ብሔራዊ ባንክ ለፋይናንስ ተቋማት አዲስ መመርያ አዘጋጀ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በአገሪቱ የሚገኙ የፋይናንስ ተቋማት የሚመሩበት አዲስ መመርያ ለማውጣት ከባለድርሻ አካላት ጋር መወያየቱን፣ የተዘጋጀውንም ረቂቅ መመርያ ተግባራዊ ለማድረግ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡
የአገሪቱን የፋይናንስ ተቋማት በበላይነት የሚቆጣጠረው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጀው አዲሱ መመርያ ባንኮች፣ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችና የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የሚገዙበት ይሆናል ተብሏል፡፡ 
የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ ብሔራዊ ባንክ ይህንን ረቂቅ ሕግ ካዘጋጀና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፋይናንስ ተቋማት አስተያየት እንዲሰጡበት ካደረገ በኋላ ባለፈው ሳምንት ከባንኩ ቦርድ አባላት ጋር መክሮበታል፡፡ 
በ15 ገጾች የተዘጋጀው አዲሱ መመርያ አሥር ዋና ዋና አንቀጾች ሲኖሩት፣  አራት ዝርዝር ማብራሪያዎችን በማካተት ተቋማቱ ተፈጻሚ ማድረግ ያለባቸውን የአሠራር ደንቦችንና የብቃት መለኪያ መሥፈርቶችን ይዟል፡፡ 
አዲሱ የኮርፖሬት ገቨርናንስ መመርያ በዋነኝነት ትኩረት ያደረገው፣ በፋይናንስ ተቋማቱ ባለአክሲዮኖች፣ በቦርድ ዳይሬክተሮችና በተቋማቱ ከፍተኛ የአመራር አባላት ላይ ሲሆን የሁሉንም የኃላፊነት ድርሻና የተጠያቂነት አሠራር ያጠቃለለ ነው፡፡ 
በተለይ በፋይናንስ ተቋማት የሚፈቀዱ የገንዘብ ዝውውሮች፣ የተቋማቱን ፖሊሲና የብሔራዊ ባንክ መመርያ የጣሰ መሆን እንደሌለባቸው አዲሱ መመርያ ይደነግጋል፡፡ 
በሌላ በኩል ከብሔራዊ ባንኩ መመርያ ውጪ ባለአክሲዮኖችም ሆኑ የቦርድ ዳይሬክተሮች ብድር መውሰድ እንዳይችሉ ይደነግጋል፡፡ ዳይሬክተሮችና ባለአክሲዮኖች በማንኛውም በሌላ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ኢንቨስት ማድረግ የማይችሉበት አንቀጽም በአዲሱ ረቂቅ መመርያ ላይ ተካትቷል፡፡ 
በዋና ሥራ አስፈጻሚውና በከፍተኛ የአመራር ኦፊሰሮች የተፈቀዱ የብድርና የውጭ ምንዛሪ ዝውውሮች በቦርዱ መፅደቅ የሚኖርባቸው ከመሆኑም በተጨማሪ፣ የብድር አፈቃቀድ ሒደቶችንም በዝርዝር የያዘ ነው፡፡ የተቋማቱ ጠቅላላ ጉባዔ የውጭ ኦዲተሮችን የመመደብ ኃላፊነቱ የተሰጠው ሲሆን፣ በዚህም ከኩባንያው ጠቅላላ አወቃቀር ጋር ግንኙነት ካለው አካል መካከል መመደብ የተከለከለ መሆኑን ያሳያል፡፡ 
መመርያው የፋይናንስ ተቋማቱ የማቋቋሚያ ሰነድ በዋነኛነት በቦርዱ ሊቀመንበርና በተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መካከል የሚኖረው ድንበር መታወቅ እንደሚኖርበት ያስቀመጠ ሲሆን የሁለቱን ከፍተኛ ኃላፊዎች ሚና፣ ተጠያቂነትና የሥልጣን ኃላፊነት በግልጽ ተለይቶ እንዲቀመጥ ያስገድዳል፡፡
 የተቋማቱ ጠቅላላ ጉባዔ፣ መደበኛና አስቸኳይ ጉባዔዎች በሙሉ ድምፅንና ምሥልን በሚያሳይ ፊልም ለብሔራዊ ባንክ መቅረብ አለበት የሚል አንቀጽ ሲካተትበት፣ በዕለቱ ከተጻፈው የአጀንዳ ዝርዝር ነጥቦች (Minutes) ጋር ተያይዞ መቅረብ የሚኖርበት መሆኑን ያመለክታል፡፡ 
በሥራ ላይ ይውላል  ተብሎ የሚጠበቀው አዲሱ መመርያ የተቋማቱን የቦርድ ዳይሬክተሮችን የአመራረጥ ሒደትን በተመለከተ አዳዲስ አሠራሮች እንዲካተቱበት የሚያደርግ ነው፡፡ መመርያው የተቋማቱ ጠቅላላ ጉባዔ ቋሚ የቦርድ አስመራጭ ኮሚቴን የመምረጥ መብት የሚሰጥ ነው፡፡ ይህ አሠራር ከዚህ ቀደም ሲካሄድ የነበረውን የምርጫ ሒደት የሚያስቀር ነው ተብሏል፡፡ የባንክ ዳይሬክተሮች ከብሔራዊ ባንክ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በተነጋገሩበት ወቅት፣ በመመርያው ላይ ተካትተው በምርጫ ሒደት ችግር ሊፈጥር ይችላሉ ያሉዋቸው ሥጋታቶች ሰንዝረዋል ተብሏል፡፡   
በመመርያው መሠረት የሚሰየመው የአስመራጭ ኮሚቴ ከቦርድ ዳይሬክተሮች ተፅዕኖ ነፃ የሆነና በቦርድ ውስጥ መቀመጫ የሌለው መሆን አለበት፡፡ በዓመታዊው ጠቅላላ ጉባዔ ለቦርድ ዳይሬክተርነት የተጠቆሙትን ዕጩዎች ብዛት  አስመራጭ ኮሚቴው የመወሰን ኃላፊነት ያለበት ቢሆንም፣ የዕጩዎቹ ብዛት ከነባሩ የቦርድ ዳይሬክተሮች በእጥፍ መብለጥ የማይኖርበት መሆኑንም ይጠቁማል፡፡ አስመራጭ ኮሚቴው ብቁ ዕጩዎችን መምረጥ የሚያስችል ግልጽነት የታከለበት ደንብና አካሄድን የሚያሳይ ሥርዓት መዘርጋት እንደሚኖርበት የሚያስገነዝበው ይህ መመርያ፣ በምርጫ ወቅት አስመራጭ ኮሚቴው ከሦስት ወራት በፊት ዕጩዎችን የመምረጥ ሒደት መጨረስ እንደሚኖርበት ይገልጻል፡፡ ከምርጫው አንድ ወር በፊትም በኩባንያው ድረ ገጽ ላይ ዕጩዎችን ማሳወቅ እንደሚጠበቅበት መመርያው ያዛል፡፡ 
የአስመራጭ ኮሚቴው የሥራ ዘመን ሦስት ዓመት ሲሆን፣ የኮሚቴው አባላት ብዛት ከአምስት ማነስ የለበትም፡፡ በትንሹ ዘጠኝ ዳይሬክተሮች የሚኖሩ ሲሆን፣ ለማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ሰባት መሆን ይኖርባቸዋል የሚል አንቀጽ አካትቷል፡፡
የቦርዱ ስብስብ በተለይ ከባንክ፣ ከፋይናንስ፣ ከኢንሹራንስ፣ ከአካውንቲንግ፣ ከሕግ፣ ከቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን፣ ከኦዲቲንግና ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና ከኢንቨስትመንት ማኔጅመንት የተውጣጣ መሆን እንዳለበትም በረቂቁ ላይ ተመልክቷል፡፡ 
በሌላ በኩልም ከሚመረጡት የቦርድ አባላት ውስጥ በትንሹ ሁለቱ ተመራጮች  የግድ ከፋይናንስ ጋር የተዛመደ የትምህርትና የልምድ ደረጃ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ እስካሁን ባለው አሠራር እንዲህ አልነበረም፡፡ በእነዚህ ተቋማት ባለው የቦርድ  አወቃቀር አነስተኛ ባለአክሲዮኖች እንዲገቡበት ይደነግጋል፡፡ የእነዚህ አነስተኛ መጠን ያላቸው ባለአክሲዮኖች በቦርዱ ውስጥ ያላቸው ውክልና ከአንድ ሦስተኛ መብለጥ የለበትም ይላል፡፡
አዲሱ መመርያ አዳዲስ አሠራሮችን የሚያስከትል ነው ተብሎ ይጠበቃል፡፡ መመርያው ጠቃሚ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ አንዳንድ ወገኖች ግን ብሔራዊ ባንክ በፋይናንስ ተቋማት የውስጥ ጉዳይ ሳይቀር ጣልቃ እየገባ ነው እያሉ ነው፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር