ኢሕአዴግ የምርጫ ሥነ ምግባር ማውጣት ብቻ ሳይሆን አርዓያ ሆኖ ይገኝ

በሽባባው በላይ
በብዙ አገሮች በሥልጣን ላይ ያሉ ፓርቲዎች የሕዝቡን ይሁንታ አግኝተው በተጨማሪ ጊዜ አገር መምራትን ይመኛሉ፡፡ በተለይ ሕጉ ከፈቀደላቸው በአንዳንድ አገሮች የመንግሥትንም ሆነ የፓርቲን ጉልበት እየተጠቀሙ ወደ ውድድር
መግባታቸው ይታያል፡፡ የሠለጠኑትና ያደጉት አገሮች ፓርቲዎች (ዕጩ ፕሬዚዳንቶች) ግን የተቀመጡበት ኮርቻው የመንግሥት ቢሆንም ከክሱ ላይ ወርደው ለመወዳደር ይጥራሉ፡፡ 
ኢሕአዴግ በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ለ25 ዓመታት ገደማ በመሪነት መቀመጡ ብቻ ሳይሆን፣ ‹‹ተጨማሪ 40 ዓመታት ካገኘሁ የአገሪቱን ህዳሴ አረጋግጣለሁ!›› ብሎ መናገር ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ስለሆነም በሥልጣን ላይ ለመቆየት ብቻ ሳይሆን፣ በሕዝብ ይሁንታ በሥልጣን ለመዝለቅ ከፍተኛ ፍላጐት እንዳለው ጥርጥር የለውም፡፡ 
እንደ አንድ አስተያየት ሰጪ ድርጅቱ 40 ዓመት ልቆይ ማለቱ ብዙ ችግር አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን የዴሞክራሲ መርሆዎች እየተሸራረፉ፣ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት እየተዳከመ፣ በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ስም የጥቂቶች ፈላጭ ቆራጭነት እያቆጠቆጠ፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ሳይረጋገጥ፣ ልማትን ሽፋን በማድረግ የሕግ የበላይነትን በመዘንጋትና መልካም አስተዳደርን ባለማረጋገጥ ወዘተ፣ ለመጓዝ ካሰበ በየትኛውም መንገድ ቢሆን ያሰበውን ሊያሳካ አይችልም፡፡ 
የኢትዮጵያ ሕዝብ ኢሕአዴግን የሚያመሰግንበት በጐ ተግባሮችና አገራዊ መሻሻሎች የመኖራቸውን ያህል የሚያማርርበትና የሚወቅስበት በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ለአብነት ብናነሳ አንዱ የ‹‹ኢትዮጵያዊነት ስሜት መድከም›› ነው፡፡ ስለአገር ክብር፣ ሉዓላዊነት፣ የነፃነት አኩሪ ታሪክ፣ የሦስት ሺሕ ዘመን ቅርስ፣ የማይናወጥ አንድነት፣ ወዘተ ከሚያነሱ ሰዎች ይልቅ የብሔርና የመንደር ባንዲራን የሚያውለበልቡ ይደመጣሉ፡፡ ሁሉም ነገሮች ካለፉት 20 ዓመታት ወዲህ የተፈጸሙና የሆኑ መስለው መቅረባቸው ታዛቢ የሌለበት ምድር እያስመሰለው መጥቷል፡፡
ሕዝቡ የኢኮኖሚ ዕድገትን የመፈለጉና የመሳተፉን ያህል ሙስና፣ መድልኦና ኢፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እየተንሰራፋ መምጣቱን ማንሳት ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ እርግጥ ሙስና የብዙ አገሮች ዋነኛ ፈተና የመሆኑ ጉዳይ የሚስተባበል ባይሆም፣ በአገራችን ከሥርዓቱ ባህሪ አኳያ እየጐላ መምጣቱ ሲታይ ብዙዎችን እያሳዘነ ነው፡፡
መገለጫው ምንም ይሁን ምን በአንድ ጀንበር ቱጃር የሚሆኑ ዜጎች ባልታየ ሥራ ውስጥ እየበዙ መምጣታቸው ከሕዝብ ሀብት ጋር እንዳይገናኝ የሚሰጉ አሉ፡፡ በየመሥሪያ ቤቱ ያለው ‹‹እንካ በእንካ›› ተገልጋይን የማማረር ድርጊትና ካለእጅ መንሻ የማይፈጸም ጉዳይ መብዛትም የምሬት ምንጭ መሆኑን ለአፍታ መዘንጋት አይገባም፡፡ በአንዳንድ መሥሪያ ቤቶች በብሔርና በዘመድ በተፈጠረ ትስስር አንዱ ሌላውን ‹‹ተው!›› የማይልበት የከፋ አድርባይነት እየታየ ነው፡፡ 
ኢሕአዴግ ከኤርትራ ጋር በተያያዘ በእንጥልጥል ያቆየው አጀንዳም ለብዙዎቹ መልስ ያላገኘ ጥያቄ ነው፡፡ ገና ከመነሻው ‹‹ኢሕአዴግ ኤርትራ እንድትገነጠል ብቻ ሳይሆን የወደብ ጥያቄ እንዳይነሳ ጉዳዩን አዳፍኖታል፤›› ከሚሉት ወገኖች አንስቶ፣ ዛሬም ድረስ ጦርነት የለም ሰላም የለም መሆኑ ‹‹ለምን?›› ያስብላል፡፡ ከዚያም ብሶ ሻዕቢያ ሲያመቸው አገራችንን ለማሸበርና ለማተራመስ እንደማይተኛ በተለያየ መንገድ እያረጋገጠ መጥቷል፡፡
የጽሑፌ መነሻም ሆነ መድረሻ ምርጫና የምርጫ ሥነ ምግባር ሆኖ ሳለ ወደ ሌላ ጉዳይ ገባሁ መሰለኝ፡፡ ገዥው ፓርቲ በአገሪቱ ታሪክ ውስጥ ስለከፈታቸው በጎ ታሪኮችም ሆነ ስለሚቀሩት ጉድለቶች ሕዝብ የሚለውን ማዳመጥ አለበት፡፡ በምንም መንገድ ቢሆን በሥልጣን ላይ የምቆየው በምርጫና በሕዝብ ይሁንታ ነው ብሎ ሳያወላውል መፅናትም ይኖርበታል፡፡ ሕዝብን ሳያረኩ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ደካማ ስለሆነ እመረጣለሁ ብሎ መደምደም ያስቸግራል፡፡ ሕዝብ ካልረካ ተወዳዳሪ ባይኖርም ላይመርጥ ይችላል፡፡ ‹‹መርጫለሁ›› ብሎም አለመርካቱንና መቃወሙን ከመግለጽ አይቆጠብም፡፡ 
በዚህ መነሻ ለዴሞክራሲያዊ ምርጫና ለፓርቲ ሥነ ምግባር የተገዛ ገዥ ፓርቲና የድርጅት አባላት መኖር ወሳኝ ነው፡፡ እርግጥ በዚህ ጽሑፍ ስለተቃዋሚዎች የምርጫ ሥነ ምግባርም ሆነ ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ ማለት ስላልተፈለገ እንጂ ጉዳዩ እነሱንም ይመለከታል፡፡ ከዚህ አንፃር በራሱ በኢሕአዴግ የምርጫ ሥነ ምግባር ላይ በግልጽ ከተቀመጠው በአፈጻጸም የሚያደነቃቅፍና ራሱ የፓርቲው አባላትና አመራሮች በተለይ በታችኛው እርከን የሚጥሏቸውን ነጥቦች ልጠቃቅስ፡፡ ዘንድሮ ከችግሩ በመማር ሕዝብና አገርን ያከበረ ተግባር እንዲፈጸም ያነቃ ይመስለኛልና ልቀጥል፡፡
ሁሉም ፓርቲዎች ሕዝቡን በነፃነት የማግኘት መብት አላቸው
በ2002 ዓ.ም. በአዲስ መልክ ተነድፎ እስካሁን እየተመራበት ያለው የኢሕአዴግ የምርጫ ሥነ ምግባር መመርያ የፓርቲዎችና ሕዝብን የማግኘት መብትን በአንቀጽ 3 ገልጾታል፡፡ እንዲህም ይላል፡፡
‹‹አገራችን ዴሞክራሲን በመገንባት ላይ የምትገኝ፣ በሕገ መንግሥት የምትመራ አገር ነች፡፡ የአገራችን ሕዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተከብረዋል፡፡ ከአገራችን ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ መብቶች ውስጥ አንዱ ደግሞ በተለያየ አግባብ ተደራጅቶ መንቀሳቀስ፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባል የመሆን (የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 31 እና 38/2 ይመልከቱ) መብት የተከበረ መሆኑ ነው፡፡ በነፃ ተንቀሳቅሰው ሕዝቡን ማግኘት፣ ጽሕፈት ቤት መክፈት፣ የሕዝብ ስብሰባዎችን መጥራት ስለዓላማቸው ማስተማርና ድጋፍ የመሰብሰብ እንቅስቃሴ ላይ አንዳችም ገደብ አይጣልባቸውም፣ ሊጣልባቸው አይገባም፤›› ይላል፡፡
ይህን ግልጽና ዴሞክራሲያዊ ድንጋጌ ካስቀመጠ በኋላ ወደ ተግባር ሲገባ የሚስተዋሉ ችግሮች አሉ፡፡ በተለይ ባለፉት ምርጫዎች በታችኛው የመንግሥትና የፓርቲው እርከን የተቃዋሚ ፓርቲ አባልና መሪ መሆን ‹‹ጠላት›› ተደርጐ ነው ሲታይ የነበረው፡፡ እውነት ለመናገር የትኛው ሰው የስብሰባ አዳራሽ በድፍረት ያከራያል (በአዲስ አበባ እንኳን)? ለቅስቀሳ መኪና ማዋስና ቤት ለቤት እየዞሩ ለመቀስቀስ ያለው ፈተና ከባድ ነው፡፡ ሠልፍ መከልከል፣ በሰበብ አስባብ ማደናቀፍ፣ ማስፈራራትና ማሰር ‹‹ሕጋዊ›› መደበኛ ሥራቸው የሚመስላቸው የኢሕአዴግ ሰዎችስ ጥቂት ይሆኑ?
የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገራቸው ጉዳይ በዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ አግባብ የመሳተፍ መብት እያላቸው ‹‹ሕግ ጥሰዋል›› በሚል ሰበብ መብታቸው አይገፈፍምን? በተለይ በትግራይ፣ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች እስከ አርሶ አደሩ ወርዶ የምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ መሞከር ‹‹የትጥቅ ትግል የመጀመር ያህል ከባድ ነበር›› የሚሉ የተቃዋሚ መሪዎች አጋጥመውኛል፡፡ ይህ ደግሞ ከተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎቹ በኩል ከሚነሳው ክፍተት ባሻገር፣ የመንግሥትና የገዥው ፓርቲ ሥልጣንና ዕርምጃ መደበላለቅና በምርጫ ሥነ ምግባር ያለመመራት ውጤት ነው፡፡ አለፍ ሲልም ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ አለመገዛት ማሳያ ተደርጐ ይወሰዳል፡፡
ስለሆነም ኢሕአዴግ ከአጉል ሥጋትና ‹‹ምኅዳሩን አጠበበ›› ሐሜት ወጥቶ ነፃውን ዳኝነት ለሕዝቡ ሊያጐናጽፍ ይገባል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በራሳቸው ያለባቸው ድክመትና ጥንካሬ አለመኖር አንሶ፣ ሌላ ጫና የሚፈጥሩ ከሕግና ከሥነ ምግባር ውጪ የሚሠሩ ፀረ ዲሞክራቶችን ከማሰማራት መቆጠብ አለበት፡፡ ለማረምና ለማስተካከልም ሊተጋ ግድ ነው፡፡ ከዚያም አልፎ ፓርቲዎች በሰላማዊ፣ በሕጋዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፣ አንድ ዕርምጃ ሄዶ ሕዝቡ ‹‹አበጀህ›› እስኪለው ድረስ መሥራት አለበት፡፡ ‹‹ሕዝቡ ተቃዋሚዎችን አይፈልግም›› በሚል ጫፍ የነካ ድምዳሜ በማናለብኝነት መሥራት ግን የትም አያደርስም፡፡
ሕግን አክብሮ መንቀሳቀስ
የድርጅቱ የምርጫ ሥነ ምግባር መመርያ አንቀጽ 4 ሕግን አክብሮ ስለመንቀሳቀስ ሲያስረዳ እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አንዱ መሠረታዊ ጉዳይ የሕግ የበላይነትን ማክበር እንደሆነ ያምናል፡፡ በአገራችን የሕግ የበላይነት እንዲከበርም በጽናት ይታገላል፡፡ የኢሕአዴግ አባላት ሕገ መንግሥቱንና ሌሎች የአገሪቱን ሕጐች በሙሉ የማክበርና የማስከበር የዜግነት ብቻ ሳይሆን የኢሕአዴግ አባልነት ግዴታም አለባቸው፡፡››
የሥነ ምግባር መመርያው ላይ የሕግ የበላይነት ቁልፍ ጉዳይ ሆኖ የመቀመጡን ያህል አፈጻጸማችን ምን ደረጃ ላይ ይገኛል ብሎ መፈተሽ አለበት፡፡ በእስር ላይ ባሉ ዜጐች አያያዝ፣ ቶርችን የመሳሰሉ ድርጊቶችን በማስቀረት፣ በየደረጃው ነፃና ግልጽ ዳኝነትን በመዘርጋት ዓመኔታን የሚያተርፍ ተግባር ያስፈልጋል፡፡ ተቃዋሚዎች ሲሳሳቱ ወህኒ የሚያወርድ፣ የኢሕአዴግ ሰዎች ሲያጠፉ በተግሳጽ የሚያልፍ የምርጫም ሆነ የሌላ ጊዜ አሠራር ሕዝብ እንዲጠራጠርና እምነት እንዲያጣ ያደርጋል፡፡ 
ባለፉት የምርጫ ጊዜያት እንደታየው ከዴሞክራሲው ለጋነት አኳያ በገዢው ፓርቲ፣ በተቃዋሚዎችና በፍትሕ አካላት ላይ ቀላል የማይባል ጉድለት ታይቷል፡፡ ተደጋግሞ እንደተስተዋለው ኢሕአዴግ ከሳሽ ሲሆን፣ የፍትሕ አካሉ የሚፈርደው በተቃዋሚዎች ላይ ነው፡፡ የተቃዋሚዎች ክስ ግን ኢሕአዴግንና የኢሕአዴግ ካድሬዎችን ሲያስቀጣ አለመታየቱ ግን ኢሕአዴግ ‹‹የመላዕክት ስብስብ አይደለንም›› ከሚለው ሐሳብ ጋር ይጋጫል፡፡
ተደጋግሞ እንደታየው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ ፍርድ ቤቶችና ምርጫ ቦርድን የመሳሰሉ ተቋማት ከአስፈጻሚው በተነጠለ አኳኋን ሌላ የመንግሥት ክንፍ ሆነው መውጣት ላይ ጉድለቶች አሉ፡፡ አንዳንዴ በገዥው ፓርቲ ከፍተኛ ሥራ አስፈጻሚዎችና የፖሊት ቢሮ አባላት የሚመሩ የዴሞክራሲ ተቋማት ለሕግ የበላይነትና ገለልተኛ ሚና ቅድሚያ ለመስጠት መቸገራቸው አይቀርም፡፡ ቅድሚያ ‹‹ለፓርቲ!›› የሚለውን የህልውና መርህ ሊዘነጉትም አይችሉም፡፡ ስለዚህ በቁርጠኝነት የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለመገንባት መንቀሳቀስ ይበልጣል፡፡ አገር ለሚመራ መንግሥት ‹‹የሕግ የበላይነተ ተረጋግጧል›› ብሎ ብቻ ከመቀመጥ ውስጥን ማየት ይሻላል፡፡ 
ለሁሉም እኩል የሚያገለግል አመቺ የውድድር ሜዳ መፍጠር
‹‹ምርጫው ነፃና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መከናወኑ የሚረጋገጠው ሁሉም ተወዳዳሪዎች እኩል የሚስተናገዱበትና የሚገለገሉበት አመቺ የውድድር ሜዳ ሲፈጠር ነው፡፡ በዚህ ረገድ በተለይ በመንግሥት በጀት የሚተዳደሩ ተቋማት በሙሉ ለሁሉም ፓርቲዎች እኩል የሚያገለግሉበት አሠራር ሊኖር ይገባል፡፡ ገዥው ፓርቲም ሆነ የአገሪቱን ሕጐች አክብረው በምርጫው የሚወዳደሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳቸውን ሲያካሂዱ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን፣ የመንግሥት አዳራሾች፣ ወዘተ እኩል የመጠቀም መብት መከበር አለበት፤›› ይላል የሥነ ምግባር መመርያው፡፡
በዴሞክራሲያዊ ምርጫ መሥፈርት ሲመዘንና በእንዲህ ያለው ገዥ ፓርቲ የምርጫ ሥነ ምግባር ሲፈተሽ፣ ያሳለፍናቸው የምርጫ ወቅቶች ችግር የነበረባቸው አንዱ ጉዳይ ይህ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ በምርጫ ወቅት በመንግሥት ተሽከርካሪዎች (በተለይ በወረዳና በቀበሌ ደረጃ) በስፋት ይጠቀማል፡፡ የመንግሥት አዳራሽ፣ የጽሑፍ መሣሪያና መሥሪያ ቤት ብቻ ሳይሆን በመንግሥት መሥሪያ ቤት ያለውን የሰው ኃይል ቢጠቀምበትም ‹‹ሕጋዊ›› ተደርጐ በቅቡልነት የቆየ ጉዳይ ነው፡፡
በተቃራኒው የተቃዋሚ ፓርቲዎች በአንዳንድ አካባቢዎች እንኳን በመንግሥት አዳራሽ ሊጠቀሙ፣ ተከራይተው ሕዝብ ለመሰብሰብ እንደሚቸገሩም አይተናል፡፡ ተሽከርካሪና የጽሕፈት መሣሪያ ይቅርና የድርጅታቸው አባል የሆነ የመንግሥት ሠራተኛ በህቡዕ ካልደገፋቸው ሊታይ የማይችልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ ቢያንስ ዘንድሮ እንዲህ ያሉ ሕገወጥ ድርጊቶች እንዲቀንሱ ካልተደረገ ዴሞክራሲው እያደገ ነው ማለት አይቻልም፡፡ በአንዳንድ የወረዳና የዞን ከተሞች የብአዴን፣ የሕወሓት፣ የኦሕዴድና የደኢሕዴን አዳራሾች ተብለው የተገነቡ የሕዝብ መሰብሰቢያዎች ሳይቀሩ በሕጋዊ መንገድ የሚቀሳቀሱ ፓርቲዎችን ሊያስተናግዱ ይገባል፡፡ በኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና መጥፋት (አንዳንዴ ሆን ብሎ እስኪመስል ድረስ) የፓርቲዎች እንቅስቃሴ አለመደናቀፉን ማረጋገጥም ግድ ነው፡፡
የአገሪቱ የፖሊስ፣ የመከላከያና ሌሎች የደኅንነት አካላትም በገለልተኝነትና በሰላማዊ መርህ ምርጫውን መደገፍና ማስተባበር ግድ ይላቸዋል፡፡ በተቃዋሚ አባልነት፣ ተሰብሳቢነትም ሆነ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሐሳብ መስጠት ዜጐችን ሊያሸማቅቅ አይገባም፡፡ እንዲያውም ሊያበረታታና ሊያስጠብቃቸው ግድ ነው፡፡ ባለፉት አንዳንድ ምርጫዎች እንደታየው ሙሉ ትጥቅ አድርጐም ሆነ ወገብ ሰባሪ ቆመጥ ይዞ በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ውስጥ ማንዣበብ የሚፈጥረው ጭንቀት አለ፡፡ ምንም የከፋ ነገር በሌለበት ሁኔታም ነፃነትን ገፎ ፍርኃትን ያረብባል፡፡
በድምሩ መንግሥትና ኢሕአዴግ ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እኩል የሚያገለግል ፍትሐዊ የውድድር ሜዳ መኖሩን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ ይህ ሆኖ ሲያበቃ በባዶ የሚያማርርና ‹‹የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ›› የሚል የፖለቲካ ኃይል ቢኖር ሕዝቡ ራሱ አጋልጦ የሚተፋው ይሆናል፡፡ በየትኛውም የዴሞክራሲያዊ ምርጫ መለኪያም ተቀባይነትን ሊያገኝ አይችልም፡፡
የተቋማትን ነፃነት ማክበር
የኢሕአዴግ የምርጫ ሥነ ምግባር መመርያ የፓርቲው መሪዎችና አባላት ለዴሞክራሲያዊ ተቋማት ነፃነት መሥራት እንዳለባቸው ያሳስባል፡፡ ‹‹ምርጫ በሚካሄድበት ወቅት በርካታ ነፃና ገለልተኛ ተቋማት የሚሳተፉበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ የምርጫ ቦርድ፣ የምርጫ ታዛቢዎች፣  ምርጫን በሚመለከት መራጩን ሕዝብ እናስተምራለን ብለው የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ ፍርድ ቤቶችና ሌሎችም ተቋማት ሁሉ ከምርጫው ጋር የተያያዘ ሥራ ይሠራሉ፡፡ እነዚህ ተቋማት ሥራቸውን በገለልተኝነትና በነፃነት የሚሠሩበትን አመቺ ሁኔታ ማረጋገጥ ለምርጫው ነፃና ፍትሐዊ መሆን አንዱ ዋስትና ነው፤›› ይላል፡፡
ይህ ጽንሰ ሐሳብ በተደጋጋሚ የሚነገር ቢሆንም ባለፉት ምርጫዎች እንደ ችግር ጐልቶ ሲታይ የነበረው በታችኛው የመንግሥት መዋቅር ነው፡፡ በተለይ በገዥው ፓርቲ ‹‹ባርኔጣ›› ቤት ለቤት የሚቀሰቅሱ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የአካባቢ አስተዳዳሪዎች በብዛት አሉ፡፡ እነዚህ አካላት ፍርድ ቤትን፣ ፖሊስንም ሆነ ምርጫ ቦርድን የሚመሩበት የመንግሥት ሥልጣን አላቸው፡፡ የሕዝብና የፓርቲ ታዛቢዎችንም ሲያስተዳድሩ የኖሩ ናቸው፡፡ ስለዚህ በታችኛው መዋቅር የምርጫውን መንፈስ ከማደፍረስ ራሳቸውን አቅበው ካልታዩ የነፃ ተቋማትን መብት መግፈፋቸው አይቀሬ ነው፡፡
የተቋማት ነፃነት ይከበር ሲባል ሁሉንም በምርጫ የሚወዳደሩ አካላትን የሚመለከት እንደሆነ ይገባኛል፡፡ ነገር ግን የመንግሥትና የገዥው ፓርቲ አካላት ኢሕአዴግ ራሱ ያወጣውን የምርጫ ሥነ ምግባር በማክበር፣ ለዴሞክራሲ ማበብና ለሕዝብ የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤትነት ሊተጉ ይገባል፡፡
በአጠቃላይ የፓርቲዎች የምርጫ ሥነ ምግባር መመርያ መዘጋጀቱ ብቻ ሳይሆን፣ መርሆዎችን ለመተግበር ጥረት ማድረጉ በጐ ጅምር ነው፡፡ በተለይ ኢሕአዴግ እንደ ገዥ ፓርቲ ካለፉት ሁለት ምርጫዎች ወዲህ የፓርቲ የሥነ ምግባር ደንብ ቀርጾ እየሠራ መሆኑም ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ይሁንና የሥነ ምግባር ሕጉ መውጣቱ ከመውጣቱ በፊት ከነበረው የተደበላለቀ አሠራርና ፀረ ዴሞክራሲያዊ አካሄድ ሊያላቅቅ ይገባል፡፡ በሒደቱ የሚበረታቱ ለውጦችና እመርታዎች ሊመዘገቡም ያስፈልጋል፡፡
በዛሬው ዳሰሳዬ የኢሕአዴግን የምርጫ ሥነ ምግባር መመርያና በፓርቲው አተገባበር ውስጥ የሚታዩ ክፍተቶችን እንደጠቃቀስኩ ሁሉ፣ በቀጣዩ ጊዜ በተቃዋሚዎች የምርጫ ሥነ ምግባር መመርያ አተገባበር ችግር ላይ ሐሳቤን እንደማካፍል ቃል በመግባት ልሰናበት፡፡ 
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡  

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር