POWr Social Media Icons

Wednesday, May 7, 2014

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚያዝያ 28 ቀን 2006 ዓ.ም. በስዊዘርላንድ ዋና ከተማ ጄኔቭ ባዘጋጀው ወቅታዊ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ግምገማ ላይ ኢትዮጵያ እየተገመገመች ነበር፡፡
በዚሀ ግምገማ ላይ ሦስት አገሮች ማለትም ናሚቢያ፣ ካዛክስታንና ቼክ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝን በተመለከተ በአቻ ገምጋሚነት ተሳታፊ ነበሩ፡፡
ይህ በተመድ የተዘጋጀ ግምገማ ለሰብዓዊ መብት አከባበር የሕዝብ በአገር ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና ማኅበራዊ ጉዳዮች ውስጥ በንቃት ተሳታፊ መሆን ዋነኛውና መሠረታዊው መርህ መሆኑን አስቀምጧል፡፡ በዚህ ግምገማ ላይ ኢትዮጵያን ወክለው የተገኙ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትም የአንድ አገር ልማትና ዕድገት የሚረጋገጠው በሕዝብ ያልተገደበ ተሳትፎ ላይ ሲመሠረት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተለይ በግምገማው ላይ ከተለያዩ አገሮችና ወገኖች የተነሱ መሠረታዊ የሚባሉት ነጥቦች ማለት የምንፈልጋቸውን በይበልጥ ያብራሩልናል፡፡ በተለይ አንኳር ተብለው የተነሱ ጉዳዮችን ስንመረምር የሕዝብ ተሳትፎ አስፈላጊነትን ቁልጭ አድርገው ያስቀምጡልናል፡፡ 
በግምገማው ላይ ከተነሱ ሐሳቦች መካከል በ2007 ዓ.ም. ሊደረግ የታሰበው ብሔራዊ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊና ሁሉንም የሚያሳትፍ መሆን እንዳለበት፣ ኢትዮጵያ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁን በድጋሚ ማጤን እንደሚገባት፣ የጋዜጠኞች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና የፖለቲከኞች በዘፈቀደ መታሰርና መጉላላት መቆም እንዳለበት፣ ሕጋዊ አካሄድን የጠበቀ የዳኝነትና የፍትሕ ሥርዓት መኖር አስፈላጊ መሆኑን፣ በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ላይ የወጣው ሕግ መሻሻል እንደሚኖርበት፣ ኢትዮጵያ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ ግብርን ሙሉ ለሙሉ ተፈጻሚ ማድረግ እንዳለበት፣ የሴቶች፣ የአካል ጉዳተኞችና በገጠር የሚኖሩ ዜጎች መብትና ጤና መጠበቅ እንዳለበት፣ ወዘተ ከተለያዩ አገሮች ማሳሰቢያ የተሰጠባቸው ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን፣ ጋዜጠኞችንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን በተመለከተ ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፣ በፀረ ሽብርተኝነት ሕጉም ሆነ በሌሎች ሕጎች በተለየ ሁኔታ የሚስተናገዱ ክስተቶች ካልሆኑ በስተቀር መንግሥት የተጠቀሱትን ሰዎች በዘፈቀደ እንደማያስር አስረድተዋል፡፡ ውይይቱም በዚህ መንፈስ ቀጥሏል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ መንግሥት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰብዓዊ መብት አያያዝንና የሕዝብ ተሳትፎን በተመለከተ ከተለያዩ አገሮችና ተቋማት ጋር ሲነጋገር፣ በአገር ውስጥም በተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ ከሕዝቡ ጋር ለምን በግልጽ አይወያይም? በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ ጊዜ መንግሥት በተለይ በሰብዓዊ መብት አያያዝ ጉዳይ ከፍተኛ ወቀሳዎች ይቀርቡበታል፡፡ በተደጋጋሚ ወቀሳዎቹንም ሲያስተባብል ተደምጧል፡፡ ነገር ግን በአገር ውስጥ ከሕዝብ ጋር ተቀምጦ በግልጽ ሲገማገም አይታይም፡፡
መንግሥት የሕዝብ ተሳትፎን መሠረት ያደረጉ በርካታ ውይይቶችን በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ማድረጉን ሲናገር እንሰማለን፡፡ ምንም እንኳ በተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ከሕዝብ ጋር ውይይት መደረጋቸው ቢሰማም የሕዝብ ውክልናው እንዴት ነበር የሚል ጥያቄ ይነሳል፡፡ ‹‹አበረታች ነው፣ ተስፋ ሰጪ ነው፣ …›› በሚሉ መሞጋገሶች የሚደረጉ ውይይቶች ከውጤታማነታቸው ይልቅ ውጤት አልባነታቸው እየታየ ነውና፡፡ በእንዲህ ዓይነት ውይይቶች ላይ ጠንካራና ጤናማ ውይይቶችን ማድረግ ሲገባ የይስሙላ ነገሮች ተበራክተዋል፡፡ 
ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሕዝብ ተሳትፎ ተተኪ ሚና የለውም ሲባል ከዚያ ተሳትፎ የሚገኙ የተለያዩ ግብዓቶች ጠቃሚ በመሆናቸው ነው፡፡ ዲሞክራሲ የተለያዩ ሐሳቦች ገበያ ነው የሚባለው ለአገር ግንባታም ሆነ ዘለቄታዊ ህልውና ወሳኝ ሊሆኑ የሚችሉ የተለያዩ አስተዋጽኦዎች በሐሳብ ተፃራሪ ከሆኑ ወገኖች ጭምር ስለሚገኙ ነው፡፡ የሕዝብ ተሳትፎ በጨመረ ቁጥር አንዱ ሌላውን በተገቢው ደረጃ ይረዳዋል፡፡ ለፖሊሲዎች ጠቃሚ የሆኑ ሐሳቦችና ዕውቀቶች ይገኛሉ፡፡ ሐሳቦች በተንሸራሸሩ መጠን ግጭትና የኃይል ተግባራት ይወገዳሉ፡፡ የሕዝብ ተሳትፎ ሲጠናከር በአንድ ሥርዓት ውስጥ ግልጽነትና ተጠያቂነት ይኖራሉ፡፡ ከሙስና ጀምሮ ለአገር ፀር የሆኑ ብልሹ አሠራሮች ይወገዳሉ፡፡ ሕዝባዊነት ይጨምራል፡፡ 
ዜጎች የአገራቸው ጉዳይ አግብቷቸው ተሳታፊነታቸው በጨመረ ቁጥር በአገሪቱ ውስጥ ለሚከናወኑ ጉዳዮች ባዕድ አይሆኑም፡፡ ይልቁንም የባለቤትነታቸው መንፈስ ስለሚጨምር ለዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ያድጋል፡፡ የሕዝብ ተሳትፎና የባለቤትነት ስሜት በማይታይበት ከባቢ ውስጥ ግን ዋጋ የሚያስከፍሉ ክስተቶች ያጋጥማሉ፡፡ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ውድመት ከማስከተላቸውም በላይ የአገርን ህልውና ይፈታተናሉ፡፡
በተለያዩ ጊዜያት በአገራችንም ሆነ በተለያዩ ሥፍራዎች ያጋጠሙ ግጭቶችና አላስፈላጊ መስዋዕትነት የሚያስከፍሉ ክስተቶች የሕዝብ ተሳትፎ አናሳነትን የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡ በመልካም አስተዳደር መጓደል፣ በብልሹ አሠራር ወይም ባለማወቅ ምክንያት ቢሳበቡም የሕዝብ ተሳትፎ በበቂ መጠን ባለመረጋገጡ ዋጋ ሲያስከፍሉ ኖረዋል፡፡ አሁንም እያስከፈሉ ናቸው፡፡ የግንዛቤ እጥረት ያለበት ማኅበረሰብ አለ ሲባል መረጃዎች በቅጡ እየተላለፉ አይደለም ማለት ነው፡፡ መረጃዎች በጠራ ሁኔታ መተላለፍ የሚችሉት ደግሞ የሕዝቡ ተሳትፎ ሲያድግ ነው፡፡  
የሕዝብ ተሳትፎ አለመረጋገጥ ከሚያስከትላቸው ችግሮች መካከል ዋናው አለመተማመን ነው፡፡ በዚህ ዘመን በዜጎችና በመንግሥት ባለሥልጣናት መካከል የሚታየው ከፍተኛ የሆነ አለመተማመን በደሃ አገሮች ብቻ ሳይሆን በበለፀጉና ዲሞክራቲክ በሚባሉት ጭምር ነው፡፡ ፍትሐዊ ያልሆነ የሀብት ክፍፍልና ሙስና ከሚፈጥሩት ጫና በተጨማሪ፣ በመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ የግልጽነትና ተጠያቂነት መጥፋት አለመተማመኑን ከፍተኛ ደረጃ ላይ እያደረሱት ነው፡፡ በተለያዩ የአገራችን ክልሎችና በፌዴራል ደረጃ ይህ ጎልቶ እየታየ ነው፡፡  
የተለያዩ ሕጎች ሲወጡ፣ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ሲቀረፁ፣ በሕዝቡ የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ተፅዕኖ የሚኖራቸው ደንቦችና መመርያዎች ሥራ ላይ ሲውሉ የሕዝቡን ፍላጎትና ስሜት ካላንፀባረቁ አደገኛ ይሆናሉ፡፡ ነገር ግን ሥራ ላይ ከመዋላቸው በፊት በሕዝብ ተሳትፎ ቢቃኙ የበለጠ ውጤታማ ይሆናሉ፡፡ መንግሥት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተለያዩ አገሮችና ተቋማት ጋር የሚነጋገረውን ያህል ከሕዝብ ጋርም ግንባር ለግንባር ይወያይ፡፡ የሕዝብ ተሳትፎ በተጨባጭ ሲረጋገጥ ሁከት፣ ጥላቻ፣ ትርምስና መደናበር ይወገዳሉ፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ ሲያገኙ ሰላምና መረጋጋት በአስተማማኝ ሁኔታ ይቀጥላል፡፡ ስለዚህ የሕዝብ ተሳትፎ በተግባር ይረጋገጥ!