POWr Social Media Icons

Monday, August 18, 2014

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሚቀጥለው ዓመት ለሚከናወነው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጳጉሜ 2 ቀን 2006 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስታዲየም የአልጄሪያ አቻውን ያስተናግዳል፡፡
በአፍሪካ ለተለያዩ አገሮች ክለቦች በመጫወት ላይ የሚገኙ የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች ነሐሴ 18 አዲስ አበባ ገብተው ዝግጅት እንደሚጀምሩ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡ 
ፖርቱጋላዊው የዋሊያዎቹ አሠልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ ከአገር ውስጥ ክለቦች የመረጧቸውን ተጫዋቾች ይዘው በብራዚል ከተለያዩ ክለቦች ጋር የወዳጅነት ጨዋታ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ለግብፅ፣ ለደቡብ አፍሪካና ለሱዳን ክለቦች የሚጫወቱት ሳላዲን ሰይድ፣ ኡመድ ኡክሪ፣ ጌታነህ ከበደና አዲስ ሕንፃ ፌዴሬሽኑ ከክለቦቻቸው ጋር ባደረገው ግንኙነት መሠረት በሚቀጥለው ሳምንት ብሔራዊ ቡድኑን እንደሚቀላቀሉ ይጠበቃል፡፡ 
በብራዚል ከተለያዩ ክለቦች ጋር የአቋም መለኪያው ጨዋታ እያደረገ የሚገኘው ብሐራዊ ቡድኑ እስከ ነሐሴ 17 ቀን ድረስ እንደሚቆይ ታውቋል፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ምንም እንኳ ያለው ነገር ባይኖርም፣ በስዊድን የሚጫወተው የሱፍ ሳላህ ዋሊያዎቹን እንዲቀላቀል አሠልጣኙ መጠየቃቸው ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡ 
-ወረርሽኙ በረራ የሚያስቆምበት ደረጃ አልደረሰም ተብሏል
የኢቦላ ምልክት የሚታይባቸው ሰዎች የሚታከሙበት የተለየ ሆስፒታል በአዲስ አበባ ከተማ ተዘጋጀ፡፡ በኮተቤ ገብርኤል አካባቢ የሚገኘውና 95 በመቶ ያህል የተደራጀው ሆስፒታል ለጊዜው 10 አልጋዎች ሲኖሩት በቀጣይ 50 ይደርሳሉ ተብሏል፡፡
በምዕራብ አፍሪካ የተከሰተውንና ከአንድ ሺሕ በላይ ሰዎች የገደለውን የኢቦላ ወረርሽኝ ተከትሎ፣ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ያለውን ዝግጁነት አስመልክቶ ነሐሴ 8 ቀን 2006 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ፣ እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያ የኢቦላ ተጠቂ ያላስመዘገበች ቢሆንም በማንኛውም ሰዓት ግን ወረርሽኙ ሊገባ ይችላል ብሏል፡፡
የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶ/ር ከሰተብርሃን አድማሱ እንደተናገሩት፣ የኢቦላን ምልክት የሚያሟላ ጉዳይ እስካሁን ወደ ኢትዮጵያ አልገባም፡፡ ኢቦላን የሚመስል ምልክትና ከምዕራብ አፍሪካ ወደዚህ የተጓጓዘ ታካሚ ሲኖር በአስቸኳይ ሪፖርት እንዲደረግ የአሠራር ሥርዓት መዘርጋቱ ተገልጿል፡፡ ከናይጄሪያ የመጡ ሁለት ቻይናውያን በኮሪያ ሆስፒታል ተኝተው ሲታከሙ በተደረገ ምርመራ ታካሚዎቹ ወባ እንደያዛቸው ታውቋል፡፡ ሆኖም ኢቦላ በማንኛውም ጊዜ ሊገባ ይችላል ተብሎ ስለሚጠበቅ፣ ኢትዮጵያ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት እያጠናቀቀች መሆኑን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡ 
ከቅድመ ዝግጅቶቹ መካከል አዲስ የተለየ ጠቅላላ ሆስፒታል ማቋቋም አንዱ ሲሆን፣ ይህም ተዘጋጅቶ የጤና ባለሙያዎች እንደተመደቡለትም ተገልጿል፡፡ 
