ሁለት ወራት የቀሩት ምርጫና የፓርቲዎቹ የቅስቀሳ ዘመቻ

አምስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ልክ የዛሬ ሁለት ወር በመላው አገሪቱ ይከናወናል፡፡ ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የፖለቲካ ፓርቲ ዕጩዎች ምዝገባ፣ የመራጮች ምዝገባና የመሳሰሉት ጉዳዮች ተፈጽመዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ውድድር እንቅስቃሴም በይፋ ተጀምሮ በመካሄድ ላይ የሚገኝ ሌላው የጊዜ ሰሌዳው አካል ነው፡፡ 
ከየካቲት 14 ቀን 2007 ዓ.ም. አንስቶ በመካሄድ ላይ የሚገኘው የፓርቲዎችና የዕጩዎች የምርጫ ውድድር የተለያዩ ገጽታዎች ነው ያሉት፡፡ ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለሥልጣን ባወጣው የፖለቲካ ፓርቲዎች ነፃ የአየር ሰዓትና የጋዜጣ ዓምድ ድልድል መሠረት፣ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሉዋቸውን የፖሊሲና የስትራቴጂ አማራጮችን የተመለከቱ እንቅስቃሴዎቻቸውን እንዲያስተላልፉ የተሰጠው አሠራር አንዱ ነው፡፡ 
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የተሰጣቸውን የአየር ሰዓትና የጋዜጣ ዓምድ ድልድል በአግባቡ እየተጠቀሙበት እንዳልሆነ የሚመለከታቸው አካላት በተደጋጋሚ ይገልጻሉ፡፡ በዚሁ ልክ ደግሞ የተወሰኑ ፓርቲዎች እንዲሁ ልናስተላልፍ ያቀረብነው የቅስቀሳ ጽሑፍ ወይም ፕሮግራም አላግባብ ሳንሱር እየተደረገ ውድቅ ሆኖብናል በማለት መልሰው ይከሳሉ፡፡
በሁለቱ ጽንፎች መካከል እየተካሄደ ባለው የፖለቲካ ፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ ወቅት፣ ፓርቲዎቹ ለሕዝብ የተለያዩ መልዕክቶችን በማስተላለፍ ላይ ይገኛሉ፡፡ ሞቅ ባለ ሁኔታ በየከተማው የተለያዩ ሥፍራዎች የሚከናወኑ የምረጡኝ ዘመቻዎችና እንቅስቃሴዎች ግን እምብዛም የሚስተዋሉ አልሆኑም፡፡ አስተያየት ሰጪዎች ይህን መሰሉ እንቅስቃሴ ከምርጫ 97 ጋር አብሮ መጥፋቱን ያወሳሉ፡፡  
ከዚህም ባሻገር ፓርቲዎች ከምረጡኝ ቅስቀሳና ዘመቻ በተጨማሪ፣ በሚያራምዷቸው ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለሞች እንዲሁም የሚያቀርቧቸው አማራጭ ሐሳቦችን መሠረት ያደረጉ ክርክሮችም እንዲሁ ወደ መራጩ እየደረሱ ነው፡፡
እነዚህ የክርክር መድረኮች የመራጩን ሕዝብ ይሁንታ ለማግኘት የሚኖራቸው ጠቀሜታ ከፍተኛ እንደሆነ የሚያስረዱ የፖለቲካ ሳይንስ የንድፈ ሐሳብ ጽሑፎች በርካታ ናቸው፡፡
የመራጩን ይሁንታ ለማግኘት ፓርቲዎች ለመከራከር ሲቀርቡ በተጨባጭ የአገሪቱን አሠራሮችና አደረጃጀቶች፣ እንዲሁም ተቋማት ላይ አሉ የሚሏቸውን ችግሮች፣ ግድፈቶችና ጉድለቶችን እየዘረዘሩ እንደሆነ በአደባባይ ታይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ለተዘረዘሩት ችግሮች፣ ግድፈቶችና ጉድለቶች መፍትሔ የሚሆኑ ተጨባጭ የተብራሩ እንዲሁም ግልጽ የሆኑ አማራጭ ሐሳቦችን ለመራጩ ማቅረብ መቻል መራጩን ለመሳብ ዋነኛው መሣርያ እንደሆነ ይገለጻል፡፡
ይህ መርህ ለሁሉም የፖለቲካ ተወዳዳሪ ኃይሎች የሚሠራ ቢሆንም፣ በሥልጣን ላይ ያለና በምርጫ አሸንፎ ሥልጣን የሚይዝ አካል የሚሄድበት መንገድ ግን ይለያል፡፡ በዚህም መሠረት በሥልጣን ላይ ያለው አካል ማሳካት አልቻልክም የሚባለውን ጉድለት አሳክቻለሁ ብሎ ሲከራከርና ለሚሰነዘሩበት የመከራከሪያ ነጥቦች ምላሽ ሲሰጥ፣ ማስረጃ ማቅረብና በዚያ አካሄድ ምን ያህል ውጤት መመዝገቡን መዘርዘር ይችላል፡፡ በአንፃሩ በሥልጣን ላይ የማይገኝ ፓርቲ ከተፎካካሪዎቹ የሚለየውን አቅጣጫ ከማጉላት ባሻገር፣ የሚያመጣቸውን አዳዲስ አሠራሮች መዘርዘር እንደሚኖርበት የፖለቲካ ሳይንስ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡ 
በዚሁ መሠረት በምርጫ ተወዳድረው ሥልጣን ለመያዝ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችም እንዲሁ ከትችትና የዕለት ተዕለት የሕዝቡን ችግር ከመንቀስና ከመዘርዘር ባለፈ፣ አማራጮችን ማቅረብ ዋነኛ ትኩረታቸው አድርገው መንቀሳቀስ እንደሚገባቸውም ያስገነዝባሉ፡፡
የዘንድሮውን ጠቅላላ ምርጫ መሠረት አድርገው እየተካሄዱ ባሉት ክርክሮች በአብዛኛው የተስተዋለው ግን፣ ከዘርፉ ምሁራን ምክር በተቃራኒው የሚቆም እንደሆነ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች ይገልጻሉ፡፡
ምንም እንኳን በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ገዥ የሆኑ ሐሳቦችን ለማዳመጥ ቢቻልም፣ እስካሁን ድረስ በተካሄዱት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል በተዘጋጀው ክርክርና በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢብኮ) አማካይነት በተካሄዱ ሁለት ክርክሮች ለማስተዋል የተቻለው፣ የተለመደው ዓይነት የማጣጣልና ዕውቅና የመንሳት ክርክር እንደነበርም ለአብነት ያነሳሉ፡፡ 
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት አማካይነት የተካሄደው ክርክር ማጠንጠኛው ርዕዮተ ዓለም ነበር፡፡ በዕለቱም በማኅበራዊ ዴሞክራሲ፣ በሊበራል ዴሞክራሲና በልማታዊ ዴሞክራሲ ተወካዮች አማካይነት ክርክር ተደርጐ ነበር፡፡ በዕለቱም ከፓርቲዎቹ ርዕዮተ ዓለም አንፃር በዝርዝር የቀረቡ አሳማኝ አማራጮች ነበሩ ለማለት እንደሚቸገሩ አስተያየት ሰጪዎቹ ይጠቁማሉ፡፡ 
በኢብኮ (የቀድሞው ኢቲቪ) አማካይነት በመካሄድ ላይ ያለው ክርክር ደግሞ መጋቢት 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ተጀምሯል፡፡ ክርክሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ባፀደቃቸው ዘጠኝ አጀንዳዎች ዙሪያ የሚደረግ ነው፡፡ በዚህም መሠረት እስካሁን ድረስ በሁለት አጀንዳዎች ላይ ፓርቲዎቹ ተከራክረዋል፡፡
የጋራ ምክር ቤቱ ያፀደቃቸው ዘጠኝ የክርክር አጀንዳዎች የመድበለ ፓርቲና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ ፌደራሊዝም፣ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ፣ የከተማና ኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲ፣ መልካም አስተዳደርና የሕግ የበላይነት፣ የውጭ ጉዳይና ደኅንነት ፖሊሲ፣ መሠረተ ልማት፣ ትምህርትና ጤና የሚሉ ናቸው፡፡
በዕቅዱም መሠረት እስካሁን ድረስ በሁለቱ አጀንዳዎች ላይ ክርክር የተደረገ ሲሆን፣ ክርክር የተደረገባቸው አጀንዳዎች ደግሞ የመድበለ ፓርቲና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና ፌደራሊዝም በሚሉት አጀንዳዎች ላይ ነው፡፡ 
የፓርቲዎች የቤት ሥራ
የምርጫ ዘመቻው በይፋ ከተጀመረ በኋላ ፓርቲዎች በተለያዩ መንገዶች ወደ ሕዝቡ እየደረሱ እንደሆነና ዕቅዶቻቸውን በማስፈጸም ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ዘመቻውንም በተጠናከረ ሁኔታ እያከናወኑ እንደሆኑ የሚገልጹ እንዳሉ ሁሉ፣ በተለየ የአሠራር ስትራቴጂ ምክንያት ዘመቻውን አጠናክረው በይፋ ያልጀመሩ ፓርቲዎችም አሉ፡፡
ከእነዚህ ፓርቲዎች መካከል የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ተጠቃሽ ነው፡፡ የፓርቲው የጥናትና የምርምር ኃላፊ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኢዴፓ ከቅስቀሳው መጀመር በፊት ያሉትን በተለይ የዕጩዎች ምዝገባን በተሳካ ሁኔታ ቢያከናውንም የምርጫ ቅስቀሳውን ሙሉ በሙሉ አልጀመረም፡፡
ኢዴፓ በምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ያከናወናቸው ተግባራት ያሉ መሆኑን የገለጹት አቶ ዋሲሁን፣ የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻን በቴሌቪዥን ከሚቀርቡ የክርክር መድረኮች ባሻገር እንዳልጀመረ ግን ገልጸዋል፡፡ ‹‹እስካሁን ባለው ሁኔታ የምርጫ ቅስቀሳውን አልጀመርነውም ማለት ይቻላል፤›› ብለዋል፡፡
ለዚህ የሚያቀርቡት የመጀመርያ ምክንያት የቁሳቁስ ዝግጅቶችን በማከናወን ላይ መሆናቸውን ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ሲገልጹ ደግሞ፣ ‹‹ከልምድ አንፃር እንደተመለከትነው ቅስቀሳ ውጤታማ የሚሆነው በመጨረሻው አንድ ወር በተጠናከረ ሁኔታ ሲሠራ ነው፡፡ ከአቅምም አንፃር አዋጭ የሚሆነው ይኼ መንገድ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ከዕጩዎች ማስመዝገቢያ ማብቂያ አንስቶ እስካሁን ድረስ ያለውን ጊዜ እየተጠቀምንበት ያለነው ቁሳቁስ ለማዘጋጀትና ለመሳሰሉት ሥራዎች ነው፣›› ሲሉም አክለዋል፡፡
በዚህም መሠረት ከሚያዝያ መጀመርያ አንስቶ የምርጫ ዘመቻው እስከሚጠናቀቅበት ግንቦት 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ ቅስቀሳን በተመለከተ ኢዴፓ በሰፊው ለመሥራት መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ 
በምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ዕጩዎችን ማስመዝገባቸውንና የቅስቀሳ ዘመቻቸውንም በዚያው መሠረት መጀመራቸውን የሚገልጹት ደግሞ፣ የመድረክ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጥላሁን እንደሻው ናቸው፡፡
‹‹የምርጫ ቅስቀሳ ሥራዎችን በተመለከተ የተለያዩ የምርጫ ቅስቀሳ ቁሳቁሶችን ዝግጅት በወቅቱ አጠናቀን ሥራ ላይ በማዋል እንገኛለን፤›› በማለት መድረክ ከአሁኑ የቅስቀሳ ሥራውን ማከናወን ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
ምንም እንኳን አስፈላጊዎቹን ዝግጅቶች ማከናወናቸውን ቢገልጹም፣ ከገዥው ፓርቲ በኩል ቅስቀሳን በተመለከተ እየደረሰባቸው ያለውን ችግር ይዘረዝራሉ፡፡ በተለይ በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት አቋማቸውን ለመዘርዘር መቸገራቸውን ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ከፍተኛ የመቆጣጠር ሥልጣን ለጋዜጠኞች ስለተሰጠ ገዥውን ፓርቲ የምንወቅስባቸው ወይም የምንተችባቸው ጽሑፎችና ፕሮግራሞች እየተገደቡብን ነው፤›› በማለት ጋዜጠኞችን ወቅሰዋል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ በበኩላቸው፣ ‹‹በአገር አቀፍ ደረጃ በየክልሉ ባሉ መዋቅሮቻችን በወረቀት የሚበተን፣ በፖስተርና በባነር በመሳሰሉት አንድ ዙር የቅስቀሳ እንቅስቃሴ አድርገናል፤›› በማለት የምርጫ ቅስቀሳን ፓርቲው በይፋ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ ‹‹በአዲስ አበባ ደግሞ ሁለት ቅዳሜዎችን ለሁለት ዙር ቅስቀሳ መጠቀም ችለናል፤›› በማለት የምርጫ ቅስቀሳ እንቅስቃሴያቸው አስቀድሞ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳውን ለማሳካት ባቀደው መሠረት እያከናወነ አለመሆኑንም አቶ ዮናታን አስገንዝበዋል፡፡ ‹‹ይህን ያህል መሄድ አለበት ብለን ባቀድነው መሠረት አልሄደም፡፡ እኛም አልረካንበትም፡፡ ችግሮች እየተቀረፉ ምን ያህል እንሄዳለን የሚለው ወደፊት የሚታይ ነው፤›› በማለት የተለያዩ ችግሮች መፈጠራቸው ለዕቅዳቸው አለመሳካት ምክንያት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ፓርቲዎቹ አጋጠሙን ካሏቸው ችግሮች በተጨማሪ ግን በቴሌቪዥን በተካሄዱ ክርክሮች ባሳዩት እንቅስቃሴ የብዙ ሰዎችን ይሁንታ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡
በዚህም መሠረት ‹‹ሕዝቡ የሚያውቃቸውን ጉዳዮች ስለምናነሳ ክርክሩን ተከትሎ የሕዝቡ ምላሽ በጣም ደስ የሚል ነው፤›› ያሉት አቶ ጥላሁን ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ የሚሰጠው አስተያየት ወደ መድረክ ቢሮም መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
‹‹የበለጠ ስለገዥው ፓርቲ ስለምናውቅ የራሳችሁን አማራጭ ለማስቀመጥ እንጂ፣ የኢሕአዴግን ችግር ለማብራራት አትድከሙ እያሉ ይነግሩናል፤›› በማለት ሕዝቡ ከመድረክ አማራጭ ሐሳቦችን እንደሚፈልግ መግለጹን ጠቁመዋል፡፡
በተመሳሳይ የሕዝቡ ምላሽ በጣም ጥሩ የሚባል እንደሆነ አቶ ዮናታንና አቶ ዋሲሁን ገልጸዋል፡፡ 
በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የፀደቁት ዘጠኝ የመከራከርያ አጀንዳዎች ለፓርቲዎች በዕጣ የተከፋፈሉ መሆኑን የተገለጸ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት መድረክ በሰባት የክርክር አጀንዳዎች ላይ ይሳተፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ መድረክ የማይሳተፍባቸው የክርክር መድረኮች ደግሞ በሁለተኝነት የተካሄደው የመከራከሪያ አጀንዳ ፌደራሊዝምና የከተማና የኢንዱስትሪ ልማት ናቸው፡፡
ኤዴፓ ደግሞ በአምስት የመከራከሪያ አጀንዳዎች ላይ እንደሚሳተፍ ሲጠበቅ፣ በዚህም መሠረት በመጀመርያው የክርክር አጀንዳ የመድበለ ፓርቲና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የሚለው አጀንዳ ላይ አልተሳተፈም፡፡ በቀጣይ በማካሄዱ የግብርናና የገጠር ልማት ፖሊሲ፣ የውጭ ጉዳይና የደኅንነት ፖሊሲ እንዲሁም በትምህርት ላይ በሚካሄዱ አጀንዳዎች ላይ ተካፋይ አይሆንም፡፡ 
በተመሳሳይ በአምስት አጀንዳዎች ላይ የሚሳተፈው ሰማያዊ ፓርቲ ደግሞ በሁለተኝነት በተካሄደው የፌደራሊዝም ክርክር ላይ ያልተሳተፈ ሲሆን፣ በቀጣይ በሚካሄዱት የከተማና ኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲና በጤና አጀንዳዎች ላይ ተሳታፊ አይሆንም፡፡ ‹‹የመድብለ ፓርቲና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አጀንዳ ላይ የተከራከርነው ተጋብዘን ስለሆነ፣ አሁንም ከተጋበዝን በዕጣ ባልወጡልን አጀንዳዎች ላይም ለመሳተፍ ዝግጁዎች ነን፤›› በማለት አቶ ዮናታን አስተያየታቸውን ቋጭተዋል፡፡        

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር