች፣ አክራረዎች እና ከዚህ ከሽብር የጥፋት ተልዕኮ ፖለቲካዊ ትርፍ እናገኛለን ብለው ለሚያልሙ ሃይሎች ጭምር ግልፅ መልእክት ይተላለፋል ተብሎም ይጠበቃል።
በሰልፉ ላይም እስከ ግማሽ ሚሊዮን የሚደርሱ የከተማዋ ነዋሪዎች እንደሚገኙ ይጠበቃል።
አይ ኤስ በኢትዮጵያዊያኑ ላይ ያደረሰው ዘግናኝ ግድያ ከአለማቀፉ ማህበረሰብ መወገዙን የቀጠለ ሲሆን፥ በርካታ ሀገራት እና አለማቀፍ ተቋማትም በአሸባሪ ቡድኑ ለተሰው ቤተሰቦችና በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ህዝብ መፅናናትን እየተመኙ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝም ኢትዮጵያውያን ሽብርተኝነት የሀይማኖት ጭምብል ለብሶ መምጣቱ ሳያዘናጋቸው ሀይማኖት ሳይለዩ በአንድ ልብ እና ሃሳብ ቆመው ሊዋጉት እንደሚገባ ገልፀዋል።
የሃይማኖት መሪዎችም ሆኑ ሰፊው ህዝብ በአሸባሪ ቡድኑ የደረሰው አሰቃቂ ግፍ ምንም አይነት ሃይማኖታዊ መሰረት የሌለው መሆኑንም እየገለጹ ይገኛሉ።
ጉዳዩን አስመልክቶም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሶስት ቀናት ብሄራዊ የሀዘን ቀን እንደሚያውጅ እየተጠበቀ ነው። መንግስትም በአሸባሪ ድርጅቱ ላይ ከአለማቀፉ ማህበረሰብ ጋር የተቀናጀ እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቱን አስታውቋል።
ከዚህም በተጨማሪ ወደ ሊቢያ፣ የመንና ወደ ሌለች በውጥረት ውስጥ ወደሚገኙ ሀገራት በመጓዝ ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያኖች በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ኢምባሲ በማቅናት ወደ ሀገራችው እንዲመለሱ አሳስቧል።
በደቡብ አፍሪካ በተለይም በደርባን ከተማ በውጭ ሀገር ዜጎች ላይ በተቃጣው ጥቃት እስካሁን ሰባት ሰዎችተገድለዋል።
ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ኢትዮጵያዊ ሲሆን በበርካቶች ላይ ደግሞ በአካል ጉዳትና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል።
በየመን ቀውስም ኢትዮጵያዊያንን ከጉዳት ለማትረፍ መንግስት የተለያዩ ተግባራትም እያከናወነ ይገኛል።
በአጠቃላይ መንግስት በደቡብ አፍሪካ፣ ሊቢያና የመን የሚገኙና ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ ፍቃደኛ የሆኑ ዜጎችን ለመመለስ መዘጋጀቱንና ለዚህም የሚረዱ ስልክ ቁጥሮችን ይፋ አድርጓል

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር