POWr Social Media Icons

Saturday, April 12, 2014

-የኮር ባንኪንግ ቴክኖሎጂ ግዥ ፈጸመ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በኢትዮጵያ በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ለመሰማራት ይጠየቅ የነበረውን የተከፈለ 100 ሚሊዮን ብር ወደ 500 ሚሊዮን ብር ከማሳደጉ በፊት 15ኛው የግል ባንክ በመሆን የአገሪቱን የባንክ ኢንዱስትሪ የተቀላቀለው ደቡብ ግሎባል ባንክ 19 ወራት አስቆጥሯል፡፡
ከሌሎች የግል ባንኮች በተለየ በአንድ የአክሲዮን ሽያጭ ፕሮግራም በሚሊዮን የሚቆጠር አክሲዮን በመሸጥ በ138.9 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል በማሰባሰብ ወደ ሥራ የገባ ባንክ ነው፡፡
በ5481 ባለአክሲዮኖች የተመሠረተው ይህ ባንክ ወደ ሥራ ከገባ በኋላ በመጀመርያው የሥራ ዓመት (10 ወራት) አትራፊ መሆን ባይችልም በአሁኑ ወቅት ግን ወደአትራፊነት እየገባ መሆኑን ባንኩ አስታውቋል፡፡
የባንኩን የ19 ወራት የሥራ እንቅስቃሴ በተመለከተ በተሰጠ መግለጫ ላይ እንደተመለከተው፣ ባንኩ መጋቢት 2006 ዓ.ም. 14.5 ሚሊዮን ብር አትርፏል፡፡ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ወርቁ ለማ እንደገለጹት፣ በመጀመርያው ዓመት ላይ ተመዝግቦ የነበረው ኪሳራ አሁን መለወጡንና በየወሩ እያተረፈ መጓዝ ጀምሯል፡፡ በመጀመርያው የሥራ ዘመንም ትርፍ ይገኛል ተብሎ ባይጠበቅም ደቡብ ግሎባል ባንክ ግን በአጭር ጊዜ ወደ ትርፍ መግባት ከመቻሉም በላይ አሁን እያስመዘገበ ያለው ትርፍ በ2006 በጀት መዝጊያ ጥሩ ትርፍ የሚያገኝ መሆኑን ያሳያልም ብለዋል፡፡ በመጋቢት 2006 ዓ.ም. ያስመዘገበው የትርፍ መጠንም አምና ከነበረው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 223 በመቶ ብልጫ ያለው ነው፡፡ 
ባንኩ ትርፍ ማስመዝገብ ከመጀመሩ ባሻገር በዋና ዋና የባንክ አገልግሎቱ እያደገ መምጣቱን የፕሬዚዳንቱ ገለጻ ያስረዳል፡፡ የባንኩ የሥራ እንቅስቃሴ በለውጥ ጎዳና ላይ ስለመሆኑም ዋና ዋና የተባሉ አስረጅዎችም አቅርበዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ባንኩ የተቀማጭ ገንዘብን ከአንድ ዓመት በፊት ከነበረው በ284 በመቶ ማደጉ አንዱ ነው፡፡ በውጭ ምንዛሪ ግኝትን በመተለከተም አምና በመጋቢት 2005 ዓ.ም. ከነበረው በ1,115 በመቶ አድጎ በመጋቢት 2006 ዓ.ም. 24.3 ሚሊዮን ዶላር መድረሱ ተገልጿል፡፡
የሰጠው ብድርም በተመሳሳይ መንገድ ዕድገት ያሳየ መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ከአምና በ276 በመቶ  ብልጫ ያለው ብድር በመስጠት መጋቢት 2006 ዓ.ም. ድረስ 302 ሚሊዮን ብር አበድሯል፡፡ ከዚህም ሌላ የባንኩ እሴት 165.7 ሚሊዮን ብር እንደሆነና የተከፈለው ካፒታሉ ደግሞ 165.7 ሚሊዮን ብር መድረሱም ተገልጿል፡፡
ይህ ባንኩ ደረሰበት የተባለው ደረጃ ከፍተኛ ሊባል የሚችል መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ከዚህም በኋላ ይህንኑ ዕድገት ተከትሎ ይጓዛል ብለዋል፡፡ ባንኩ እያስመዘገበ ያለው ውጤት ዕድገቱን የሚያሳይ ቢሆንም፣ በሥራ ሒደቱ የተለያዩ ተግዳሮቶች እንደነበሩበት ሳይጠቁሙ አላለፉም፤ በተለይ የኔትወርክ ችግርና የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ዋናዎቹ ናቸው፡፡ 
እንደ ባንኩ ፕሬዚዳንት ገለጻ፣ በባንኩ የ19 ወራት የሥራ ጉዞ እንደቁልፍ ሥራ ተደርጎ የተወሰደው ባንኩን በዘመናዊ የባንክ አገልግሎት አሰጣጥ ለመግባት የኮር ባንኪንግ ሲስተም ግዥ መፈጸሙ ነው፡፡              
ባንኩ ባወጣው ጨረታ መሠረት አሸናፊ ከሆነው ኩባንያ ፍሌክስ ኪውብ የኮር ባንኪንግ ግዥ አከናውኗል፡፡ ግዥው የተፈጸመው ኦራክል ፋይናንሻል ሰርቪስስ ከሚባል የህንድ ኩባንያ ነው፡፡ ግዥውን ለመፈጸም ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርገናል ያሉት አቶ ወርቁ፣ ፍሌክስ ሲተምን ለመምረጥ የተፈለገው በርካታ የአገር ውስጥ ባንኮች እየተጠቀሙበትና ጥሩ ውጤት በማምጣቱ ጭምር ነው፡፡ ባንኩ ገዛሁት ያለው ሲስተም በ115 አገሮች ውስጥ ባሉ 319 ባንኮች ውስጥ እየተሠራበት ነው ተብሏል፡፡ 
ቴክኖሎጂውን ሥራ ላይ ለማዋል፤ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ለሚያስፈልጉ የሶፍትዌርና ተጓዳኝ ግዥዎች ባንኩ ወደ 21 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚያወጣም ተገልጿል፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ ባንኩ ቀልጣፋና ዘመናዊ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለው ሲሆን አዳዲስ አገልሎቶችን ተግባራዊ ለማድረግ ያግዘዋል ተብሏል፡፡ በተለይ ባንኩ በዕቅድ ከያዛቸው እንደ የኤጀንት ባንኪንግ ዓይነት አገልሎቶቹ ይህ ቴክኖሎጂ የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው ተብሏል፡፡   
የሞባይል ወይም የኤጀንት ባንኪንግ ሲስተም በፍጥነት ተግባር ላይ ለማዋል እንደሚፈልጉ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ለዚህም ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ ለዚሁ ሥራ በወጣ ጨረታ መሠረት የአቅራቢዎች ምላሽ በመሰብሰብ ላይ ነው፡፡ በኤጀንት ባንኪንግ ሥራ ላይ ትኩረት የተደረገው በቀላሉ ደንበኞች ጋር ለመድረስ መልካም አማራጭ በመሆኑ ጭምር ነው፡፡  
የኢትዮጵያ ባንኮች አትራፊ ሆነው እንደሚቀጥሉና ባንካቸውም የደረሰበት ውጤት ያሳያል ያሉት አቶ ወርቁ፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚም ተጨማሪ ባንኮች ለመሳብ ዕድል ያለው ነው ይላሉ፡፡ አቶ ለማ አዳዲስ ባንኮች መፈጠር የሚኖርባቸውና አሁን ባሉት ባንኮች ብቻ የአገሪቱን ኢኮኖሚ የሚፈለገውን ያህል የሚደግፉ ባለመሆናቸው ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡
ተጨማሪ ባንክ ይኑር በሚለው ጉዳይ አንዳንድ ብዥታዎች እንዳሉም አስታውስዋል፡፡ የአገሪቱ ውስጥ ያሉ ባንኮች ውድድር ጠንክሯል፣  እያደገ ነው፣ ስለዚህ ተጨማሪ ባንክ አያስፈልግም በሚለው አመለካከት አይስማሙም፤ ይህ አመለካከት ብዥታ ነው ይሉታል፡፡ ይህንን አመለካከታቸውን ለማጠናከር እንደመረጃ ያቀረቡት የኬንያን ባንኮችን  ነው፡፡
ከኢትዮጵያ በሕዝብ ብዛት በግማሽ በምታንሰው ኬንያ ውስጥ 43 ባንኮች አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን 19 ብቻ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ በኢትዮጵያ ተጨማሪ ባንኮች መኖር ይገባቸዋል፤ አትራፊ መሆናቸውንም እያረጋገጥን በመሆኑ በተለይ ባለሀብቶች ለዚህ ዘርፍ ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ አቶ ወርቁ ተናግረዋል፡፡

ገዥው ፓርቲ በከተማ ኣስተዳደር ስም በሲዳማ ዞን ሃዋሳ ዙሪያ ወረዳ ውስጥ ይገኙ የነበሩትን የገጠር ቀበሌዎችን በሃዋሳ ከተማ ኣስተዳደር ስር በማጠቃለል በልማት ስም የኣርሶ ኣደሮች ይዞታ የሆነውን መሬት በመንጠቅ በልዝ ለባለጋብቶች ለማከፋፈል እና ኣርሶ ኣደሮችን መሬት ኣልባ ለማድረግ በኦሮሚያ ክልል ያደረገው ጥረት ኣለመሳካቱ ሰሞኑን ተሰምቷል። ዝርዝር ዜና የሪፖርተር ጋዜጣ ነው።

 

የኦሮሚያ ልዩ ዞኖችን በሚያጠቃልለው ማስተር ፕላን ላይ መግባባት አልተቻለም

-በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማስተር ፕላኑን ተቃወሙ
-ከአዲስ አበባ አዳማ በአዲሱ መንገድ ግራና ቀኝ መሬት መሸጥ ቁጥጥር ሊደረግበት ነው
አዲስ አበባ ከተማና በዙሪያዋ የሚገኙትን አምስት ልዩ የአሮሚያ ዞን ከተሞች  ሰበታ፣ ቡራዩ፣ ሱሉልታ፣ ለገጣፎና ገላን አጠቃሎ በተሠራው ማስተር ፕላን ላይ መግባባት ባለመቻሉ ግምገማዊ ውይይት በማድረግ የመግባቢያ ፊርማ ለማድረግ የተጀመረው ስብሰባ ሳይጠናቀቅ መቋረጡን ምንጮች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡
መጋቢት 19 ቀን 2006 ዓ.ም. የልዩ ዞኑና የአዲስ አበባ ከተማ ተወካዮች በማስተር ፕላኑ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት የተሰበሰቡ ቢሆንም፣ በተሠራው ማስተር ፕላን ላይ አንድ ዓይነት አቋም ሊይዙ አለመቻላቸው ታውቋል፡፡ ከአንዳንድ ተሳታፊዎች መግባባቱን ወደኋላ ሊመልሱ የሚችሉ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በመነሳታቸው፣ በዕለቱ ይካሄዳል ተብሎ በነበረው የጋራ ውይይት ላይ ልዩነት መፈጠሩን ምንጮች አስረድተዋል፡፡
በአዳማ በተደረገው ውይይት በልዩ ዞኖቹ በኩል የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አብዱልአዚዝ መሐመድና አዲስ አበባን በመወከል ከንቲባ ድሪባ ኩማ በጋራ ውይይቱን የመሩት ቢሆንም፣ በውይይቱ የተሳተፉ የተለያዩ ቢሮ ኃላፊዎችና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ባነሱዋቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምክንያት በዕለቱ ሊቋጭ ዕቅድ ተይዞለት የነበረው ግምገማዊ ውይይት ለሌላ ጊዜ መተላለፉን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን መሠረት ያደረገ የጋራ ማስተር ፕላን አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት፣ የአዲስ አበባና ዙሪያዋ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ልማት ፕላን ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ተቋቁሞ፣ ከስምንት ዓመታት በላይ ጥናትና ውይይት ከተደረገበት በኋላ፣ ማስተር ፕላኑ ተሠርቶ መጠናቀቁንና በመጪው ግንቦት ወር ይፋ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቅ ነበር፡፡
ፕሮጀክቱ በ1996 ዓ.ም. በቀድሞው ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ መጠንሰሱን የሚናገሩት ምንጮች፣ ለፕሮጀክቱ መጠንሰስ ዋና ምክንያት የሆነው በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙት የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች በኢኮኖሚ ተጠቃሚ አለመሆናቸውን ታሳቢ ያደረገ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡
በተሠራው ማስተር ፕላን ላይ ሁለቱ ወገኖች ተወያይተውና ተፈራርመው ለመለያየት በአዳማ ያደረጉት ስብሰባ በተለይ በአንዳንዶቹ የውይይቱ ተሳታፊዎች ያልተጠበቀ ጥያቄና አስተያየት ግራ የተጋቡት አቶ ድሪባ፣ ስብሰባውን ለመገናኛ ብዙኃን ዝግ በማድረግ ውይይቱን መቀጠላቸውን ምንጮች አስረድተዋል፡፡
ጥያቄዎቹና አስተያየቶቹ የተነሱት ከፍተኛ ኃላፊነት ላይ ባሉ ግለሰቦች በመሆኑ፣ ምናልባት ስለማስተር ፕላኑ በቂ ግንዛቤ እንዳልተፈጠረ በመገንዘብ እንደገና ግንዛቤ ለማስያዝ ስብሰባው በዝግ እንዲካሄድ ሳይደረግ እንዳልቀረ ምንጮች ግምታቸውን ተናግረዋል፡፡
ማስተር ፕላኑን በሚመለከት መጋቢት 19 ቀን 2006 ዓ.ም. አዳማ ላይ ተደርጎ የነበረው ግምገማዊ ውይይትና ይፈጸማል ተብሎ የነበረው የስምምነት ፊርማ ለምን እንደተቋረጠ ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዳዊት ንጉሴ፣ ስብሰባው ተደርጎ እንደነበር አረጋግጠው፣ በወቅቱ መፈራረሙ የቀረው ስምምነት ጠፍቶ ሳይሆን፣ ለሁለት ቀናት ይደረጋል የተባለው ግምገማዊ ውይይት በአንድ ቀን እንዲያልቅ በመደረጉና ጊዜ ባለመብቃቱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ማስተር ፕላኑ አዲስ በመሆኑ መረጃ የሚፈልጉ ወገኖች እንደነበሩና ጥያቄ ማንሳታቸውን የገለጹት አቶ ዳዊት፣ አንዳንድ ግለሰቦች፣ ‹‹አዲስ አበባ ኦሮሚያን አስፋፍታ ልትይዝ ነው፣ ወደ ኦሮሚያ ምድር ልትስፋፋ ነው፤›› የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ መያዛቸው፣ ለጥያቄያቸው በቂ ምላሽ እንደተሰጣቸው ጠቁመዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በበላይ አመራሮችና በቦርድ የሚመራ በመሆኑ፣ በሁሉም ነገሮች ላይ ስምምነት ላይ ተደርሶ ፕሮጀክቱ በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ እንደሆነና ምንም ዓይነት ችግርና አለመግባባት እንደሌለ አስረድተዋል፡፡ 
ልዩ ዞኖቹን ያጠቃለለውን የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንን በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፓለቲካ ፓርቲዎች ተቃውመዋል፡፡ ፓርቲዎቹ በጋራ ባወጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ ‹‹ፊንፊኔ የኦሮሚያ ዋና ከተማ መሆኗ በሕገ መንግሥታችን ተደንግጎ እያለና በሕገ መንግሥት አንቀጽ 49(5) ላይ በጉልህ ኦሮሚያ ከፊንፊኔ አስተዳደር ልዩ ጥቅም ይከበርላታል በሚል ቢደነገግም፣ መንግሥት በተገላቢጦሽ በፊንፊኔ ዙሪያ ያሉትን ከተሞች በልማት ሰበብ በፊንፊኔ ሥር ለማዋል የሚያደርገው የረቀቀ ተንኮል ሕገ መንግሥቱን የሚስ ነው፤›› ብለዋል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ የኦሮሞ ሕዝብ ሳይወያይበት፣ ሳይመክርበትና ምክንያቱን ሳይረዳ በሁለቱ ወገኖች ውሳኔ ብቻ መደረግ ስለሌለበት ድርጊቱ በአስቸኳይ እንዲቆምም ፓርቲዎቹ ጠይቀዋል፡፡
በማስተር ፕላኑ 85 በመቶ የሚሆነው መሬት ለግብርና የሚውል ሲሆን፣ 15 በመቶ የሚሆነው ለመኖርያ ቤት ግንባታ የሚውል ነው፡፡ በአጠቃላይ በማስተር ፕላኑ ክልል ውስጥ 13 ሚሊዮን ሕዝብ ይኖራል ተብሎ ሲገመት፣ ስምንት ሚሊዮኑ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ እንደሚኖሩ፣ በነበረው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን እስከ 55 ፎቅ ብቻ መገንባት ይቻላል የሚለው ተነስቶ ከዚያም በላይ መገንባት እንደሚቻል ታውቋል፡፡
ማስተር ፕላኑ የሚያቅፋቸውን ልዩ ዞኖች በተለይም ከአዲስ አበባ አዳማ በተሠራውና በቀጣይም በሚሠራው ዋና መንገድ (ኤክስፕረስ ዌይ) ግራና ቀኝ ያሉ መሬቶች በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ ሕገወጥ በሆነ መንገድ እየተቸበቸቡ መሆኑን ተከትሎ፣ ጥብቅ ቁጥጥር ለማድረግ መወሰኑን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አብዱልአዚዝ መሐመድ ትዕዛዝ ምንም ዓይነት የመሬት ሽያጭ በሕገወጥ መንገድ እንዳይካሄድ ለማድረግ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ ትዕዛዝ መተላለፉ ተገልጿል፡፡
2ኛው ዙር የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬና ነገ ይካሄዳል፤ ሃዋሳ ከነማ ከመብራት፧ ሲዳማ ቡና ከመከላከያ ይጫወታሉ መልካም እድል ለሲዳማ ክላቦች
አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 4 ፣ 2006 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) ሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬና ነገ ይካሄዳል።
ዛሬ ወላይታ ዲቻ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 9 ሰዓት ላይ ሲገናኙ ፤ መብራት ሃይል ከሃዋሳ ከነማ በ11 ሰዓት ከ30 ላይ ይጫወታሉ።
ነገ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሙገር በአዲስ አበባ ስታዲየም 10 ሰዓት ላይ ይገናኛሉ።
አርባ ምንጭ ከነማ ከኢትዮጵያ መድህን ፣ ሲዳማ ቡና ከመከላከያ ፣ ዳሽን ቢራ ከሃረር ቢራ በተመሳሳይ 9 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።
በሌላ በኩል ሊጠናቀቅ  አምስት ሳምንታት በቀረው በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ስቶክ ሲቲ ከኒውካስትል ፣ ስንደርላንድ ከኤቨርተን ፣ ዌስት ብሮም ከቶተንሃም በተመሳሳይ 11 ሰዓት 07 ላይ ይገናኛሉ።
ነገ የሊጉ መሪ ሊቨርፑል ሁለት ተስተካካይ ጨዋታ ካለውና በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ በሶስተኛነት ከተቀመጠው ማንቸስተር ሲቲ ጋር 9 ሰዓት ከ37 ላይ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
ቸልሲ በበኩሉ ከሜዳው ውጭ ስዋንሲን 12 ሰዓት ከ07 ላይ ይገጥማል።
በእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ዛሬ አርሰናል ከዊጋን አትሌቲክ ምሽት 1 ሰዓት ከ07 ላይ ጨዋታውን  ያደርጋል።
በፕሪሚየር ሊጉና በኤፍ ኤ ካፕ ጨዋታዎች የተጨመረው 7 ደቂቃ ፥ ከሃያ አራት አመታት በፊት ሊቨርፑል ከኖቲንግሃም ፎረስት ሲጫወቱ የደረሰውን የሂልስ ቦሮውን አደጋ ለማስታወስ መሆኑ ተገልጿል።
በ33ተኛው ሳምንት የስፔን ላሊጋ ዛሬ ግራናዳ ከባርሴሎና 3 ሰዓት ላይ ሲገናኙ ፤ ሪያል ማድሪድ ከአልሜሪያ ምሽት 5 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።