POWr Social Media Icons

Saturday, March 28, 2015

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አርሶ አደርን ጨምሮ ከአርቲስትና ከተማሪ ጋር ለምርጫ ይወዳደራሉጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦና ሕዝቦች ክልል በወላይታ ዞን በቦሎሶሶሬ ሁለት የምርጫ ክልል ገዥው ፓርቲን በመወከል ለፓርላማ እንደሚወዳደሩ ታወቀ፡፡ 
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚወዳደሩበት የምርጫ ክልል ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተፎካካሪ የሚሆኑ ዕጩዎችን ያቀረቡት ፓርቲዎች ደግሞ አዲስ ትውልድ ፓርቲ (አትፓ)፣ መድረክና ሰማያዊ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ በእነዚህ ፓርቲዎች አማካይነት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመፎካከር የቀረቡት ደግሞ አትፓን በመወከል አርቲስት ደስታ ደአ፣ መድረክን የወከሉት አርሶ አደሩ አቶ ተስፋዬ ኃይሌና ሰማያዊ ፓርቲን  የወከሉት ተማሪ ቀኙ ሴባ የተባሉ ዕጩዎች ናቸው፡፡ 
በ1987 እና በ1992 ዓ.ም. በተካሄዱ ምርጫዎች የደቡብ ክልል ምክር ቤት አባል የነበሩት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ደቡብ ክልልን በምክትልነትና በፕሬዚዳንትነት አስተዳድረዋል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1997 ዓ.ም. ለፓርላማ ተወዳድረው የፓርላማ አባል ከሆኑ በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ፣ የሕዝብ አደረጃጀትና ተሳትፎ አማካሪና በፓርላማ የመንግሥት ተጠሪ ሆነው መሥራታቸው አይዘነጋም፡፡ እንደገና በ2002 ዓ.ም. ተወዳድረው ፓርላማ ከገቡ በኋላ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላ ከመስከረም 11 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትርነት በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ለሦስተኛ ጊዜ ነው ለፓርላማ የሚወዳደሩት፡፡
በዚሁ የምርጫ ክልል ቦሎሶሶሬ ሦስት ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉም እንዲሁ ገዥው ፓርቲን ወክለው፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሚደረገው ምርጫ እንደሚወዳደሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በዚሁ በደቡብ ክልል ስልጤ ዞንም እንዲሁ ከፍተኛ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ገዥው ፓርቲን ወክለው ከተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲ ዕጩዎች ጋር ውድድር ያደርጋሉ፡፡
በስልጤ ዞን ከሚወዳደሩት ዕጩዎች መካከል የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ዋና ኃላፊ አቶ ሬድዋን ሁሴንና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል የመንግሥት ተጠሪ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
አቶ ሲራጅ ፈጌሳ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና ሰማያዊ ፓርቲን ከሚወክሉ ዕጩዎች ጋር የሚወዳደሩ ሲሆን፣ አቶ ሬድዋን ሁሴን ደግሞ ከመድረክ ዕጩ ጋር ይወዳደራሉ፡፡ ወ/ሮ ሙፈሪያት በሚወዳደሩበት የቅባት ምርጫ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች የሚወዳደሩ ብቸኛ ዕጩ ናቸው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በክልሉ የሲዳማ ዞን በኦሮሬሳ የምርጫ ክልል የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ መድረክን ከሚወክል ዕጩ ተወዳዳሪ ጋር ይወዳደራሉ፡፡ 
በደቡብ ክልል ከመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተጨማሪ ታዋቂ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችም እንዲሁ ተፎካካሪ ሆነው ቀርበዋል፡፡
የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ከሆኑት መካከል በ1992 እና በ1997 ምርጫ አሸንፈው የፓርላማ አባል የነበሩት ታዋቂው ፖለቲከኛ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ መድረክን ወክለው በሐድያ ዞን ሲቄ 02 የምርጫ ክልል ይወዳደራሉ፡፡
በዚሁ ዞን ሶሮ 02 የምርጫ ክልል ደግሞ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ሽፈራው ተክለ ማርያም ከሰማያዊና ከመድረክ ተወካዮች ጋር ይወዳደራሉ፡፡ 
በክልሉ ከሚወዳደሩ ሌሎች የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች መካከል የመድረክ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጥላሁን እንደሻው በሰገን ሕዝቦች ዞን ቡርጂ የምርጫ ክልል የሚወዳደሩ ሲሆን፣ በሲዳማ ዞን ሐዋሳ ምርጫ ክልል ደግሞ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ሲዳ ኃይሌ ይወዳደራሉ፡፡
የቤቶች፣ የከተማ ልማትና የኮንስትራክሽን ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ኃይሌም እንዲሁ ገዥው ፓርቲን ወክለው በክልሉ ጉራጌ ዞን እዣ 1 የምርጫ ክልል ከቅንጅትና ከሰማያዊ ፓርቲ ዕጩዎች ጋር ይወዳደራሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በክልሉ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እንደሚወዳደሩ ለማወቅ ተችሏል፤ ከእነዚህም መካከል የንግድ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ያዕቆብ ያላ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ታደለች ዳለቾና የቀድሞ የውኃ ሀብት ሚኒስቴርና የወቅቱ የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር የሕዝብ ግንኙነት ጉዳይ አማካሪ የሆኑት አቶ አስፋው ዴንጋሞ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡      

0 comments :