POWr Social Media Icons

Tuesday, July 15, 2014The Jesus Film - Sidaama / Sidamo / Sidaamu Afoo / Sidaminya / Sidámo 'A...

ስነ ሲኒማ የኣንድን ህዝብ ባህል፤ ታሪክ፤ ሰብዕና፤ ዘዴ_ልማዳዊ ኣኗኗር፤ቱፍት፤ እሴት በኣጠቃላይ ማንነት ለማስቀዋወቅ ያለው ፋይዳ የእትዬሌሌ ነው። በኣሁኑ ጊዜ ከቴክኖሎጂ እድገት ጋር ተያይዞ በዓለማችን ላይ ስነ ሲኒማ የህዝቦችን የእለተ እለት ኣኗኗር በመሸከፍ ህዝቦች በስልጣኔ የደረሱበትን ደረጃ ለመጪው ትውልድ በታሪክ በማስቀረት ላይ ነው።

በኣገራችንም ብሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኣቅሚቲ በሚመረቱ ፍልሞች ራሳችንን እና ኣኗኗሯችንን በፊልሞች ማየት ጀምረናል። በዘፈን ክሊፖች እና በቲቪ ላይ ድራማዎች የተጀመረው የኣገራችን ስነ_ሲኒማ ዛሬ ላይ ኤች ዲ ጥራት ወዳላቸው ባለ 35 ሚ/ሜትር ፊልሞች ኣድጓል፤ ምንም እንኳን ኣሁንም ብዙ የምቀረው ቢሆንም።

በኢትዮጵያ የሲኒማ ኢንዱስትሪ ላይ በመታየት ላይ ባለው እድገት በዋናነት በኣማርኛ ቋንቋ የምመረቱ የሲኒማ ስራዎች በመበራከት ላይ ሲሆኑ፤ ከኣማርኛ ቋንቋ ቀጥሎ በኦሮሚፋ እና ትግርኛ ቋንቋ የተሰሩ ስራዎች ይበዛሉ።

የሲዳማ ኣፎ በኣገሪቱ የሰነ ሲኒማ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያለው ቦታ እጅግ በጣም ዝቅተኛ ነው። በሲዳማ ኣፎ የተሰሩ ስነ ሲኒማ ነክ ስራዎች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። ኣሉም ብባሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ታትመው የወጡትን መንፈሳዊ መዝሙሮች ክሊፖች ካልሆኑ በስተቀር ለላ ስራ ለመጥቀስ ይከብዳል።

በርግጥ በሲዳማ ኣፎ የምሰራጭ የቴለቪዥን ጣቢያ ኣለመኖሩ፤ ህዝቡ በራሱ በኣብዛኛው የገጠር ነዋሪ መሆኑ እና የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ባለበት ኣለመሆን፤ በኣጠቃላይ የሰነ ሲኒማ ባህል ኣለመኖሩ ለሲዳማ ሲኒማ ኢንዱስትሪ ዝቅተኛነት እንደምክንያት ማንሳት ይቻላል። በእነዚህ እና በሌሎች ባልጠቀስኳቸው ኣያሌ ምክንያቶች የተነሳ በሲዳማ ኣፎ የተሰራ ሙሉ ፊልም፤ ዶክሜንትሪ እና ወዘተ የለም።

የሆነ ሆኖ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሲዳማ ውስጥ መንፈሳዊ ይዘት ያላቸው የሰነ ሲኒማ ስራዎች እድገት እያሳዩ ነው። ከላይ እንዳነሳሁት በመዝሙዝ ክሊፕ ስራዎች መሰረት የጣለው የመንፈሳዊ ሰኒማ ኢንዱስትሪ ዛሬ ላይ የኢየሱስ ፊልም በሲዳማ ኣፎ እስከመተርጎም ደርሷል።

ምናልባት ወደ ፊት ሙሉ በሙሉ በሲዳማ ምድር በሲዳማውያን የተሰሩ የፊልም ስራዎች ይኖሩናል ብዬ ገምታለሁ። ለማንኛውም በሲዳማ ኣፎ  በተተርጎመው የኢየሱስ ፊልም ውስጥ በድምጽ የተሳተፉትን ተዋኒያን በርቱ ለማለት እወዳለሁ።    
        

“ይርጋለም
ዋ… ይርጋለም
የልጅነቴ ህልም ቀለም
ዓይኔን የከፈትሽው ጨረር
ወርቃማይቱ ጀንበር” ብሎ ደበበ ፅፎታል።
ደራሲ ደበበ ሰይፉ ፎቶ ከ ኣዲስ ገጽ
ሲዳማ በኢትዮጵያ የሰነ ጽሁፍ ታርክ ኣንቱ የተባሉ ጸሃፊትን ኣፍርታለች። በተለይ ኣንጋፋዋ የሲዳማ ከተማ የሆነችው ይርጋዓለም/ ዳሌ በርካታ ደራሲያን እና ጸሃፍት የፈለቁባት ከተማ ናት። ይርጋዓለም ለስነ ጽሁፍ የሚመች ድባብ ኣላት። ነዋሪዎቹዋም ይህንን ደባብ ተጠቅመው የጥበብ ስራዎቻቸውን ለሰነ ጥበብ ኣፍቃሪያን ማድረሳቸውን ተያይዘውታል።
“ይርጋለም
ዋ… ይርጋለም
የልጅነቴ ህልም ቀለም
ዓይኔን የከፈትሽው ጨረር
ወርቃማይቱ ጀንበር” ብሎ ደበበ ፅፎታል።

ምንም እንኳን በሲዳማ ቋንቋ ይህ ነው የምባል የጎላ ስራ ከይርጋዓለም ባይወጣም በኣማርኛ ቋንቋ ግን ኣያሌ ስራዎች ለንባብ በቅተዋል። 

የወራንቻ ኢንፎርሜሽን ኔትዎርክ ይርጋዓለም_ዳሌ በኣገሪቱ ሰነ ጽሁፍ ያላትን ሚና ለመዘከር ኣንጋፋ ጸሃፊቷን ለኣንባቢያን ያስተዋውቃል፤
ለዛሬ ደራሲ እና ባለቅኔ ደበበ ሰይፉ እነሆ ብለናል፦   

የደራሲው ሥራዎች
1.  የብርሃን ፍቅር(ግጥምና ቅኔ)

2.  ለራስ የተፃፈ ደብዳቤ(ግጥምና ቅኔ)
3.  ከባሕር የወጣ ዓሣ(ተውኔት)

ስለደራሲው በጥቂቱ
ደበበ ሰይፉ የአማርኛ ባለቅኔ ነበሩ። ሚያዚያ 16 ቀን 1992 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ደበበ ሰይፉ ዘርፈ ብዙ የጥበብ ሰው ነው፡፡ ገጣሚ፣ ሃያሲ፣ መምህር፣ ጸሐፊ-ተውኔት፣ የሥነ-ጽሑፍ ተመራማሪ… ነው፡፡ “የብርሃን ፍቅር” እና “ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ” የግጥም ሥብስቦቹ የተደጎሱባቸው መጻሕፍቱ ናቸው፡፡ ከዚህ ለጥቆ ያለው መረጃ /አቀናባሪ አሉላ ከ EthioCurrent Assimba –Voice Room/ አማካኝነት /የደበበ ሰይፉን 7ኛ ዓመት የሙት ዓመት ምክንያት በማድረግ ሚያዝያ16,1999ዓ.ም የተቀናበረ ነው፡- “..ደበበ ሰይፉ ሐምሌ 5 ቀን 1942 ዓ.ም. በሲዳሞ፡ ይርጋለም ተወለደ። የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በይርጋለምና በአዲስ አበባ ኮከበ ጽባህ ትምህርት ቤቶች ተማረ። ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሁፍ ትምህርት ክፍል ከፍ ባለ ማዕረግ የመጅመሪያ ድግሪውን አገኘ። በእንግሊዘኛ ሥነ ጽሁፍ የማስተር ድግሪውን ተቀበለ። ከ1966 እስክ 1984 በረዳት ፕሮፌሰርነት አገለገለ። ለበርካታ ዓመታት የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ፕሬዜዳንት ሆኖ ሰራ። በቀድሞው ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ያልታተሙ መፃህፍት ገምጋሚም ነበር። ከ1985 ዓ.ም. ጅምሮ ለሰባት ዓመታት ታሞ ማቀቀ። ሚያዝያ 16 ቀን 1992 ዓ.ም. በተወለደ በሃምሳ ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። ሚያዝያ 17 ቀን 1992 ዓ.ም. ንፋስ ስልክ በሚገኘው የቅዱስ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን መካነ መቃብር በድኑ አረፈ። ከተማሪነቱ አንስቶ በርካታ ግጥሞች ጽፏል። «የብርሃን ፍቅር» የተሰኘ የመጀመሪያ የግጥም መድበሉን በ1980 ዓ.ም. በኩራዝ አሳታሚ ድርጅት አሳተመ። የብርሃን ፍቅር ሁለተኛ ክፍል የሆነውንና ፦ «ለራስ የተፃፈ ደብዳቤ» የተሰኘውን መድበሉን ደግሞ በ1992 ዓ.ም. በሜጋ አሳታሚ ድርጅት ታተመ። በተውኔቱ ዘርፍ «የቲያትር ጥበብ ከፀሐፌ ተውኔቱ አንፃር» የሚለው መጽሐፉ፤ «ሳይቋጠር የተፈታ» እና «ከባህር የወጣ ዓሣ» የተሰኙት ቲያትሮቹ ቢጠቀሱ ይበቃል…ጥናታዊ ፅሁፎቹም በርካታ ናቸው።
አታልቅስ አትበሉኝ
አትሳቅስ በሉኝ
ግዴለም ከልክሉኝ፤
የፊቴን ፀዳል
አጠልሹት በከሰል፤
የግንባሬን ቆዳ
ስፉት በመደዳ፤
ጨጓራ አስመስሉት።
ግዴለም።
አትጫወት በሉኝ
ዘፈኔን ንጥቁኝ
ግዴለም።
ብቻ ፤ አታልቅስ አትበሉኝ
አትጩህ አትበሉኝ ።
ከሰባት ዓመት በፈት ደበበ ሰይፉ እንዳረፈ ሰሞን ስሙን፦ በጋዜጣ፤ በመጽሔት፤ በሬዲዮና በቴሌቪዥን ሲነሳ ሲወሳ ከርሟል። እስከዛሬም ይታወሳል። ዛሬም ሰባተኛ የሙት ዓመቱን እንዘክረዋለን። ይህን የምናደርገው ፕሮፌሰር ስለሆነ ፤ ገጣሚ ስለሆነ ፤ አንደበተ ርቱዕ ስለሆነ ፤ ፀሐፊ ተውኔት ስለሆነ ፤ ጠቢብ ስልሆነ ብቻ አይደለም ። በዛሬው ዘመን ስለሱ ተወሳ - አልተወሳ ምንም ቁም ነገር የለውም። ሳንታሮ ታኒካዋ ፅፎት ጆርጅ ጊሽ ጀር የተረጎመውን፦ “What the dead man left behind” የሚለውን ግጥም አስታውሶ ትካዜ ባሟሸው ዝምታ ማለፍም ይቻል ነበር። ነገር ግን ጋሽ ደበበ ሁሉንም «ልዩ» ነገር እንደነበር የማያውቁት እንዲያውቁት ያስፈልጋል። ጋሽ ደበበ ሁሉንም «ልዩ» ነገር ነበር። ልዩ ፕሮፌሰር፤ ልዩ ባለቅኔና ገጣሚ፤ ልዩ ተናጋሪ (ኦራተር)፤ ልዩ ተፈላሳፊ፤ ልዩ ፀሕፊ ተውኔት፤ ልዩ ጠቢብ፤ ልይ ሩህሩህና ደግ፤ ልዩ «ቅዱስ» አማፂ፤ ልዩ ልዩ ነበር።
ፍርሃት አዶከብሬ
ፍርሃት አዶከብሬ
አያ እናት አይምሬ
የቁም መቃብሬ
የቅዥት አገሬ።
ከሥጋ ከነብሴ ከደሜ ቆንጥሬ
ከአጥንቴ ሰንጥሬ፤
ምስህን ሰጥቼህ ላመልህ ገብሬ፤
ያው ነህ አንተገና
ልጓምህ አይላላ።
ትጋልበኛለህ በእሾህ በቆንጥር ላይ
ጨለማ እንደ ግራር በቅሎበት በሚታይ
አንዲት ዘሃ-ጮራ
በማትደፍርበት
እውነት - ፍቅር - ውበት
በተቀበሩበት።
ቅዱስ አማፂ ሆኖ ሳለ ከውስጡ አልነቀል ያለውን የፍርሃት ርዝራዥ በ«ፍርሃት አዶከብሬ» ውስጥ ያሳየናል። ካልፈራህ እንዴት ቅዱስ አማፂ ትሆናለህ? ትፈራለህ፤ ትደፍራለህ። ድፍረት በፍርሃትህ ልክ ነው። በፈራኸው መጠን ትደፍራለህ። የማትፈራ ከሆንክ፦ የማትደፍር ነህ። የማትደፍር ከሆንክ የማትደፈር ነህ፤ (ብዙ ጊዜ)። የማትፈራም የማትደፍርም ከሆንክ ደግሞ በድን ነህ። ቅዱስ አማፂነትህ የፍርሃትና የድፍረትህ ድምር ውጤት የሚሆንበት (አብላጫ) ጊዜ አለ። «ጋሼ ደበበ እንዴት ኮሚኒስት እንደሆነ» አንድ ስው ሲያወጋ፡- ያኔ ተማሪ ነበር አሉ። ስታዲየም ዙሪያ አንድ ምግብ ቤት ገባ። እርቦታል። ምግብ አዘዘ። የመብል አምሮት የሠራው ምራቅ በአፉ ግጥም እያለ ትንሽ «አፋዊ» ኩሬ ይሰራል። ያዘዘው ምግብ እስኪቀርብለት በመጠባበቅ ላይ እያለ አንድ ሰው በዝግታ ወደ ውስጥ ገባ። ቡትቶ ለብሷል፤ ዓይኖቹ በደረቀ ፊቱ ውስጥ ተቀርቅረዋል። እንደራበው ያስታውቃል። ተያዩ። የዓይን ግጭቱ ቁም ነገር ያዘለ ከባድ ሃሳብ ሰራ። ያ ሰው ሊናገር ከሚችለው በላይ ለጋሽ ደበበ መልዕክቱ ደረሰው፦ «እርቦኛል ፤ በልተህ ሲተርፍህ እንድትሰጠኝ» ነው ያሉት የሰውየው ዓይኖች። ጋሽ ደበበ ግን ከዚህ በላይ ገባው። አምሮት በሰራው ምራቅ ግጥም ያለ አፉ ክው አለ። የታዘዘው ምግብ እየመጣ ነበር። እፈቱ ተቀመጠ። መብሉን አየው ጋሽ ደበበ። ከመቀመጫው ተነሳ። አነሳው ምግቡን። ለሰውየው ሰጠው። መስጠት ጀምሮ መስጠቱ ከማብቃቱ በፊት በአንድ ጊዜ ሁለት ነገሮች ሆኑ…ከውጭ ግር ያሉ ቡትቶ የለበሰው ሰውዬ ጉስቁል አጃቢዎች መሻማት ጀመሩ። ይሄ አንዱ ነገር ነው። የምግብ ቤቱ ባለቤት ባለቡትቶውን ሰውዬ መቀጥቀጥ ጀመሩ፤ ይሄ ደግሞ ሌላው ነገር ነው። ምግቡ ተደፋ። ጐስቋላው ሰውዬ ደማ። ምግቡ፤ ደሙ፤ አሸዋው፤ አፈሩ፤ ጠጠሩ ሺህ ዓመት እዚያ ቦታ የቆመ ያህል ተሰማው። ተነቀሳቀሰ። ወዴት እንደሚሄድ ሳያውቅ መራመድ ጀመረ። ከዚያን ቅፅበት ጅምሮ በኮሚኒዝም ተጠመቀ። ታላቁ መብረቅ ከሰባት ዓመት በፈት አመለጠ። ትናንት ከኛ ጋር ነበር፤ ዛሬ የለም። የጊዜ ጉዳይ ነው። በጊዜ ላይ ሲፈላሰፍ የቋጠራቸው ስንኞች ስለስብዕናው የሚሰጡት ስዕል አለ።
ምንጭ: ውክፔዲያ
(በተለይ በመለስተኛና በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ)
በሳምራዊት ኅሩይ
የኢትዮጵያ ትምህርት ከፍተኛ የውድቀት ታሪክ በእጅጉ ከደርግ ዘመን ጋር ተያይዞ የመጣ ነው፡፡ ፖለቲካዊ ትርምስ፣ ርዕዮተ ዓለማዊና ፕሮፓጋንዳዊ እመቃ፣ የዘመቻና የጦርነት ጣጣዎች ኅብረተሰቡንና ትምህርቱን አዳሽቀውታል፡፡
በየትም ቦታ ቅድሚያ ይሰጠው የነበረው የፓርቲ፣ የፖለቲካ፣ የፕሮፓጋንዳ፣ የክብረ በዓልና የዘመቻ ሥራ ነበር፡፡ የሚያስመሰግነው፣ የሚያሸልመውና የሚያሾመው ይህ ዓይነቱ ‘አብዮታዊ ሥራ’ ነበር፡፡ ከትምህርቱ አስተዳደር አንስቶ እስከ መምህራን ድረስ በ‹‹አብዮታዊ ግዴታዎች›› መጠመድና ሥራ መፍታት እየበዛ ትምህርቱ ተዝረከረከ፡፡ ሥራ ትጋትና ዋጋ አጥቶ፣ ሥራ ጠሉ ሁሉ ‹‹አብዮታዊ›› እና ‹‹ጓድ›› እየተባለ ጥቅማ ጥቅሙን ሲቀራመትና የታታሪው ገምጋሚና አዛዥ ሲሆን የሥራ ፍቅርና ትጋት ሞተ፡፡ ‹‹አብዮታዊ አስተዋጽኦ››፣ ‹‹ጓድ››ነትና የ‹‹ጓድ›› ዘመድነት ከትምህርት ቤት የማያባርር፣ ልዩ ፈተና የሚያሰጥ፣ ፈተና የሚያሳልፍ፣ ከደንብ ውጪ ለመድገምና ማትሪክን ደጋግሞ በመደበኛነት ለመፈተን የሚያስችል እየሆነ በመምጣቱ የሙያ ሥነ ምግባሩ ተቦዳደሰ፡፡ 
የመምህራን ከሥራ መጓደል የተማሪን ታጉሮ መዋል እያስከተለ፣ የመምህራን የሥራ ስሜትና ሥነ ምግባር መውደቅ የተማሪውን ችሎታ እያደከመ፣ 12ኛ ክፍል ደርሶ የማለፍ ዕድልም ህልም እየሆነ መሄድ ራሱ ተስፋ እያሳጣ የተማሪው የትምህርት ስሜትና ትጋት ይጠፋል፡፡ የወጣት አጥፊነት ይለማል፡፡ የትምህርቱ መፋለስና የይስሙላ መሆን የግምግማና የማለፊያ ሥርዓቱን ያፋልሰዋል፡፡ በአግባቡ ያላስተማረ መምህር በቀላል ፈተና፣ ብዙ ተማሪ ከወደቀም ነጥብ በመጨመር ጉድ መሸፈን ውስጥ ይገባል፡፡ ያልሠራና ተስፋ ያጣ ተማሪም በበኩሉ በኩረጃ፣ በዛቻ፣ በልመናም ሆነ በጥቅም ልውውጥ ማርክ የማግኘት ትግል ውስጥ ይገባል፡፡ ሳይሠሩ ማግኘትና ማለፍ በተስፋፋበት ሁኔታ ውስጥ፣ ‘‘ለፍተህ አግኝ፣ አላስኮርጅም፣ ማርክም አልጨምርም’’ የሚል መምህር ቅራኔና ግጭት ውስጥ ይገባል፡፡ በተማሪ መውደቅ የሚደሰት ተደርጐ ይቆጠራል፡፡ የጥሩ መምህር መመዘኛ ውሉን ይስታል፡፡ የትምህርት ሥርዓቱ ብዙ ተማሪ አሳልፎ ከታች ለሚመጣው ቦታ ለማስለቀቅ ማለፊያውን እያወረደው ሲሄድ መማር የክፍል ቆጠራ ጉዳይ መሆኑ አጠቃላይ ይሆናል፡፡ ከአስተዳደሩ አጐሳቋይነት በተጨማሪ የተማሪው ሥርዓት እየለቀቀና ተተናኳይ እየሆነ መሄድ፣ የመምህራኑን ታጋሽነት፣ ቅንነትና ጨዋነት እየሸረሸረው፣ በመምህራኑም በኩል የሚታየው ብልሽትና ተተናኳሽነት ይበልጥ ተማሪውን እየመረዘ መከባበርና መግባባት ያዳግታል፡፡ በአጠቃላይ አላሻቂው ማኅበራዊ አካባቢ፣ የትምህርት አስተዳደሩ፣ መምህሩና ተማሪው አንዳቸው ሌላቸውን ቁልቁል እየጐተቱ በኢሕአዴግ ዘመንም ይኼው እየተባባሰ ቀጥሎ፣ ዛሬ የምንገኝበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ 
የጥራቱን ጉዳይ እንተወውና ቀድሞ ሁለተኛ ደረጃን አልፎ ወደ ኮሌጅ ለመግባት ጥቂቶች ብቻ የሚችሉበት በር ዛሬ ሰፍቷል፣ ገናም ይሰፋል፡፡ በዚህ በኩል የነበረው ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ተገፏል፡፡ ግን ተማሪ ተስፋ መቁረጥን ፈረካክሶ በስሜትና በትጋት የመማር ለውጥ አላሳየም፡፡ ድህነትና የኑሮ መቃወስ በዚህ ውስጥ የራሱን ድርሻ ያበረክታል፡፡ ይህ እንደታወቀ ሆኖ ከትምህርት ጋር በተያያዙ ሁለት ሥር የሰደዱ ችግሮች ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ የችሎታ ማነስና የትምህርት አካሄድ ችግር፡፡ 
ሀ) የተጠራቀመ የችሎታና የዕውቀት ማነስ
ሀ.1. ከክፍል ደረጃ ወደ ክፍል ደረጃ እየተንከባለለና እየተደራረበ የመጣ የዕውቀትና የልምምድ ማነስ ችግር ተማሪውን ጠፍሮታል፡፡ በዚህም ምክንያት ለየደረጃው የሚሰጠውን ትምህርት ለመሸከም ለማዋሀድ ይቸገራል፡፡ በየጊዜው የሚታየው ከወጣት አጥፊነት ጋር በተያያዘ ምክንያት ቀልጦ መቅረት፣ ማርፈድና ትምህርትን ጥሎ (‘ፎርፎ’) መሄድ ችግሩን ያባብሰዋል፡፡ 20 ቀን የቀረ የሚታገድበት ደንብ ቀርቶ በነበረበት ወቅትም (በኢሕአዴግ ዘመን) መምህሩ ሁሉ ቀሪ መቆጣጠር ትቶ ለፈተና ጊዜ ብቻ የሚመጣው በርክቶ ነበር፡፡ ግማሽ ዓመት ሙሉ ጠፍቶ ሳያሟላ የቀረ ተማሪ ገንዘብ ከፍሎ እየተፈነተ የሚያልፍበት መንገድም ተከፍቶ ነበር፡፡ ዛሬም በብዙ ተማሪዎች ዘንድ ውሎ ከመመለስ በስተቀር ውጤት አመጣሁ ብሎ የመሥራት ብርታትና ጥረት ችግር እንደሆነ ይገኛል፡፡ ሒሳብና ፊዚክስ ከኤድስ ጋር ተመሳስለዋል፡፡ አይገባንም የሚል ሽንፈትም ተንሰራፍቷል፡፡ 
ሀ.2. የእንግሊዝኛ ‹‹ማስተማሪያ›› ቋንቋና ችሎታ 
በሌሎች ትምህርቶች በኩል ያለውን የማስተማር መማር ተግባር ቀስፎ የያዘው ትልቁ ችግር፣ የእንግሊዝኛ ችሎታ ማነስ ነው፡፡ ችግሩ መምህሩንም ተማሪውንም ይመለከታል፡፡
የሚሰጠው የእንግሊዝኛ ትምህርት በእንግሊዝኛ ቋንቋ የመገልገል ክህሎትን ለማስጨበጥ የሚያስችል አይደለም፡፡ ለዚያውም የምንባብ ሐሳብ፣ የቃላት ትርጉምና የዓረፍተ ነገር አሰካክ ገለጻ አገርኛ ቋንቋ ይገባበታል፡፡ 
በሌሎች ትምህርቶች በኩልም መምህሩ የራሱንና ተማሪዎቹን የቋንቋ ችግር አሸንፎ ዕውቀትን ለማድረስ በጉራማይሌ ሲያስተምር ኖሯል፡፡ (ዛሬ የሳተላይት ትምህርት ተጀምሮም ቢሆን የክፍል መምህሩ ከጉራማይሌ አልወጣም፡፡ ወዶ ሳይሆን ለማስረዳት ሲል)
ለተማሪው የሚሰጠው ማስታወሻ (ጭማቂ)፣ መጽሐፉና ፈተናው ግን ሁሌም በእንግሊዝኛ ነው፡፡ (ከአገርኛ ቋንቋ ትምህርት በስተቀር) የሚያነብና የሚያጠናው በማይገባው (በደንብ በማይረዳው) ቋንቋ ይሆናል፡፡ ስለዚህም ልሥራ ያለ ችግሩን የሚወጣው በአብዛኛው በሽምደዳ ነው፡፡ ከዚህ ዝቅ ያለው በፈተና ጊዜ ከሌላው ለመኮረጅ ወይም ማስታወሻ ይዞና ደብተር ገልጦ ለመገልበጥ የሚታገል ነው፡፡ 
ለ. ጤናማ ያልሆነ የትምህርት አካሄድ
ለ.1. በየክፍል ደረጃው የሚሰጠው ትምህርት ውዝፍ ችግርን ሊያቃልልና ሊጠግን ይቅርና ለዚያ ደረጃ የተወሰነውን ትምህርት አጣጥሞ ለማገባደድ በማያስችሉ ችግሮች ውስጥ ተይዞ ቆይቷል፡፡    
ጫጫታ፣ ሹክሹክታ፣ መማሪያ ደብተርንና መጽሐፍን ይዞ አለመምጣት፣ የክፍልና የቤት ሥራ አለመሥራት፣ ለመማር ፍላጐትና ትኩረት ማጣት የትምህርት ሒደት ፈተናዎች ናቸው፡፡ 
ከእነዚህ ጋር ተያይዞ በሚመጡ ጭቅጭቆችና ትንቅንቆች (ቁጣ፣ ስድብ፣ ተንበርከክ/ውጣ፣ ኩርኩም፣ ማጥፊያ ውርወራ፣ ድብድብ፣ ወዘተ) የትምህርት ሥራው ሲበጣጠስ ኖሯል፡፡ 
ከዚህ ባሻገር ተንጠባጥቦ የሚመጣ አርፋጅና ከቀደመ መምህር ጋር ወጥቶ የነበር ተመላሽ ተማሪ፣ በየክፍሉ እየተዞረ የሚነገር ማስታወቂያ፣ ዕርዳታ የማሰባሰብ ቅስቀሳ፣ የቲኬት ሽያጭና ገንዘብ ለቀማ፣ ወዘተ ክፍለ ጊዜን ሲሻሙ የቆዩ ችግሮች ናቸው፡፡ 
ከዕውቀት ማነስና ከፍላጐት ማጣት ጋር የሚዋደደው ጥፋተኛነት በምክር፣ በግብግብ፣ ወደ ቢሮ በመላክም ሆነ ወላጅ በማስመጣት የሚፈታ አልሆነም፡፡ መምህራን ረባሹና ትምህርት ጠሉ የተቀነሰበት ሰላማዊ ክፍል ለማግኘት ሲሉ ቀሪ መቆጣጠርን የተውበት፣ እንዲያውም ቀሪ አላደርግህም ፈተና ሲኖር ብቻ ና ብለው እስከመደራደር የደረሱባቸው ገጠመኞች ተከስተው ያውቃሉ፡፡ 
ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ የትምህርት ቤት አስተዳደር የቀሪ ቁጥጥርን በግቢ ውስጥ ያለ ትርምስን ለማቃለል መሣሪያ አድርጐ ሙጥኝ ያለበትና ስም ጥሪ ዋና ሥራ እስከመምሰል የደረሰበት ጊዜ ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ ባለበት መጥቶ የማያውቀውና ደብተር የለሹ ዱርዬ ሁሉ ይታጨቅና ንትርክ እየናረ አስተማሪ ጥሎ የሚወጣበት፣ ወይም እዚያው ሆኖ የ‹‹ምን አቃጠለኝ›› ሥራ የሚሠራበት አጋጣሚ ሲደጋገም ቆይቷል፡፡
ለ.2. የመምህርና የተማሪ ግንኙነት
የመምህርና ተማሪው ግንኙነት ከተበለሻሸ ብዙ ጊዜው ነው፡፡ አስተማሪው በተማሪ ዘንድ በጥያቄ በማፋጠጥ፣ በማንጓጠጥ፣ በዛቻ፣ ማርክ በመንፈግ፣ ከክፍል በማስወጣት፣ ወላጅ በማስመጣት፣ ቀሪ በመቆጣጠር፣ ወዘተ ጥቃት ሲፈጽም የሚውል ተደርጐ ይታያል፡፡ በአስተማሪውም ዘንድ ሙያውን እያማረረ የሚያስተምር ብዙ ነው፡፡ ወደ ክፍል ሊያስተምሩ መሄድ ወደ ‹‹ትንቅንቅ›› የመሄድ ያህል ሆኖ ቆይቷል፡፡ የክፍልን ፀጥታ ከመቆጣጠሪያ ሁነኛ መሣሪያዎች አንዱ መኮሳተርና ደምን ማስቆጣት ነው፡፡ አንዱን ተለቅ ያለውን የፀጥታ አደፍራሽ በሆነ ምክንያት መምታት ወይም የሚያሸማቅቅ ስድብ መስደብ ተደማጭነትና ተከባሪነት ለማግኘት አገልግሎት ላይ የሚውሉ ዘዴዎች ናቸው፡፡ በሳቂታነት ባህርይ የሚታወቅ መምህር ተማሪ በሚያናግርበት ጊዜ ኩስትርትሩ ወጥቶ ማየት እንግዳ አይደለም፡፡ ለማዋዛት ሲሞከር ከተማሪ በኩል ሊገለጽ የሚችለው ያልታረመ ባህርይ ይህንኑ ሲያበረታታ ኖሯል፡፡ በአጠቃላይ የተማሪና የአስተማሪ ፍቅርና መተሳሰብ ክፉኛ ተዳክሟል፡፡ 
ሐ. ተማሪ ተኮር የትምህርት አሰጣጥ ሥራ ላይ ሊውል አለመቻል 
የተማሪ ተኮር ትምህርት አሰጣጥ ጠቃሚነት አያጠያይቅም፡፡ ነገር ግን ቀደም ብለው በተጠቀሱና በሌሎች ችግሮች ምክንያት ተግባራዊ የማድረግ ጥረቱ ከንቱ ውትወታና ድካም ሆኗል፡፡
የባህል ልሽቀትና የወጣት አጥፊነት ተማሪውን ልሶ ለመጨረስ ጉልበት ማበጀታቸው (በተለይ በከተሞች)፣ ተማሪዎች ላሉበት ደረጃ የተዘጋጀውን ትምህርት ለማዋሀድ (Assimilate) የሚያስችል ቅርስ የሌላቸው መሆኑ፣ ትምህርት በሚቀርብበት ቋንቋ ላይ የችሎታ ችግር ያለባቸው መሆኑና ይህን መሰሉን ጉድለት የሚሞላ ድጋፍ ማጣት ተጋግዘው በግል ንባብ፣ በግልና በቡድን ሥራ የሚካሄድን ትምህርት ውጤታማነት አዳክመውታል፡፡ ከጥቂቶች በስተቀር አብዛኛው ተማሪ ሌሎች ሲሠሩ የሚመለከት፣ ሌሎች የሠሩትን የሚገለብጥና ባልተሳተፈበት የቡድን ሥራ ስሙን የሚያጽፍ ነው፡፡ 
በአንድ ክፍለ ጊዜ ተማሪ ተኮር የትምህርት አሰጣጥ ሊሰጥ የሚችለው ትምህርት በመጠን አነስተኛ መሆን፣ በሌላ በኩል የዓመቱን በርካታ የትምህርት ጭነት የማገባደድ ኃላፊነት ደግሞ ቶሎ ቶሎ ማጉረፍን የሚጠይቅ መሆኑ ሌላው ችግር ነው፡፡ 
በተጨማሪ ከፊል ወይም ሙሉ ክፍለ ጊዜን የሚወስድ ማስታወሻን (ኖትን) በሰሌዳ ላይ መለቅለቅም በራሱ ‘‘ትምህርት’’ ሆኖ ጊዜን ሲሻማ ኖሯል፡፡ በራስ አንብቦ የራስን ማስታወሻ የማዘጋጀት ነገር እንኳን የሁለተኛ ደረጃ የኮሌጅ ተማሪም ችግር ሊሆን በቅቷል፡፡ 
ኖት በመጻፍ ክፍለ ጊዜ መፍጀትና በተለያዩ ጣልቃ ገብ ነገሮች የትምህርት ሒደት መቆራረጥ የሳተላይት ትምህርት በሚሰጥባቸው ትምህርቶችና የተወሰኑ የክፍል ደረጃዎች ላይ የተቃለለ ቢሆንም አጠቃላይ ችግሩ እንዳለ ነው፡፡ የሳተላይት ትምህርትም ቢሆን ለተማሪ ተኮር የትምህርት አሰጣጥ የሚያወላዳ አይደለም፡፡
እንደ መፍትሔ አንዳንድ ነገሮች 
ሀ. ለጤናማ ግንኙነት 
1.መምህራንና ተማሪዎች ታላቅ የልማት ኃይል ናቸው እየተባለ ከተሠለፉበት ሙያ ውጪ በሌሎች ሥራዎች ማሰማራት እየተለመደ መጥቷል፡፡ በነፃ ፈቃደኝነት የሚገባባቸውና የሙያ ግዴታ የሆኑ ተግባራት እየተደበላለቁ ችግር መፍጠራቸው መቆም አለበት፡፡ በትምህርት ቤት ውስጥ ተወዳዳሪ የሌለው የልማት ተግባር በተማሪዎች ትጋት፣ ዕውቀትና ችሎታ ላይ ለውጥ ማምጣት ነው፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከትምህርቱ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ተግባራትም (ለምሳሌ ቤተ መጻሕፍትን ማደራጀት፣ የመጻሕፍትና የገንዘብ ዕርዳታ ማፈላለግ፣ የተጓዳኝ ትምህርት ክበቦችና የውድድር ሥራዎች) መደበኛውን የትምህርት ሥራ በሚጐዳ አካሄድ፣ ማለትም መምህራንና ተማሪዎች ከመደበኛው የትምህርት ገበታ እየተፋቱ የሚከናወኑ ከሆነም እያፈሰሱ መልቀም ይሆናል፡፡ 
2.የትምህርት ቤት አመራር፣ የመምህራንና የተማሪዎች ግንኙነት ዕድሳትን ይሻል፡፡ ‘‘በትምህርት ቤት ውስጥ ዋናው ሰው መምህሩ ነው’’ የሚል መፈክር ለትምህርት ቤቶች እንግዳ አይደለም፡፡ የተግባር ትርጉም ካጣ ግን ቆይቷል፡፡ መምህሩ በሁኔታዎች መዝማዥነት ከአራቂነትና ከቀራፂነት ደረጃ ወርዶ ከተማሪ እኩል ራሱን አስተካክሎ ‘‘የእኔ ወንድም ሥራዬን ልሥራበት ልቀቅልኝ ወይ ልልቀቅልህ’’ ባይ እስከመሆን ደርሷል፡፡ የትምህርት ሥራና የትምህርት ቤቶች ውጤታማነት የመምህራንን የማስተማር ብቃት፣ ፍላጐትና ትጋት በመንከባከብና በማበልፀግ ላይ የቆመ መሆኑ የትምህርት አመራሩም ሥራ ይህንን ማገልገል መሆኑ ተስቷል፡፡ መምህሩን አስተዳደሩ ላንቀጥቅጥ እያለ የሚሠራው ሥራ ውጤት አያስገኝም፡፡ የትምህርት አመራርና መምህሩ እንደ አንድ የሥራ ኃይል ልብ ለልብ ሆነው መንቀሳቀስ መቻላቸው እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህም በስብሰባ ብዛትና በ‘‘ዱላና በካሮት’’ ሥልት በመጥመድ ተጨባጭ አይሆንም፡፡ እስከማስወገድ ሊደርስ የሚችል ዕርምጃ መውሰድ የሚያስፈልግበት ሁኔታ እንደሚኖር ዕውቅ ነው፡፡ ነገር ግን የመቀጣትና የመባረር አደጋን (ፍርኃትን) ሸር አድርጐ መሣሪያ አድርጐ ለመጠቀም መሞከር አጥጋቢ ውጤት አያስገኝም፡፡ ከፍላጐቱ ውጪ መምህሩ ቤተ መጻሕፍት ማዘውተር አለማዘውተሩን በመከታተል መምህሩን አንባቢ ማድረግ እንደማይቻል በተግባር ታይቷል፡፡ ለደካማ ተማሪዎችና ለሴት ተማሪዎች የትርፍ ጊዜ እገዛ መስጠትን የሥራ አፈጻጸም መመዘኛ አድርጐ፣ ለራስሀ ስትል እወቅበት የሚል ሥልትም የረባ ውጤት አላስገኘም፡፡ 
የትምህርት ቤት አስተዳደር ራሱን ከመምህሩ ነጥሎ ከድብድብና ከስድብ የፀዳ የትምህርት አሰጣጥ እንዲኖር ተቆጣጣሪና የተማሪዎችን በደል ሰሚ፣ በመምህራንና በተማሪ መካከል ፈራጅ የመሆን ዓይነት ሚና መያዝ፣ እንዲሁም ፓርቲ ቀረብ ተማሪዎችንና የተማሪ መማክርት አባላትን እንደ መረጃ መጠቀም በሦስቱ ወገኖች መሀል ያለውን ግንኙነት ሲያበላሽ የቆየ ነው፡፡ መቅረትም አለበት፡፡ ተማሪ እንደ ወሬ አቀባይ መታየት የለበትም፡፡ አስተማሪው እንደ ተሳዳቢና ደንፊ ተደርጐ የሚታይበትና የሆነበት ግንኙነት መለወጥ አለበት፡፡ ብልሽቱ ከተስተካከለ መምህሩ በብዙ መንገድ የተማሪውን ችግር የሚጋራ፣ አንዳንዴም ከወላጅ ይበልጥ የተማሪው ጭንቀት አዳማጭና አማካሪ የሚሆን የቅርብ አለኝታ ነው፡፡ ይህንን የመምህሩን ሚና አስተዳደሩም ሆነ የተማሪዎች መማክርት (ካውንስል) በፍፁም አይተኩትም፡፡ ወደዚህ የሚያመጣ የመምህርና የተማሪ ግንኙነት መገንባት አለበት፡፡ በትምህርት አሰጣጥም ሆነ በሌላ ቅሬታ ቢኖር ተማሪው መጀመሪያ መምህሩን ማዋየት መልመድ አለበት፡፡ አስተዳደሩም መምህሩን ዘሎ የመጣ ስሞታ ሲደርሰው በቀጥታ መምህሩ ባለበት ተማሪው ቅሬታውን አውጥቶ እንዲያቃልል፣ ለሌላ ጊዜም ከሁሉ በፊት ወደ መምህሩ መሄድን እንዲገነዘብ ማድረግ ይገባዋል፡፡ ይህ ዝም ብሎ የሚመጣ ሳይሆን በሁሉም በኩል ‘‘እናትህን … ልበላት’’ ‘‘የእንትን ልጅ’’ እየተባባሉ ቡጢና ካራ እየተሰናዘሩ የሚዋልበትን ሁኔታ ለመለወጥ የሚያስችል አዲስ መተማመንና መከባበር ለመፍጠር መትጋትን ይጠይቃል፡፡  
3.በሌላ በኩል የመምህሩ የሥራ ውጤታማነት መለኪያ የሚሆነው ሆኖ አብዛኛውን ከ75 በመቶ ያላነሰ ነጥብ ቀጥታ በተማሪዎች ላይ የሚያስከትለው የችሎታና የባህርይ ለውጥን የሚመለከት ሊሆን ይገባዋል፡፡ መምህሩ ከፍርኃት ነፃ ሆኖ የሚሠራበት ሁኔታ መፈጠር (በግላዊ ጥላቻ ወይም በፖለቲካ አመለካከቱ ምክንያት አድልኦና ጥቃት ሊደርስበት የማይችል መሆኑን በተግባር የሚያሳምን አሠራር መዘርጋት) ይኖርበታል፡፡ የትምህርት ቤቱ አመራር ከተወሰነ የፖለቲካ ቡድን አባላት ወይም ሸሪኮች ጋር ልዩ ቅርበት መፍጠር ወይም ግልጽ ባልሆነ መንገድ ሰዎችን መርጦ ከማስጠጋት መራቅ መቻል አለበት፡፡ የመምህራንን ትብብር የሚጠይቅ ሥራ ሲገጥመው በግልጽ መጠየቅንና ችግሮችን በማሳሰቢያ፣ በማስጠንቀቂያና በቅጣት ወረቀቶች ለመፍታት ከመሞከር በበለጠ የቅርብ ውይይት ማድረግን መልመድ ያስፈልገዋል፡፡    
4.ከመምህራን ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ለመሥራት የሚያስችል ሁኔታና ግንኙነት ከተፈጠረ ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት ቀላል ይሆናል፡፡ 
ረብሻንና አልማጭነትን አሳፋሪ ማድረግ ይቻላል፡፡ 
በመግቢያና በእረፍት ሰዓት እየጐተጐቱና እያባረሩ የማስገባትን ልምድ ማስቀረት ይቻላል፡፡
በክፍል ውስጥ ሥራ ከተጀመረ በኋላ ማንኳኳት የማይኖርበትን፣ በሕመም ከቢሮ ጋር በተያያዘ ጉዳይ ወይም በትምህርት ምክንያት ካልሆነ በቀር ተማሪ በግቢ ውስጥ የማይንቀዋለልበትን ሁኔታ የሁልጊዜም ማድረግ ይቻላል፡፡
መምህሩ በፈተና ላይ ነፃ ለቅቆ እንዲኮረጅ ለማድረግ የማይደፍርበትን ጨዋነት ማዳበር ይቻላል፡፡ 
ተማሪው ለቀጣዩ ደረጃ የሚያበቃ ዕውቀት መጨበጡ በተከታታይ ምዘናና ድጋፍ በአግባቡ ተረጋግጦ እንዲያልፍ ማድረግ ይቻላል፡፡
የመምህራን በሙሉ ስሜት ለጐበዞችም ሆነ ለደካሞች እገዛ ማድረግ ተጨባጭ መሆን ይችላል፡፡
ከመላው ተማሪ ጋር በመሆን የአጥፊነት ዝንባሌዎችና ባህሎች በትምህርት ቤት ውስጥ ከመቆጣጠር አልፎ ማረም ይቻላል፡፡
ለ. የእንግሊዝኛ ችሎታን ለማሻሻል 
በአገራችን ያለው የእንግሊዝኛ ትምህርት ችግር ከሁሉም በላይ በትምህርት አሰጣጡ ላይ ያመዘነ ነው፡፡ ቋንቋን የመማር ነገር በቋንቋው መገልገል ነው፡፡ በቋንቋ በመገልገል ረገድ ትልቁና የመጀመሪያውን ደረጃ የሚይዘው መናገር ነው፡፡ የእኛ አገር ትምህርት ደግሞ የተገላቢጦሽ ተማሪው በአብዛኛው አዳማጭ አስተማሪው ተናጋሪ የሆነበት ነው፡፡ በእንግሊዝኛ በኩል ያለብንን ችግር ለማስወገድ ይህንን በተቃራኒው እንዲገለበጥ ማድረግ ነው፡፡ 
የ ‘do/does’ ዓይነት ልብ እያወቃቸው አፍ የሚሳሳታቸውን ሰዋሰዎች ከሳምንት ባልበለጠ የጥያቄና መልስ የቃል ልምምድ ተማሪዎች ሊለምዷቸው ይችላሉ፡፡ “If I were … I wish …” ከተባለ የሚከተለው ሐረግ የዚህ ዓይነት ቅንብር በንግግር መጠቀሚያ በማድረግ ሊያከትም ይችላል፡፡ በዚህ መልክ በተለያዩ ሁኔታዎች ላይ የተመሠረቱ ጭውውቶችን አጥንቶ በመለማመድ ልዩ ልዩ የአጠያየቅና የአመላለስ ሥልቶችን፣ የፍላጐት፣ የምርጫ፣ የቁጭት፣ የምኞት፣ የአድናቆት፣ የግርምት፣ የማማከር፣ ወዘተ መግለጫዎችን የተመለከቱ መሠረታዊ መግባቢያዎችን በአጭር ጊዜ መጨበጥ ይቻላል፡፡
በአንደኛ ደረጃ የሚሰጥን የእንግሊዝኛ ትምህርት በዚህ መስመር ውስጥ ማስገባት ያሻል፡፡ እታች “Show me your nose. This is my …” በሚሉ ሥልቶች ዙሪያ መሽከርከር፣ “I wish … I had better … can I … not only … but also” የሚሉ ዓይነት ሥልቶችን ለመጠቀም ደግሞ ከፍተኛ ክፍል ውስጥ መግባት የሚል አመለካከት መቅረት አለበት፡፡ ታዳጊዎችም እንደ ትልልቆች ምኞትን፣ መገረምን፣ ደስታን፣ ወዘተ ስለወደፊቱ፣ ስላለፈውና ሰርክ ስለሚያደርጉት ሁሉ ይገልጻሉና በዕድሜያቸው ደረጃ መግለጽ የሚሹትን መጥኖ ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ 
ተማሪዎች በእንግሊዝኛ ትንሽ ያህል ለመነጋገር የሚያስችል ስንቅ ከያዙ ችሎታቸውን በብዙ ለማዳበር መፈለጋቸው አይቀርም፡፡ የእንግሊዝኛ ዓለም አቀፍ ቋንቋነት፣ በኢትዮጵያ ትምህርት ውስጥ ያለው የመማሪያ ቦታና የአዋቂነት ምልክትነቱ ያበረታታቸዋል፡፡ አንድ ተማሪ በእንግሊዝኛ ሊናገር ሲሞክር ጉረኛ እያሉ የማሸማቀቅ ድርጊት በአመዛኙ በራስ አለማወቅ ከማፈር የሚመጣ ነውና ብዙው ተማሪ የማያሳፍር ዕውቀት እያገኘ ሲሄድ አሽሟጣጭም ይታጣል፡፡ ትምህርት በእንግሊዝኛ አማካይነት የሚሰጥበት የክፍል ደረጃ ላይ ሲገባም ቅጥአምባር አይጠፋም፡፡
የተማሪዎች የክፍል ውስጥ ብዛት እንደ ችግር መነሳቱ አይቀርም፡፡ ይሁን እንጂ እንግሊዝኛን ማወቅ የሁሉም ችግር እንደመሆኑ የተማሪውን ስሜት መያዝ እስከተቻለ ድረስ እንኳን በመማሪያ ክፍል በአዳራሽም ውስጥ ውጤታማ ሥራ መሥራት ይቻላል፡፡
ተማሪዎችን በአንድ ላይ እያስጮሁ በቃል መለማመድ አንድ አማራጭ ነው፡፡ በቡድን መድቦ የጭውውት ድርሻ እየተለዋወጡ አጥንተው እንዲመጡና በክፍል ውስጥ እያስከወኑ ነጥብ መስጠት፣ በተወሰነ ረድፍ ያሉ ተማሪዎችን እንደ አንድ ሰው አንድ ድርሻ እንዲወስዱ፣ ቀሪው ረድፍ ደግሞ ሌላውን ድርሻ ይዘው እንዲቀባበሉ ማድረግም ሌላ መንገድ ነው፡፡ በቀጣይነት በተላመዷቸው የዓረፍተ ነገር ሥልቶች የየራሳቸውን ጭውውት በቡድን አዘጋጅተውና አጥንተው መጥተው እንዲጫወቱ ማድረግና ነጥብ መያዝ ይቻላል፡፡ በሚጥሩት ተማሪዎች ላይ የሚታየው ለውጥና ነጥብ መሰጠቱ ቸልተኞቹንም እያነቃቸው ይሄዳል፡፡
ሐ. በሌሎች ትምህርቶች ያለ የዕውቀት ጉድለት ስለማካካስ
1.በመምህራን፣ በአስተዳደርና በተማሪዎች መካከል ያለው ግንኙነት መስተካከል ከቻለ የማይገፋ ዳገት አይኖርም፡፡ ካለፉ የክፍል ደረጃዎች እየተንከባለለ የመጣ የዕውቀት ማነስን በግምገማ ለይቶ አውቆ አስፈላጊውን ማካካሻ እንደ ሁኔታው መቀየስ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ርዕሰ ትምህርቶችን ለየቡድኑ ከፋፍሎ ቡድኖች በደንብ ተዘጋጅተውበት በልዩ ክፍለ ጊዜ እርስ በርስ እንዲማማሩበት ማድረግ፡፡ 
2.የዕውቀት መጉደል የሚመጣው ከዓመት ዓመት ያለውን ትምህርት ሳይማሩ በመቅረት ብቻ አይደለም፡፡ የመማሪያ ሥልቱ ከምልከታና ከሙከራ መራቁና የትምህርት ይዘትን የመመጠን ችግር የጉድለት መንስዔም ይሆናል፡፡ ይህን መሰሉ ችግር ከታች ጀምሮ ያለ ነው፡፡ በአንድ ሕፃን ልጅ ጉንጭ ውስጥ መዓት ጥሬ ከትቶ ከማስጨነቅ የማይለይ ትምህርት፣ በአራትና በአምስተኛ ክፍል ደረጃ ይሰጣል፡፡ የአምስተኛ ክፍል ተማሪ የአፍሪካ ተራሮችን መገኛና ከፍታ፣ የአፍሪካ ረግረጎችን፣ የአፍሪካ አገሮች ሕዝብ ቁጥርን (በገጠር፣ በከተማ፣ በዕድሜ በፆታ) መማር አለበት? 
ከክፍል ክፍል የሚሰጡት ትምህርቶች ደረጃ በደረጃ አንዱ በሌላው ላይ እየተገነባ ተማሪውንም መገንባት ይኖርበታል፡፡ የዚህ ዓይነት አወቃቀር የሌለውና ፈተና ስለሚመጣ ብቻ ተጠንቶ ከፈተና በኋላ ወዲያው የሚረሳ ትምህርት ከትምህርት አይቆጠርም፡፡ መረሳት የሌለበት ትምህርት ከተማሪው የዕውቀት ቅርስ ውስጥ ሊቆይ በሚችልበት አኳኋን መተላለፍ፣ በተለያየ የጥልቀት ደረጃ መመላለስና መገንባት ይኖርበታል፡፡ 
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡   
የአገሪቱ የግብይት ሥርዓት ሁሌም የሚተች ነው፡፡ ይሻሻላል ተብሎ ሲጠበቅ ብሶበት ይገኛል፡፡ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ያሉ ተዋንያኖች ከእንከን ፀድተው አያውቁም፡፡
ጥቂት የማይባሉ ነጋዴዎች ከሸማቾች ሮሮ አምልጠው ያውቃሉ ተብሎ አይታሰብም፡፡ የንግድ ሥርዓታቸው ሚዛናዊ አይደለም፡፡ የራስን ጥቅም ያስቀድማሉ፡፡ በሸማቾች ሲረገሙ መስማትም የተለመደ ነው፡፡ ይህ አብዛኛውን የንግዱ ኅብረተሰብ የሚገልጽ ነው ባይባልም፣ ጥቂት የማይባሉ ነጋዴዎች መገለጫ ሊሆን እንደሚችል ግን ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ 
የእስከዛሬውን ትተን ሰሞኑን ብዙዎቻችንን ያስገረመን፤ እንደውም ያበሳጨንን ድርጊት በአስረጅነት መግለጽ ይቻላል፡፡ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን እንደተሰማው መንግሥት ከሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ ለመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ የመጨመሩን መረጃ ተከትሎ እየፈጸመው ነው የተባለው ድርጊት ነው፡፡ ነጋዴዎቻችንን ያስገረመን ብቻ ሳይሆን መች ይሆን እንዲህ ካለው ተግባር ፀድተው ሸማቾችን በአግባቡ የሚያስተናግዱት? ብለን አሁንም እንድንጠይቅ የሚያደርግ ነው፡፡
ደመወዝ ሊጨመር ነው የሚለውን ወሬ የሰሙ አንዳንድ ነጋዴዎች ወዲያው የዋጋ ለውጥ አደረጉ፡፡ ዋጋ ጨመሩ፡፡ ነገሩ ሠርግና ምላሽ ሆነላቸውም ብንል ማጋነን አይሆንም፡፡ ደመወዝ ከተጨመረ እኛም ዋጋ መጨመር አለብን የሚለው ስግብግብ ስሜትቸው ፈጥጦ ወጣና ሸማቹን ምስቅልቅል ስሜት ውስጥ ከተቱት፡፡ በደመወዝ ጭማሪው ሊደሰት የሚገባውን የኅብረተሰብ ክፍል ከወዲሁ አሸማቀቁት፡፡ ምን ዋጋ አለው ብሎ ከንፈሩን እንዲመጥ አስገደዱት፡፡ 
ይህ አሳዛኝ ድርጊት ነው፡፡ ገና ለገና ደመወዝ ሊጨመር ነው ተብሎ ወሬው እንደተሰማ ለዋጋ ጭማሪ መንቀልቀል ጤናማ የንግድ ባህሪ አይደለም፡፡ ሆኖም አደረጉት፡፡ 
ከሁሉም በላይ አስገራሚ የሚሆነው ደግሞ ደመወዝ ተጨምሮልሃል የተባለው ሠራተኛ የተጨመረለት ደመወዝ ገና ኪሱ ሳይገባና ምን ያህል እንደተጨመረለት እንኳን ሳይታወቅ ይህ ወሬ መስማቱ ነው፡፡ የቱንም ያህል የደመወዝ ጭማሪ እንደተደረገ ቢታወቅ እንኳ አሁን ባለው ደረጃ የዋጋ ጭማሪ ማድረጉ ፈጽሞ ትክክል አይደለም፡፡ መስገብገብና ለአገልግሎታቸው ከፍሎ ለሚጠቀም ዜጋቸው የሚገባም አይደለም፡፡ 
ደመወዝ ተጨመረ መባሉ ብቻ በፍጹም ዋጋ ሊያስጨምር የሚያስችል ምክንያት አይደለም፡፡ መንግሥትም እንደገለጸው የሚደረገው የደመወዝ ጭማሪ የዋጋ ጭማሪን ሊያስከትል ወይም በኢኮኖሚ ውስጥ ተፅዕኖ ሊፈጥር በሚችል ደረጃ አይደለም፡፡ 
ይህ ከሆነ ደግሞ ለዋጋ ጭማሪ የሸሚዛቸውን እጅጌ ሰብስበው ሸማቹን ለመንጠቅ የተዘጋጁ ነጋዴዎችን ድርጊት በፍጹም ዝም ሊባል የማይቻል መሆኑን ነው፡፡ የሚያመላክተን የደመወዝ ጭማሪው ተደርጓል የሚለው መረጃ ከተሰማ በኋላ አንድ የማውቃቸው የመንግሥት ሠራተኛ ‹‹እንኳን ደስ አልዎት ደመወዝ ሊጨመርልዎ ነው፤›› ስላቸው፣ ‹‹እንኳን አብሮ ደስ አለን›› ሊሉኝ አልፈቀዱም፡፡ ምክንያቱን ያወኩት ቆየት ብሎ ነው፡፡ ከእርሳቸው እንደተረዳሁትም ከደመወዝ ጭማሪው ጐን ለጐን በተለያዩ ሸቀጦች ላይ ተጨመረ የተባለው ዋጋ ስሜታቸውን ነክቷል፡፡ 
የንዴታቸው ብዛት ሌላው ቢቀር ምነው ደመወዝ እስክንቀበል እንኳን ቢታገሱን ብለው ደመወዝ ጭማሪውና ነጋዴዎች ዋጋ እየጨመሩ ነው የተባለው ወሬ ተደበላልቀው ደስታቸውን በአግባቡ እንኳን ሊያጣጥሙ ያለመቻላቸውን ልረዳ ችያለሁ፡፡ 
በሌላ በኩል ግን መንግሥት ሁኔታውን በመከታተል ላይ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ዋጋ የሚጨምሩ ነጋዴዎችንም እቀጣለሁ ብሏል፡፡ ግን እንዴት? የሚለው ጥያቄ በአግባቡ ካልተመለሰ ሸማቹ ባልተገባ ሁኔታ ተጎጂ ሊሆን ነው፡፡ 
በተናጠል ስናየው መንግሥት ደመወዝ የሚጨምርላቸው ዜጎች ቁጥር እጅግ አነስተኛ ቢሆንም፣ ነጋዴዎቹ የፈጠሩት አላስፈላጊ ተግባር ግን የሚጎዳው ሁሉንም ነው፡፡ ምክንያቱም አንተ ደመወዝ ስለተጨመረልህ የምትከፍለው ይህንን ያህል ነው፡፡ አንተ ደግሞ ካልተጨመረልህ ዋጋ ይቀነስልሃል አይባልምና የችግሩ ሰለባ የሚሆነው ሁሉም ሸማች በመሆኑ በሁሉም ዜጎች ላይ የሚያሳርፈው ተፅዕኖ የከበደ ይሆናል፡፡ 
በነገራችን ላይ በሸቀጦችና በአገልግሎት ላይ ብቻ ሳይሆን የዋጋ ጭማሪ የተደረገው የቤት ኪራይ ዋጋ ላይ ሳይቀር እንጨምራለን ያሉም መኖራቸውን መዘንጋት የለበትም፡፡ ከሦስት ቀናት በፊት ቤት አከራያቸው ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ 300 ብር ጨምሬያለሁ የሚል መልዕክት የደረሳቸው የአንድ ቤተሰብ አባላት በንዴት ምነው ደመወዝ ጭማሪው በቀረ እስከማለት ደርሰዋል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ነገ ተነገወዲያ በዚሁ በደመወዝ ጭማሪ ሰበብ በሁሉም አገልግሎቶች ላይ ዋጋ እንዲጨመር የሚገፋፋ ጭምር ስለሚሆን መንግሥት ጉዳዩን በልዩ ትኩረት ሊመለከተው ይገባል፡፡ ዕርምጃውም ፈጣን ካልሆነ ደመወዝ የተጨመረላቸው ሠራተኞች ጭማሪውን በአግባቡ እንዳያጣጥሙ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ሌሎችም የኅብረተሰብ ክፍሎች በዋጋ ጭማሪው እንዳይጎዱ እንዲሁም ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሊፈጠሩ የሚችሉ አደጋዎችን ለመከላከል መቀልጠፍ ያስፈልጋል፡፡