POWr Social Media Icons

Sunday, October 5, 2014

አዲስ አበባ፣ መስከረም 25፣ 2006 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የ4ኛው ዙር የመጨረሻው የስራ ዘመን  የጋራ መክፈቻ ስነ ስርዓት ነገ ይካሄዳል።
በመክፈቻ ስነሰርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ ንግግር ያደርጋሉ።
በፕሬዚዳንቱ ንግግርም የ2007 ዓ.ም ዋና ዋና የመንግሰት የትኩረት አቅጣጫዎች ይዳሰሳሉ ተብሏል።
ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክው፥ በመክፈቻ ስነስርአቱ ላይ የሁለቱ ምክር ቤቶች አባላትና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይታደማሉ።
ስነ ስርአቱ በቴሌዥንና በሬድዮ በቀጥታ ይተላለፋል።
ከሰሞኑ የአብዛኛው የስፖርት ቤተሰብ መነጋገሪያ የሆነው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የአፍሪካ ዋንጫን ማዘጋጀት አለመቻል እንደ አንድ አገራዊ አጀንዳ እያነጋገረ ይገኛል፡፡
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አዲስ አበባ ላይ ጠቅላላ ጉባኤውን ማሰናዳቱን ተከትሎ አብዛኛው የስፖርት አፍቃሪ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. የ2017 የአፍሪካ ዋንጫ የአስተናጋጅነቱ ዕድል እንዲሰጣት ለካፍ ያቀረበችው ጥያቄ እንድትጠቀምበት ይረዳታል ተብሎ ቢጠበቅም፣ የኋላ ኋላ ግን ‹‹አቅም የለንም›› በሚል ምክንያት ፍላጐቷን ወደ ጎን ማድረጓ ከፌዴሬሽኑ ተሰምቷል፡፡
‹‹ሲጀመር ምን ያህል አቅም ኖሮን ነበር?›› ሲል የሚጠይቀው የእግር ኳስ ቤተሰብ አገሪቱ የ2017ቱን የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ዕድሉ እንዲሰጣቸው ከጠየቁ አገሮች አንዷ ሆና መቅረቧ አስገራሚና በዕቅድ ያለመመራት አሠራር መኖሩን በግልጽ እንደሚያመለክት ያወሳሉ፡፡
ካፍ ባለፉት ሳምንታት በአዲስ አበባ ባደረገው ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ከተመለከታቸው አጀንዳዎች የ2019 የአፍሪካ ዋንጫ ለካሜሮን፣ የ2021 ለአይቨሪኮስት፣ የ2023 ለጊኒ የአስተናጋጅነቱን ዕድል የሰጠበት ይጠቀሳል፡፡ የ2017ቱን ቀደም ሲል የአስተናጋጅነቱን ዕድል ለሊቢያ የተሰጠ መሆኑ ቢታመንም፣ ወደ ኋላ ላይ ግን በአገሪቱ በተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት ካፍ ዕድሉን ለሌሎች አገሮች አሳልፎ እንደሚሰጥ ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ አልጄሪያና ዚምባቡዌ የ‹‹እናዘጋጃለን›› ጥያቄያቸውን ለካፍ አስገብተዋል፡፡ የመጨረሻው ቀን ገደብም መስከረም 30 ቀን መሆኑም ይታወቃል፡፡
ፌዴሬሽኑ ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ሦስት የአፍሪካ ዋንጫዎች ማስተናገዷን በመጥቀስ፣ በአህጉር ደረጃ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠውን የ2017ቱን የአፍሪካ ዋንጫ ለማስተናገድ በዚህ እየተጠናቀቀ በሚገኘው ወር መጀመርያ ለካፍ ያቀረበችውን ጥያቄ ማንሳቱን በይፋ አስታውቋል፡፡ በማያያዝም በ2020 የሚደረገው የቻንና በ2025 የሚደረገውን የአፍሪካ ዋንጫ ለማስተናገድ ዕድሉ እንዲሰጣት ጠይቋል፡፡ ፌዴሬሽኑ እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ የቻለው ከፌዴሬሽኑና ከፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን የተውጣጣ የባለሙያዎች ቡድን በማቋቋም ዝርዝር ግምገማና ጥናት ካደረገ በኋላ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የተሟላና አስተማማኝ ሰነድ አቅርቦ ከመወዳደር አንፃር የመሠረተ ልማትና ተዛማጅ የግብዓት እጥረት መኖሩን በማረጋገጡ ነው፡፡
የእግር ኳስ ቤተሰቡም ፌዴሬሽኑ ግራ የሚያጋባ የአስተናጋጅነት ጥያቄ ከማቅረቡ በፊት አመራሮቹ ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋር መክረው ይፋ ማድረግ ይጠበቅባቸው እንደነበርም ይገልጻሉ፡፡ 
ጉዳዩን አስመልክቶ ሪፖርተር ካነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች አምባሳደር ዶ/ር ቶፊቅ አብዱላሒ ይጠቀሳሉ፡፡ አምባሳደሩ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ እንዲህ ዓይነቱን አህጉራዊ የውድድር ዝግጅት ለማሰናዳት ሲያስብ በቅድሚያ የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች ላይ በጥሞና ማጥናትና ከሚመለከተው አካል ጋር መምከርና ከስምምነት መድረስ ነበረበት፡፡
ካፍ ለውድድር አዘጋጅነት ለሚመርጣቸው አገሮች የሚያበቁ መስፈርቶች ምን ምን እንደሆኑ ጠንቅቆ ማወቅ፣ አውቆም ፍላጎቱን አጣጥሞ ለመሄድ ከባለድርሻ አካላት ማለትም ከስፖርት ኮሚሽን ጋር በሐሳቡ ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ ሐሳቡ መቅረብ እንደነበረበትም ይገልጻሉ፡፡ አሁን ግን የተሠራው ሥራ በተቃራኒው ከመሆኑም በላይ አካሄዱም ለአገሪቱም ሆነ ለእግር ኳሱ እንደማይበጅ ጭምር አስረድተዋል፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አሁን ያደረገው ዓይነት በዕቅድ ያልታገዘ አካሄድ ሲፈጸም ይህ የመጀመርያው እንዳልሆነ የሚገልጹት አምባሳደሩ፣ የቀድሞው አመራሮች አምና ሐዋሳ ላይ በተደረገው አገር አቀፍ የስፖርት ምክር ቤት የምክክር መድረክ ላይ ‹‹ኢትዮጵያ የ2017 አፍሪካ ዋንጫ ለማስተናገድ ጥያቄ ማቅረቧን ነግረውናል፡፡ ይሁንና ባሳለፍነው ሳምንት የ2017 አስተናጋጅ አገር ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያ አልተካተተችም፡፡ ይህም እንደዚህ ዓይነት ያሉ ትልልቅ አጀንዳዎች ምንም እንኳን የእግር ኳስ ውድድር ቢሆንም፣ ግን ደግሞ በጊዜ ሰሌዳ በዕቅድ ተይዞና የሚመለከተው ባለድርሻ አካል ሳይቀር ይሁንታን ያገኘ መሆን ይጠበቅበት ነበር፤›› ብለዋል፡፡
አምባሳደሩ ሌላው ያከሉት፣ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አባል አገሮች ብዛት 52 ሲሆን፣ ነገር ግን አፍሪካውያን ይህን ያህል ድምፅ ይዘው በፊፋ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ እንዴትና በምን አኳኋን ሊጠቀሙበት አለመታየታቸው የተረዱት ላለመሆኑ ማሳያዎችን ያቀርባሉ፡፡
በሚቀጥለው የፈረንጆች አዲስ ዓመት የፊፋ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንደሚኖር የሚገልጹት አስተያየት ሰጪው፣ ሁሉም የካፍ አባል አገሮች አሁን በሥልጣን ላይ ለሚገኙት ሴፕ ብላተር ድምፃቸውን ለመስጠት ባለፉት ሳምንታት በአዲስ አበባ በተደረገው የካፍ ጠቅላላ ጉባዔ ከስምምነት መድረሳቸውን ማረጋገጣቸውን ይገልጻሉ፡፡
ሆኖም ግን ይህ ተፈጻሚ ለመሆኑ ሥጋት እንደሚፈጥርባቸው ለዚህም እ.ኤ.አ. በ1998 ፈረንሳይ ላይ በተዘጋጀው የዓለም ዋንጫ ማግሥት አሁን በሥልጣን ላይ የሚገኙት ሴፕ ብላተር ዕጩ ሆነው ከመቅረባቸው አስቀድሞ ለፊፋ ፕሬዚዳንትነት በብቸኝነት የቀረቡት ሲዊድናዊው ጆሃንሰን እንደነበሩ፣ የካፍ አባል አገሮችም ለጆሃንሰን ድምፃቸውን ለመስጠት መጀመርያ ቡርኪና ፋሶ ላይ ተስማምተው ካበቁ በኋላ ሚስተር ብላተር መጨረሻ ላይ ተወዳዳሪ እንደሚሆኑ ሲያሳውቁ፣ አፍሪካውያኑ የተከፋፈሉበትና በኋላም ጥቂቶቹ ቀደም ሲል በወሰዱበት አቋም መሠረት ለጆሃንሰን ድምፃቸውን ሲሰጡ በርካታዎቹ ግን አሁን በሥልጣን ላይ ለሚገኙት ብላተር መስጠታቸውን ያስታውሳሉ፡፡
አፍሪካውያን ባላቸው ድምፅ አቋም ይዘው ቢዘልቁ ግን ባላቸው ድምፅ ተፅዕኖ መፍጠር እንደሚችሉ ይህ ተፅዕኖ ለአህጉሪቱ እግር ኳስ መሠረተ ልማት ሳይቀር የጎላ ድርሻ እንደሚኖረውም ያስረዳሉ፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጨምሮ በእንደዚህ ዓይነቶቹ መድረኮች በአቋማቸው ሊፀኑ እንደሚገባ ጭምር ይመክራሉ፡፡
ምንጭ፦ ሪፖርተርጋዜጣ 
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ሙሉ በሙሉ መንግሥት በሚመድበው ወጪ ይገነባሉ የተባሉ የሁለት መንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታዎችን ለሁለት አገር በቀል ኮንትራክተሮች ከ2.2 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ዋጋ እንዲገነቡ ሰጠ፡፡ 
ሁለቱ አገር በቀል ኮንትራክተሮች የሚገነቡዋቸውን የሁለት መንገዶች ፕሮጀክት ኮንትራት ስምምነት ባለፈው ዓርብ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ጋር ተፈራርመዋል፡፡ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች የሚገኙትን ሁለት የመንገድ ፕሮጀክቶች ሥራዎችን የተረከቡት ደግሞ ማክሮ ጀኔራል ኮንትራክተር ትሬዲንግና ሰንሻይን ኮንስትራክሽን ናቸው፡፡ ሁለቱም ኮንትራክተሮች በመንገድ ሥራ ዘርፍ ላይ ከዚህ ቀደም የተለያዩ የመንገድ ፕሮጀክቶች ላይ የተሰማሩ ሲሆን፣ በእጃቸው ያለውን ሥራ በአግባቡ ገንብተው በማጠናቀቃቸው ተጨማሪ ሥራ ሊሰጣቸው መቻሉ ተጠቅሷል፡፡
በስምምነቱ ወቅት እንደተገለጸው ማክሮ ኮንስትራክሽን እንዲገነባ የተሰጠው የመንገድ ፕሮጀክት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞንና የባሌ ዞንን የሚያገናኘውን የአዳባ አንገቱ መቶ ኪሎ ሜትር መንገድ ነው፡፡ ማክሮ ኮንስትራክሽን ይህን መንገድ ለመሥራት የተዋዋለው 1.25 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ግንባታውም በሦስት ዓመታት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ሁለተኛውን የመንገድ ፕሮጀክት ኮንትራት የተፈራረመው ደግሞ ሰንሻይን ኮንስትራክሽን ነው፡፡ ሰንሻይን ኮንስትራክሽን የተሰጠው የመንገድ ፕሮጀክት በደቡብ ክልል የሞሮቾ፣ ዲምቱና ቢታና የ60.8 ኪሎ ሜትር መንገድ ነው፡፡ ይህንን መንገድ ለመገንባት ሰንሻይን ኮንስትራክሽን የተዋዋለበት ዋጋ 995.01 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ በኮንትራት ውሉ መሠረት ግንባታው በሁለት ዓመት ከአምስት ወራት የሚጠናቀቅ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ሰንሻይንና ማክሮ የሚገነቡዋቸው ሁለቱ መንገዶች ከዚህ ቀደም ምንም ዓይነት የመንገድ መሠረተ ልማት ያልነበራቸው እንደሆኑ በኮንትራት ስምምነቱ ላይ ተገልጿል፡፡ 
የሞሮቾ፣ ዲምቱና ቢታና መንገድ ከአዲስ አበባ ሞምባሳ ናይሮቢ የመንገድ ኮሪደር ጋር በማገናኘት በመንገዱ ላይ ሊፈጠር የሚችለውን የትራፊክ መጨናነቅ በመቀነሰና በማቃለል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሏል፡፡ የመንገዱ ግንባታ የትላልቅና የአነስተኛ የውኃ መተላለፊያ ቱቦዎችና በርካታ ስትራክቸር ሥራዎችን ያካተተ ነው፡፡ 
ከዚሁ መንገድ ግንባታ ጋር ተያይዞ እንደ ሁለተኛ ምዕራፍ የተያዘው የሞሮቾ፣ ዲምቱና ቢታና ሶዶ 43.3 ኪሎ ሜትር መንገድ ሥራ እንደሚሠራ የተገለጸ ሲሆን፣ ለዚህም የዲዛይንና የግንባታ ዝግጅቱ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን አስታውቋል፡፡ 
እንደ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ መረጃ የአዳባ አንገቱ ፕሮጀክት መገንባት በተለይ ከአዲስ አበባ በዶሎ መና በኩል አንገቱ ለመድረስ 712 ኪሎ ሜትር ያስኬድ እንደነበር፡፡ አዲሱ መንገድ ግን 400 ኪሎ ሜትር በማሳጠር ጉዞው 312 ኪሎ ሜትር ብቻ እንዲሆን ያስችላል፡፡
በማክሮ የሚሠራው መንገድ ድልድዮችን፣ ትላልቅና አነስተኛ የውኃ መተላለፊያ ቱቦዎችንና ሌሎች ስትራክቸሮችን የያዘ ነው፡፡ 
ሰንሻይን ኮንስትራክሽን ለሚገነባው መንገድ የምሕንድስናና የማማከር ሥራውን አማካሪ ለመምረጥ በሒደት ላይ ነው፡፡ ማክኖ ለሚገነባው መንገድ ግን የምሕንድስናና የማማከር ሥራውን እንዲሠራ ኔት ኮንሰልቲንግ ኢንጂነርስ የተባለ አገር በቀል ኮንትራክተር እንደተመረጠ ታውቋል፡፡ 
የሁለቱን መንገድ ፕሮጀክቶች ኮንትራት ስምምነት በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በኩል የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዛይድ ወልደገብርኤል ፈርመዋል፡፡ ሰንሻይንን በመወከል የሰንሻይን ፕሬዚዳንት አቶ ሳሙኤል ታፈሰ፣ ማክሮን በመወከል ደግሞ የተቋሙ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤልያስ ማሞ ፈርመዋል፡፡ በኮንትራት ስምምነቱ ላይ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር እንደገለጹት፣ ሁሉም ኮንትራክተሮች በአስፓልት ኮንክሪት ግንባታ ልምድ ያላቸው መሆናቸውን ነው፡፡ 
ከዚህም በላይ ግንባታዎቹ በአገር በቀል ኮንትራክተሮች መገንባታቸው የውጭ ምንዛሪን እንደሚያድን ተገልጾ፣ በመንገድ ግንባታ ዘርፍ አገር በቀል ኮንትራክተሮች ተሳትፎና አቅም እያደገ መሆኑን ያሳያል ተብሏል፡፡ ሥራው የተሰጣቸው ኮንትራክተሮች እንዳመለከቱትም በተሰጣቸው የጊዜ ገደብና በተቀመጠው የጥራት ደረጃ እናስረክባለን ብለዋል፡፡ 
ሰንሻይን ከዚህ ቀደም ከፊንጫ ለምለም በረሃ፣ ሙከጡሪ ዓለም ገበያ፣ ያቤሎ ተተሌ፣ ከአሊ ውኃ እስከ ጉራራ፣ ከባንቢስ ቶንጎ፣ ከዝዋይ ቡታጅራ፣ ከቡታጅራ ጉብሬ፣ ከዓለም ገበያ ዋል ባረክ መንገዶችን ገንብቶ በማጠናቀቅ ያስረከበ ሲሆን፣ ከመሃል ሜዳ ሐሙስ መንገድ ፕሮጀክትን ደግሞ በመገንባት ላይ የሚገኝ መሆኑ ተገልጿል፡፡  
ማክሮ ኮንስትራክሽንም ከዚህ ቀደም ከባለሥልጣኑ ከተረከባቸው ሥራዎች የበቶ አንድና ሁለት ድልድይ ግንባታዎችን አጠናቅቆ አስረክቧል፡፡ እንደ ባለሥልጣኑ ገለጻ ከሆነ ማክሮ በአሁኑ ወቅት ከሃርገሌ ዶሎ ባዲ አዶና ከነሃሌ አብአላ ያሉ የመንገድ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ላይ ነው፡፡ ሁለቱም ፕሮጀክቶች ከ97 በመቶ ላይ መጠናቀቃቸውንም ይጠቅሳል፡፡
ምንጭ፦ ሪፖርተርጋዜጣ 
አንዳንድ የታሪክ ሰነዶችና መጻሕፍት የኢትዮጵያን ፖለቲካ ‘ተማሪ-መራሽ’ ፖለቲካ ይሉታል፡፡ የተደራጀ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የፈለቀው በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሲሆን፣ የአፄ ኃይለ ሥላሴና የደርግ መንግሥታትን ከሥልጣን ለማፈናቀል የተማሪዎች ሚና ቁልፍ ነበር፡፡
የወቅቱ የኢሕአዴግ መሪዎች የፖለቲካና የትጥቅ ትግል ለማድረግ የወሰኑት፣ ህልምና ራዕያቸውን የነደፉት በዛሬው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ (ያኔ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተብሎ ይጠራ በነበረው) ነበር፡፡
እነዚህ የኢሕአዴግ መሪዎች ካሳኳቸው ድሎች አንዱ የሆነው የየካቲት 1966 አብዮት 40ኛ ዓመት ከተዘከረ ከጥቂት ወራት በኋላ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በመላው አገሪቱ የሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና መምህራን የመንግሥትን ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ፕሮግራም ለማስተዋወቅ ባለመ ሥልጠና ላይ እየተካፈሉ ይገኛሉ፡፡ ከ40 ዓመት በፊት የተለያዩ አመለካከቶችን ለመጨፍለቅ ሞክሯል ባሉት መንግሥት ላይ ያመፁት ወጣቶች ያመጡት አብዮት በደርግ ተዘርፏል በማለት የትጥቅ ትግል አድርገው ሁለተኛ ለውጥ ቢጎናፀፉም፣ ይህ ሥልጠና በቀድሞዎቹ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በአሁኑ የኢሕአዴግ ከፍተኛ አመራሮች የበላይነት ሲካሄድ ከገዥው ፓርቲ አመለካከት ውጪ ያሉ አማራጭ ሐሳቦችን ይጨፈልቃሉ መባሉ የታሪክ ምፀት ሆኗል፡፡
በመልካም አስተዳደር፣ በዲሞክራሲ ግንባታና በልማት ሥራዎች ላይ ያተኩራል በተባለው ሥልጠና፣ የሥልጠናው አስገዳጅነትና በይዘቱ ርዕዮተ ዓለማዊ አዝማሚያ ላይ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ በሥልጠናው ጊዜ፣ ወጪና በኢሕአዴግና በትምህርት ሚኒስቴር ሚናዎች ላይም አስተያየቶች ተሰንዝረዋል፡፡ በገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግና በመንግሥት መካከል ስላለው ልዩነት፣ በመንግሥትና በዩኒቨርሲቲዎች መካከል ስላለው ግንኙነትና የዩኒቨርሲቲዎችን ሚና ለመወያየትም ሥልጠናው መልካም አጋጣሚ መፍጠሩን ያመለከቱም አልታጡም፡፡
የሥልጠናው ሒደትና ይዘት
ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ የትምህርት ሚኒስቴር ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሰጠው ሥልጠና ከ300,000 በላይ ተማሪዎችንና በርካታ መምህራንን ማሳተፉ ተዘግቧል፡፡ በሦስት ዙር ለ15 ቀናት በቆየው ሥልጠና ተማሪዎቹ በተመደቡበት የሥልጠና ማዕከል በመገኘት በአሠልጣኞች የቀረበውን ገለጻ የተከታተሉ ሲሆን፣ የተለያዩ ጥያቄዎችን በማቅረብ ንቁ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ሪፖርተር ካነጋገራቸው ተሳታፊዎች ለመረዳት ተችሏል፡፡
ሥልጠናውን መስጠት ለምን እንዳስፈለገ ለሚቀርበው ጥያቄ በመንግሥት በኩል የሚቀርበው ምላሽ ከተለያዩ አካላት ከሚቀርበው ምክንያት ጋር በቀጥታ የሚጣረዝ ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰቡ የገዥው ፓርቲና የመንግሥት ተቃዋሚ እንደሆነ የሚከራከሩ አካላት፣ ሥልጠናው እነዚህን አካላት በምርጫ 2007 የኢሕአዴግ አጋር የማድረግ ተልዕኮ እንዳለው ይገልጻሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ በቅርቡ ከአዲሰ አበባና ከኦሮሚያ ልዩ ዞን መሪ ፕላን ጋር በተያያዘ በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የነበረው አመፅ ዳግም እንዳይነሳ ለማድረግ ሥልጠናው እንደተዘጋጀ ሲገልጹ ተስተውለዋል፡፡
የሥልጠናው ባለቤት የትምህርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ ደሳለኝ ሳሙኤል፣ ሥልጠናው የመንግሥት አሠራሮችን ለዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ከማስተዋወቅ ባሻገር ከምርጫ 2007 ጋር በምንም መንገድ የማይገናኝ እንደሆነ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የመንግሥት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ፕሮግራምን በሚገባ የተረዳ ተማሪ የሚሠራቸው ጥናትና ምርምሮች በተሻለ የኅብረተሰቡን ችግር የመፍታት አቅም እንዳላቸው፣ ተማሪዎቹ ነገ ለሚጠብቃቸው ሕይወትና ኃላፊነት የመንግሥትን አሠራር አስቀድመው ማወቃቸው ጠቃሚ በመሆኑ ሥልጠናው መዘጋጀቱንም አቶ ደሳለኝ አብራርተዋል፡፡
ተማሪዎችና መምህራን ለወትሮው ለዕረፍት በሚጠቀሙበት ጊዜ ሥልጠናው ክረምትን ጨምሮ ባልተለመደ ሁኔታ መሰጠቱም ቅሬታ ቀርቦበታል፡፡ በየዓመቱ መጀመሪያ ላይ ካለፈው ዓመት የመማር ማስተማር ሒደት ግምገማ ማድረግ የተለመደ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ደሳለኝ፣ የትምህርት ጊዜን ላለመሻማትና በአዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ የተነሳ የሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች መግቢያ ጊዜ የተለያየ በመሆኑ፣ በክረምቱ ወቅት ሥልጠናውን ለመስጠት እንደመረጡም አመልክተዋል፡፡
በይዘት ደረጃ ሥልጠናው በዋነኛነት በአራት የተለያዩ ርዕሶች ማለትም ‘የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግልና አገራዊ ህዳሴያችን’፣ ‘የተሃድሶ መስመርና የኢትዮጵያ ህዳሴ’፣ ‘የልማታዊ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ትግላችንና ፈተናዎቹ’ እና ‘የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት መርሆዎች’ በሚሉ ርዕሶች የተሰጠ ሲሆን፣ በአብዛኛው ጠዋት ጠዋት የአሠልጣኞች ገለጻ ሲቀርብ፣ ከሰዓት በኋላ ግን ለጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥበትና በቡድን ውይይት የሚደረግበት አሠራር እንዳለ ተሳታፊዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
አሠልጣኞቹ ለሥራው የተመደቡት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በመረዳትና በማስረዳት አቅማቸው፣ እንዲሁም በማወያየት ክህሎታቸው እንደሆነ አቶ ደሳለኝ ጠቁመዋል፡፡ የሥልጠናው ተሳታፊዎችም በአብዛኛው አሠልጣኞቹ ተግባቢዎችና አቀራረባቸውም ቀላል የሚባል እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ የተማሪዎቹ አሠልጣኞች መካከለኛ ባለሥልጣን ሲሆኑ፣ የመምህራኑ አሠልጣኞች ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ የሆኑት ቁልፍ የኢሕአዴግ አመራር አቶ በረከት ስምኦንን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እንደሆኑ ለመረዳት ተችሏል፡፡ 
ስለሥልጠናው ያላቸውን አጠቃላይ ዕይታ በተመለከተ የተለያዩ ጥያቄዎች የቀረበላቸው ተሳታፊዎች የተደበላለቀ ስሜት እንዳላቸው ከሰጡት ምላሽ ለመረዳት ይቻላል፡፡ ሩሃማ ሚካኤል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት የ5ኛ ዓመት ተማሪ ናት፡፡ ሩሃማ በሥልጠናው ላይ የቀረቡት ጥያቄዎች በአብዛኛው የተመለሱ ባይሆኑም፣ ከቀረቡት ጽሑፎች ይበልጥ አስደሳች እንደነበሩ ገልጻለች፡፡ ‹‹መጀመሪያ አካባቢ የተማሪዎች ተሳትፎ የተገታ ነበር፡፡ በኋላ ግን ሥልጠናው አንድ ፅንፍ የያዘ አስተሳሰብ ሲያራምድ ተማሪዎቹ ስሜታዊ ሆነው መሳተፍ ጀመሩ፡፡ ተሳትፎአቸው ሚዛን ለመጠበቅ ያለመ ይመስል ነበር፤›› ያለችው ሩሃማ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ለፖለቲካ ግብዓት ሲውል በሥልጠናው ላይ ኢትዮጵያ ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ እንደተፈጠረች ተደርጎ እንደቀረበም አብራርታለች፡፡ ‹‹ከኢሕአዴግ መሩ መንግሥት ውጪ ያለፉት መንግሥታት ምንም በጎ ነገር እንደሌላቸው ተደርጎ ሲወቀሱ ነበር፡፡ እውነቱ ግን ኢሕአዴጎች የሚናገሩትን ያህል መላዕክት አይደሉም፡፡ ሌሎቹ መንግሥታትም እነሱ እንዳቀረቧቸው ጭራቆች አልነበሩም፤›› ብላለች፡፡ 
የአሠልጣኞቹ አቀራረብ ዲሞክራሲያዊ እንደነበር የምትናገረው ሩሃማ፣ ለሚቀርቡላቸው አስቸጋሪ ጥያቄዎች የግል አስተያየታቸውን ከማካፈል ይልቅ በጥንቃቄ የተነገራቸውን ብቻ እንደሚመልሱና ወደ ጽሑፎቹ ዳግም እንደሚመለሱም አስታውሳለች፡፡ በሥልጠናው የኢሕአዴግ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳን ለመስማት ጠብቃ እንደነበር የገለጸችው ሩሃማ፣ የሥልጠናው ሒደትና ይዘትን ከምርጫ ጋር በተዘዋዋሪ ማገናኘት ቢቻልም በቀጥታ አለመነሳቱን አመልክታለች፡፡ ይሁንና በተሳተፊ ተማሪዎችና በአሠልጣኞች መካከል አለመተማመንና ጥርጣሬ ሰፍኖ ማስተዋሏ ግን እንደገረማት ገልጻለች፡፡ ‹‹እያንዳንዱ ነጥብ ላይ ተማሪዎቹ ጥያቄዎች አንስተዋል፡፡ ከአፄ ቴዎድሮስ ጀምሮ የነበሩ መንግሥታትን ድርጊትና ባህርይ ከኢሕአዴግ ጋር ሲያነፃፅሩም ነበር፡፡ አብዛኛው ተማሪ ስለ አገሪቱ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ፍልስፍና ዕውቀት እንደሌለውም በግልጽ ይታይ ነበር፤›› በማለት፣ የነበረውን ውጥረት አስታውሳለች፡፡ ከሥልጠናው ስላገኘችው አዲስ ነገር ተጠይቃ ምንም እንዳልጨበጠች ገልጻለች፡፡ 
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አምስተኛ ዓመት የሕግ ተማሪ የሆነውና ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ ወጣት ግን፣ ሥልጠናውንና አሠልጣኞቹን በጣም ጥሩ ሆነው እንዳገኛቸው ይናገራል፡፡ እንደ ሩሃማ ሁሉ ለበርካታ ጥያቄዎች መልስ አለመሰጠቱን የሚናገረው ወጣቱ፣ መልስ ያልተሰጠው ከክፋት ሳይሆን ከጥያቄዎቹ ብዛትና አንዳንዳቹም ጥያቄዎች ከሥልጠናው ይዘት ወጣ ያሉና አሠልጣኞቹ በቂ መረጃ ያልያዙባቸው በመሆናቸው እንደሆነ እንደተሰማው ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ ለአንዳንድ ጥያቄዎች አሠልጣኞቹ በሚመቻቸው መንገድ መመለሳቸውን እንደ ድክመት ያየው ወጣቱ፣ ጥቂት የማይስማማባቸውን ጉዳዮች ሥልጠናው ቢያካትትም በአጠቃላይ ግን ምክንያታዊና ጠቃሚ ሥልጠና መሰጠቱን ተቀብሏል፡፡ ‹‹መንግሥት የመረጣቸውን የፖሊሲ አቅጣጫዎች ለምን እንደተከተለ አሳማኝ ማስረጃዎችን አቅርቧል፡፡ የአሠልጣኞቹ አቀራረብ የጓደኝነት ስሜትን የሚፈጥር ነበር፡፡ በሥራው ዓለም የሚጠብቀንን ተግዳሮት አስቀድመን እንድንዘጋጅበት የማድረግ አቅም የነበረው ሥልጠና ነው፤›› በማለትም አብራርቷል፡፡ 
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዓመት የሕክምና ተማሪ የሆነች ስሟ እንዳይጠቀስ የጠየቀች ሌላ ወጣት ግን፣ በሥልጠናው ዋናው ያተረፈችው የ900 ብር አበል እንደሆነ በቀልድ መልክ ተናግራለች፡፡ ይሁንና በሥልጠናው የቀረቡት ጽሑፎችና የተሳታፊዎች ጥያቄ የአመለካከት ልዩነት ለአገሪቱ የልማት ጥያቄ ትልቅ ተግዳሮት መሆናቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ እንድታስተውል እንዳደረጓት ትገልጻለች፡፡ ‹‹እውነቱን ለመናገር ሥልጠናው የሚሽከረከርባቸው ዋነኛ ነጥቦች ላይ የነበረኝ ግንዛቤ እጅግ ዝቅተኛ ነበር፡፡ አሁን ሁሉም ነገር ገብቶኛል እያልኩ አይደለም፡፡ ነገር ግን ቢያንስ ምላሽ የሚፈልጉ ጥያቄዎችን ግን በሚገባ እንድለይ ሥልጠናው አግዞኛል፤›› በማለት ሥልጠናው የፖለቲካ ንቃተ ህሊናዋን እንዳሳደገው አመልክታለች፡፡ 
ባለፈው ሰኞ ሥልጠናው ለዩኒቨርሲቲ መምህራን የተጀመረ ሲሆን የተወሰኑ ተማሪዎችም በሦስተኛ ዙር ሥልጠና ተካፋይ ሆነዋል፡፡ ከሠልጣኝ መምህራን መካከል አንዱ የሆኑትና ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ መምህር፣ ከሥልጠናው ምንም አዲስ ነገር እንዳላገኙ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ‹‹አንድ ጓደኛዬ ተመሳሳይ የሆነውን ይኼን ሥልጠና ለሦስተኛ ጊዜ ነው የወሰደው፤›› ሲሉም የሥልጠናው ይዘትና አቀራረብ ሳይከለስ ዓመታት ማስቆጠሩን አመልክተዋል፡፡ የምርጫው ጉዳይ በቀጥታ የሥልጠናው አካል ባይሆንም፣ መምህሩ ግን ሥልጠናውን ለማድረግ መነሻ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ‹‹እንዲህ ዓይነት መድረኮች የሕዝቡን ቅሬታና የልብ ትርታ ለማወቅ ጠቃሚ ናቸው፡፡ መንግሥት ወይም ገዥው ፓርቲ ስለራሱ አመለካከትና ስለሠራቸው ሥራዎች ሲያወሳ ዞሮ ዞሮ እንደ ምርጫ ቅስቀሳ የሚወሰድ ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲ ባለቤቶች እኛ ነን የሚል አንድምታም አለው በማለት ሥልጠናው የምርጫ ግብዓት እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ፣ በፖለቲካው መድረክ ደግሞ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በመምራት ቁልፍ ተጨዋች የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና ከሥልጠናው ተካፋዮች አንዱ ናቸው፡፡ ዶ/ር መረራ ሥልጠናውን በሦስት ቀናት መጨረስ እየተቻለ ሁለት ሳምንት እንዲወስድ መደረጉ ጥቅሙ እንዳልታያቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የሥልጠናው ይዘት ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ይገለጹ የነበሩ ሐሳቦችን ይዞ እንደመጣም አመልክተዋል፡፡ ‹‹ባለፉት 23 ዓመታት ኢሕአዴግ በሚዲያና በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የሚሰብካቸው አጀንዳዎች ናቸው የሥልጠናው መሠረታዊ ጉዳዮች ሆነው የቀረቡት፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ ሥልጠናው ገዥው ፓርቲ የሠራቸውን ሥራዎች ከማቅረብ ይልቅ፣ አጠቃላይ መሠረታዊ አገራዊ ጉዳዮችን በውይይት ለመፍታት ያለመ ቢሆን የተሻለ ይሆን እንደነበርም አስረድተዋል፡፡
ዶ/ር መረራም እንደ ወላይታ ሶዶው መምህር የሥልጠናው ዋና ዓላማ ከምርጫው ጋር የተገናኘ እንደሆነ እንደሚገምቱ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ ከምርጫ ጋር በተገናኘ ምሁራኑንና ወጣቱን የሚፈራ ይመስለኛል፡፡ በጊዜ አቅጣጫና አጀንዳ ለማስያዝ ያለመ ሥልጠና ነው፡፡ እነዚህ አካላት በሚያነሱት የመብት ጥያቄ ምርጫውን አወዛጋቢ እንዳያደርጉት ያሠጋል፤›› ሲሉም ምክንያታቸውን አብራርተዋል፡፡
በሥልጠናው ወቅት ተሳታፊዎች ያነሷቸው በርካታ ጠንካራ ጥያቄዎች ከጠበቁት በላይ እንደነበርም ዶ/ር መረራ ጠቁመዋል፡፡ በኢትዮጵያ የልማታዊ መንግሥት ርዕዮተ ዓለም፣ በምርጫ፣ በዲሞክራሲ ግንባታ ሒደት፣ በብሔራዊ መግባባት፣ በዲሞክራሲ ግንባታ ሒደት፣ በትምህርት ፖሊሲ፣ በሙስና፣ በፓርላማው ሚናና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ጠቃሚ ጥያቄዎች መጠየቃቸውን ያስታወሱት ዶ/ር መረራ የአሠልጣኞቹ ምላሽ ‹‹የእኛ እምነት››፣ ‹‹የመንግሥታችን ፖሊሲ›› በሚሉ መግቢያዎች ተጀምሮ ከተጠናው ውጪ ያልዘለለ አዲስ አጀንዳና መረጃ ያልሰጠ መሆኑን ተችተዋል፡፡ 
ይህንን መሰል ሥልጠናን በየጊዜው መስጠት ከወጪና ከጊዜ አንፃር አስቸጋሪ ስለሚሆን በቀጣይ ካሪኩለሙ ውስጥ በማስገባት የትምህርት ሥልጠናው አንድ ክፍል ለማድረግ መታሰቡን ሁሉ የሚጠቁሙ ሪፖርቶች አሉ፡፡ አቶ ደሳለኝ ሥልጠናው በቀጣይነት እንደሚሰጥ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ከሥልጠናው ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለጹ ተማሪዎች እንዲያውም ቀደም ብለው ሥልጠናውን መውሰድ እንደነበረባቸው በመግለጽ እንደዘገየባቸው አመልክተዋል፤›› ሲሉም ሥልጠናውን የመስጠት የመንግሥት ፍላጎት ከሠልጣኞቹ ፍላጎት ጋር የተጣጣመ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
የሥልጠናው አስገዳጅነት
ለተማሪዎችም ሆነ ለአስተማሪዎች በሥልጠናው መሳተፍ አስገዳጅ እንደሆነ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በመገናኛ ብዙኃን ጭምር አስታውቀዋል፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ለሪፖርተር ሥልጠናው አስገዳጅ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤም በመገናኛ ብዙኃን ይህንኑ አረጋግጠዋል፡፡ በተለይ ተማሪዎች ሥልጠናውን ማጠናቀቃቸውን የሚያረጋግጥ ሠርተፍኬት ካልያዙ ከቀጣዩ ሴሚስተር ምዝገባ ውጪ እንደሚሆኑም ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶ ነበር፡፡ 
አቶ ደሳለኝ ሳሙኤል የሥልጠናው አስገዳጅነት የተማሪዎቹን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከማሰብ የመጣ እንደሆነ ተከራክረዋል፡፡ ‹‹በትምህርታቸውና በሥራው ዓለም ውጤታማ እንዲሆኑ የሚጠቅም ሥልጠና በመሆኑ እንደ ትምህርታቸው አካል ነው የምንወስደው፡፡ ስለዚህ ይህ ጠቃሚ ሥልጠና እንዳያመልጣቸው ስንል አስገዳጅ እንዲሆን አድርገነዋል፤›› በማለትም አክለዋል፡፡ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እውነቱ ብላታ ለአንድ የአገር ውስጥ ሚዲያ በሰጡት ቃለ ምልልስ ሥልጠናው አስገዳጅ እንዳልሆነ በመግለጽ፣ የቀደመውን የመንግሥት አቋም ለመቃወም ቢሞክሩም ተማሪዎቹና አስተማሪዎቹ ግን የሥልጠናውን አስገዳጅነት አረጋግጠዋል፡፡
ሩሃማ ሥልጠናው አስገዳጅ ሰለመሆኑና ሠርቲፍኬት ያልያዘ እንደማይመዘገብ ከቲቪ ዜና መስማቷን ገልጻለች፡፡ አሠልጣኞች ሥልጠናው አስገዳጅ አይደለም ይሉ እንደነበር የጠቀሰችው ሩሃማ፣ ማታ ማታ በመኝታቸው የሚገኙ ሰዎች ላይ ቁጥጥር መደረጉና ከግቢ መውጣት መከልከሉ የአስገዳጅነት መለያ እንደሆኑ አመልክታለች፡፡ ክረምት እየሠሩ ቤተሰብ የሚደግፉ ተማሪዎች ያቀረቡት ቅሬታም ምላሽ አለማግኘቱ ሌላኛው ማሳያ እንደሆነ ገልጻለች፡፡ የጅማ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ተማሪና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ተማሪም በተመሳሳይ ሥልጠናውን በግድ መውሰዳቸውን አረጋግጠዋል፡፡ 
ለመምህራኑም ሥልጠናውን አስመልክቶ የተላከው የኢሜይል መልዕክት በተመሳሳይ የሥልጠናውን አስገዳጅነት በግልጽ የሚያመለክት ነው፡፡ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህራን የተላከው መልዕክት ለምሳሌ ሥልጠናውን መከታተል አስገዳጅ እንደሆነ፣ ሥልጠናውን ያልተከታተለ መምህር ጉዳይ በከባድ አሳማኝ ምክንያት እንኳን ቢሆን በዩኒቨርሲቲው አመራሮችና በትምህርት ሚኒስትሩ የጋራ ውይይት እንደሚወሰን ይጠቅሳል፡፡ 
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ መምህር ግን በይፋ ሥልጠናው አስገዳጅ ስለመሆኑ እንዳልተነገራቸው ገልጸዋል፡፡ በተገኙ መምህራን ላይ የሚደረገው ቁጥጥር ግን በተዘዋዋሪ የሥልጠናውን አስገዳጅነት እንደሚያሳይ አመልክተዋል፡፡ ስብሰባውን ባይከታተሉ ምን የሚደርስብዎ ይመስልዎታል በሚል ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽም፣ ‹‹ደመወዜ ሊቆረጥ፣ ከሥራዬ ልባረር ወይም ደግሞ ለጥናትና ምርምር የሚፈቀደውን ገንዘብ ልከለከል እችላለሁ የሚል ፍርኃት ስላለኝ ነው ሥልጠናውን ያለፍላጎቴ እየተከታተልኩ ያለሁት፤›› ብለዋል፡፡ ዶ/ር መረራ በበኩላቸው ይደረግ የነበረው ቁጥጥር የሥልጠናውን አስገዳጅነት የሚያሳይ ቢሆንም፣ የዩኒቨርሲቲውን ማኅበረሰብ ማስገደድ ጎጂ ውጤት የሚያስከትል እንደሚሆን አስጠንቅቀዋል፡፡
ርዕዮተ ዓለማዊ ተፅዕኖዎች
በሥልጠናዎቹ ገዥው ፓርቲ የሚያምንበት ርዕዮተ ዓለም ስኬትና ሌሎች ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች የሚከተሏቸው ሌሎች ርዕዮተ ዓለሞች ውድቀት በብዛት መንፀባረቁን የተቃወሙ በርካቶች ናቸው፡፡ ወትሮም መንግሥትና ፓርቲን በመቀላቀል ከመታማት አልፎ የማያውቀው ኢሕአዴግ፣ በዚህ ሥልጠና መንግሥትና ገዥው ፓርቲ አንድ ሆነው እንደቀረቡም ተተችቷል፡፡ 
በመንግሥት ወጪ በተዘጋጀው ሥልጠና ላይ ከልማታዊ መንግሥት ርዕዮተ ዓለም ውጪ ያሉት አማራጮች እንደ ኒዮ ሊበራል ያሉ ርዕዮተ ዓለሞች መተቸታቸው ‘ከመርህ አኳያ አግባብ ያልሆነ’ ሲሉ ተሳታፊዎች ገልጸውታል፡፡ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ግን በአውራ ፓርቲ ሥርዓት በአብዛኛው የአንድ ፓርቲ አመለካከትና ፖሊሲ የመንግሥት ፖሊሲ ነፀብራቅ መሆኑ መሬት ላይ የሚገኝ ሀቅ በመሆኑ፣ ሥልጠናው ላይ የተንፀባረቀው የመንግሥት እንጂ የፓርቲው አመለካከት እንዳልሆነ ተከላክለዋል፡፡
ሩሃማ በሥልጠናው ወቅት መንግሥትና ፓርቲ የተለያዩ ተቋማት መሆናቸውን መለየት አስቸጋሪ እንደነበር ገልጻለች፡፡ የሥልጠናው ባለቤት የትምህርት ሚኒስቴርን ከኢሕአዴግ ለመለየትም ከባድ እንደሆነ አመልክታለች፡፡ አሠልጣኞቹ ይህንን ችግር ለማለፍ ‹‹የኢሕአዴግ መንግሥት›› በማለት ይጠቀሙ እንደነበርም አስታውሳለች፡፡ መንግሥት ወይም ገዥው ፓርቲ የማይከተላቸው ርዕዮተ ዓለሞች በብዙ የዓለም ክፍል ተቀባይነት ያላቸውና ጠቃሚ ተብለው የሚገለጹ ነገሮችን ለማንሳት አሠልጣኞቹ ማመንታታቸውንም አመልክታለች፡፡ የጅማ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ተማሪና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ተማሪው ግን መንግሥት የራሱን ርዕዮተ ዓለም ሲያስረዳ በአጋጣሚ የሌሎችን ድክመት ቢያወሳም፣ ገለጻ ከማድረግ ባለፈ ሌሎቹን ለማጣጣል መድረኩን ተጠቅሟል ብሎ ለመቀበል አስቸጋሪ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ 
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ መምህር ግን የተለየ አስተሳሰብ ነው ያላቸው፡፡ የአንድን ፓርቲ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለምና የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሕዝቡን ሀብት በመጠቀም መስጠት መሠረታዊ የሆነ የሚቃወሙት ነገር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በምርጫ ያሸነፈና መንግሥት የመሠረተው አንድ ፓርቲ ስለመሆኑ የተጠየቁት መምህሩ፣ የምርጫው ውጤት ላይ የሚነሳው ጥያቄ ወደ ጎን ቢተው እንኳን የህዳጣን ድምፅ (Minority View) በብዙኃን ድምፅ (Majority View) ሊጨፈለቅ እንደማይገባው ተከራክረዋል፡፡ ግብር የሚከፍለው ሁሉም አካል እስከሆነ ድረስ ሌሎች አማራጭ ድምፆችም የመደመጥ መብታቸው ሊከበር እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
ዶ/ር መረራ የኢሕአዴግ ርዕዮተ ዓለምን ስኬት እያጋነኑ በማቅረብና የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ርዕዮተ ዓለም፣ ብቃትና መጠን እየኮሰመኑ ማቅረብ ኢሕአዴግ ከጠበቀው በተቃራኒ ለተቃዋሚዎች ድጋፍ ሊያስገኝ እንደሚችል አመልክተዋል፡፡ ‹‹ተሳታፊዎቹ ተቃዋሚዎችን እንደዚህ የሚተቸው ለምንድነው በሚል ለሚጠይቁት ጥያቄ መልስ ለማግኘት ሲሞክሩ የገዥው ፓርቲን ድክመት ነው የሚያገኙት፤›› በማለትም ሥልጠናው ተቃዋሚዎችን ላይጎዳ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ በሥልጠናው ላይ ኒዮ ሊበራል ርዕዮተ ዓለም ፀረ ልማትና የወደቀ ተብሎ ቢከሰስም፣ ኢሕአዴግ በኒዮ ሊበራሎች ዕርዳታና ድጋፍ አገር እየመራ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
አቶ ደሳለኝ ሳሙኤል በፓርላማ ውስጥ ያሉትን ወንበሮች በአጠቃላይ በሚባል ደረጃ ያሸነፈና መንግሥት የመሠረተ ፓርቲ ያዘጋጀው ሰነድ የመንግሥትና የሕዝብ ሰነድ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ሥልጠናው ላይ የተሳተፉት አሠልጣኞች የገዥው ፓርቲ አባላት ቢሆኑም፣ የሥልጠናው ተሳትፎአቸው ግን በመንግሥት ባላቸው ኃላፊነት መሠረት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ የኢሕአዴግ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደስታ ተስፋውም በተመሳሳይ በሥልጠናው ላይ ኢሕአዴግ የመሪነት ሚና እንዳልነበረው ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ነፃነትና ሚና
ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ነፃና ገለልተኛ ተቋም ሆነው በዕውቀትና በፍልስፍና አመንጭነታቸው የሌሎች የውጭ ኃይሎችን (የመንግሥትን ጨምሮ) ባህርይ በመግራት ትልቅ ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ ምሁራን ይጠቁማሉ፡፡ ይሁንና በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከመንግሥት ቀጥተኛ ተፅዕኖ ነፃ የሆኑበት ጊዜ እንደሌለ የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ፡፡ 
አቶ አየናቸው አሰፋ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ ተመራማሪ ሲሆኑ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋኩልቲ ለስምንት ዓመታት ያህል አስተምረዋል፡፡ በቅርቡ ላጠናቀቁት ለሁለተኛ ዲግሪ ማሟያ ጽሑፋቸው የመረጡትም ርዕስ ‹‹ልማታዊ መንግሥትና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ›› የሚል ነበር፡፡ አቶ አየናቸው በየትኛውም ዓለም መንግሥትና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፍፁም የተለያዩ እንደልሆኑ አመልክተዋል፡፡ ተቋማቱ የሚመሩበት ርዕዮተ ዓለም ‹‹ከየትኛውም ርዕዮተ ዓለም ነፃ መሆን›› እንደሆነ ግን ጠቁመዋል፡፡
የአገሮችና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግንኙነት በዋነኛነት በሁለት ፅንፍና በመሀል ላይ ባሉ የተለያዩ አዝማሚያዎች እንደሚገለጽም አቶ አየናቸው ያስረዳሉ፡፡ በአንዱ ፅንፍ ጥብቅ ቁጥጥር የሚያደርጉ አገሮች አሉ፡፡ እነዚህ አገሮች የሶሻሊዝም ጫና ያለባቸውና በአብዛኛው ፈላጭ ቆራጭና አምባገነን እንደሆኑም ጠቁመዋል፡፡ አገሮቹ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን እያንዳንዱን እንቅስቃሴ እንደሚወስኑ ያመለከቱት አቶ አየናቸው፣ ለምሳሌ የካሪኩለም ቀረፃ፣ የመምህራን ምልመላ፣ የተማሪዎች ቅበላ መሥፈርት፣ የገንዘብ አስተዳደር፣ የዲግሪ መሥፈርትና ቅርፅ የመሳሰሉትን ጉዳዮች መንግሥታቱ የሚወስኑ እንደሆነ፣ በአብዛኛው ዲግሪ የሚሰጠው በዩኒቨርሲቲዎቹ ሳይሆን በመንግሥት በራሱ ነው እንደሚባልም ገልጸዋል፡፡ 
በሌላኛው ፅንፍ የሚገኘው ፈቃጅ መንግሥት ደግሞ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መጫወቻ ሜዳውን የሚያመቻች እንደሆነ አቶ አየናቸው አስረድተዋል፡፡ ይህንንም ሰፋ ያሉ ፖሊሲዎችን በመቅረፅ፣ የሕግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት፣ ጥራትና ደረጃን በማውጣትና ፍትሐዊ ውድድር እንዲኖር በማድረግ እንደሚያሳካ የገለጹት አቶ አየናቸው፣ ተቋማቱ ከፍተኛ ነፃነት እንዲኖራቸው እንደሚያደርግም ጠቅሰዋል፡፡ አሜሪካ ለዚህ ሞዴል ተጠቃሽ ብትሆንም፣ የአውሮፓ አገሮች ግን ከጥብቅ ቁጥጥር ወደ ፈቃጅ (Regulatory) አገርነት እየተቀየሩ እንደመጡ አብራርተዋል፡፡ 
በሁለቱ ፅንፎች መካከል መንግሥታት ሙሉ በሙሉ እጃቸውን ሳያወጡ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር አብረው እንደሚሠሩም አመልክተዋል፡፡ ልዩነቱም መንግሥት ጣልቃ የሚገባበት መጠንና ተቋማቱ የሚጎናፀፉት ነፃነት እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡ ተቋማቱ የዜጎችን መሠረታዊ ፍላጎት የሚነኩ በመሆናቸውና መንግሥትም በተለያየ ሁኔታ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግላቸው በመሆኑ መፈላለጋቸው ቀጣይነት እንዳለውም አስረድተዋል፡፡ 
ኢትዮጵያ እከተለዋለሁ በምትለው የልማታዊ መንግሥት ሞዴል ወይም ርዕዮተ ዓለም መንግሥታት የጠቅላይነት ባህርይ ስላላቸው ተቋማቱ አብዛኛው የመንግሥት መሣሪያ እንደሆኑም አቶ አየናቸው ጠቅሰዋል፡፡ አንድ ወጥ አስተሳሰብ ለማስፈን የሚፈልጉት ልማታዊ መንግሥታት የተቃውሞና የአብዮት መነሻ የሆኑትን ተቋማት በጥንቃቄ እንደሚያዩም አብራርተዋል፡፡ በዚህ የተነሳም የተቋማቱ ተልዕኮ በመንግሥታቱ እንደሚወሰንም ጠቁመዋል፡፡ ይሁንና እንደ ደቡብ ኮሪያ ያሉ ልማታዊ መንግሥታት ተቋማቱ ያላቸውን በነፃነት የመሥራት ሚና ሳይገፉ የመንግሥትንም ዓላማ ለማስፈጸም እንዲረዱ፣ የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችንና ማበረታቻዎችን በመስጠት ሚዛን እንደጠበቁ አመልክተዋል፡፡
በኢትዮጵያ በዩኒቨርሲቲ መምህራንና በአስተዳደሩ ወይም በፖሊሲ አውጪዎቹ መካከል ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ክርክር እንዳለ ያመለከቱት አቶ አየናቸው፣ የፖሊሲ ሥልጠናን በአስገዳጅ ሁኔታ መስጠቱና ርዕዮተ ዓለማዊ ጫናዎች መስተዋላቸው ተቋማዊ ነፃነትን አፈር ድሜ የሚያበላና ፅንፍ የያዘ ድርጊት ሆኖ እንደተሰማቸው ገልጸዋል፡፡ በሌሎች አገሮች ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመንግሥትና በገበያው ፅንፍ የያዙ ፍላጎቶች የተወጠሩና እሱን ሚዛን ለማስያዝ ደፋ ቀና ቢሉም፣ በኢትዮጵያ ግን የገበያው ሚና እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑ ተቋማቱ በቀጥታ በመንግሥት ተፅዕኖ ሥር እንዲወድቁ ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡ ይሁንና ዩኒቨርሲቲዎች አማራጭ ሐሳብ የማቅረብና መምህራኑም ከርዕዮተ ዓለም ተፅዕኖ ነፃ መሆናቸውን ማረጋገጥ ለህልውናቸው አስፈላጊ እንደሆነ ተከራክረዋል፡፡
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ መምህርና፣ የዶ/ር መረራ ጉዲና አስተያየትም ተመሳሳይ ነው፡፡ ተቋማቱን ለመንግሥት ፖሊሲ ማስፈጸሚያነት መጠቀም አንድ ነገር ቢሆንም፣ ተቋማቱ እንደ አንድ የመንግሥት አካል መውሰድ ግን ትልቅ ችግር የሚያስከትል በመሆኑ በድጋሚ ሊጤን ይገባል የሚል ነው፡፡ (ሚኪያስ ሰብስቤ ለዚህ ጽሑፍ አስተዋጽኦ አድርጓል)
ምንጭ፦ ሪፖርተርጋዜጣ