POWr Social Media Icons

Monday, June 16, 2014

... በአገሪቱ ያልተማከለና የተመጣጠነ የከተሞች ዕድገትን ለማረጋገጥ ዘጠኝ የከተማ ዕድገት መሰላሎችና ዞኖች በአዲስ አበባ፣ በመቐለ፣ በባህር ዳር፣ በነቀምቴ፣ በወልዲያ/ኰምቦልቻ፣ በጅማ፣ በድሬዳዋ፣ በሐዋሳና በጐዴ እንደሚፈጠሩና የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ስኬት ለእነዚህ ስምንት ከተሞች እንደ መልካም ተሞክሮም እንደሚያገለግል መረጃው ያመለክታል፡፡...

የሃዋሳ ከተማ የወደፊት እጣፋንታ ከወዲሁ ለመገመት እንዲያስችሎት  የሚከተለውን ጽሑፍ ያንቡ፦

የተቀናጀው ማስተር ፕላን በልማትና በፖለቲካዊ ጥያቄዎች መካከል

ባለፈው ሳምንት ግንቦት 30 ቀን 2006 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም ጥናት ማዕከልና የደቡብ አፍሪካው ዌስተርን ኬፕ ዩኒቨርሲቲ በመተባበር ያዘጋጁት ሴሚናር በከተሞች አስተዳደር ላይ ያተኮረ ነበር፡፡
የሴሚናሩ ተሳታፊዎች ከምሁራን፣ ከመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ከኦሮሚያ፣ ከአዲስ አበባና ከፌዴራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት፣ ከተለያዩ የጥናትና ምርምር ተቋማት ተወካዮች፣ ከፌዴራሊዝም ተማሪዎችና ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የተውጣጡ ነበሩ፡፡
ከላይ የተገለጸው ሴሚናር ከመካሄዱ ከሁለት ቀናት በፊት የአዲስ አበባና በአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ለውጭ ሚዲያዎችና በእንግሊዝኛ ቋንቋ ለሚሠሩ ሚዲያዎች በማስተር ፕላኑ የዝግጅት ሒደት ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጠ ሲሆን፣ በጽሕፈት ቤቱ ዳይሬክተር በአቶ ማቴዎስ አስፋው የተመራው ቡድን አዲስ አበባንና ኦሮሚያን የወከሉ ኃላፊዎችን አካቶ ለተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ሞክሯል፡፡
በሁለቱ ቀናት ዝግጅቶች ትኩረት የሳበው አጀንዳ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ክልል ግንኙነት ነው፡፡ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ማስተር ፕላኑ የልማት ጥያቄዎችን ብቻ ሳይሆን ሕገ መንግሥታዊና ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን ጭምር እንደመለሰ አብራርቷል፡፡ ሥራዎቻቸውን ያቀረቡ ምሁራን ግን የማስተር ፕላኑ ረቂቅ ቴክኒካዊ የሆኑ የአርክቴክቸር ጉዳዮች ላይ በማተኮሩ አወዛጋቢ ለሆኑ ሕገ መንግሥታዊና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ምላሽ አለመስጠቱን ተችተዋል፡፡
ተመሳሳይ ጥያቄዎች 
በሁለቱም ፕሮግራሞች ላይ የተገኙ ተሳታፊዎች ጥያቄዎች ተመሳሳይ ነበሩ፡፡ አዲስ አበባ ወደ ኦሮሚያ ክልል ትስፋፋለች ወይ? የጋራ ማስተር ፕላኑ በኦሮሚያ ልዩ ዞን ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተፅዕኖ በተለይም ከቋንቋ፣ ከባህልና ከማንነት ጋር የተያያዙትን ተፅዕኖዎች እንዴት መቋቋም ይቻላል? በማስተር ፕላኑ የዝግጅት ሒደት የኦሮሚያና የልዩ ዞኑ ተሳትፎ ምን ያህል እውን ሆኗል? ማስተር ፕላኑ ተፅዕኖ ይፈጥርበታል በተባለው አካባቢ ከሚኖሩ ነዋሪዎች ጋር ቀጥተኛ ውይይት ለምን አልተደረገም? ለልማት በሚደረገው እንቅስቃሴ የሚፈናቀሉ የኦሮሞ ገበሬዎች በቂ የካሳ ክፍያ እንዲያገኙና ኑሮአቸው በዘላቂነት እንዲቀየር ምን እየተሠራ ነው? በማስተር ፕላኑ ዝግጅትና አተገባበር ላይ የፌዴራል መንግሥቱ ሚና ምንድን ነው? ማስተር ፕላኑ የሚጠይቀውን ከፍተኛ ፋይናንስ ለማግኘት የኦሮሚያ ልዩ ዞን ስለሚቸገር አዲስ አበባ የገንዘብ አቅምን በመጠቀም ተፅዕኖ አትፈጥርም ወይ? የኦሮሚያ ልዩ ጥቅምን ጨምሮ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡ ድንጋጌዎች ከማስተር ፕላኑ ጋር ያላቸው ግንኙነት ለምን በግልጽ አልተቀመጠም? በማስተር ፕላኑ ላይ የኦሕዴድ አመራር አንድ አቋም አለው ወይ? የሚሉት ጥያቄዎች ከሞላ ጐደል በተሳታፊዎች የተነሱ ነበሩ፡፡ 
እነዚህ ጥያቄዎች ስለ ማስተር ፕላኑ መሰማት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ አካላት ሲቀርቡና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በአገር ውስጥና በውጭ አገር ሲያነጋግሩ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ለጥያቄዎቹ አጥጋቢ መልስ ባለመስጠቱ ለሰዎች ሕይወት መጥፋት አስተዋጽኦ አድርጓል የሚባለው መንግሥት፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስለማስተር ፕላኑ ዝርዝር መረጃዎችን በአግባቡ በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡ 
በሁለቱ ፕሮግራሞች ላይ የተሳተፉት የመንግሥት ተወካዮች ከዚሁ የቅርብ ጊዜ ትኩረት ጋር በተጣጣመ መንገድ የማስተር ፕላኑ ረቂቅ ስላለበት ወቅታዊ ሁኔታና ስለያዛቸው ዝርዝር ጉዳዮች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በተለይ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ማቴዎስ አስፋው አስቀድሞ የማስተር ፕላኑን ዓላማ ሲያብራሩ፣ ለሚቀርብላቸው ሕገ መንግሥታዊና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘት የሚቻለው ከፖለቲከኞች ነው በሚል ይዘሉ የነበረ ቢሆንም፣ በዚህኛው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ግን በሙሉ የራስ መተማመን ለጥያቄዎቹ ምላሽ ሲሰጡ ተስተውለዋል፡፡ ከከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የመጡትና የመንግሥትን የከተሞች አስተዳደር ፖሊሲ በሴሚናሩ ላይ ያብራሩት አቶ አቡዬ አንለይ በበኩላቸው፣ ማስተር ፕላኑ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ለማሳካት ለከተሞች የተሰጠውን ሚና የሚያሳይ በመሆኑ፣ ከሕገ መንግሥታዊና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ባሻገር የዜጐችን ሕይወት በአፋጣኝ ለመቀየር ከሚደረገው ጥረት ጋር ማየት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡
መንግሥት አቋሙን አልቀየረም
የአዲስ አበባ ስፋት 54,000 ሔክታር መሆኑ የተወሰነው በደርግ ጊዜ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ማቴዎስ፣ አሁን ሲለካ ግን የአዲስ አበባ ስፋት 52,000 ሔክታር መሆኑን እንደተደረሰበት አስታውቀዋል፡፡ ስለዚህም አዲስ አበባ እንኳን ወደ ኦሮሚያ ክልል ልትስፋፋ ኢሕአዴግ ከተረከባት በኋላ እንኳን አዲስ አበባ አሁን በ2,000 ሔክታር ያነሰች መሆኗን አቶ ማቴዎስ ይከራከራሉ፡፡ 
አዲስ አበባ ከኦሮሚያ ልዩ ዞን ጋር በጋራ ለመሥራት መሞከሯ ብዙ ጥያቄዎችን እንዳስነሳ ግንዛቤው እንዳላቸው የጠቆሙት አቶ ማቴዎስ፣ ይህ ተነሳሽነት የተወሰደው በአንዳንድ ወገኖች እንደሚቀርበው አዲስ አበባ ያለባትን የተጨማሪ መሬት ጥያቄ ከኦሮሚያ ልዩ ዞን በመውሰድ ለመመለስ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡ ከዚህ ቀደም አዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን በተናጠል ያወጡት ማስተር ፕላን አንዳቸው የሌላቸውን ተጨባጭ ሁኔታ ግምት ውስጥ ባለማስገባታቸው ችግሮች መፈጠራቸውን ያመለከቱት አቶ ማቴዎስ፣ ለአብነትም የኢንዱስትሪ ፍሳሾች፣ የወንዞችና የአካባቢ ብክለት ችግሮች በተለይም በኦሮሚያ ልዩ ዞን ላይ መፍጠራቸውን ጠቅሰዋል፡፡ አንዳቸው ለመኖሪያ ቤት በሰጡት ቦታ ኩታ ገጠምና አጐራባች ላይ ኢንዱስትሪ እንዲመሠረት ሌላኛው ሲወስንም ከፍተኛ ችግሮች ተፈጥረው እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ እንደ አቶ ማቴዎስ ገለጻ ሁለቱ አካላት በጋራ በመሥራት ማስተር ፕላናቸውን ለማቀናጀት ነሐሴ 14 ቀን 2004 ዓ.ም. በሒልተን ሆቴል በተደረገ ስብሰባ የወሰኑት እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ነው፡፡
ማስተር ፕላኑ አሁንም በረቂቅ ደረጃ እንዳለ የጠቆሙት አቶ ማቴዎስ በመጀመሪያው ረቂቅ ላይ ግንቦት 2005 ዓ.ም. ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ ከዞንና ከወረዳ ምክር ቤት ተወካዮች ጋር ውይይት መደረጉን አመልክተዋል፡፡ በሰኔ 2005 ዓ.ም. ደግሞ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጋር ለሁለተኛ ጊዜ በገልማ አባ ገዳ አዳራሽ (አዳማ) ውይይት መደረጉን ገልጸዋል፡፡ በአዲስ አበባ በአሥሩም ክፍላተ ከተሞች በረቂቁ ላይ ከሕዝቡ ጋር ውይይት ቢካሄድም፣ በኦሮሚያ ውስጥ ከሚመለከታቸው ነዋሪዎች ጋር ውይይት ለማካሄድ በዝግጅት ላይ እያሉ ግጭቶች መፈጠራቸውን አመልክተዋል፡፡ በቀጣይ ጊዜያት ውይይቱን በኦሮሚያ ክልል እንደሚቀጥሉም አቶ ማቴዎስ አስታውቀዋል፡፡ 
በአዲስ አበባ የቤቶች ልማት የሚካሄደው በኦሮሚያ አጐራባች አካባቢ በመሆኑ በቀጣይ አዲስ አበባ ቤቶች የምትገነባው ወደ ኦሮሚያ ድንበር ተሻግራ ነው በሚል የሚቀርበው ቅሬታም መሠረተ ቢስ እንደሆነ አቶ ማቴዎስ ጠቁመዋል፡፡ የ10/90፣ 20/80 እና 40/60 የቤቶች ግንባታ የሚካሄደው መሀል አዲስ አበባን በማፍረስ መሆኑንም እንደማስረጃ አቅርበዋል፡፡ ማስተር ፕላኑ የቤቶች ልማት፣ የመንገድ ግንባታና የቀላል ባቡር ፕሮጀክቶችን አቀናጅቶ መያዙንም ገልጸዋል፡፡ 
በሕግ የተቀመጠው የአዲስ አበባና የኦሮሚያ መብት በማስተር ፕላኑ በምንም መንገድ እንደማይነካ ከፍተኛ አጽንኦት ሰጥተው የገለጹት አቶ ማቴዎስ በመንገድ፣ በውኃ፣ በመብራትና ማኅበራዊ አገልግሎቶች አዲስ አበባ ከኦሮሚያ ጋር መተሳሰሯ ግን እውነት መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በማስተር ፕላኑ የተዘረዘሩ ፕሮጀክቶችን ወጪ የመሸፈን ጥያቄ በሁለቱም አስተዳደሮች በተናጠል ሊታይ የሚችልበት ዕድል ያለ ቢሆንም፣ የጋራ ፕሮጀክቶችን በጋራ እንደሚሸፍኑ ለዚህም የፌዴራል መንግሥት ድጋፍ የሚያደርግባቸው ሁኔታዎች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡ 
ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ጋር አብራ በመሥራቷ የቋንቋ አጠቃቀምን ጨምሮ የማንነት ጥያቄው ተፅዕኖ ይፈጥርባታል የሚለውንም ቅሬታ አቶ ማቴዎስ አጣጥለውታል፡፡ ልዩ ዞኑ የሚከተለው የቋንቋ አጠቃቀም ፖሊሲ ማንነትንና ባህልን የመጠበቅ ሁኔታ በኦሮሚያ ክልል ሕገ መንግሥትና በሌሎች ሕጐች በተቀመጠው ሁኔታ እንደሚፈጸም ያስታወሱት አቶ ማቴዎስ፣ ሁለት የተለያዩ ባህሎች ያሏቸው አካላት አንዳቸው በሌላኛው ላይ የሚኖራቸው ተፅዕኖ ግን ማስተር ፕላኑ ባይኖርም ሊወገድ እንደማይችል አስረድተዋል፡፡ ከተሜነትና የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት የሚያመጣውን ተፅዕኖ መቋቋሚያ መንገዶችን መፍጠር እንደሚያስፈልግም መክረዋል፡፡ 
አርሶ አደሮች ሲፈናቀሉ የሚሰጠው ካሳ አነስተኛ ስለመሆኑ የተጠየቁት አቶ ማቴዎስ፣ ሥጋቱ ትክክለኛ እንደሆነ አምነው የካሳው አነስተኛ መሆን ብቻ ሳይሆን የገበሬዎቹ ቀጣይ ሕይወትና የከተሜነት ሕይወትን እንዲላመዱ የማድረግ ጥረት ከዚህ በፊት በዕቅድ ያልተያዘ እንደነበረ አመልክተዋል፡፡ ማስተር ፕላኑ የከተማና ገጠር ትስስር ላይ አተኩሮ የሚሠራ በመሆኑ እነዚህ ችግሮች እንደሚቀረፉም ያላቸውን ተስፋ አቶ ማቴዎስ ገልጸዋል፡፡
አቶ ማቴዎስ ከሚመሩት ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው ከሆነ፣ ማስተር ፕላኑ የአዲስ አባባንና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ነዋሪዎችን ሕይወት ለመለወጥ እንደ ትልቅ መሣሪያ የሚያገለግል ሲሆን፣ የአካባቢው የተመጣጠነ ዕድገት እ.ኤ.አ. በ2025 በአፍሪካ ካሉ ምርጥ አሥር የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ውስጥ አንዱ እንደሚያደርገው፣ እ.ኤ.አ. በ2040 ደግሞ ከአምስቱ ምርጥ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች አንዱ ለመሆንና ዓለም ዋንጫንና ኦሎምፒክን ለማዘጋጀት ዝግጁ እንደሚያደርገው ያመለክታል፡፡ በአገሪቱ ያልተማከለና የተመጣጠነ የከተሞች ዕድገትን ለማረጋገጥ ዘጠኝ የከተማ ዕድገት መሰላሎችና ዞኖች በአዲስ አበባ፣ በመቐለ፣ በባህር ዳር፣ በነቀምቴ፣ በወልዲያ/ኰምቦልቻ፣ በጅማ፣ በድሬዳዋ፣ በሐዋሳና በጐዴ እንደሚፈጠሩና የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ስኬት ለእነዚህ ስምንት ከተሞች እንደ መልካም ተሞክሮም እንደሚያገለግል መረጃው ያመለክታል፡፡
