የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ድህነት ቢቀንስም ወደባሰ ድህነት የገቡ እንዳሉ ይፋ አደረገ

-መንግሥት የመረጃና የጥናት ሥልት ችግሮች አሉ ይላል
የዓለም ባንክ ይፋ ያደረገው የኢትዮጵያ የድህነት ጥናት ባለፉት አሥር ዓመታት ድህነት መቀነሱን ቢያሳይም፣ በአስከፊ ድህነት ውስጥ ይገኙ የነበሩ ሰዎች ወደ ተባባሰ የድህነት አረንቋ ማምራታቸውን አመለከተ፡፡
የዓለም ባንክ ጥር 12 ቀን 2007 ዓ.ም. ይፋ ያደረገው ጥናት እንዳሳየው፣ በዓለም አቀፍ የድህነት መስመር መለኪያ መሠረት (በቀን 1.25 ዶላር ገቢ ሥሌት) በአገሪቱ እ.ኤ.አ. ከ2000 እስከ 2011 ባሉት ዓመታት የድህነት መጠን ከነበረበት 55 በመቶ ወደ 30 በመቶ ቀንሷል፡፡ በዚህም በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በአስከፊ ድህነት ውስጥ የሚገኘው ሕዝብ ቁጥር 25 ሚሊዮን መሆኑን፣ በባንኩ የአፍሪካ ቀጣና የድህነት ቅነሳና የኢኮኖሚ ማኔጅመንት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ባለሙያዋ ሩት ቫርጋስ ሒል ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 
ሩት እንዳብራሩት ከሆነ እ.ኤ.አ. በ2005 ከነበሩት ድሆች ይልቅ እ.ኤ.አ. በ2011 የነበሩት ድሆች የበለጠ ደህይተዋል፡፡ ‹‹እጅግ ዝቅተኛ በሆነ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ደሃ ቤተሰቦች እ.ኤ.አ. ከ2005 ጀምሮ የኑሮ መሻሻል አላሳዩም፣ እንዲያውም አንዳንዶቹ በፊት ከነበሩበት በባሰ ድህነት ውስጥ ይገኛሉ፤›› በማለት የገለጹት ሩት፣ ከዓለም ድህነት መስመር ውጪ ያሉት 12 በመቶ ተጋላጮችም መልሰው ወደ ድህነት አዘቅት ውስጥ የመግባት ዕድላቸው ሰፊ መሆኑን አሳስበዋል፡፡ 
በጥናቱ መሠረት እ.ኤ.አ. በ2005 የነበሩት የአገሪቱ ድሆች መጠን እ.ኤ.አ. በ2011 ከነበሩት ድሆች ገቢ መጠን ጋር ሲነፃፀር፣ በ2011 የነበሩት ድሆች በ2005 ከነበሩት ያነሰ የገቢ መጠን እንደነበራቸው መታየቱን ሩት ይፋ አድርገዋል፡፡ በመሆኑም እስከ 2011 በነበሩት ስድስት ዓመታት ውስጥ ድሆች የነበሩ ሰዎች ወደባሰ ድህነት ውስጥ ለመግባት ተገደዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ደህና ኑሮ ያላቸው ሰዎችም እ.ኤ.አ. ከ2005 ጀምሮ በነበሩት ስድስት ዓመታት ውስጥ ከነበሩበት የኑሮ ደረጃ መንሸራተታቸው ተመልክቷል፡፡ በተለይ በከተሞች አካባቢ ይህ ክስተት መስተዋሉን የዓለም ባንክ ጥናት ያትታል፡፡ ይህም ሆኖ በአገሪቱ ሲመዘገብ የቆየው የኢኮኖሚ ዕድገት በርካታ ድሆችን ተጠቃሚ ማድረጉ መረጋገጡን ሩት አስታውቀዋል፡፡ 
ምንም እንኳ ከመንግሥት ፊስካል ፖሊሲ ድሆች ተጠቃሚ ቢሆኑም፣ ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆኑ ታክሶች በመጣላቸው ጫና ማሳደሩን፣ ዝቅተኛ የኑሮ የገቢ ደረጃ ባለቸው ቤተሰቦች ላይ ቀጥተኛ ያልሆኑ ታክሶችና የግብርና ዘርፍ ላይ የተጣሉ ታክሶች በድሆች ላይ ኑሮን ማክበዳቸውን የዓለም ባንክ አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ሲባባስ የነበረው የዋጋ ግሽበት በዝቅተኛ የገቢ ክልል ውስጥ የሚገኙ ዜጐች ላይ ጫና ማሳደሩን ተንትኗል፡፡ ምንም እንኳ ድሆች የሚከፍሉት የታክስ መጠን በኢትዮጵያ አነስተኛ ቢሆንም፣ መንግሥት በሚከተለው የፊስካል ፖሊሲ ምክንያት ግን ዋጋ መክፈላቸው አልቀረም፡፡ በመሆኑም በባንኩ ትንታኔ መሠረት ከአሥር ሰዎች አንዱ ደሃ ለመሆን ተገዷል ወይም ደግሞ ደሃ የነበሩ ቤተሰቦች ይበልጥ ድሆች ሆነዋል፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ጉዋንግ ዚ ቼን በበኩላቸው መንግሥት አቅም ኖሮት ድሆች የሚከፍሉትን ታክስ ቢያነሳ እንደሚደግፉ ገልጸዋል፡፡ 
በአገሪቱ ከሚገኙት ክልሎች ውስጥ እ.ኤ.አ. ከ2005 በፊት በደህና ደረጃ ይገኙ ከነበሩት መካከል እንደ ሶማሌና አፋር ያሉት ክልሎች እ.ኤ.አ. በ2011 ወደ ድህነት ቀጣና መውረዳቸውም በጥናቱ ታይቷል፡፡ ከዚህ ባሻገር በአዲስ አበባና በድሬዳዋ የሚታየው የድሆችና የሥራ አጦች ቁጥር እስከ 27 ከመቶ እንደሚሆን አስታውቋል፡፡ በመሆኑም መንግሥት በከተሞች አካባቢ መሠረታዊ የሴፍቲኔት ፕሮግራምን መተግበር እንደሚገባው የዓለም ባንክ ይመክራል፡፡ ይህም ሲባል በገጠርና በከተማ አካባቢ የሚታየው የድህነት ሁኔታ በተፈጥሮው የሚለያይ እንደመሆኑ መጠን፣ ከተማ ነክ አገልግሎቶችን ለድሆች ማዳረስ የከተማ ድህነትን ለመቅረፍ እንደሚያስችል ባንኩ አስታውቋል፡፡  
የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ለድህነት መቀነስ መጠን ከፍተኛውን ድርሻ ተጫውቷል ያለው የግብርና ዘርፍን ነው፡፡ ከግብርና ይልቅ በኢኮኖሚው ውስጥ ከፍተኛ ዕድገት ካስመዘገቡት ዘርፎች ውስጥ የአገልግሎት መስክ ቢሆንም፣ ይህ ዘርፍ የዕድገቱን ያህል በድህነት ላይ ለውጥ አለማሳየቱ አነጋግሯል፡፡ ግብርና ለድህነት መቀነስ ለውጥ ካሳየባቸው መካከል የማዳበሪያ አቅርቦት መስፋፋት ተጠቃሽ ተደርጓል፡፡ ሆኖም ግን የማዳበሪያ ዋጋ መናር በገበሬዎች ዘንድ ራስ ምታት ሆኖ ይገኛል፡፡ ስለዚህ የተጠየቁት የኢኮኖሚ ባለሙያዋ ሩት ምንም እንኳ የማዳበሪዋ ዋጋ ቢጨምርም፣ የአየር ሁኔታው የተስተካከለ መሆኑና የምግብ ዋጋ መናር ለገበሬዎች ተጠቃሚነት ሚና ነበራቸው ሲሉ አስረድተዋል፡፡ 
የመንግሥት ባለሥልጣናት ይፋ ስለተደረገው ሪፖርት አዎንታዊ ምልከታ እንዳሳዩ፣ ጥናቱ ባመላከታቸው ውጤቶች ላይም ስምምነት እንዳላቸው ጥናቱን የመሩት ሩት ተናግረዋል፡፡ በመንግሥት በኩል ሪፖርቱ ይፋ መደረጉን በማስመልከት የተገኙት የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዶ/ር ጌታቸው አደም፣ ሪፖርቱ የመረጃና የጥናት ሥልቶች ላይ ችግሮች እንዳሉበት ተችተዋል፡፡ በተለይ የድህነት መጠን ተባብሶባቸዋል በተባሉትና ከድህነት ወለል በታች የሚገኙት አሥር በመቶ ሰዎች፣ ወደባሰ ድህነት አምርተዋል ተብሎ በቀረበው ላይ ጥያቄ ሰንዝረዋል፡፡ በዶ/ር ጌታቸው ጥያቄ መሠረት ከድህነት ወለል በታች ከሚገኙት መካከል ወደባሰ ድህነት ገብተዋል ስለተባሉት ሰዎች ጥናቱ ግልጽ አለመሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ 
በዓለም የምግብ ፕሮግራም ምርምር ኢንስቲትዩት ከፍተኛ አጥኚ የሆኑት ዶ/ር አለማየሁ ታፈሰ፣ ስለጥናት ውጤቱ ሙያዊ አስተያየታቸውን አቅርበዋል፡፡ በመረጃ አጠቃቀምና ጥናቱ የተካሄደባቸው ዘዴዎች ላይ ስላዩዋቸው ግድፈቶች ተናግረዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚስቶች ማኅበር፣ ከኢትዮጵያ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩት፣ ከጣሊያን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲና ከሌሎችም ተቋማት የተገኙ ተሳታፊዎች ጥያቄዎቻቸውን ለዓለም ባንክ ኃላፊዎችና አጥኝዎች አቅርበዋል፡፡
በባንኩ አዎንታዊ ግምት መሠረት እ.ኤ.አ. በ2030 በአገሪቱ የተንሰራፋው የ30 በመቶ ድህነት መጠን ወደ ስምንት ከመቶ ይቀንሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ባንኩ በሥራ ፈጠራ መስክ ላይ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ከተባሉት መካከል ለኢንዱስትሪ ዞን ግንባታ 250 ሚሊዮን ዶላር ባለፈው ዓመት ብድር መስጠቱ ይታወሳል፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር