ሲዳማ ቡና ጠንካራ ግስጋሴውን ቀጥሎበታል

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 9ኛው ሳምንት የጨዋታ መርሀ ግብር እሁድ 9 ሰዓት ይርጋለም ላይ ወላይታ ድቻን ያስተናገደው ሲዳማ ቡና 2ለ0 በመርታት በሊጉ አናት ላይ የሚያቆየውን ድል አስመዝግቧል፡፡
ሲዳማን መሪ ያደረጉትን ሁለት ጎሎች ኤሪክ ሙራንዳ አስቆጥሯል፡፡ ሲዳማ ድሉን ተከትሎ በ9 ጨዋታዎች 17 ነጥብ በመያዝ በሊጉ አናት ላይ ተቀምጧል፡፡ ወላይታ ድቻ በአንጻሩ ከመሪዎቹ ተርታ የሚያሰልፈውን ነጥብ አሳልፎ ሰጥቷል፡፡
በተመሳሳይ ቀን እና ሰዓት አዲስ አበባ ስታዲዮም ላይ ወልዲያ ከነማን 2ለ0 ያሸነፈው መከላከያ ከሲዳማ ቡና በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ደረጃ ተቀምጧል፡፡
ተስፋየ በቀለ እና መሀመድ ናስር ለመከላከያ የድል ጎሎችን አስቆጥረዋል፡፡ ወልዲያ ከነማ ካደረጋቸው 9 ጨዋታዎች ስድስት ተሸንፎ፣ ሁለት አቻ ወጥቶ እና አንድ አሸንፎ 5 ነጥብ በመያዝ በሊጉ ግርጌ ተቀምጧል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመብራት ኃይል ያደረጉት ጨዋታ በአዳነ ግርማ ብቸኛ ጎል ጊዮርጊስ ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዞ ወጥቷል፡፡ ሻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ15 ነጥብ ከመሪዎቹ ተርታ ተሰልፏል፡፡
በቅዱስ ጊዮርጊስ  የተረታው መብራት ኃይል በዓመቱ ለመጀመሪያ ጊዜ  ሽንፈት ያስመዘገበበት ጨዋታ ሆኗል።
ወደ አሰላ በመጓዝ ሙገር ሲሚንቶን የገጠመው ደደቢት ነጥብ ሳይዝ ተመልሷል፡፡ ደደቢት በሙገር ሲሚንቶ 2ለ1 ተረቷል፡፡
ጎንደር ላይ አርባ ምንጭ ከነማን ያስተናገደው ዳሽን ቢራ 1ለ0 በመርታት ሙሉ ሶስት ነጥብ አግኝቷል፡፡
ቅዳሜ አዲስ አበባ ስታዲዮም በተካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ ኢትዮጵያ ቡና ከሀዋሳ ከነማ እንዲሁም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአዳማ ከነማ በተመሳሳይ 1ለ1 ተለያይተዋል፡፡
ሊጉን ሲዳማ ቡና በ17 ነጥብ ሲመራ መካላከያ በ16፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ15 ይከተላሉ፡፡ ቢንያም አሰፋ በ7 እንዲሁም ሳሚ ሳኑሚ በ6 የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን ይመራሉ፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር