የተጫዋቾች የዝውውር ረቂቅ ሰነድ ለምን አነጋጋሪ ሆነ?

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ መንቀሳቀስ ከጀመረ ከስድስት አሠርታት በላይ እንዳስቆጠረ ማስረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በዚህ ታሪካዊ ጉዞው ፌዴሬሽኑም ሆነ ክለቦች ከመነሻው እንደሌሎቹ አገሮች ወጥ የሆነ አደረጃጀት ኖሯቸው ሊቀጥሉ ባለመቻላቸው ዛሬም በተለያዩ የአሠራር ክፍተቶች እሰጣ ገባ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ)፣ የአገሪቱ ክለቦች በፊፋ የክለብ አደረጃጀትና የተጨዋቾች የዝውውር መርሕ እንዲተዳደሩ የተለያዩ ሥልጠናዎችን ሲሰጥ መቆየቱ እንደማሳያ ሊወሰድ እንደሚገባውም የሚናገሩ አሉ፡፡ 
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና ክለቦች በአገሪቱ የሚፈፀመው የእግር ኳስ ተጨዋቾች ደረጃና ዝውውር በሕግና በሥርዓት እንዲመራ በፊፋ ዝቅተኛውን የተጨዋቾች ደረጃና ዝውውር መስፈርት ያሟላ እንዲሆን፣ በተጨማሪም አሠራሩ በሕጋዊ ወኪል እንዲመራና ሒደቱም ተጨዋቾችን፣ ክለቦችንና መንግሥትን ተጠቃሚ በማድረግ ለአገሪቱ የእግር ኳስ ዕድገት መፋጠን የራሱን አወንታዊ ሚና ይጫወታል በሚል የተለያዩ አንቀፆችን የያዘ የተጨዋቾች ደረጃና የዝውውር መመሪያ ረቂቅ ሰነድ ለውይይት አቅርበዋል፡፡ ረቂቅ ሰነዱ ከጥር 25 ቀን 2007 ዓ.ም. በኋላ ሕጋዊ መመሪያ ሆኖ በፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እንደሚፀድቅና እስከዚያ ግን ክለቦች በረቂቅ ሰነዱ በተካተቱ ነጥቦች ውስጥ አለን የሚሉትን ሐሳብ እንዲያንሸራሽሩ ጥር 12 ቀን 2007 ዓ.ም. ፌዴሬሽኑና ክለቦች በካፒታል ሆቴል ባደረጉት የመጀመሪያ የውይይት መድረክ ከስምምነት ደርሰዋል፡፡
ሆኖም ግን መመሪያው ደንብ ሆኖ ሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት ረቂቅ ሰነዱ ለክለቦች ቀደም ብሎ እንዲደርስ ተደርጎ በተለይ የክለብ አስተዳዳሪዎችና ባለቤቶች ጉዳዩን በሰከነና በጥልቀት እንዲመክሩበት መደረግ ነበረበት በሚል አንዳንድ ክለቦችና ተጨዋቾች ቅሬታቸውን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ፡፡ 
በአገሪቱ የተጨዋቾች ደረጃና ዝውውር ላይ መሠረታዊ የሚባሉ ችግሮች በጣም ብዙ መሆናቸውን የሚገልጹት የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተክለወይኒ አሰፋ፣ መመሪያው ያስፈለገበት ዋና ምክንያት ያለው የተጨዋቾች የዝውውር ሥርዓት ዓለም አቀፍ አሠራርን የተከተለ አለመሆኑ፣ እንደዚህ ዓይነቱ የዝውውር ሥርዓት በተለይም ‹‹የፊርማ ክፍያ›› የሚባለው በማንኛውም አገር የማይታወቅ በመሆኑ፣ በሥርዓቱም ያለውን የገንዘብ ዝውውር ለመቆጣጠር አስቸጋሪ መሆኑ፣ ክለቦች ለተጨዋቾች የሚከፍሉት የፊርማ ገንዘብና ተጨዋቾች ለክለቦች የሚሰጡት አገልግሎት ሊጣጣም ባለመቻሉ፣ አሠራሩ በክለቦች መካከል ተመጣጣኝ ፉክክር እንዳይኖር ከማድረጉም በላይ በተለይ በሒደቱ የፊርማ ገንዘብ የማይጠየቅባቸው ታዳጊዎችና ወጣት ተጨዋች ትኩረት እንዳያገኙ የሚያደርግ መሆኑንና በዋናነትም የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት እንዲስፋፋ በማድረጉና መንግሥት ከዘርፉ ማግኘት የሚገባው የገቢ ግብር ማሳጣቱን በማስረዳት የመመሪያው አስፈላጊነት አብራርተዋል፡፡
ጊዜ ተወስዶ በደንብ መታየት አለበት ስለሚባለው አቶ ተክለወይኒ፣ ‹‹ረቂቅ ሰነዱን ያዘጋጀው ኮሚቴ ከራሳቸው ከክለቦችና ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎች እንደተመለከቱትና ስለመመሪያው አስፈላጊነት ተገቢውን ጊዜ ወስደው ተነጋግረውበታል፡፡ ከዚህ በላይ ጊዜ ያስፈልገናል የሚሉ ካሉ ከመመሪያው በተቃራኒ ያሉ አካሎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ መመሪያው ባለመኖሩ የአገሪቱ እግር ኳስ የተፎካካሪነት አቅም ብቻ ሳይሆን፣ በክለቦች መካከልም ያለመመጣጠን ችግር እየተፈጠረ ነው፡፡ ባለው ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር የክለቦች የፋይናንስ አቅም እየተደካመ ነው፡፡ መንግሥት ተገቢውን የገቢ ግብር እያገኘ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ይህን ሁሉ ሕገወጥ እንቅስቃሴ በማስቆምና ሥርዓት ለማስያዝ የማንሠራ ከሆነ የእኛ እዚህ መቀመጥ አስፈላጊነቱ ምንድነው?›› በማለት ነው ስለረቂቅ ሰነዱ ምንነት ለተሳታፊዎች ያስረዱት፡፡
የስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አምበሳው እንየው በበኩላቸው፣ መንግሥት ለስፖርቱ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ በሚገኝበት በዚህ ወቅት፣ የተጨዋቾችን ዝውውር ሽፋን በማድረግ እያቆጠቆጠ የመጣው የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት መፍትሔ ሊቀመጥለት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ችግሩን ለማስወገድ እንደ አማራጭ እየተዘጋጀ ያለውን ይህን ሰነድ ክለቦች ትኩረት ሰጥተው ተገቢውን ውይይት እንዲያደርጉበትም ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ሥራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ረቂቅ ሰነዱን ካዘጋጁት አንዱ ናቸው፡፡ ባለሙያው፣ ይህ የተጨዋቾች ደረጃና ዝውውርን አስመልክቶ የተዘጋጀው ረቂቅ ሰነድ ክለቦችና ፌዴሬሽኑ ቀደም ሲል በተስማሙበት መሠረት ተዘጎጅቶ በውይይት እንዲዳብር የቀረበ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡
የጥናት ቡድኑ ስብስብ ከኢትዮጵያ ቡና፣ ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ከዳሸን ቢራ፣ ከአርባ ምንጭ ከነማ፣ ከሊግ ኮሚቴ፣ ከይግባኝ ሰሚ ኮሚቴና ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት የተውጣጡ ባለሙያዎች እንደሆኑና ስብስቡ የተቋቋመውም ካለፈው 2006 ክረምት ጀምሮ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የፌዴሬሽኑ አመራር ቦርድ የጥናት ቡድኑ ባቀረበለት የጥናት ሰነድ መሠረት በዋናነት፣ ‹‹የተጨዋቾች የፊርማ ገንዘብ፣›› የሚለው ቀርቶ በወርሃዊ ክፍያ በሚለው እንዲተካና ለዚያ ደግሞ እንደገና ጥናት ተደርጎ ለውይይት የሚሆን ረቂቅ ሰነድ የሚያዘጋጅ ቡድን ከኢትዮጵያ ቡና አቶ ገዛኸኝ ወልዴ፣ ከኢትዮጵያ መድን ድርጅት አቶ ስንታየሁ በቀለ፣ ከፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን አቶ አበባው ከልካይ፣ ከአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን አቶ ንጉሤ ለማና የጥናት ቡድኑ ሰብሳቢ የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተክለወይኒ አሰፋ እንዲሆኑ ማድረጉን ጭምር ተናግረዋል፡፡
ጥናቱ እንደ ክፍተት የተመለከተው
በኢትዮጵያ በተለይም በአሁኑ ወቅት ከተጨዋቾች ዝውውር ጋር ተያይዞ እየተሠራበት የሚገኘው አሠራር ለአገሪቱ እግር ኳስም ሆነ ለክለቦች፣ ተጨዋቾችና መንግሥት ምንም ዓይነት ጥቅም እያስገኘ እንዳልሆነ፣ ይልቁንም የክለቦችን የፋይናንስ አቅም እያዳከመ ስለመሆኑ፣ ለተጨዋቾችም ቢሆን በስማቸው እንደወሰዱ ተደርጎ የሚነገረው ገንዘብ ሙሉ በሙሉ የእነሱ እንዳልሆነ፣ በመሐል ለሕገወጥ ደላሎች እንደሚውል፣ በዚህ ዓይነቱ ሕገወጥ አሠራር በፕሮፌሽናል ስም ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ተጨዋቾች ሳይቀር የፊርማ ገንዘብ ወስደው የጠፉ እንዳሉ፣ በፕሮፌሽናል ስም የሚመጡት ብዙዎቹ ተጨዋቾች የችሎታቸው ጉዳይ ጥያቄ እያስነሳ መሆኑ፣ ተጨዋቾች ከደመወዝ ይልቅ ትኩረት ሰጥተው የሚከራከሩት ለፊርማ ተብሎ ስለሚሰጣቸው ገንዘብ መሆኑ፣ ገንዘቡን ከወሰዱ በኋላ ለክለባቸው ተገቢውን አገልግሎት እንደማይሰጡ፣ ክለቦች የቅጣት ዕርምጃ እንውሰድ ቢሉ እንኳን የተጨዋቾች ወርሃዊ ክፍያ ከሁለትና ሦስት ሺሕ ብር ስለማይበልጥ ተጫዋቾች የሚጣልባቸውን የቅጣት ውሳኔ በፀጋ እንደሚቀበሉት፣ ክለቦች ታዳጊዎችን አሳድገው ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም ማሳጣቱ፣ በዚህም ክለቦች ለታዳጊና ለወጣት ተጨዋቾች የሚሰጡት ትኩረት እያነሰ መምጣቱና እንደዚህ ዓይነት የዝውውር ሥርዓት በየትኛውም አገር አለመኖሩ ሲጠቀስ፣ ሌላውና ትልቁ ነገር በአንድ የውድድር ዓመት ለተጨዋቾች ዝውውር በፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ብቻ 140 ሚሊዮን ብር ቢንቀሳከስ መንግሥት ከዚህ ገንዘብ ውስጥ 42 ሚሊዮን ብር የሚያጣ ስለመሆኑም ጭምር ክፍተት ተብሎ መወሰዱን አቶ ገዛኸኝ አስረድተዋል፡፡
ረቂቅ ደንቡን አስመልክቶ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ሌሎች የፕሪሚየርና ብሔራዊ ሊግ ክለቦች፣ ሰነዱ በአብዛኛው የሚደገፍ ጎን እንዳለው፣ ሆኖም ደንቡን ክለቦች በአንድ ቀን ያውም በፕሮጀክተር በመታገዝ እንዲመለከቱ ተደርጎ ወደ ሕጋዊ መመርያነት ይለወጥ መባሉ አግባብ እንደልሆነ፣ ከዚህ ይልቅ ሰነዱ ቀድሞ ለክለቦች እንዲደርሳቸው ተደርጎ ክለቦችም ግብረ መልሶቻቸውን ይዘው መጥተው እንዲወያዩበት ቢደረግ የበለጠ ተዓማኒነት ያለው የዝውውር መመሪያ ይሆን እንደነበር ነው ያስረዱት፡፡ በተጨማሪም እንደ ማሳያ የተነሳው በውድድር ዓመቱ በብሔራዊ ሊግ እየተወዳደረ የሚገኘው የሐረር ሲቲ ክለብ ለያዛቸው 25 ተጫዋቾች፣ ለአንዳቸውም የፊርማ በሚል ገንዘብ አለመክፈሉና ሁሉንም ተጫዋቾች ያስፈረማቸው በወርሃዊ ክፍያ መሆኑን ነው፡፡ ክለቡም ተጫዋቾች ከሚያገኙት ጥቅም ተገቢውን የመንግሥት የሥራ ግብር እንደሚከፍል ጭምር ተነግሯል፡፡ 
ሊሻሻል የሚገባው የረቂቅ ሰነዱ ይዘት 
ጥር 12 ቀን 2007 ዓ.ም. በካፒታል ሆቴል በተደረገው ውይይት ላይ ከፕሪሚየር ሊግ ክለቦች 11፣ ከብሔራዊ ሊግ ክለቦች ደግሞ 42 ተገኝተዋል፡፡ በውይይቱ ያልተሳተፉ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ደደቢትና ሲዳማ ቡና ሲሆኑ፣ ከብሔራዊ ሊግ ደግሞ ያልተገኙት በጠቅላላው 42 ናቸው፡፡ 
ረቂቅ ሰነዱ ምንም እንኳ በተለያዩ አገሮች የተጨዋቾች ደረጃና የዝውውር ሥርዓቱን አስመልክቶ የሚሠራባቸውን መመሪያዎች በአስረጂነት የተጠቀመ ቢሆንም፣ ከአገሪቱ ሕገ መንግሥትም ሆነ የክለቦችን መብቶች የሚጋፉ አንዳንድ አንቀፆች መካተታቸውን የሚገልጹ አሉ፡፡
ከእነዚህ ውስጥ የፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ዝውውር በሚለው ሥር በአንቀጽ 13 በንዑስ አንቀጽ 4.5 እንደሚገልጸው፣ ‹‹አንድ ተጨዋችና አንድ ክለብ በሚያደርጉት የዝውውር የውል ስምምነት ውስጥ የጊዜ ገደቡን ወይም መጠን በስምምነት ሊወስኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን የውሉ ዘመን ከአንድ ዓመት ማነስ ወይም ከአምስት ዓመት መብለጥ የለበትም፤›› በሚል የተቀመጠው ተገቢ እንዳልሆነ፣ ይህም በክለቡና በተጨዋቹ የሚወሰን እንጂ አስገዳጅ ሊሆን እንደማይገባውና መታየት እንዳለበት ይጠይቃሉ፡፡ 
የውጭ አገር ተጨዋቾችን ዝውውር አስመልክቶ በአንቀጽ 14 ንዑስ አንቀጽ 1.7 እንደተመለከተው፣ አንድ ክለብ ሦስት የሚሆኑ የውጭ አገር ተጨዋቾችን ለክለቡ እንዲጫወቱ ማስመዝገብ እንደሚችል በደንብ መገደቡ አግባብነት የሌለው መሆኑ፣ ምክንያቱም የአገሪቱ ክለቦች በየዓመቱ በአህጉራዊው ውድድር ላይ ማለት በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮናና በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ የሚሳተፉ ሊኖሩ ስለሚችሉ፣ ጨዋታውም በፊፋ ሕግና ደንብ መሠረት የውጭ ተጨዋቾችን አዘዋውረው ከሚያጫውቱ አገሮች ጋር በመሆኑ በኢትዮጵያ በሦስት መወሰኑ ተገቢ እንዳልሆነ ሊጤን እንደሚገባው ያሳስባሉ፡፡ 
የውሰት ዝውውር በሚለው ሥር በአንቀጽ 16 በንዑስ አንቀጽ 7፣ ‹‹አንድ ተጨዋች ከአንድ ክለብ ወደ ሌላ ክለብ በትውስት በሚዛወርበት ወቅት ቀደም ሲል ከነበረበት ክለብ ያገኝ የነበረው ጥቅማ ጥቅም አይቀንሱበትም፣ ወይም ቀሪ አይሆንበትም፤›› የሚለው በሕግ ፊት ተጨዋቹ ከሁለቱም ክለቦች ተጠቃሚ ይሆናል የሚለውን ትርጉም ስለሚይዝ ሊስተካከል እንደሚገባውም ይገልጻሉ፡፡
በክፍል አምስት የወጣት ተጨዋቾች ተገቢነት፣ ምዝገባ፣ መብቶችና ግዴታዎች በሚለው፣ አንቀጽ 17 በንዑስ አንቀጽ 1.2 እንደተመለከተው፣ ዕድሜው ከ15 እስከ 17 ዓመት የሆነ ወጣት ከ17 ዓመት በታች የወጣቶች የሻምፒዮና ውድድሮች ተመዝግቦ መጫወት እንደሚችል ይገልጻል፡፡ ይህ ማለት በቅርቡ ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ወጣቶች ሻምፒዮና የተጫወተው የኢትዮጵያ ወጣት ብሔራዊ ቡድን ላይ የደረሰው ዓይነት ችግር የሚፈጥር በመሆኑ ማሻሻያ ሊበጅለት እንደሚገባ፣ እዚሁ ላይ በአንቀጽ 17 ንዑስ አንቀጽ 1.3 ዕድሜው 18 እና ከዚያ በላይ የሆነው ወጣት ተጨዋች በአዋቂዎች ውድድር ተመዝግቦ መጫወት አይችልም የሚለው የሚወሰነው በተጫዋቹ አቅምና ችሎታ እንጂ በደንብ ሊሆን እንደማይገባው፣ ለዚህም ብራዚላዊው ሮናልዶ ዳሲልቫ፣ አርጀንቲናዊውን ሊዮኔል መሲ እና ሌሎችም በርካታ ተጨዋቾች በ18 ዓመታቸው ለዋናው ብሔራዊ ቡድኖቻቸው መጫወት መቻላቸው በአስረጂነት ጠቅሰው፣ አንቀጹ መሻሻል እንዳለበትም ይጠቁማሉ፡፡ 
ከዚህ ውጪ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና ክለቦች እንደነዚህ ዓይነቶቹን ደንብና መመሪያዎች በሚያወጡበት ወቅት ጉዳዩን ከሕግና መሰል ጉዳዮች ጋር አጣጥመው ማስኬድ የሚችሉ የሕግ ባለሙያዎችን ማካተት እንደሚገባቸው እነዚሁ ረቂቅ ደንቡን አስመልክቶ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ረቂቅ ሰነዱን አስመልክቶ በአገሪቱ እየተደመጠ የሚገኘው ቅሬታና ትችት አግባብ አለመሆኑንም ያክላሉ፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር