የደቡብ ክልል የፓርቲዎች የጋራ መድረክ ኢራፓን በአባልነት ሲቀበል፤ ሲአን/መድረክ በሲዳማ ዞን በቡርሳና በቦርቻ ምርጫ ክልል በአባላትና ደጋፊዎቼ ላይ ደረሰ ያለውን ድብደባና ወከባ የዞኑ የጋራ ምክር ቤት እንድያጣራ ወሰነ

የደቡብ ክልል የፓርቲዎች የጋራ መድረክ ኢራፓን በአባልነት ተቀበለ
በመጪው ምርጫ በደቡብ ክልል የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መድረክ የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ /ኢራፓ/ን የጋራ ምክር ቤቱ ስድስተኛ አባል አድርጎ ተቀበለ፡፡
የጋራ መድረኩ ዛሬ ባካሄደው አምስተኛ መደበኛ ጉባኤ በክልሉ የሚወዳደሩ ክልላዊ ፓርቲዎች በመሰረቱት የጋራ መድረክ ላይ እንዲሳተፍ በክልሉ ምርጫ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት በኩል ቀደም ሲል ጥሪ ተደርጎለት ያልተገኘውንና ዛሬ የአባልነት ጥያቄ ያቀረበውን የኢራፓ ጉዳይና ሌሎች ሶስት አጀንዳዎች ላይ ተወያይቷል፡፡
የኢትዮጵያውያን ራዕይ ፓርቲ /ኢራፓ/ ተወካይ አቶ ሺበሺ መኮንን በግል ጉዳይ ምክንያት እስካሁን በመድረኩ ምስረታና ስብሰባ ላይ ሳይገኙ በመቆየታቸው ይቅርታ ጠይቀው የጋራ መድረኩ አባል ለመሆን ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
የጋራ መድረኩ በቀረበው ጥያቄ ላይ በመወያየት ኢራፓ አመራሮች በማይኖሩበት ወቅት ተወካይ በመላክ በመድረኩ ምስረታና ስብሰባ ላይ መካፈል ሲችል ይህን አለማድረጉ ተገቢ አለመሆኑ ተገልጾለት ለወደፊቱ አመራሩ በማይገኝበት ወቅት በውክልና ሌላ ሰው ተካፋይ እንዲሆን ማድረግ አንዳለበት ተገልጾለት የጋራ መድረኩ አባል እንዲሆን ያቀረበው ጥያቄ በሙሉ ድምጽ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡
ሲአን/መድረክ በሲዳማ ዞን በቡርሳና በቦርቻ ምርጫ ክልል በአባላትና ደጋፊዎቼ ላይ ጥር 22 ቀን 2007 ስብሰባ ላይ በፖሊስ ድብደባና ወከባ ደርሶባቸዋል በማለት ጉዳዩን የጋራ መድረኩ አጣርቶ የእርምት አርምጃ አንዲወስድ ባቀረበው አቤቱታ ላይም መድረኩ ውይይት አድርጓል፡፡
የሲአን/መድረክ ተወካይ በቡርሳና ቦርቻ በድርጅቱ አባላትና በደጋፊዎች ላይ ደረሰ ያለውን ድብደባና ወከባ ለጋራ መድረኩ ከማቅረቡ በፊት ችግሩ የተፈጸመው በዞን ስለሆነ በመጀመሪያ ደረጃ ባለው የጋራ ምክር ቤት በማቅረብ ጉዳዩ እንዲታይ ማድረግ እንዳለበትና በዛ በኩል ችግሩ ካልተፈታ በጽሁፍ ማመልከቻ ማቅረብ እንዳለበት ተገልጾለታል፡፡
ሲአን/መድረክ በአባላትና ደጋፊዎቼ ደረሰብኝ ያለውን አቤቱታ ሲያቀርብ ገዥው ፓርቲ ታንክና ባንክ በእጁ ስላለ ያስፈራራል በማለት የተናገረው ከጋራ ምክር ቤቱ ስነስርዓትና ደንብ ውጪ በመሆኑ ሊታረም እንደሚገባ ከደኢህዴን ፣ከኢዴፓና አትፓ ፓርቲ የቀረበውን ሀሳብ ጉባኤው ተቀበሎ ሲአን/መድረክ ለወደፊቱ ከመሰል ስህተት እንዲታረም ማሳሰቢያ ተሰጥቶታል፡፡
ፓርቲዎቹ በበጀት አጥረት ተንቀሳቅሰው ዕጩዎቻቸውን ለማስመዝገብ እንደተቸገሩ ጠቁመው ምርጫ ቦርድ የዕጩዎች ምዝገባ ጊዜውን እንዲያራዝምና ለፖለቲካ ፓርቲዎች የተመደበውን በጀት በፍጥነት እንዲለቅ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የክልሉ ምርጫ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብርሀም ጌዴቦ ምርጫ ቦርድ በሀገር አቀፍ ደረጃ ካሉ ፓርቲዎች ጋር በመወያየት በዕጩዎች የምዝገባ ቀን ማራዘምና በበጀቱ መለቀቅ ላይ በሁለት ቀናት ውስጥ ውሳኔ እንደሚሰጥ መግለጹን ተናግረዋል፡፡
የጋራ ምክር ቤቱ አባል ፓርቲዎች ደጋፊዎቻቸውና አባሎቻቸው በመራጭነት እንዲመዘገቡ ከማድረግ አንጻር ትኩረት ሰጥተው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው የጋራ ምክር ቤቱ አሳስቧል፡፡
የጋራ ምክር ቤቱ ከአስራ አምስት ቀናት በኋላ ለሚያደርገው መደበኛ ስብሰባ ኢዴፓን በሰብሳቢነት በመምረጥ ስብሰባውን አጠናቋል፡፡
- See more at: http://www.ena.gov.et/index.php/politics/item/1633-2015-02-04-01-23-56#sthash.lGzPp07N.dpuf

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር