POWr Social Media Icons

Wednesday, August 6, 2014

ዜናው የhttp://www.ethiopianreporter.com ነው

-ከ180 ሚሊዮን ብር በላይ ወጥቶበታል 
-ብሮድካስት ባለሥልጣን ፈቃድ አልሰጠሁም አለ
ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ በመቋቋም ሒደት ላይ የነበረው የደቡብ ክልል ቲቪ ከ180 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ሥራውን አጠናቆ ነሐሴ 17 ቀን 2006 ዓ.ም. ከተመረቀ በኋላ፣ በቀን የአሥር ሰዓት ሥርጭት እንደሚጀምር ተገለጸ፡፡ 

የደቡብ ክልል ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮሐንስ ቱሬ ለሪፖርተር እንደገለጹት ከሆነ፣ በኢቲቪ በቀን ለአንድ ሰዓት ይተላለፍ የነበረው የክልሉ መንግሥት የቲቪ ፕሮግራም በክልሉ የሚኖሩትን በርካታ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቋንቋ፣ ባህል፣ ማኅበራዊ ኑሮ፣ ፖለቲካዊ ሥርዓት፣ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በላቀ ሁኔታ ለመግለጽ በቂ እንዳልሆነ በመታመኑ፣ ጣቢያውን የማቋቋም ሥራው በፕሮፖዛል መልክ በ2004 ዓ.ም. ከተሠራ በኋላ በ2005 ዓ.ም. የክልሉ መንግሥት አፅድቆት ነው የማቋቋሙ ሒደት የተጀመረው፡፡ 

በማቋቋም ሒደቱ ስቱዲዮ በመገንባት፣ የመሣሪያዎች ግዥ በመፈጸምና ሠራተኞችን በመቅጠር ያለፉትን ሁለት ዓመታት እንዳለፉ የጠቆሙት አቶ ዮሐንስ፣ ጣቢያውን ሙሉ በሙሉ ሥራ ለማስጀመር ከሚያስፈልጉ ሠራተኞች መካከል 70 በመቶ የሚሆኑ 110 ሠራተኞችን መቀጠራቸውን አመልክተዋል፡፡ 

ክልላዊና አገራዊ ጉዳዮችን በማንሳት ከዚህ በፊት ለሕዝብ እይታ ያልቀረቡ ርዕሰ ጉዳዮችን በማቅረብ የክልሉ ነዋሪዎችን ለማስተማርና ለማዝናናት ጣቢያው ቁልፍ መሆኑን አቶ ዮሐንስ አስረድተው፣ በመረጃ ነፃነት ሕጉ አማካይነት የክልሉ ነዋሪዎችና ሌሎች ተመልካቾች ወቅታዊ መረጃ እንዲያገኙ ለማድረግ ጣቢያው እንደሚሠራ አስገንዝበዋል፡፡ አቶ ዮሐንስ በቀን 18 ሰዓት በ47 ቋንቋዎች እየሠራ የሚገኘው የደቡብ ሬዲዮ ለደቡብ ቲቪ ጠቃሚ ተሞክሮ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ 

በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ማስተባበሪያ ኃላፊ አቶ ወርቅነህ ጣፋ ግን፣ ባለሥልጣኑ የቴሌቪዥን ሥርጭት ፈቃድ ከሰጣቸው ክልሎች መካከል የደቡብ ክልል እንደማይገኝ አስታውቀዋል፡፡ እስካሁን ፈቃድ የወሰዱት ክልሎች ኦሮሚያ፣ ሐረሪና የኢትዮጵያ ሶማሌ ሲሆኑ፣ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ መስተዳድሮችም እንዲሁ ፈቃድ አግኝተዋል ብለዋል፡፡ ከደቡብ ክልል በተጨማሪ የአማራ ክልል በቅርቡ የጣቢያውን ስቱዲዮ ያስመረቀ ሲሆን፣ ትግራይ ክልልም የስቱዲዮ ግንባታውን በማጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡ 

አቶ ወርቅነህ ብሮድካስት ባለሥልጣን አዲስ ፈቃድ ለመስጠት የቴሌቪዥን አሠራርን ከአናሎግ ወደ ዲጂታል ለመቀየር የሚደረገው ሥራ መጠናቀቁን መጠበቅ ግድ እንደሚሆንበት የጠቆሙ ሲሆን፣ ሒደቱ በ2007 ዓ.ም. መጨረሻ ወይም በ2008 ዓ.ም. መጀመሪያ አካባቢ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡ 

በብሮድካስቲንግ አዋጁ የግል ቴሌቪዥን የተፈቀደ ቢሆንም፣ እስካሁን በኢትዮጵያ የቴሌቪዥን ጣቢያ ባለቤትነት ከመንግሥት አልወጣም፡፡ በቅርቡ ለግል ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ፈቃድ ያልተሰጠው ጣቢያዎቹ ሊያስከትሉ የሚችሉትን ጉዳት በመፍራት መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ መግለጻቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ 
_______________________________________________________________

We welcome comments that advance the story through relevant opinion, anecdotes, links and data. If you see a comment that you believe is irrelevant or inappropriate, please! inform us. The views expressed in the comments do not represent those of Bloggers.

ፎቶ ከ ሪፖርተር ጋዜጣ
ቻይና በአፍሪካ ውስጥ ያላት ንግድና ኢንቨስትመንት ለአሜሪካ ራስ ምታት እንደሆነ ይነገራል፡፡ አሜሪካ በአፍሪካ ለምታደርገው ዕርዳታም ሆነ ኢንቨስትመንት ከሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ጀምሮ ቅድመ ሁኔታ ታስቀምጣለች፡፡

ኩባንያዎቿም በአፍሪካ ኢንቨስት ከማድረጋቸው በፊት ስለ ደኅንነት፣ ፀጥታና ሰላም ብሎም በአገሪቱ ስላለው የሠራተኛ አያያዝ መብት በቅድሚያ መወያየት ይፈልጋሉ፡፡ 

ቻይና ደግሞ በምትሠራባቸው አገሮች የውስጥ ጉዳይ እጇን አታስገባም፣ አትጠይቅም፡፡ ትኩረቷ ያለው ኢንቨስትመንቷ ላይ ነው፡፡ በዚህም ከአፍሪካ መሪዎች ጋር ተመቻችታለች፡፡ በንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም በኮንስትራክሽን ዘርፍ በአፍሪካ መሠረቷን ጥላለች፣ ተጠናክራለች፡፡ የአፍሪካ መሪዎችንና የንግድ ማኅረሰብ አባላትን ሲያሻት በተናጠል፣ ሲያሻት በቡድን እያወያየች በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች በጋራና በተናጠል ትሠራለች፡፡ ብድር ለመስጠትም የምትሰጠውን አገር የውስጥ ጉዳይ ከቅድመ ሁኔታ ወይም ከመደራደሪያ ውስጥ አታስገባውም፡፡  በመሆኑም በአፍሪካ ውስጥ ከአሜሪካ በበለጠ ሰፊ ድርሻ ይዛ ትሠራለች፡፡

ቻይና ለአፍሪካ የምትልከውም ሆነ ከፍሪካ ወደ አገሯ የምታስገባው አሜሪካ ከአፍሪካ ጋር ካላት ሲነፃፀር የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል፡፡ በመሆኑም አሜሪካ በቻይና እጅ ከገባው የአፍሪካ ኢንቨስትመንት መቋደስና በአፍሪካ ውስጥም መኖሯን ማሳወቅ ትፈልጋለች፡፡ በመሆኑም አሜሪካ ከዚህ በፊት አድርጋ የማታውቀውን የአሜሪካና የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ እያካሄደች ነው፡፡

የአፍሪካ መሪዎች ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ስብሰባ ተቀምጠዋል፡፡ ባለፈው ሰኞ በተጀመረውና ረቡዕ በሚያበቃው የአሜሪካና የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ የላይቤሪያ፣ የጊኒና የሴራሊዮን መሪዎች በአገራቸው ከተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ሲቀሩ የዚምቧቡዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ፣ የሱዳኑ ኦማር አል በሽር፣ የመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ የሽግግር ፕሬዚዳንት ካትሪን ሳምፓ ፓንዛና የኤርትራው ኢሳያስ አፈወርቂ በስብሰባው አልተጋበዙም፡፡

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ አምና በሴኔጋል፣ በታንዛንያና በደቡብ አፍሪካ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ የተዘጋጀው ጉባዔ፣ በአፍሪካ ቻይና እየቀደመች አሜሪካ ኋላ እየቀረች ባለችበት የንግድና የቢዝነስ ጉዳዮች ላይ ይመክራል፡፡

ቻይና በአፍሪካ የ200 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት አላት፡፡ ይህም አሜሪካ በአፍሪካ ካላት ኢንቨስትመንት በእጥፍ ይበልጣል፡፡ የቻይናና የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔን ቻይና እ.ኤ.አ. በ2001 የጀመረች ሲሆን ጃፓን፣ ህንድ እንዲሁም አውሮፓ በቀጣይ ማካሄድ ጀምረዋል፡፡ ለአሜሪካ ደግሞ ይህ የመጀመርያው የአፍሪካና የአሜሪካ መሪዎች ጉባዔ ነው፡፡

የቢቢሲው ጥናት አድራጊና ተንታኝ ሮብ ዊልሰን እንዳተተው እ.ኤ.አ. በ2013፣ 67 በመቶ የሚሆነው የአፍሪካና የአሜሪካ ንግድ በአምስት አገሮች ማለትም በናይጄሪያ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በአንጐላ፣ በግብፅና በአልጄርያ ውስጥ ብቻ የተካሄደ ነው፡፡
አሜሪካ ለእነዚህ አገሮች ከምትልከው የበለጠ የአገሮቹን ምርቶች ታስገባለች፡፡ ከምታስገባቸው ምርቶች ነዳጅ ከግማሽ በላይ ይይዛል፡፡ አሜሪካ በአፍሪካ ካላት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትም 74 በመቶ ያህሉ በናይጄሪያ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በግብፅ፣ በአልጄርያና በሞሪሽየስ ነው፡፡

ቻይና ግን ከአሜሪካ የበለጠ ቢዝነስ በአፍሪካ እንዳላት የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ጥናት ያሳያል፡፡ ከሰሀራ በታች ከሚገኙ አገሮች አምስቱ ወደ ውጭ ከሚልኩት 75 በመቶ ያህሉን ለቻይና ያቀርባሉ፡፡ ስድስት አገሮች ደግሞ ከውጭ ከሚያስገቡት 80 በመቶው ከቻይና የሚመጣ ነው፡፡

አሜሪካ ከአፍሪካ መሪዎች ጋር የመጀመርያውንና ትልቅ የተባለለትን ጉባዔ እያካሄደች ያለችው፣ ቻይና በአፍሪካ ያላትን የንግድና የኢንቨስትመንት ድርሻ ለመሻማት ነው የሚሉ አሉ፡፡

ጉባዔው የአሜሪካ ግብዣ በተነፈጋት ዚምባቡዌም ትችትን አስከትሏል፡፡ የዚምባቡዌ የመረጃ ሚኒስትር ጆናታን ሞዮ ጉባዔው የረባ አጀንዳ እንደሌለው አድርገው አጣጥለውታል፡፡ ‹‹አሜሪካ በአፍሪካ ላይ የራሷን ፍላጐት ለማሳደር ያለመ ጉባዔ ነው፡፡ በአፍሪካ ቻይና ቀድማ ስለተገኘች ፈርታ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ሃምሳ የአፍሪካ መሪዎች በጉባዔው እንዲሳተፉ ጥሪ ያደረገችው አሜሪካ ከዚህ ጉባዔ ብዙ አተርፋለሁ ብላ ትጠብቃለች፡፡ የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔውን ከመጀመራቸው አንድ ቀን አስቀድሞ 500 ከሚጠጉ ወጣት አፍሪካውያን ተማሪዎች ጋር ‹‹ለሚቀጥለው ትውልድ ኢንቨስት ማድረግ›› በሚል ጭብጥ የመከሩት ፕሬዚዳንት ኦባማም፣ የአፍሪካ መሪዎችም ጭብጡን እንደሚጋሩት ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ለወጣቶቹ ባደረጉት ንግግር በዓለም እንዲሰፍን የሚፈለገው ሰላም፣ ደኅንነት፣ ፍትሕና ሀብት አፍሪካ ጠንካራ፣ ሀብታምና ራሷን በራሷ የምታስተዳድር ካልሆነች አይሳካም ብለዋል፡፡ ‹‹የአፍሪካ መሪዎች ለአኅጉሪቱ ችግሮች ራሳቸው መፍትሔ መፈለግ አለባቸው፤›› ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

የአሜሪካ አፍሪካ ጉባዔን ‹‹ታሪካዊ ሁነት›› የሚሉት ፕሬዚዳንት ኦባማ፣ በአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ መጥራታቸው አሜሪካ በአፍሪካ ማስፋፋት ለምትፈልገው ኢንቨስትመንት በር እንደሚከፍት ገልጸዋል፡፡
የኬንያው ዕለታዊ ጋዜጣ ዘ ስታንዳርድ አሜሪካ ተነሳሽነቷን ለአፍሪካ ለማስተዋወቅ፣ የንግድ አጋሮችን ለመለየትና በአኅጉሪቱ ፈጣን ምላሽ የሚፈልገውን ሽብርተኝነትን በመዋጋት ዙሪያ አብሮ ለመሥራት መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ ሆኖም ፕሬዚዳንት ኦባማ ከመሪዎች ጋር የአንድ ለአንድ ውይይት የማያደርጉ መሆኑ አስተችቷቸዋል ብሏል፡፡

አብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች በተለይም ኬንያና ናይጄሪያ በፀረ ሽብር ዙርያ ከአሜሪካ ጋር አብረው ይሠራሉ፡፡ ሆኖም በዚህ ጉባዔ አሜሪካ ትልቅ ትኩረት የሰጠችው ለንግድና ኢንቨስትመንት ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ የአሜሪካ ኩባንያዎች ብዙም በአፍሪካ የታወቁ አይደሉም፡፡ በአፍሪካ ያለው የንግድና የኢንቨስትመንት ክፍተትም በቻይናውያን ባለሀብቶች እየተሞላ ነው፡፡

ጉባዔው ይህን ለማስተካከል ወሳኝ ነው ተብሏል፡፡ በአፍሪካ ምድር ሥፍራ የሚሰጠው ከሆነም ጉባዔው ለአፍሪካ ጠንካራ መልዕክት አለው፡፡ ሆኖም ፕሬዚዳንት ኦባማ ከእያንዳንዱ የአፍሪካ አገሮች መሪዎች ጋር በተናጠል ለመወያየት ጊዜ አለማግኘታቸው አንድ መሰናክል ሆኗል፡፡ አብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች መሪዎች ከአሜሪካ ይልቅ ከቻይና ጋር የንግድ ስምምነት ማድረግን ይመርጣሉ፡፡ ለዚህም ዋና ምክንያታቸው ክብር ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ በክብር ለየብቻ እንዲያወያዩዋቸው ይፈልጋሉ፡፡ የጉባዔው የመጨረሻ ተፅዕኖም የሚታየው የአፍሪካ መሪዎች በሚፈልጉት መጠን ፕሬዚዳንት ኦባማ ሲያደርጉላቸው ነው፡፡

ቻይና ደግሞ ቀድማ የአፍሪካ መሪዎችን መያዝ ችላለች፡፡ የድቡብ አፍሪካው ቢዝነስ ዴይሊ በርዕሰ አንቀጹ በቅርቡ እንዳስነበበው፣ አሜሪካ የአፍሪካው አውቶብስ እንዳያመልጣት መሮጥ ጀምራለች፡፡ ሆኖም መሠረተ ልማትና የንግድ ልውውጥ መጠን መለኪያ ከሆነ ቻይና ቀድማ ሄዳለች፡፡

ጉባዔው ለውጥ ያመጣል ተብሎ ቢጠበቅም የዋሽንግተኑ ስብሰባ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ከማጠናከር ባለፈ፣ በፖሊሲ ዙርያ የሚፈለገውን ለውጥ አያመጣም ሲሉ አንዳንድ ተንታኞች ሲገልጹም ተሰምቷል፡፡

የአፍሪካ መሪዎች ማክሰኞ በዋይት ሃውስ የእራት ግብዣ ከተደረገላቸው በኋላ ረቡዕ ከፕሬዚዳንት ኦባማ ጋር በንግድ፣ በፀጥታና በመልካም አስተዳደር ዙርያ ይመክራሉ፡፡ 900 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የንግድ ስምምነትም በአፍሪካና በአሜሪካ ኩባንያዎች መካከል ይፈረማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
 ምንጭ፦ ሪፖርተር ጋዜጣ