የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ተፋሰስ ባለስልጣን ችግሮቹን ቀርፎ ወደ ተግባር በመሸጋገር አገራዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ተባለ

የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ተፋሰስ ባለስልጣን በአጭር ጊዜ ወደ ስራ በመግባት የተጣለበትን አገራዊ ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።
ምክር ቤቱ ማሳሰቢያውን የሰጠው በምክር ቤቱ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ተፋሰስና የአዋሽ ተፋሰስ ባለስልጣናት የ6 ወራት የዕቅድ አፈፃፀማቸውን ዛሬ በገመገመበት ወቅት ነው።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶክተር ገመዳ ብነግዴ የባለስልን መስሪያ ቤቱን አስመልክተው በሰጡት ማሳሰቢያ መስሪያ ቤቱ  ከተቋቋመ አንድ  ዓመት ቢሞላውም አስካሁን ድረስ ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ አለመግባቱና በአጭር ጊዜ ወደ ስራ  በመግባት የተጣለበትን አገራዊ ኃላፊነት ሊወጣ ይገባል።
እነዚህ ተፋሰሶች አሳሳቢ በሚባል ደረጃ ላይ እንደሚገኙና ባለስልጣኑ ከሌሎች የተፋሰስ ልማት ስራዎች ልምድ በመቀመር ፈጥኖ ተፋሰሶቹ ከአደጋው ሊታደጋቸው እንደሚገባ ጠይቀዋል።
የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴርም በተፋሰስ ልማት ላይ የተሰማሩ መስሪያ ቤቶች አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ማድረግ እንዳለበት ነው ቋሚ ኮሚቴው ያሳሰበው።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ከበደ ከንቹላ መስሪያ ቤቱ በተሟላ መልኩ ወደ ተግባር አለመሸጋገሩን በሚመለከት ለቋሚ ኮሚቴው በሰጡት ምላሽ ለዘርፉ የሚመጥኑ ባለሙያዎች ባለማግኘቱ የተሟላ የሰው ኃይል ባለመኖሩ መሆኑን አስረድቷል።
በተመሳሳይ ቋሚ ኮሚቴው የአዋሽ ተፋሰስ ባለስልጣን የ6 ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ላይ ግምገማ አድርጓል።
ባለስልጣኑ በረጅም ዓመታት ያካበተውን የተፋሰስ ልማት ልምድ አዳዲስ ለሚቋቋሙ የተፋሰስ ልማት ስራዎች ሞዴል በመሆን ልምዱን ሊያካፍል ይገባል ብሏል።
ባለስልጣኑ በውሃ አስተዳደር የመረጃ ቋት በማደራጀትያከናወናቸው ስራዎች ቋሚ ኮሚቴው በጥንካሬ ጎኑ ገምግሞታል።
በተለይ ባለስልጣኑ ከሌሎች ተቋማት ጋር ጠንካራ ግንኙነት በመፍጠር ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ የሆነውን በሰቃ ኃይቅ ለመከላከል ያከናወናቸው ስራዎችና ውሃን ለልማት ለማዋል ያደረጋቸው ጥረቶች ይበልጥ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡
ይህ እንዳለ ሆኖ ቋሚ ኮሚቴው በባለስልጣኑ አጠቃላይ አፈፃፀም በሰጠው አስተያየት አፈፃፀሙ ከ75 በመቶ በታች በመሆኑ ዝቅተኛ በሚባል ደረጃ ላይ መሆኑን አስቀምጧል።
ለዚህም ባለስልጣኑ በውሃ አስተዳደር ፣በላይኛው ተፋሰስ የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑና፣ የበጀት አጠቃቀሙም ዝቅተኛ መሆኑን ቋሚ ኮሚቴ
ገምግሟል።
በተለይ በታችኛው አዋሽ የተፋሰስ ልማት የሚደረገውን የጎርፍ አደጋ መከላከል ስራ ተገቢው ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ቋሚ ኮሚቴው ገልጿል።
ያም ሆኖ አፈፃፀሙ ከእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ አንፃር ሲገመገም  የባለስልጣኑ አፈፃፀም ከእቅዱ ጋር የተጣጣመ መሆኑንና መስሪያ ቤቱ ይህንን ዘላቂ ለማድረግ ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ እንዳለበት ነው ቋሚ ኮሚቴው ያብራራው።
- See more at: www.ena.gov.et

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር