የምርት ዘመኑን ቡና ወደ ውጭ መላከ እንዳልቻሉ ቡና ላኪዎች ገለጹ

በምርት ዘመኑ የተገኘው አዲስ ቡና ወደ ውጭ እየተላከ እንዳልሆነ ቡና ላኪዎች ገለጹ፡፡
ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ሁለት የቡና ላኪዎች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ባለፉ ስድስት ወራት የተሸጠው ቡና ከአገር የወጣው በክረምት ወራት ነው፡፡
የሽያጭ ስምምነቱ ባለፈው ዓመት ቢደረግም በዚያው ዓመት መውጣት ባለመቻሉ፣ በዚህ ጊዜ መውጣት ያለበት አዲስ ቡና ግን መውጣት አልቻለም፡፡ ወቅቱ የታጠበ ቡና ወጥቶ አልቆ የደረቀ ቡና የሚላክበት ቢሆንም፣ በተለያዩ ምክንያቶች አፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆኑን ነጋዴዎች አመልክተዋል፡፡
ሽያጩ ሳይፈጸም የቀረው የተቀመጠው የቡና ዋጋ ሊወርድ ይችላል በሚል የቡና ገዥዎች ግብይት ለመፈጸም ባለመፈለጋቸው መሆኑን ሪፖርተር ያነጋገራቸው ነጋዴዎች ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አገር ውስጥ የሚገኙ ቡና አምራቾች የብራዚል ቡና በድርቅ በመመታቱ የዓለም የቡና ዋጋ ከፍ ሊል ስለሚችል፣ የሚያመርቱትን ቡና ለገበያ እያቀረቡ አይደለም በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንድ የንግድ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አዲሱ ቡና በሚፈለገው ደረጃ መውጣት ያልቻለው ቡና ላኪዎቹ በገለጿቸው ሁለት ምክንያቶች እንደሆነ አረጋግጠዋል፡፡ 
የመጀመርያ የዓለም ገበያ ከፍተኛ የዋጋ መዋዠቅ ውስጥ በመሆኑ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ትላልቅ ገዥዎች ግዥ ከመፈጸም ተቆጥበዋል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የብራዚል ቡና በድርቅ በመመታቱና ብራዚል ምን ያህል ቡና ለገበያ እንደምታቀርብ በውል ባለመታወቁ፣ ገዥውም አቅራቢውም ወደ ቡና ግብይት ለመግባት ቁጥብ በመሆናቸው ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል ንግድ ሚኒስቴር ባለፉት ስድስት ወራት ከቡና ወጪ ንግድ ከዕቅዱ በላይ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡ ሚኒስቴሩ ውጤቱ የተገኘው የከረመ ቡና ተሟጦ እንዲወጣ በመደረጉ እንደሆነ በመግለጽ የቡና ላኪዎቹን ምክንያት አጠናክሯል፡፡  በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመርያዎቹ ስድስት ወራት 73,593 ሜትሪክ ቶን ቡና በመላክ 269.03 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት አቅዶ ነበር፡፡ በዚህ መሠረት በግማሽ ዓመቱ 72,556 ሜትሪክ ቶን ቡና በመላክ 308 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት ተችሏል፡፡ 
ይህ የወጪ ንግድ አፈጻጸም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በመጠንም በገቢም ብልጫ እንዳለው ተመልክቷል፡፡ ሚኒስቴሩ ለዚህ ስኬት በዋናነት ያስቀመጠው  የዓለም የቡና ዋጋ ጥሩ መሆኑንና የከረመ ቡና በሰፊው እንዲወጣ መደረጉ ነው፡፡ 
ኃላፊው እንዳሉት በኢትዮጵያ በኩል አሁን ያለው የስድስት ወራት አፈጻጸም መልካም ነው፡፡ ነገር ግን በቀጣዮቹ ወራት መሻሻል ካላሳየ አስቸጋሪ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ብለዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የቡና ግብይት ዳይሬክተር አቶ ጌታሁን ቢኮራ አስተያየት እንዲሰጡ የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር