POWr Social Media Icons

Saturday, January 24, 2015

መንግስት መሰረተቢስ ውንጀላ ነው በሚል ያጣጥለዋል
የኢትዮጵያ መንግስት በአገሪቱ የግል ሚዲያ ላይ የሚያደርገው የተራቀቀ ጫና፣ ሚዲያዎቹ በመጪው ግንቦት ወር የሚካሄደውን ምርጫ በተመለከተ በሚሰሩት ዘገባ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ምህዳሩን እያጠበበባቸው ነው ሲል ሂዩማን ራይትስ ዎች ገለጸ፡፡
መንግስት የግሉን ሚዲያ እንደ አንድ የታመነ የመረጃና የትንተና ምንጭ ሳይሆን እንደ ስጋት በመቁጠር የተጠና ጫና ያደርስበታል ያሉት የሂውማን ራይት ዎች የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ሌስሊ ሌፍኮው ሚዲያው በመጪው ምርጫ ቁልፍ ሚና መጫወት ቢኖርበትም፣ በአንጻሩ ግን በርካታ የአገሪቱ ጋዜጠኞች ምርጫን በተመለከተ በሚያቀርቡት ዘገባ ለእስር እንዳረጋለን የሚል ስጋት እንዳደረባቸው ገልጸዋል፡፡
መንግስት በአገሪቱ የግል ሚዲያ ላይ የሚያደርገው ጫና እየተባባሰ በመምጣቱ ባለፈው አመት ብቻ ስድስት የግል የህትመት ውጤቶች ተዘግተዋል፤ በ22 ጋዜጠኞች፣ ብሎገሮችና አሳታሚዎች ላይ የወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል፤ ከ30 በላይ ጋዜጠኞችም እስራትን በመፍራት አገራቸውን ጥለው ተሰደዋል ብሏል ሂዩማን ራይትስ ዎች ከትናንት በስቲያ ባወጣው ሪፖርት፡፡
“ጋዜጠኝነት ወንጀል አይደለም፣ የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት ጥሰት በኢትዮጵያ” የሚል ርዕስ ያለው  ሪፖርቱ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ላለፉት አራት አመታት ነጻ ዘገባን የሚያቀጭጩ ተግባራትን ሲፈጽም እንደቆየ ጠቅሶ፣ በእነዚህ አመታትም ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብታቸውን በመጠቀማቸው 19 ጋዜጠኞች መታሰራቸውንና 60 ያህሉም መሰደዳቸውን ገልጿል፡፡
ሂውማን ራይትስ ዎች በስደትና በአገራቸው የሚገኙ ከ70 በላይ ጋዜጠኞችን አነጋግሬ ያዘጋጀሁት ነው ባለው በዚህ ሪፖርቱ፣ በአገሪቱ አብዛኞቹ የህትመትና የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች በመንግስት ቁጥጥር ስር እንደሚገኙ ጠቁሞ፣ ጥቂት የግል የህትመት ውጤቶችም እንዳይዘጉ በመስጋት ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ሲዘግቡ በአብዛኛው በራሳቸው ላይ ሳንሱር እንደሚያደርጉ ጠቁሟል፡፡መንግስት በበኩሉ፤ ሂዩማን ራይትስ ዎች የሚያወጣቸው የነፃነትና መብት ጥሰትን የተመለከተ ሪፖርቶች መሰረተ ቢስ እንደሆነ በመግለፅ በተደጋጋሚ ማጣጣሉ ይታወቃል፡፡
Source: www.addisadmassnews.com

0 comments :