የኢንዱስትሪ ፓርኮች ረቂቅ አዋጅ ከሕገ መንግሥቱ ጋር እንዲታረቅ የፓርላማ አባላት ጠየቁ

መጋቢት 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ረቂቅ አዋጅ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ቢኖረውም፣ ከሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች ጋር የሚቃረኑ አንቀጾችን የያዘ በመሆኑ እንዲስተካከል የፓርላማ አባላት ጠየቁ፡፡
የቀረበው ረቂቅ አዋጅ አገሪቱ የቀረፀቻቸውን ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች መሠረት በማድረግ ከ40 እስከ 50 ዓመታት ባሉት ጊዜያት ውስጥ በኢንዱስትሪ የዳበረችና ዜጎቿም ከፍተኛ ገቢ ያላቸው እንዲሆኑ እንዲሁም፣ እስከ 2017 ዓ.ም. ባለው የስትራቴጂው ምዕራፍ አገሪቱ ከድህነት ተላቃ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ጎራ መቀላቀል እንድትችል ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡
ረቂቅ አዋጁ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እንዲከናወን የሚፈቅድ ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በመሬት አጠቃቀም ላይ የሚታየውን የኪራይ ሰብሳቢነት አደጋ ለማስቀረት፣ የሎጂስቲክስና የጉምሩክ አገልግሎት ችግሮችን ለማስወገድ፣ መሠረት ልማቶችን በማሟላት የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ያለብዙ ውጣ ውረድ እንዲሳተፉና በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ምርትና ኤክስፖርት ተግባር እንዲሸጋገሩ የሚያስችል መሆኑን የአዋጁ መግቢያ ይገልጻል፡፡
የረቂቅ አዋጁ ክፍል አንድ አንቀጽ ሁለት ንፁስ አንቀጽ ሦስት ለመሬት የሚሰጠው ትርጓሜ አግባብነት ላይ የፓርላማ አባላት ጥያቄያቸውን አንስተዋል፡፡ ‹‹መሬት ማለት ለኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ዓላማ የተሰየመ ማንኛውም መሬት ነው፤›› ይላል፡፡
የምክር ቤቱ የመከላከያና የውጭ ደኅንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሜቲ ሰብሳቢ አቶ ተሰፋዬ ዳባ በረቂቁ ላይ የተቀመጠው ድንጋጌ፣ ሕገ መንግሥቱ ለክልሎች የሰጠውን መሬት የማስተዳዳር መብት ጋር የሚጣረስ መሆኑን በመጠቆም ማስተካከል እንደሚገባው ጠቁመዋል፡፡
የረቂቅ አዋጁ ድንጋጌዎች የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚሰየሙት በፌዴራል መንግሥት መሆኑንና ፓርኮቹ ደግሞ በኢትዮጵያ ግዛት ወሰን ውስጥ የሚፈጸም በመሆኑ፣ የክልሎችን መሬት የማስተዳደር መብት ይጋፋል ብለዋል፡፡
የተነሳው ጥያቄና ሌሎች የረቂቁን አንቀጾች በዝርዝር በመመልከት የውሳኔ ሐሳብ ይዞ እንዲቀርብ፣ ለኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ረቂቅ አዋጁ ተመርቷል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር