በፕሪሚየር ሊጉ ሲዳማ ቡና ነጥብ ሲጥል ኢትዮጵያ ቡና ድል ቀንቶታል

አዲስ አበባ ጥር 16/2007 በ13ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መሪው ሲዳማ ቡናና ንግድ ባንክ አንድ አቻ ሲለያዩ ኢትዮጵያ ቡና ወልድያ ከነማን በሰፊ ውጤት አሸንፏል።
በዛሬው ጨዋታ ልዩ ክስተት ሆኖ የተስተዋለው የኢትዮጵያ ቡናው አጥቂ ቢንያም አሰፋ በአንደኛ ዙር የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ፉክክር ላይ በዓመቱ የመጀመሪያው ሀትሪክ የሰራ ተጫዋች ሆኗል።
በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ላይ ኢትዮጵያ ቡና ወልድያ ከነማን ባስተናገደበት ጨዋታ ቡና ጨዋታውን 5 ለ 2 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፎ ወጥቷል።
ቢንያም አሰፋ ፣ሀብታሙ ረጋሳና አስቻለው ግርማ ቡና ድሉን እንዲያጣጥም ኳስን ከመረብ ያገናኙ ተጨዋቾች ናቸው።
በተመሳሳይ ብርሃኑ በላይና አብይ በየነ ደግሞ ለወልድያ ከነማ ግቦችን ያስቆጠሩ ተጨዋቾች ነበሩ ምንም እንኳን ከሽንፈት ባይታደጉትም።
ቡናዎች በመጀመሪያ የጨዋታ አጋማሽ ጥሩ መንቀሳቀስ ችለዋል። ወልድያ ከነማዎች ከእረፍት መልስ ተጠናክረው ቢገቡም ከሸንፈት አልዳኑም።
የኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኝ ጥላሁን መንገሻ ''ቡድኑ እኔ ወደምፈልገው አቋም እየመጣ ነው'' ብለዋል። ሀትሪክ ለሰራው ቢንያም አሰፋና ለአህመድ ረሺድ ባሳዩት ጥሩ አቋም ደስተኛ መሆኑንም ገልጿል።
አስር ሰአት ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሲዳማ ቡና ያደረጉት ጨዋታ አንድ ለአንድ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
ከእረፍት በፊት ሁለቱም ቡድኖች ያለምንም ግብ ሲለያዩ በሁለተኛው አጋማሽ ሲዳማ ቡናዎች በአንዱአለም ንጉሴ መምራት ችለው ነበር፣ ነገር ግን የንግድ ባንኩ አጥቂ ፍሊፕ ዳውዝ የአቻነት ጎሉን በማስቆጠሩ ውጤትን ተጋርተው ወጥተዋል።
ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃ ሲቀሩ የሲዳማ ቡናው ተጫዋች ሞገስ ታደሰ በሰራው ጥፋት የቀይ ካርድ ሰለባ ሆኗል። በጨዋታው ላይ  የዳኝነት ክፍተትም ተስተውሏል።
በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የሲዳማ ቡና አሰልጣኝ ዘላለም ሺፈራው  ''የዳኝነት ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፣ስለሆነም ፌዴሬሽኑ ትኩረት ሰጥቶ መፍትሔ ሊያበጅለት ይገባል''ብሏል።
በነገው ዕለት ቀጥሎ በሚካሄደው የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታ በአበበ ቢቂላና በክልል ስታዲዮሞች ኤሌክትሪክ ከወላይታ ዲቻ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከደደቢት፣ አርባ ምንጭ ከነማ ከአዳማ ከነማ፣ሙገር ሲሚንቶ ከመከላከያ፣ዳሽን ቢራ ከሀዋሳ ከነማ  ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል።
በፕሪሚየር ሊጉ 13 ጨዋታ ያደረገው ሲዳማ ቡና በ27 ነጥብ ሲመራ 11 ጨዋታ ያደረገው ቅዱስ ጊዮርጊስ እና 12 ጨዋታ ያደረገው ኢትዮጵያ ቡና በእኩል 21 ነጥብ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
በዘንድሮው አመት ሊጉን የተቀላቀለው ወልድያ ከነማ በ 5 ነጥብ በሊጉ ግርጌ ላይ ይገኛል።
- See more at: http://www.ena.gov.et/index.php/sport/item/1312-2015-01-25-05-35-40#sthash.U8kkFDRS.dpuf

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር