30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የፊታችን ቅዳሜ በኢኳቶሪያል ጊኒ ይጀመራል

(ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢኳቶሪያል ጊኒ አስተናጋጅነት የሚካሄደው 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከነገወዲያ ይጀመራል።
30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በመጪው ቅዳሜ በምዕራብ አፍሪካዋ አገር ኢኳቶሪያል ጊኒ እና በኮንጎ መካከል በሚደረገው የመክፈቻ ጨዋታ ይጀመራል።
ከ35 ሺህ በላይ ተመልካቾችን የሚይዘው ባታ ስታዲዮም የመክፈቻ ጨዋታውን የሚያስተናድ ሲሆን፥ አዘጋጇኢኳቶሪያል ጊኒ ውድድሩን ማላቦ፣ ባታ፣ ሞንጎሞ እና ኢብየን በተባሉ ከተሞቿ ታዘጋጃለች። 
የፊታችን ቅዳሜ በሚጀመረው የ2015ቱ የአፍሪካ ዋንጫ አስተናጋጇ ኢኳቶሪያል ጊኒ ከኮንጎ ስትፋለም፥ በዕለቱ ቡርኪና ፋሶ  ጋቦንን ትገጥማለች።
በምድብ አንድ አስተናጋጇ ኢካቶሪያል ጊኒ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ጋቦን እና ኮንጎ የተደለደሉ ሲሆን፥ ከዚህ ምድብ ጎረቤታሞቹ ኢካቶሪያል ጊኒ እና ጋቦን እ.ኤ.አ በ2012 ውድድሩን አሰናድተው ሩብ ፍፃሜ ድረስ መጓዝ መቻላቸው ይታወሳል።
እሁድ ከምድብ ሁለት ዛምቢያ ከኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ የሚጫወቱ ሲሆን፥ ቱኒዚያ በበኩሏ ከኬፕ ቨርዴ ጋር ጨዋታዋን ታደርጋለች።
በምድብ ሁለት ዛምቢያ፣ ቱኒዚያ ኬፕ ቨርዴ እናኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ሲመደቡ፥ አልጄሪያ የሞት ምድብ በተባለውና ጋና ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ሴኔጋልን ባገናኘው  ምድብ ሶስት ውስጥ ተደልድላለች።
በብራዚሉ የዓለም ዋንጫም ጠንካራ የተከላካይ ክፍል እንዳላት ያስመሰከረችው አልጄሪያ ከባድ በተባለው ምድብ ውስጥ መደልደሏ ትኩረትን ስቧል።
በማጣሪያ ጨዋታዎችም በስተመጨረሻ በማሊ ከደረሰባቸው የ2 ለ 0 ሽንፈት በስተቀር ሁሉንም በድል የተወጡት የበራሃ ቀበሮዎቹ፥ በከባድ ምድብ ቢገኙም ከምድብ የማለፍ ቅድመ ግምትን ግን የነፈጋቸው አለ ለማለት አያስደፍርም።
በመጨረሻው ምድብ አራት ላይም አይቮሪኮስት ፣ ማሊ ፣ ካሜሮን እና ጊኒ ተደልድለዋል።
በማጣሪያው ተመሳሳይ ምድብ ውስጥ የነበሩት አይቮሪኮስትና ካሜሮን ዳግም በአፍሪካ ዋንጫው ተገናኝተዋል።
በዚህ የአፍሪካ ዋንጫ የማትሳተፈው ኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማን በዋና ዳኝነት ወክላለች።
ኢኳቶሪያል ጊኒ የማስተናገዱን ዕድል ያገኘችው ሞሮኮ በምዕራብ አፍሪካ የተቀሰቀሰውን የኢቦላ ቫይረስ በመስጋት ውድድሩ እንዲራዘም ያቀረበችው ጥያቄ በካፍ ተቀባይነት ባለማግኘቱ እንደሆነ ይታወሳል።
ብዙም ያልተወራለት የኢኳቶሪያል ጊኒው የአፍሪካ ዋንጫ ምን አዳዲስ ነገሮችን ያሳይ ይሆን የሚለው ግን ውድድሩ ቅዳሜ ሲጀመር ምላሽ የሚያገኝ ጥያቄ ይሆናል?

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር