POWr Social Media Icons

Monday, May 12, 2014

ከማህበራዊ መረብ የተገኘ
ደሳለኝ መሳ
በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ክልሎች መካከል የመሰረተ ልማትና የልማት ልዩነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ መምጣቱን የተለያዩ ፀሐፊዎችና ባለሙያዎችም ጭምር ይስማሙበታል፡፡ መንግሰት በየጊዜ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል በክልሎች መካከል አረጋግጫለው ብሎ ቢከራከርም በተጨባጭ ከሚታየው ነገር አንፃር የኢህአዴግ ክርክር ውሃ የሚቋጥር አልሆነም፡፡ በዚህ መጣጥፍ ልያነሳ የፈለኩት መንግስት ለአየር ማረፊያ ግንባታን ለማስፋፋት ካለው ፍላጎትና ተግባር አንፃር የፍትሐዊነት ጉድለት እንዳለው ከማሳየትም አልፎ አሁን በሲዳማ እየተሞከረው ያለው ነገር ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን እንደምችል ለማመላከት ነው፡፡
ማንም ሰው ለመገንዘብ እንደምችለው (አልገነዝብም ካሉት ውጭ) ሐዋሳ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳች ካለችው የጎብኚዎች ሳቢቷና ከአካባቢም ከሚገኘው የኢኮኖሚ ወሳኝነቷ አንጻር አየር ማረፍያ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ነገር እስከ አሁን ድረስ ተፈፃሚ አልሆነም፤ ሀዋሳና አካባቢውም እድለኛ መሆን አልቻለም፡፡ ሀዋሳና አካባቢዋ አንድ አየር ማረፍያ እንኳን ሳይኖራት የተለያዩ ከልሎች ከአንድ በላይ አየር ማረፊያ ተከፋፍለዋል፡፡ ለምሳሌ የትግራይን ክልልን ብናይ በቅርቡ ዓለም አቀፍ በረራ ማስተናገድ ከጀመረው የመቐለ “አሉላ አባነጋ” አየር ማረፍያ በተጨማሪ በሌሎች አራት ከተሞች የሀገር ውስጥ በረራ የሚያስተዳግዱ አየር ማረፊያዎች ተገንብቶላቸዋል፡፡ በአማራ ክልልም በቅርቡ ወደ ጎሮቤት ሀገር በረራ ማስተናገድ የጀመረውን የባህር ዳሩን ጨምሮ በጎንደርና በወሎ የሀገር ውስጥ በረራ የሚያስተናግዱ አየር ማረፊያዎች አላቸው፡፡ ከባህር ዳር እሰከ ጎንደር ያለው ርቀት 225 .ሜ ሲሆን በዚህ ርቀት ሁለት አየር ማረፊያ አላት የአማራ ክልል፡፡ ስለዚህ ከባህር ዳር የሚነሳው አውሮፕላን 15 ደቂቃ ባልሞላሳዓት ጎንደር ይገባል ማለት ነው(ከአዲስ አበባ ወደ ጎምደር የሚፈጀው ደግሞ 45 ደቂቃ ነው)፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ከአዲስ አበባ ወደ ሀዋሳ መምጣት የሚፈልግ ጎብኚ፣ ሸቀጥ… በፈጣን ተሽከርካሪ የ430- 500 ሰዓት አሰልች ጉዞ ተጉዙ ሐዋሳ ይገባል፡፡ ስለዚህ ወደ ሐዋሳ ከመምጣት ወደ ጎንደር መሄድ አዋጭ ይሆናል፡፡ በኦሮሚያ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት፣ አፋር… ብያንስ አንድ አየር ማረፊያ አላቸው፡፡ ነገር ግን ሲዳማ አካባቢ ደህና መነኸሪያ ያሰራ ከተማ(ሀዋሳን ጨምሮ) ማግኘት ከባድ ነው፡፡ አንዳንድ የኢህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣናት ”ሀዋሳ ለአዲስ አበባ ቅርብ ከተማ ስለሆነች አየር ማረፊያ አያስፈልግም” ብሎ ይናገራሉ፡፡ ከባህር ዳር እስከ ጎንደር ያለውን ርቀትና ከአዲስ አበባ እስከ ሀዋሳ ያለውን ርቀት (275 .) አላዩም፤ ወይንም አይተው እንዳላዩ ሆነዋል፡፡ በሌላ በኩል የኢትየጵያ አየር ማረፊዎችን ማስፋፊያ እቅድ ለአዲስ አበባ ቅርብ የሆኑ ከተሞች አየር ማረፊያ አያስፈልጋቸውም የሚል ነገር አልተካተተበትም(በውስጥ ምስጥር ካልሆነ በስተቀር)፡፡ ይልቁንም ለማስፋፊያ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ከተሞች፡
1. የክልል ዋና ከተሞቸች
2. በቱርስት ሳቢነታቸው ከፍ ያሉ አካባቢዎች
3. ወደ መሃል ሀገር(ገበያ) የሚቀርቡ የግብርናና የፋብርካ ምርቶች ያሉባቸው አካባቢዎች
ብሎ ያስቀምጣል፡፡
ከላይ የተጠቀሱትን ከሞላ ጎደል ከፋብርካዎች እጥረት ውጭ በተቀረው ሀዋሳ በተፈጥሮ ምክንያት የታደለች ናት፡፡ ነገር ግን እስከ አሁን ድረስ ምንም የታሰበላት ያለ አይመስልም፡፡ ከታሰበም መረት የረገጠ ነገር አይታይም፡፡ መሬት ያለመርገጡ ዋና ምክንያት የመንግስት ትኩረት አናሳ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በቅርብ ቀን እየተደረገ ያለው ነገር ቀድሞ ሙያዊ ጥናት ስለመደረጉ ጥርጣሬ ውስጥ የሚገከቱ ነገሮች እየታዩ መሆናቸው ነው፡፡ ይህም ነገር ቁልጭ ብሎ የሚታየው ደግሞ የአየር ማረፊያ ቦታ ምርጫ ይሠራል ተብሎ ከተወራበት የአሁኑ ለሶስተኛ ጊዜ የቦታ ለውጥ ማረጉ ነው፡፡ የመጀመሪያው ጥቁር ወሃን ተሻግረው ወደ ሀዋሳ እንደገቡ የሚያገኙትን በልምድ ብቻ “አየር ማረፊያ” ተብሎ የሚታወቀውን አውላላ ሜዳ ላይ አንደምሰራ አቀዱ፡፡ ይህ ሜዳ ባልታወቀ ምክንለያት ተተወና ወደ ይርጋለም በሚወስደው መንገድ ከቱላ ከተማ አለፍ ብሎ ከሚገኘው ሞሮቾ ከተማ አካባቢ ለአየር ማረፊያ እንደተመረጠ ተነገረን፤ እንቅስቃሰም ተጀምሮ ለወራት ቀጠለ፡፡ ከወራት በኋላ ተቋረጠ፡፡ አሁን ደግሞ ለሦስተኛ ጊዜ አየር ማሪፊያው ወደ ዶረ ባፋኖ(ሐዋሳ ዙሪያ ወረዳ) ሳማ ተብሎ ወደሚጠራ መንደር በረዋል፡፡ በበረረበትም አያሌ አርሶ አደሮችን እንደሚያፈናቀል እየተነገረ ነው ያለው፡፡ አሁንም አየር ማረፊያው ስለማረፉ የታወቀ ነገር ባይኖርም በአካባቢው በህዝቡ ላይ ሁለት ችግሮች እንደሚገጥም እየተነገረ ነው፡፡
1. ዶረ ባፋኖ(ሐዋሳ ዙሪያ) ወረዳ በቦቆሎ፣ በበርበሬ በበቆሎና ወዘተ ምርት ለአካባቢው አርሶ አደርና ለተቀረው ሲዳማ ህዝብ መጋቢና በጣም ጠቃሚ ከመሆኑና መሬቱም ለእርሻ አመችና ለም ከመሆኑ ጋር ተያይዘው የአርሶ አደሮች መፈናቀል ለራሳቸውና ለተቀሩ አጎራባች ሲዳማ ዞን ወረዳዎች ነዋሪ የሆኑ ህብረተሰብ ላይ ከፍተኛ ችግር ይፈጥራል፡፡ ለዚህም ከፍተኛ ስጋት ተፈጥረዋል፡፡
2. ሌላው ደግሞ ከሳማ አካባቢ የተፈናቀሉ በርካታ የሲዳማ አርሶ አደሮች ምትክ ቦታ ይሰጣቸዋል ተብሎ አሁን ካሉበት(ሳማ) ግማሽ ቀን ተጉዘው የሚደርሱበት ሩኬሳ ተብሎ በሚታወቅ ቦታ ላይ ተወስደዋል፡፡ ይህ አካባቢ ደግሞ ሲዳማ ከኦሮሚያ ከሚያዋስኑ አካባቢዎች አንዱ በመሆኑ ሌላ ስጋት መፍጠሩ አልቀረም፡፡ በሌላ በኩል ከመጀመሪያ ጀምረው የሰፈሩ የሲዳማ አርብቶ አደሮች አካባቢው(ተፈናቃዮች ይሰፉሩበታል የተባለውን) ለከብቶቻቸው ወሳኝ በመሆኑ ለማንም አሳልፎ መስጠት በከብቶቻቸው መምጣት እንደሆነ እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡ በተጨመሪ ተፈናቃዮቹ ይህንን ያህል ርቀት ተጉዞ አካባቢውን ለእርሻ መጠቀም እንደምከብዳቸው በማሳወቅ ከነባሮቹ አርሶ አደሮች ጋር መጋጨትም እንደማይፈልጉ ለሲዳማ ዞን አስተዳደር ስሞታ እያቀረቡ ነው፡፡
መንግስት ደግሞ በግድ ሊያሰፍራቸው እንደሆነም የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በግድ የሚሰፍራቸው ከሆ ደግሞ የሲዳማ ህዝብ(ተፈናቃዩ) ከመንግስት፣ ከነባር ሩኬሳ አርብቶ አደር ሲዳማዎችና አጎራባች ኦሮሞ ህዝቦች ጋርም መጋጨት ይሆናል፡፡ ስለዚህ መንግስት ጉዳዩን በጥንቃቄ ሊያይ ይገባል፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ እዛው ሳማ ተብሎ በሚታወቅ አካባቢ ሰፋፊ የመንግስት ለም ሜዳ አለ፡፡ ለምን አርሶ አደሮች በቅርበት ባህላዊና ማህባራዊ ኑሮዋቸውን በለመዱበትና በመሰረቱበት ሳይርቁ እንድሰፈሩ አልተደረገም? ያም የማይሆን ከሆነ ሌላ አካባቢ ለእርሻ የሚመቹ ሰፋፊ መሬት ወዳለበት ወረዳ ውስጥ ማስፈር አይቻልም ይሆን? ለምሳሌ በርቻ ወረዳ ከኢትጵያ በድርቅ ከሚታወቁና ደረቅ አካባቢዎች አንዱ ሲዳማ ውስጥ የሚገኝ 43 ቀበሌ ያቀፈ ወረዳ ነው፡፡ የዚህ ወረዳ ነዋሪዎች ከወሃ(ዝናብ) እጥረት የተነሳ አርሶ አደሮች በምግብ እራሱን መቻል አቅቶት ለዘመናት የመንግስትን እጅ የሚያይ ሆኖ እስከ አሁን ዘልቀዋል፡፡ ታዲያ ለምን ቦርቻ ወረዳ ነዋሪወችን ወደ ለም፣ ለእርሻ አመችና ዝናብ በወቅቱ ወደሚያገኙ አካባቢ በማዛወር ቦታውን ለአየር ማረፊያነት መንግስት አይጠቀምም? ለመሆኑ ለአየር ማረፊያነት የተመረጠ ቦታ ለሲዳማ አማካይነት አለው?
በመጨረሻም፡ በብሔሮች መካከል የረገበውን ውጥረት እንዳያገረሽ መንግስት ጉዳዩን በጠንቃቄ ቢያይ ይመረጣል፡፡ ይሄ የማይሆን ከሆነና በማስገደድ የሚወሰድ እርምጃ ጥሩ ላይሆን ይችላል፡፡ ህዝቡን እርስ በርሱ እንዳያፋጅም ያሰጋል፡፡
ለማንኛውም አየር ማረፊያው በሰላም ያርፍ ዘንድ ምኞተ ነው!!!  
የሲዳማ ፓርቲዎች ህብረት ለነጻነት እና ፍትህ የሰሞኑ ጋዜጣዊ መግለጫ በኣንባቢያ ዘንድ ክርክር ጫረ

የተባበሩት የሲዳማ ፓርቲዎች ለነጻነት እና ፍትህ በምጻረ_ቃል (USPFJ) ሰሞኑን በኢትዮጵያ ውስጥ በኦሮሞ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ በኣገሪቱ የጸጥታ ኃይሎች የተወሰደውን የኃይል እርምጃ በመቃወም ጋዜጣዊ መግለጫ ስጥቷል። በመግለጫውም ለበርካታዎች ሞት እና ኣካል ጉዳት ምክንያት የሆነውን የመንግስት እርምጃ ኮንኗል።

ይህንን የድርጅቱን መግለጫ የወራንቻ ኢፎርሜሽን ኔትዎርክ ከጋዳ ድህረገጽ ላይ በማግኘት ለኣንባቢያኑ ያደረሰ ሲሆን፤ የህብረቱን ጋዜጣዊ መግለጫ ተከትሎ የተለያዩ ሰዎች ኣስተያየት በመስጠት ላይ ናቸው።

በርካታ ኣንባቢያን ለወራንቻ ኢንፎርሜሽን ኔትዎርክ በጻፏቸው መልዕክቶች እንዳመለከቱት፤ የተባበሩት የሲዳማ ፓርቲዎች ህብረት ለነጻነት እና ፍትህ፤ በበርካታ ሲዳማውያንን እና የሰብኣዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች የተወገዘውን፦ የኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይሎች በቅርቡ በሃዋሳ ከተማ የኣላሙራ እና ታቦር ከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሲዳማ ተወላጅ ተማሪዎች ላይ የወሰዱትን የኃይል ጥቃት ካለማውገዙ በላይ በጥቃቱ ልጆቻቸው ለተጎዱባቸው ቤተሰቦች ኣጋርነቱን ኣለመግለጹን እንዳዛዘናቸው ገልጸዋል።

ከኣስተያየት ስጪዎቹ መሃከል፦ ስሙን T H በማለት የጠራው እና የዩቨርሲቲ መምህር መሆኑን የገለጸው ኣስተያየት ሲጪ እንዳለው፤ ህብረቱ ምንም እንኳን እታገልለታለው ከሚለው ህዝብ ጋር የግንባር ለግንባር ግንኙነት የሌለው ብሆንም ባለፉት ኣመታት በሲዳማ ውስጥ ያለውን የፖለቲካ እና ስብኣዊ መብት ጥስቶችን በማጋለጥ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ኣስተውሰዋል።

ኣክለውም ህብረቱ በቅርቡ በኦሮሞ ተማሪዎች ላይ በመንግስት የተወሰደውን የኃይል እርምጃ ማውገዙ ምንም ስህተት እንደሌለው ገልጸው፤ የህብረቱ ድርጊት በባህል ከሲዳማ ህዝብ ጋር ኣንድ ለሆነው የኦሮሞ ህዝብ መብት መከበር ያለውን ድጋፍ እና ኣጋሪነት ያሳያል ብለዋል።

ኣያይዘውም የህብረቱ መግለጫ የሲዳማ ህዝብ እና የኦሮሞ ህዝብ በጋራ በተለያዩ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮቻቸው ላይ እንድሰሩ መንገድ ይከፍታል በማለት ኣስተያየታቸውን ስጥተዋል።

ካላ ቃዋቶ ቤላሞ የተባሉት ሌላኛው ኣስተያየት ሲጪ በበኩላቸው፤ ህብረቱ በኣሮሞ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ የተፈጸመውን ግፍ መቃዎሙ ትክክል ሆኖ ሳለ፤ በተመሳሳይ መልኩ በሲዳማ ተማሪዎች ላይ የተፈጸመውን ግፍ ተቃዉሞ መግለጫ ኣለመስጠቱ ኣሳዛኝ ነው ብለዋል።

እኝሁ ኣስተያየት ሲጪ እንዳሉት፦ የሃዋሳ ከተማ ኣላሙራ እና ታቦር ትምህርት ቤት ተማሪዎች ያነሷቸው የመብት ጥያቄዎች ማንኛውም ለሲዳማ ህዝብ መብት እታገላለው የምል ኣካል በሙሉ ሊያነሳው የሚገባ ኣንገብጋብ የመብት ጥያቄ በመሆኑ ህብረቱ ለተማሪዎቹ ያለውን ድጋፍ በኣደባባይ መግለጽ ይገባው ነበር በማለት ኣስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የካላ ቃዋቶች ኣስተያየት የተጋሩ ሌላኛው ኣስተያየት ሰጪ እንደጻፉት፦ የተባበሩት የሲዳማ ፓርቲዎች ህብረት ለነጻነት እና ፍትህ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ በማህበራዊ ገጾች ላይ የሚጽፋቸው ጽሁፎች በብዛት የኦሮሞ ህዝብ የተመለከቱ ናቸው ብለዋል።

ኣክለውም የራሷ እያረረባት የሰው ታማስላለች እንደምባለው በሲዳማ ፖለቲካዊ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ላይ ትኩረት ስጥቶ መስራት እያለበት በሌላ ኣጄንዳ ላይ ትኩረት መስጠቱ በሲዳማ ህዝብ ዘንድ ያለው ተቀባይነት ያሳጣዋል ብለዋል።

ክቡራን ኣንባቢያን በጉዳዩ ላይ ያላችሁን ኣስተያየት በሚከተለው ኣድራሻ ይላኩልን:
Worancha Information Network
e-mail: nomonanoto@gmail.com 
እኛም ከሰፊው የሲዳማ ህዝብ ጋር እንጋራዋለን።