አቶ አቡዬ አንለይ በበኩላቸው የከተማ ልማት ፖሊሲ በ1997 ዓ.ም. በሚኒስትሮች ምክር ቤት መፅደቁን ጠቁመው፣ በአሁኑ ጊዜ ‹የኢትዮጵያ ከተሞች ፕሮስፔሪቲ ኢኒሼቲቭ› በሚል መጠሪያ አረንጓዴ፣ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋሙና በሚገባ ሁኔታ የሚተዳደሩ ከተሞችን ለመፍጠር እንደ መመርያ እያገለገለ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ፖሊሲው ከተሞች የገጠር ልማትን እንዲያፋጥኑ ለማድረግ የገበያ፣ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትና የኢንዱስትሪዎች ማዕከላት ሆነው የሚያገለግሉ ከተሞችን መፍጠር አስፈላጊ እንደሆነ እንደሚያስቀምጥም አቶ አቡዬ ጠቁመዋል፡፡ የከተሞች ዕድገት የኢኮኖሚ ዕድገት፣ መልካም አስተዳደርንና የዜጐችን ተሳትፎ በማቀናጀትም የሚፈጸም እንደሚሆን አቶ አቡዬ አስረድተዋል፡፡
የከተሞች አስተዳደር ፖሊሲ ነገሮችን ወጥ በሆነ ሁኔታ የሚያይና በኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓት ለአካባቢዎቹ ልዩ ሁኔታ የተሰጠውን ዕውቅና ከግምት ውስጥ ያስገባ እንዳልሆነ፣ ተሞክሮም የሚወሰደው አሃዳዊ መንግሥት ከሆኑት እንደ ፈረንሳይዋ ሊዮን ከተማ መሆኑ ተፅዕኖ አልፈጠረም ወይ ተብለው የተጠየቁት አቶ አቡዬ፣ የከተማ አስተዳደርን ለመቅረፅ ተሞክሮው ከአሃዳዊ ወይም ከፌዴራል አገር መሆኑ ለውጥ ያመጣል ብለው እንደማያምኑ፣ ፖሊሲው የተቀረፀውም ሆነ የሚተገበረው በኢትዮጵያውያን እንጂ በሊዮን ከተማ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ የከተሞች ዕድገት የነዋሪዎቹን ማንነት በማይነካ መልኩ የሚፈጸም ለመሆኑም ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡
ያበጠችው አዲስ አበባ
በሴሚናሩ ላይ “Contemporary Issues on Federal Capital Addis Ababa” በሚል ርዕስ የጥናት ሥራቸውን ያቀረቡት ዶ/ር አሰፋ ፍስሐ ረቂቁ ማስተር ፕላን ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር እንደሆነና ወሳኝ የሆኑ ፖለቲካዊ፣ ሕጋዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖዎችን ከባለድርሻ አካላት አኳያ ያልዳሰሰ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
በብዙ የፌዴራል አገሮች ዋና ከተሞች በመጠን ትልቅ እንዳልሆኑና ዋና የኢኮኖሚ መናኸሪያዎችም እንዳልሆኑ ዶ/ር አሰፋ ጠቁመው፣ ከዚህ በተቃራኒ አዲስ አበባ ግን የአገሪቱ የፖለቲካ፣ የፋይናንስ፣ የባህል፣ የኢኮኖሚ ማዕከል እንደሆነችና በስፋትና በሕዝብ ቁጥርም ተወዳዳሪ እንደሌላት ገልጸዋል፡፡
ዋና ከተማዎች በፌዴራል መንግሥት ቁጥጥር ሥር (Federal Districts)፣ በክልል ቁጥጥር ሥር (Cities within Regions)፣ እና ራሳቸውን የቻሉ (City States) ሊሆኑ እንደሚችሉ ያስቀመጡት ዶ/ር አሰፋ፣ ራሳቸውን የቻሉ ከተሞችና በፌዴራል መንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉ ዋና ከተሞች የመስፋፋት ጥያቄ አወዛጋቢ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
አዲስ አበባ የአዲስ አበባ አስተዳደር፣ የፌዴራል መንግሥት፣ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ መሆኗ ልዩ እንደሚያደርጋት የሚገልጹት ዶ/ር አሰፋ፣ አዲስ አበባ የሁሉም ነገር ማዕከል መሆኗ ዝነኛው የፌዴራሊዝም ተመራማሪ ዳንኤል አላዛር፣ ‹‹በእውነተኛ የፌዴራል ሥርዓት አንድ ከተማ ብቻ ጐልቶ ሊወጣ አይገባም፤›› በማለት ከተናገሩት አባባል ጋር እንደምትፃረርም አመልክተዋል፡፡ 
የአገሪቱን 50 በመቶ ኢንቨስትመንት አዲስ አበባና በዙሪያዋ ያሉ የኦሮሚያ ከተሞች እንሚሸፍኑት የጠቀሱት ዶ/ር አሰፋ፣ ይኼ ከተማዋ ካላት የተሻለ የመሠረተ ልማት ግንባታ፣ የገበያ ተደራሽነትና የገቢ ምንጭነት አንፃር በርካታ ዜጐችን እንደሳበና የመስፋፋት ፍላጐትን እንደጨመረም አመልክተዋል፡፡
የረቂቅ ማስተር ፕላኑ ጸሐፊዎች ፕላኑ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን የኦሮሚያ ልዩ ጥቅምን ተፈጻሚ እንደሚያደርግ እምነቱ እንዳላቸው የጠቆሙት ዶ/ር አሰፋ፣ ፕላኑ ከቋንቋና ባህል ጋር የተያያዘ የኦሮሞ ማንነትን ይነካል በማለት ቅሬታዎች እየቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከገበሬዎች መፈናቀልና የካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ በአብዛኛው ትኩረት የተሰጠው በሕጋዊ መንገድ ስለሚከፈለው የካሳ ክፍያ ቢሆንም፣ ዶ/ር አሰፋ በከበርቴ ደላሎች አማካይነት የሚፈጸመው ሕገወጥ የካሳ ክፍያ በከተሞች የመሬት ሽያጭን እያጧጧፈና ገበሬዎችን እያፈናቀለ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
ዶ/ር አሰፋ የረቂቁ ማስተር ፕላን ዝግጅት ለዘመናት የቆየውን የፖሊሲ ቀረፃ ችግር የሚያሳይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ፖሊሲዎችን የሚመለከታቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች በማማከር ከመቅረፅ ይልቅ በኢትዮጵያ ፖሊሲዎችን ከሕዝብ ዕይታ ውጪ መቅረፅ የተለመደ መሆኑን በመጥቀስ፣ ሒደቱ ግልጽነት የጐደለው እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡
በአዲስ አበባ ላይ ሦስቱ አካላት ያላቸው ሚና ግልጽ አለመሆኑን በመጠቀም የራሳቸውን የፖለቲካ አጀንዳ ለማሳካት አንዳንድ የፖለቲካ ልሂቃን ግጭት እየቀሰቀሱ እንደሆነ ያስታወሱት ዶ/ር አሰፋ፣ በዝርዝር ጉዳዮች ላይ በጥሞና መነጋገርና ተቋማዊ አደረጃጀት መፍጠር አስፈላጊ እንደሆነ መክረዋል፡፡ በመጨረሻም ስለማስተር ፕላኑ ሲነሳ የሚጠቀሱት አዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን እንደሆኑ የጠቀሱት ዶ/ር አሰፋ የፌዴራል መንግሥቱ ሚና ምን እንደሆነም ግልጽ እንዳልሆነ አመልክተዋል፡፡
በጋዜጣዊ መግለጫና በሴሚናሩ ላይ ተገኝተው የነበሩ ምሁራንና ሌሎች ተሳታፊዎች ስለማስተር ፕላኑ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ግንዛቤ ያዳበሩ መሆናቸውን የጠቆሙ ሲሆን፣ እንደ ፕላኑ ሁሉ ባለሥልጣናቱ አዲስ አበባ፣ ኦሮሚያና የፌዴራል መንግሥቱ የፖለቲካና የሕግ ግጭት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ በሚል የሚሰጠውን ሐሳብ በአግባቡ ከመመለስ ይልቅ፣ ችግሩ እንደሌለ በመግለጽ መመለሳቸው ዘላቂ መፍትሔ ስለማይሆን፣ ረቂቁ ፕላን እነዚህን ጥያቄዎች የመመለስ ዕድል እንዲኖረው ቢደረግ መልካም መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡  
ምንጭ፦ ethiopianreporter.com