በሐዋሳ ከተማ የተከራካሪያቸውን ጠበቃ ገድለዋል የተባሉት ባለሀብት በሞት እንዲቀጡ ተወሰነ

-በጥይት ተመትተው የተረፉት ሌላው ጠበቃ አካላቸው አይንቀሳቀስም 
በሐዋሳ ከተማ የተከራካሪያቸውን ጠበቃ ገድለዋል የተባሉት ባለሀብት በሞት እንዲቀጡ ተወሰነበደቡብ ክልል በሐዋሳ ከተማ መስከረም 27 ቀን 2007 ዓ.ም. የተከራካሪያቸውን ጠበቃ በሽጉጥ ገድለዋል ተብለው ክስ ተመሥርቶባቸው የነበሩት የ‹‹ብሉ ናይልና ኢቪኒንግ ስታር›› ሆቴሎች ባለቤት አቶ ታምራት ሙሉ፣ መጋቢት 4 ቀን 2007 ዓ.ም. በሞት እንዲቀጡ ሐዋሳ የሚገኘው የደቡብ ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቅጣት ውሳኔ ሰጠ፡፡
ፍርደኛው አቶ ታምራት የተከራካሪያቸውን ጠበቃ አቶ ዳንኤል ዋለልኝ በጥይት መትተው ከገደሏቸው በኋላ፣ ረዳት ጠበቃ የነበሩትን አቶ ዳግማዊ አሰፋን አንገታቸው አካባቢ በጥይት መትተው በማምለጥ ለ15 ቀናት ያህል ተሰውረው መክረማቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያመለክታል፡፡
የደቡብ ክልል ፍትሕ፣ ፀጥታና ፖሊስ ኮሚሽን የመርማሪ ቡድን በፍጥነት በማቋቋም ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነትና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመተባበር ባደረገው ክትትል፣ አቶ ታምራት ወደ አዲስ አበባ እየሄዱ ሳለ በኦሮሚያ ክልል ገላን ከተማ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም ክሱ ያስረዳል፡፡
ፍርደኛው በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ለፖሊስም ሆነ ፍርድ ቤት ቀርበው በሰጡት የዕምነት ቃል ድርጊቱን መፈጸማቸውን አረጋግጠዋል፡፡ አቶ ታምራት ሟች ጠበቃ ዳንኤልን ሊገድሉዋቸው የቻሉት፣ ቀደም ብሎ በሟች ደንበኛ ተከሰው የተወሰነ ጊዜ ከተከራከሩ በኋላ በሟች አማካይነት ጉዳዩን በስምምነት ይጨርሳሉ፡፡ ከጠበቃ ዳንኤል ጋርም በዚያ ምክንያት ይተዋወቁና ይግባባሉ፡፡ ነገር ግን አቶ ታምራት በሌላኛው የጠበቃ ዳንኤል ደንበኛ ሌላ ክስ ሲመሠረትባቸው፣ ጠበቃ ዳንኤል ጥብቅና እንዳይቆሙላቸው ፍርደኛው ይነግሩዋቸዋል፡፡ ጠበቃ ዳንኤል ግን ይቃወማሉ፡፡ የደንበኛቸውን ጉዳይ የሚይዙት እሳቸው መሆናቸውን፣ ከአቶ ታምራት ጋር ለመነጋገር የጥብቅና ሥነ ምግባሩም ስለማይፈቅድላቸው መነጋገር የሚችሉት ከደንበኛቸው ጋር ብቻ መሆኑን ያስረዷቸዋል፡፡ ሥራቸውንም ይቀጥላሉ፡፡ በጠበቃ ዳንኤል የተናደዱት አቶ ታምራት ሲዝቱባቸው ከርመው መስከረም 27 ቀን 2007 ዓ.ም. የሚሠሩበት ቢሮ ድረስ ሄደው ግድያውን እንደፈጸሙባቸው ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስረድቷል፡፡
የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን በማሰባሰብ እንዲሁም የክልሉ ገቢዎችና ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አቶ ታምራትን በታክስ ጉዳይ ክስ መሥርቶባቸው 12 ዓመታት የእስር ቅጣት የተጣለባቸውን የውሳኔ ሰነድ በማቅረብ ዓቃቤ ሕግ ክሱን ሲመሠርት፣ አቶ ታምራት በጠበቃቸው አማካይነት ክሱን ተቃውመዋል፡፡ ድርጊቱን በደም ፍላት እንደፈጸሙት በመግለጽ የተመሠረተባቸውን ክስ የተቃወሙ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ ሳይቀበላቸው በመቅረቱ የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተው ወደ ክርክሩ ገብተዋል፡፡ 
ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ አቶ ታምራት ላይ የመሠረታቸው ክሶች አራት ናቸው፡፡ የግፍ አገዳደል፣ በከባድ የሰው መግደል ሙከራ፣ ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ክምችትና ከባድ ዛቻ የሚሉ ናቸው፡፡ ዓቃቤ ሕግ 13 የሰው ምስክሮችን አቅርቦ 12ቱን አሰምቷል፡፡ የግፍ አገዳደልና ከባድ የመግደል ሙከራ በሚለው ላይ የተቆጠሩት ምስክሮች አቶ ታምራት ሽጉጣቸውን በጨርቅ ጠቅለውና በፌስታል አድርገው ዕቃ በማስመሰል፣ የጠበቃ ዳንኤልን ጸሐፊ በማነጋገር ወደ ውስጥ ገብተው ሟቹን ተኩሰው ጎናቸው ላይ በመምታት ሲገድሉ ማየታቸውን፣ ረዳት ጠበቃ ዳግማዊ አሰፋ ‹‹ሰው ገድለህ የት ታመልጣለህ?›› በማለት ሲከተሏቸው እሳቸውንም ተኩሰው አንገታቸው አካባቢ ሲመቱ ማየታቸውንና ሌሎች ድርጊቶችን በመናገር የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ 
ዓቃቤ ሕግ በፍርደኛው ቤት የተገኙ አምስት የተለያዩ ዘመናዊ ያልሆኑ ሽጉጦች፣ 102 ጥይቶችና ሁለት ኤፍዋን ቦምቦችን በሚመለከት ሕገወጥ መሆናቸውን አስረድቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ የዓቃቤ ሕግን ክስና የምስክሮች ቃል ከመረመረ በኋላ ፍርደኛው አቶ ታምራት እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል፡፡
አቶ ታምራት ሁለት መከላከያ ምስክሮችን የቆጠሩ ሲሆን፣ መከላከያ ምስክሮቹ አቶ ታምራትና ሟች ጠበቃ ዳንኤል መልካም ግንኙነት እንደነበራቸው፣ ጠበቃ ዳንኤል በተደጋጋሚ ወደ ብሉ ናይል ሆቴል እየሄዱ ከአቶ ታምራት ጋር ይገናኙ እንደነበር መስክረዋል፡፡ የጦር መሣሪያዎቹ ለቱሪዝም አገልግሎት የሚውሉ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡ አቶ ታምራት ወንጀሉን ለመፈጸም ያነሳሳቸውን ምክንያት ግን እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ሁለቱ ወገኖች ያቀረቡትን ማስረጃና የክስ ሒደት መርምሮና መዝኖ፣ አቶ ታምራት የዓቃቤ ሕግን ክስ ሙሉ በሙሉ ሊያስተባብሉ ባለመቻላቸው የካቲት 27 ቀን 2007 ዓ.ም. በሁሉም ክሶች ጥፋተኛ ብሏቸዋል፡፡
በደቡብ ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት መጋቢት 4 ቀን 2007 ዓ.ም. የተሰየሙ ሦስት ዳኞች፣ አቶ ታምራት ጥፋተኛ የተባሉባቸውን አራት ክሶች በቅጣት አወሳሰን መመርያው አማካይነት ሲመለከቷቸው፣ ሁሉም የመጨረሻውን ቅጣት የሚይዙ ሆነው አግኝተዋቸዋል፡፡ አቶ ታምራት በአንድ የክስ መዝገብ በተደራራቢ ወንጀል ጥፋተኛ ከመባላቸው አንፃር በአራቱም ላይ ቅጣት መጣል እንደማይቻል ገልጸው፣ ሁሉንም ክሶች አካቶ የሚይዝ ወንጀል ‹‹የግፍ አገዳደል ወንጀል›› በሚለው ሥር እንዲጠቃለሉ አድርገዋል፡፡ የመጀመሪያ ክስ የሆነው የግፍ አገዳደል ወንጀል ቅጣት ደግሞ ሞት በመሆኑ፣ የብሉ ናይል ሆቴልና የኢቪኒንግ ስታር ሆቴል ባለቤት አቶ ታምራት ሙሉ ምትኩ በሞት እንዲቀጡ የቅጣት ውሳኔ ሰጥተዋል፡፡ ረዳት ጠበቃ አቶ ዳግማዊ አሰፋ አንገታቸው አካባቢ በደረሰባቸው የጥይት ምት ጉዳት አዲስ አበባ በሚገኘው ኮሪያ ሆስፒታል በተደረገላቸው ምርመራ፣ አከርካሪያቸው ውስጥ ያለ አንድ መቅኒ ስለፈሰሰ አካላቸው እንደማይታዘዝ (ፓራላይዝድ) መረጋገጡም ታውቋል፡፡ ክሱን የመሠረተው የደቡብ ክልል ከፍተኛ ዓቃቤ ሕግ ሲሆን፣ ክርክሩን ያደረጉት ዓቃቢያነ ሕግ አቶ ሲሳይ ጌታሁንና አቶ አበዙ አስፋው ናቸው፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር