በሀዋሳ ከተማ የተገነቡ የመሰረተ ልማት ተቋማት ተመረቁ

በሀዋሳ ከተማ  የተገነቡ  የመሰረተ ልማት ተቋማት ተመረቁሐዋሳ ሚያዚያ 17/2007 በሀዋሳ ከተማ የሚከናወኑ የልማት ስራዎች እንዲጠናከሩ የፌዴራል መንግስት የሚያደርገው ድጋፍ እንደሚቀጥል በምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ማዕረግ የፋይናንስና መልካም አስተዳደር ክላስተር ዘርፍ አስተባባሪና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚንስትር አስታወቁ፡፡
በከተማዋ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ተቋማት ዛሬ ተመርቀዋል፡፡
በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ሚንስትሩ ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል እንዳሉት በሀገሪቱ የሚገኙ ከተሞች ለኑሮና ለስራ ምቹ እንዲሆኑ ለማድረግ የመሰረተ ልማት ተቋማት መስፋፋት የጎላ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡
መንግስት ለዘርፉ ልማት በሰጠው ትኩረት  ባለፉት አመታት በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡
በፈጣን እድገት ላይ የምትገኘው ሀዋሳ በመሰረተ ልማት አቅርቦት መስክ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት በተለያዩ መስኮች መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡
መንግስት በከተሞች ፈጣን ልማት ለማምጣት የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመው በቅርቡ የመሰረት ድንጋይ የተጣለለት የኢንደስትሪ ፓርክ ፣ ከሞጆ ሀዋሳ የሚገነባው የፍጥነት መንገድ ፣ የሀዋሳ አለም አቀፍ አየር ማረፊያና የባቡር መስመር ለከተማዋ ዕድገት መፋጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ገልጸዋል፡፡
በከተማው የሚገነባው የኢንደስትሪ ፓርክ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሀይል የሚፈልግ በመሆኑና እድገትን ተከትሎ የሀይል ፍላጎት በመጨመሩ መንግስት ከፍተኛ በጀት መድቦ የኤሌክትሪክ አቅርቦቱን ለማሳደግ የሚያስችል የማስፋፊያ ግንባታ እያካሄደ ነው፡፡
የማስፋፊያ ግንባታው ሲጠናቀቅ የኤሌክትሪክ ሀይል መቆራረጥን ችግር ሙሉ በሙሉ ማስቀረት እንደሚያስችል ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
በስልክ አገልግሎቱ የሚስተዋለውን የኔትወርክ መቆራረጥ ችግር ለማቃለልም በተመሳሳይ የማስፋፊያ ስራዎች እየተካሄደ ነው፡፡
ስራውንም በቅርበት እየተከታተሉት መሆናቸውን ሚኒስትሩ ጠቁመው በሀዋሳ ከተማ ለሚከናወኑ የልማትና የመሰረተ ልማት አቅርቦት ስራዎች የፌዴራል መንግስት የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥልበትም አስታውቀዋል፡፡
የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬ በበኩላቸው የክልሉ መንግስት ከተሞችን ለኑሮ ምቹና ተስማሚ ለማድረግ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የተለያዩ የመሰረተ ልማት ተቋማት ግንባታዎችን እያካሄደ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በርካታ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተስማምተውና ተከባብረው የሚኖሩባት ሀዋሳ  በሀገሪቱ ከሚገኙ ከተሞች በተደጋጋሚ በከተሞች ሳምንት ክብረ በዓላት ላይ አሸናፊ እንድትሆን ያደረጋት በመሰረተ ልማት ውጤታማ በመሆኗ ነው፡፡
ርዕሰ መሰተዳድሩ እንዳሉት የከተማ አስተዳደሩና ህብረተሰቡ ተቀናጅተው ያከናወኗቸው  የልማት ተግባራት ሀዋሳ በሀገር አቀፍ ደረጃ ላገኘችው ዕውቅና ባለቤቶች ናቸው፡፡
ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን በመሰለፍ ያስመዘገበውን ፈጣን ልማትና እድገት  በመልካም አስተዳደር ፣በግብር አከፋፈልና በመሬት አስተዳደር መስክም ያሉትን የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች በማስቀረት ላይ እንዲደግመው አቶ ደሴ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዮናስ ዮሴፍ እንዳሉት አስተዳደሩ የህዝቡን የመሰረተ ልማት አቅርቦት ጥያቄ ምላሽ የሚሰጡ ተግባራት እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በከተማዋ እየተከናወኑ ካሉት መካከል 60 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው አስፓልት፣ ከ356 ኪሎ ሜትር በላይ የጠጠርና የድንጋይ ንጣፍ መንገድ ግንባታ ተጠናቆ ዛሬ ለምረቃ መብቃታቸውን ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም ከከተማዋ እድገት ጋር የተመጣጠነ የኤሌክትሮ ሜካኒካል የእንስሳት እርድ ማካሄጃ መሳሪያ የተተከለለት  ዘመናዊ ቄራ ከ68 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በመገንባት  ስራ ላይ ውለዋል፡፡
ከዚህም ሌላ የትምህርትና የጤና ተቋማት ማስፋፊያ ፣ የከተማው አስተዳደር ቢሮ ፣ የፍሳሽ ማስወገጃና ማጣሪያ ፣የባህል ማዕከልና ሌሎች የመሰረተ ልማት ተቋማት  ዛሬ ለምረቃ የበቁ ናቸው፡፡
ለግንባታዎቹ በአጠቃላይ ከአንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ  ወጪ መደረጉንም ከንቲባው አመልክተዋል፡፡
በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር ካነጋገራቸው ነዋሪዎች መካከል አቶ ተከስተብርሃን ሀጎስ እንዳሉት በከተማዋ ከ20 ዓመት በላይ ኖረዋል፡፡
ቀደም ሲል የከተማዋ የአስፋልት መንገድ መስመር በአንድ በኩል  ብቻና ይህም ቢሆን ለብልሽት ተዳርጎ እንደነበር አስታወሰው "አሁን ባለው ሁኔታ ግን ከተማዋ ምቹ የሆኑ በርካታ የአስፋልት መንገዶች ባለቤት መሆን ችላለች "ብለዋል፡፡
ሌላው ነዋሪ ኮረኔል ቦጋለ መገነ በበኩላቸው ከሰላሳ ዓመት በፊት ሀዋሳን ከሚያውቋት ጋር አሁን ያለውን ለውጥና መሻሻል ሲመለከቱ ግርምት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡
- See more at: http://www.ena.gov.et/index.php/economy/item/3967-2015-04-25-23-25-01#sthash.SN7zVzvr.dpuf

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር