ሲኣንን በኣባልነት የያዘው መድረክ የሕዝብ ታዛቢዎች ምርጫ በድጋሚ እንዲካሄድ ጠየቀ

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ታኅሳስ 12 ቀን 2007 ዓ.ም የተደረገው የሕዝብ ታዛቢዎች ምርጫ፣ በሕጉ መሠረት የተከናወነ ባለመሆኑ እንዲደገም ጥያቄ አቀረበ፡፡
መድረክ ይኼን ያስታወቀው ባለፈው ዓርብ ስድስት ኪሎ አካባቢ በሚገኘው ዋና ጽሕፈት ቤቱ ነው፡፡ ‹‹ያለ ገለልተኛ የምርጫ አስፈጻሚና የሕዝብ ታዛቢ ነፃ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒነት ምርጫ ሊኖር ስለማይችል፣ ኢሕአዴግ ከሀቀኛ ታቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በአስቸኳይ ይደራደር፤›› በማለት መግለጫ አውጥቷል፡፡
መግለጫውን የሰጡት የመድረክ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ የውጭ ጉዳይ ኃላፊው ዶ/ር መረራ ጉዲናና ዋና ጸሐፊው አቶ ገብሩ ገብረ ማርያም ሲሆኑ፣ ከምርጫው ጋር ተያያዥ የሆኑ በርካታ ጉዳዮችን አንስተው ገለጻ አድርገዋል፡፡
‹‹ታኅሳስ 12 ቀን 2007 ዓ.ም. የተደረገው የሕዝብ ታዛቢዎች ምርጫ በሕጉ መሠረት የተከናወነ ባለመሆኑ፣ የምርጫውን ሕግጋት ባከበረ መንገድ በድጋሚ እንዲካሄድ እንጠይቃለን፤›› ሲሉ ፕሮፌሰር በየነ አስታውቀዋል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያካሄደውን የሕዝብ ታዛቢዎች ምርጫ በተሻሻለው የኢትዮጵያ የምርጫ ሕግ አዋጅ ቁጥር 532/1999 መሠረት ተቃዋሚ ፓርቲዎች በደብዳቤ ተጠርተው በተገኙበት ሳይሆን፣ የኢሕአዴግ አባላት የተሰየሙበት በመሆኑ የሕዝብ ታዛቢዎች ምርጫ በአዋጁ አንቀጽ 82 ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 መሠረት ለሕዝቡና ሕጋዊ ዕውቅና ላላቸው ፓርቲዎች ጥሪ ተደርጎ ገለልተኝነታቸው እየተረጋገጠ እንዲመረጡ እንጠይቃለን፤›› በማለት አዲስ የሕዝብ ታዛቢዎች ምርጫ እንዲካሄድ ጠይቋል፡፡
መግለጫው በዋንኛነት ያተኮረው በመጪው ግንቦት ወር በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ነው፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩን ማስፋት የተመለከቱና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችም የተነሱበት ነበር፡፡
‹‹ኢሕአዴግ ከመድረክና ከሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር የአገራችንን መሠረታዊ የምርጫ ችግሮች ስለሚፈቱበት ሁኔታ ለመወያያት አስቸኳይ የውይይትና የድርድር መድረክ እንዲያመቻች በአስቸኳይ እንጠይቃለን፤›› በማለት ከምርጫ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ከመንግሥት ጋር ለመወያያት እንደሚፈልግ መድረክ አስታውቋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም መድረክና አባል ፓርቲዎቹ ከገዢው ፓርቲ ጋር ለመወያየትና የመፍትሔ አቅጣጫዎቹን ለማስቀመጥ ለረዥም ጊዜ ጥረት ማድረጋቸውን የተጠቀሰ ሲሆን፣ ‹‹ሆኖም ከገዢው ፓርቲ በኩል ለረዥም ጊዜ ምላሽ ሳያገኙ ቆይተዋል፣›› በማለት በድጋሚ ለድርድር ጥሪውን እያቀረበ እንደሆነ ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል፡፡
መድረክ በመግለጫው፣ ‹‹የዓለም አቀፍ ለጋሽ መንግሥታት፣ ለምሳሌ በቅርቡ የአውሮፓ ኅብረት እያደረጉ እንዳለው በአገራችን የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ ተስፋ መቁረጥ አይኖርባቸውም፤›› ካለ በኋላ፣ ‹‹በኢሕአዴግ ላይ ዲፕሎማሲያዊ  ግፊት በማድረግ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያላቸውን ወዳጅነት እንዲያረጋግጡ ጥሪ እናስተላልፋልን፣›› በማለት ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ከጎኑ እንዲቆም ጥሪውን አስተላልፏል፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር