POWr Social Media Icons

Thursday, September 11, 2014


ሻሸመኔ ጳጉሜ 5/2006 ኢትዮጵያ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የምታስገባውን መድሃኒት፣ምግብ ማቀነባበሪያ፣የኮስሞቲክስና ነዳጅ ዘይት ወጪ በሂደት ለማስቀረት ምርምር እያካሄደ መሆኑን የወንዶ ገነት ግብርና ምርምር ማእከል አስታወቀ።

በማእከሉ የመአዛማ፣መድሃኒትና ነዳጅ ዘይት እጽዋቶች አስተባባሪና ተመራማሪ አቶ በእምነት መንገሻ ሰሞኑን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ባለፉት አምስት ዓመታት ማእከሉ ምርምር ካካሄደባቸው 30 እጽዋቶች መካከል 20ዎቹ ለምግብ፣ለመጠጥ ማቀነባበሪያ፣ ለስኳር ፣ ለመድሃኒትና ነዳጅ ዘይት የሚያገለግሉ መሆናቸው በሙከራ ተረጋግጧል።

ከውጪና ከሐገር ውስጥ አሰባስቦ ምርምር ያካሄደባቸውን እጽዋቶች በልማቱ ለሚሳተፉ አርሶ አደሮችና ባለሃብቶች ማሰራጨቱን ገልጸዋል።

ማእከሉ ከንግድ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ባካሄደው የገበያ ጥናት መሰረት ሐገሪቱ ከውጭ ለምታስገባቸው የምግብ ማቀነባበሪያ፣መድሀኒትና ነዳጅ ዘይት ውጤቶች በየአመቱ ከሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደምታወጣ መረጋገጡን አስታውቀዋል።

ከጃትሮፋ ተክል ነዳጅ፣ከመአዛማ እጸዋቶች ኮስሞቲክስ፣የጸጉርና ገላ የውበትና ጤንነት መጠበቂያ፣ለመድሀኒት ቅመማ  የሚያገለግሉ እጽዋቶች በምርምር ማግኘቱን ገልጸዋል።

ማእከሉ ሐገሪቱ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለማስቀረትና ምርቱን በማስተዋወቅ ለአለም አቀፍ ገበያ ለማቅረብ ለጀመረው ኢንዱስትሪ መር ስትራቴጂ እቅድ ነድፎ እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የሚያፈልቃቸውን የምርምር ውጤቶች ለአርሶ አደሩና ባለሃብቱ በማስተዋወቅና በማሰራጨት ተጠቃሚው ህብረተሰብ ዘንድ እንዲደረስ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።

በሰው ሰራሽና በተለያየየ ምክንያት የተራቆተውን መሬት በማእዛማ እጽዋቶች ሸፍኖ የአፈር ለምነትን በመጠበቅ አስተማማኝ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ከከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተመርቀው በማህበር የተደራጁ ወጣቶች እጽዋቶቹን አልምተውና እሴት ጨምረው ለገበያ እንዲያቀርቡ ትምህርት እየሰጠ መሆኑንም ገልጸዋል።

የማእከሉ ተመራማሪ አቶ ወልደማሪያም ጌጃና ወጣት ተመራማሪ ደስታ ፍቃዱ እንደሚሉት በምርምር የተገኙ 18 ማእዛማ እጽዋት፣ ስምንት መድሀኒትነት ያላቸው ተክሎች፣ሶስት ለባዮፊውል አገልግሎት የሚውሉ እጽዋቶች በሐገር አቀፍ የጥራት ደረጃቸው መረጋገጡን ተናግረዋል።

በምርምር የተገኙ የሰብል ዓይነቶችን በስፋት ለተጠቃሚው ለማቅረብ የማስተዋወቅና የገበያ ጥናት እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት በማእከሉ የኢኮኖሚ ቡድን አስተባባሪ አቶ ሙሉቀን ፊሊጶስ ከአርሶ አደሮች ማሰልጠኛ ተቋም ባለሙያዎች፣ከባለሃብቶችና አመራሮች ጋር በመቀናጀት የሐገር ውስጥ ገበያን ፍላጎት አማልቶ ለውጪ ገበያ ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከሐረማያ ዩኒቨርስቲ ሁለተኛ ዲግሪ ያለውና በወንዶ ግብርና ምርምር ማእከል የሚሰራው ወጣት በክሪ ሁሴን ኢትዮጵያ የጀመረችውን የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ የተፈጥሮ ሀብትን መልሶ ማልማት ጋር ለማያያዝ እየሰራ መሆኑን ተናግሯል።

በአርሲ ነጌሌ ወረዳ ሰበሬሮጊቻ ቀበሌ አርሶ አደር ጉርጌሳ ለተሞ ከምርምር ማእከሉ ያገኙትን አምስት አይነት ማእዛማ እጽዋት በማልማት ለገበያ አቅርበው ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከሰብል እርሻ በተጨማሪ በአነስተኛ መሬት እጽዋቱን በማልማት ሻሸመኔ ከተማ ለሚገኘው ናቹራል አፍሪካ ድርጅት በማቅረብ በአመት ከ10 ሺህ ብር የሚበልጥ ገቢ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

ለሌሎች አርሶ አደሮች ሞዴል በመሆናቸው የስራ መነሳሳት እንደፈጠረላቸው አስታውቀዋል።

የናቹራል አፍሪካ ድርጅት ባለቤት አቶ ራስ ጸሐይ እንደሚሉት ከወንዶ ግብርና ምርምር ባገኙት ስልጠናና ድጋፍ በመታገዝ ያመረቱትን የምግብ፣መድሃኒትና ቅባት ውጤቶች ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ሆነዋል።

ከአዲስ አበባ 270 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የወንዶ ገነት ግብርና ምርምር ማእከል የእንሰሳት ሃብት ልማት፣የአፈርና ውሃ ጥበቃና ሌሎችም የምርምር ስራዎች በማከናወን ላይ ነው።
ምንጭ፦ ኢዜኣ