ወረርሽኙ ወደ ምዕራብ አፍሪካ ከሚደረጉ የአየር በረራዎች ጋር ተያይዞ የመግባት ዕድሉ ሰፊ በመሆኑ፣ ከናይጄሪያ አራት ከተሞችም ወደ ኢትዮጵያ በረራዎች ስላሉና በቀን በአማካይ 500 የሚደርሱ ተጓዦች እዚህ ስለሚደርሱ ሥጋቶች አሉ፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ኢቦላን ለመግታት በረራዎችን ማስቆም ያስፈልጋል የሚሉ አስተያየቶች የሚደመጡ ቢሆንም፣ እንደ ዶ/ር ከሰተብርሃን ወረርሽኙ በረራ የሚያስቆምበት ደረጃ ላይ አልደረሰም፡፡ 
‹‹በዓለም አቀፍ ደረጃ አሥጊና አፋጣኝ ምላሽ የሚሹ በሽታዎች ከመከሰታቸውና ከአየር በረራ ጋር ተያይዞ የዓለም ጤና ድርጅት ያስቀመጠው ደረጃ አለ፡፡ አሁን የተከሰተውን ኢቦላ በተመለከተ የተቀመጠው ደረጃ ደግሞ ወደ አገሮቹ መብረርን አይከለክልም፡፡ በረራ ከማቆም ዕርምጃ ላይ የሚደረሰውም በድርጅቱ ደረጃና ምክር ላይ መሠረት ተደርጐ ነው፤›› ብለዋል፡፡ 
በሽታው እንዳይገባ ከመቆጣጠር አኳያ ከኤርፖርቶች ድርጅት፣ ከኢሚግሬሽን፣ ከኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከፖሊስና ከሚመለከታቸው አካላት የተውጣጡና በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ያሉ ሥራዎችን የሚያስተባብር ኮማንድ ፖስት (የማዘዣ ጣቢያ) መቋቋሙ ታውቋል፡፡
ከምዕራብ አፍሪካ ወደ ኢትዮጵያ የሚደረጉ በረራዎች ላይ የተሳፈሩ በሙሉ ተመርምረው የሚያልፉበት ሥርዓት የተዘረጋ መሆኑን፣ ትኩሳት ወይም ኢቦላን የሚያስጠረጥሩ ምልክቶች የታዩባቸው ለብቻቸው ተለይተው የሚቆዩበት (ኳራንታይን) መዘጋጀቱ ተነግሯል፡፡ ከ20 በላይ ሐኪሞችና ነርሶች በፈቃደኝነት በፈረቃ 24 ሰዓት እየሠሩ መሆናቸውን፣ በአውሮፕላን ማረፊያው በተዘጋጀው የመመርመሪያ ጣቢያ ውስጥ የኢቦላ ቫይረስ የያዘው ማንም ሰው ከመጣ የሚያክሙ የሠለጠኑ ባለሙያዎችም መዘጋጀታቸው ተገልጾ፣ ሦስት አምቡላንሶችም በአውሮፕላን ማረፊያው መመደባቸው ተወስቷል፡፡
የኢቦላ መግቢያ አውሮፕላን ማረፊያው ብቻ ባለመሆኑ ኢትዮጵያ ድንበር በምትጋራቸው መውጫና መግቢያ በሆኑ አካባቢዎች ሁሉ የቁጥጥር ሥርዓት እንዳለና የኢቦላ ምልክት ካለ ሪፖርት የሚደረግበት አሠራርም መዘርጋቱ ተገልጿል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ኬንያ ከምዕራብ አፍሪካ ካላት በሳምንት ከ700 ያላነሰ የአየር በረራ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የኢቦላ ተጋላጭ ናት ብሏል፡፡ በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ መንግሥት ከኬንያ መንግሥት ጋር በዓለም ጤና ድርጅት አማካይነት መረጃ የሚለዋወጥ መሆኑ ተገልጾ፣ ከኬንያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር ለመሥራትም መወሰኑ ታውቋል፡፡
ላይቤሪያ በሙከራ ላይ ያለውን የኢቦላ መድኃኒት ለቫይረሱ ተጠቂዎች ለመስጠት ወስናለች፡፡ የዓለም ጤና ድርጅትም በሙከራ ላይ ያለውን የኢቦላ መድኃኒት ለሕሙማኑ መስጠት ካለው የቫይረሱ አስከፊ ባህሪ አንፃር ሥነ ምግባራዊ ነው ብሏል፡፡ ኢትዮጵያ መድኃኒቱን አስቀድማ ለማስገባት ተዘጋጅታለች ወይ? በሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ዶ/ር ከሰተብርሃን፣ ‹‹የኢቦላ ተጠቂ ኢትዮጵያ እስካልገባ ድረስ አስቀድሞ ማከማቸት ካለው እጥረት አንፃር ያስቸግራል፡፡ ከመጣ ግን የዓለም ጤና ድርጅትንና አምራቾቹን እናነጋግራለን፤›› ብለዋል፡፡       
በአሁኑ ጊዜ የምዕራብ አፍሪካዎቹ ጊኒ፣ ሴራሊዮንና ላይቤሪያ በከፍተኛ ደረጃ የኢቦላ ተጠቂ መሆናቸው ሲገለጽ፣ ናይጄሪያም ሰዎች እየሞቱባት እንደሆነ ታውቋል፡፡ በርካታ አየር መንገዶች በኢቦላ የተጠቁ አገሮች የሚያደርጉትን በረራ ቢያግዱም፣ የዓለም የጤና ድርጅት ግን የአየር ጉዞ ለኢቦላ መተላለፍ ያለው ተጋላጭነት ዝቅተኛ ነው ብሏል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የኢቦላ ቫይረስ በአየር የሚተላለፍ አይደለም የሚል ነው፡፡