POWr Social Media Icons

Sunday, February 15, 2015

በዓለም ላይ ፈጣን ከሚባሉት አንዱ የሆነው ‹‹ቡሌት ትሬን››ከይርጋጨፌ፣ ከሐረርና ከሲዳማ ቡናዎች በመቀጠል በዓለም የተመዘገ የኢትዮጵያ የጫካ ቡና የመሆን ዕድል እንዳለው ይነገርለታል፡፡
ይህ የተፈጥሮ የጫካ ቡና በአሁኑ ወቅት ተፈጊነቱ እየጨመረ ሲሆን በተለይ በጃፓን ቡና ጠጭዎች ዘንድ ከምንጊዜው በላይ እየተወደደ መምጣቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በጅማ ዞን አስተዳደር ውስጥ ከሚገኙ አካባቢዎች ውስጥ በተለይ በለጠና ጌራ የተባሉት በቻካ ቡና ሀብታቸው ይታወቃሉ፡፡ የሰው ንክኪ የሌለው የጫካ ቡና እየለቀሙ የሚተዳደሩ በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ቡናቸው በጃፓን ገበያ ተፈላጊነቱ እንዲጨምር ካቻሉት መካከል ሬንፎረስት አሊያንስ የተባለው አሜሪካ ኩባንያ የጫካውን ቡና ተፈጥሯዊ ይዞታ እያረጋገጠ የምሥክር ወረቀት መስጠት መጀመሩን ተከትሎ ነበር፡፡
ከሰባት ዓመታት በፊት የተጀመረው ማረጋገጫ የመስጠት ተግባር ከወደጃፓን ስመ ወፍራም የሆኑ ኩባንያዎችን ለመሳብ አብቅቷል፡፡ የበለጠ-ጌራ የጫካ ቡናን በመግዛት ላይ የሚገኘው ዩሺማ ኮፊ ኮርፖሬሽን (ዩሲሲ) ሲሆን፣ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ቡናውን እንዲገዛ መንገዱን ያመቻቸው፣ የጃፓን ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) ነው፡፡ በጃይካ በኩል የተመሠረተው የዩሲሲና የበለጠ-ጌራ ቡና አምራቾች ግንኙነት እየዳበረ መጥቶ በአሁኑ ወቅት ቡናቸው የልዩ ጣዕም ቡናነቱ ተመስክሮለት፣ በጃፓኑ ፈጣን ባቡር ለሚሳፈሩ ተጓዦች እየተሸጠ ይገኛል፡፡
በዓለም ላይ ፈጣን ከሚባሉት አንዱ የሆነውና ‹‹ቡሌት ትሬን›› የሚባል መጠሪያን ያተረፈው የባቡር ትራንስፖርት ላይ በየቀኑ ከአሥር ሺሕ በላይ የቡና ስኒዎች እየተሸጡ ሲሆን፣ ዩሲሲ ከዚህ በፊት በዚህ መጠን ለተሳፋሪዎች ቡና  ሸጦ እንደማያውቅ፣ የኩባንያው አማካሪ የሆኑትና በቅርቡ ጅማን ጎብኝተው የተመለሱት ናዖሚ ናካሒራም ሆኑ በጃይካ የግብርና ሥራዎች ኃላፊ ፉሚያኪ ሳሶ ገልጸዋል፡፡
በአብዛኛው የልዩ ጣዕም ባለቤት የሆኑት የበለጠ-ጌራ ቡናዎች፣ በቅርቡ በተደረገ የመቅመስ ሥነ ሥርዓት በአብዛኛው ከመቶ መለኪያ ነጥብ ከ80 በላይ በማምጣት ውጤታማ መሆናቸው ታይቷል፡፡ ናሂካራ እንደሚያምኑት የበለጠ-ጌራ ጫካ ቡናዎች ኢትዮጵያ በባለቤትነት ካስመዘገበቻቸው የይርጋጨፌ፣ የሐረርና የሲዳማ ቡናዎች በመቀጠል በዓለም ሊታወቁ የሚችሉበት አቅም እንዳላቸው፣ ሆኖም ይህንን ከግብ ማድረስ የመንግሥት ሚና መሆኑን ሳሶ ተናግረዋል፡፡
የበለጠ-ጌራ ቡናን የሚጠጡት ጃፓናውያን ቶኪያ እስከ ኦሳካ ከተማ በሚምዘገዘገው ባቡር ውስጥ በሚሳፈሩበት ወቅት ሲሆን፣ በሚጠጡበት የቡና ስኒ ወይም ኩባያ ላይ የበለጠ-ጌራ ቡና ታሪክና የአምራቾቹ ማንነት በመጠኑ የሚጠቅስ በመሆኑ ደኑን ለመጠበቅ የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ የሚያስረዳ በመሆኑም ጭምር በዚህ ወር የሚደረገው የሽያጭ መጠን ሳይታሰብ ከፍ እንዲል አስችሎታል፡፡ ጃፓናውያን ለሚገዙት ምርት ከጥራትና ከዋጋ ቀጥሎ ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት የሚሰጡ መሆናቸውን ተከትሎ የበለጠ-ጌራ ቡና ተፈላጊነት መጨመሩም ይነገራል፡፡
የሲሲ ኩባንያና የጃፓን ባቡር ኩባንያ በዚህ ወር የኢትዮጵያን የጫካ ቡና ለመንገደኞች ያቀረቡበትን ምክንያት ከሃምሳ ዓመት በፊት ከተከናወነ ታሪካዊ ክስተት ጋርም ያያይዙታል፡፡ ይኸውም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከጀርመንና ከጣልያን ጋር በመሰለፍ የፍልሚያው አቀንቃኝ ሆና በስተመጨረሻ፣ የአሜሪካ ኒውክሌር አረሮች የጠበሷት ጃፓን፣ ከጦርነቱ ማክተም በኋላ ያንሰራራችበትን አጋጣሚ ከኢትዮጵያ ጋር ታያይዘዋለች፡፡ ይኸውም እ.ኤ.አ. በ1964 ያስተናገደችው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ለጃፓን ማንሰራራት ትልቅ ቦታ ሲሰጠው፣ በኦሊምፒኩ ባለድል የነበረው ኢትዮጵያ ኩራት አበበ ቢቂላን ምንጊዜም ትዘክራለች፡፡ ከአምሳ ዓመት በኋላም በኦሊምፒኩ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያያዝ ታሪክ ለመፍጠር በማሰብ፣ የበለጠ-ጌራ ቡናን በማስተዋወቅ፣ እግረ መንገዳቸውንም ለመጪው 2024 ኦሊምፒክ ጨዋታዎች አዘጋጅ ለመሆን ያላቸውን ፍላጎት ማሳያነት ተጠቅመውበታል፡፡
Source: www.ethiopianreporter.com

0 comments :