የግል የኅትመት ሚዲያዎች በወገንተኝነት ተወቀሱ

‹‹ምርጫና የሚዲያ ሚና›› በሚል ርዕስ በተዘጋጀው ውይይት ላይ የተሳተፉ አወያዮችየኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለሥልጣን የግል የኅትመት ሚዲያዎች ወገንተኞች ናቸው ሲል ወቀሰ፡፡
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንና ከብሮድካስቲንግ ባለሥልጣን ጋር በመተባበር ‹‹ምርጫና የሚዲያ ሚና›› በሚል ርዕስ የካቲት 6 ቀን 2007 ዓ.ም. ባዘጋጁት መድረክ ላይ ነው፣ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ልዑል ገብሩ ይህንን የተናገሩት፡፡
የግል የኅትመት ሚዲያዎች ዛሬም ቢሆን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን የማጥላላትና ጥላሽት የመቀባት አባዜ ያለባቸውና የብሔር ብሔረሰቦችን ማንነት የሚያንቋሽሹ ወገንተኛ ኅትመቶች ናቸው ብለዋል፡፡ ቢሆንም የተወሰኑት የግል ኅትመቶች ሥራቸውን በአግባቡ እንደሚሠሩ አለመጥቀስ ተገቢ አለመሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ይህም ሆኖ ግን የውይይቱ ዋና ዓላማ በምርጫው ወቅት የሚዲያው ሚና ምን መሆን እንደሚገባው ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመወያየት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ ከ1997 ምርጫ እስከ 2002 ምርጫ ድረስ የሚዲያ ተቋማት ምርጫን የዘገቡበት ሁኔታ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ፋኩልቲ መምህር በሆኑት ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ተዳሷል፡፡ ጋዜጠኞች በማንኛውም ፓርቲ ላይ አደጋ ሊያመጡ የሚችሉ ዘገባዎችን በማጣራትና ትክክለኛውን ማረጋገጥ እንደሚገባቸው አስረድተዋል፡፡
በእሳቸው ዳሰሳ መሠረት የ1997 ምርጫ በሚዲያዎች ሰፊ ሽፋን በማግኘት እስካሁን ወደር የሌለው ነው፡፡ ነገር ግን ጤናማ ያልሆኑ ፍረጃዎች የበዙበት፣ ከሙያው መርሆዎች ውጪ በርካቶች ዘገባ በመሥራታቸው ሕዝቡ የተጎዳበት እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ሌላው በኢትዮጵያ ምርጫ የሚዲያዎች ዘገባን በተመለከተ ንግግር ያደረጉት የዛሚ ፐብሊክ ኮኔክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘሪሁን ተሾመ፣ የ1997 ዓ.ም. ምርጫ የተዘገበው በብዕር ሳይሆን በደም መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች መገናኛ ብዙኃን ሰላምን ከሚያደፈርሱ ተግባራት በመታቀብ ዘገባዎችን ማቅረብ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡ ሥራቸውንም ሲያከናውኑ ነፃና ፍትሐዊ መሆን እንደሚገባቸውም አሳስበዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር