POWr Social Media Icons

Saturday, March 15, 2014

ጎግል በኣለም ደረጃ “ሲዳማ” በምል ቃል ስለ ሲዳማ ጎግል የምያደርጉ ሰዎች ቁጥር ካለፉት ኣስር ኣመታት ጀምሮ እያደገ መምጣቱን የገለጸ ሲሆን፤ በተለይ እንደ ፈረንጆቹ ዘመን ኣቆጣጠር በ2013 ከፍተኛ ቁጥር ያለው የኢንተርኔት ተጠቃሚ ሲዳማን መፈለጉ ታውቋል።

እንደጎግል መረጃ በተለይ እኣኣ ከ2007 በፊት ሲዳማ ብዙም ጎግል የተደረገ ቃል ባይሆንም፤ በ2008 ኣጋማሽ ላይ በርካታ ሰዎች “ሲዳማ”ን ጎግል ማድረጋቸው ተመልክቷል። ቀጥሎም በ2009 መጀመረያ ላይ የሲዳማ ጎልጋዮች ቁጥር የወረደ ሲሆን በተመሳሳይ ኣመት መጨረሻ ላይ እንደገና ኣድጓል።

2010 ጀምሮ የጎልጋዮች ቁጥር ኣንዴ ስያድግ ሌላ ግዜ ሲወርድ ቆይቶ በበላፈው ኣመት መጀመሪያ ላይ በታሪኩ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ መጨመሩ ታውቋል። ነገር ግን ከ2013 ኣጋማሽ ጀምሮ ይቁጥር በመውረድ ላይ ይገኛል።

ጎግል እንዳመለከተው “ሲዳማ” የምትለውን ቃል የምጎለጉሉ ሰዎች ትራፊክ በኣብዛኛው የምፈጠረው ከሰሜን ኣሜሪካ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ እና ሰሜን ኣውሮፓ ኣገራት እንድሁ የትራፊክ ምንጮች ናቸው።


የሲዳማ ጎልጋዮች ቁጥር መጨመር እና መውረድ ከሲዳማ ዞን የፖለቲካ ሁኔታ ጋር የተያያዘ መሆኑን የወራንቻ ኢንፎርሜሽን ኔትዎርክ ትንተና ያመለከተ ሲሆን፤ ለዚህም ማሳያ በሲዳማ ዞን ውስጥ የፖለቲካ ትኩሳት የነበረባቸው ኣመታት ማለትም በ2006 እና 2013 የተፈጠረውን ትራፊክ ማየት ይቻላል።
ከይረጋዓለም ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር


ፍቼ በዓል በሲዳማ
ፎቶ ከሲዳማ ባ/ቱ/መ/ኮ/መምሪያ

“ፍቼ” በሲዳማ ባህል ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየ የዘመን መለወጫ በአል ነው፡፡ በአሉ ከሁለት ሳምንት ላላነሰ ጊዜ በድምቀት የሚከበር ሲሆን አከባበሩም ቅደም ተከተላዊ ሂደትና በደረጃ እየሰፋ የሚሄድ የጋራ የአከባበር አድምታ ያለው ነው፡፡ ስለሆነም ፍቼ በቤተሰብ ወይም በጎረቤት ደረጃ ተሰባስቦ በማክበር የሚያበቃ ሳይሆን ከዚህም በሰፋ መልኩ በባህላዊ አደባባይ /ጉዱማሌ/ በጋራ በድምቀት የማክበር ሂደትን ያካትታል፡፡ ለአከባበሩ እያንዳንዱ ቤተሰብ በቅድሚያ እንደ አቅሙ ቅድመ ዝግጅት ያደርጋል፡፡ ከዚሁ አንጻር የቤቱ እመቤት ለበአሉ ቅቤ ታጠራቅማለች ወተት በታጠነ ማለፊያ “ቁሹና” /የወተት እቃ/ ታከማቻለች የእንሰት ውጤት የሆነውን ቆጮ ለበአሉ በሚሆን መጠንና ጥራት ከወዲሁ ታሰናዳለች፡፡


አባወራው በፍቼ ማግስት /በጫምበላላ/ እለት ለከብቱ የሚያበላውን ቦሌ ያዘጋጃል፡፡ ልጃገረዶች ለበአሉ መዋቢያ ለእግሮቻቸውና ለእጆቻቸው ጣቶች ቀለበት፣ ለፀጉራቸው መስሪያ “ሄቆ” /የተለያዩ ቀለማት ያሉት የቱባ ክር/፣ ጨሌ፣ ለአንገታቸው ቡሪቻና ዶቃ የጌጥ አይነት ለጸጉራቸው ማሸሚያ ግንባራቸው ላይ የሚያስሩትን በእራፊ ጨርቅ ላይ ደርድረው የሚሰፉትን ኢልካ /አዝራር/ ወዘተ የመሳሰለውን ያስገዛሉ እግራቸውና እጃቸው ላይ የሚቀቡትን እንሶስላ ያዘጋጃሉ፡፡

 

ፍቼ/Fichchaa/
የሲዳማ ሸንጎ
ፎቶ ከሲዳማ ባ/ቱ/መ/ኮ/መምሪያ

የፍቼ ዕለተ በዕለተ ቃዋዶ በአሉ መከበር የሚጀምረው ከአመሻሽ ጀምሮ ነው፡፡ ለዚህም በቅቤ የራሰ “ቡሪሳሜ” ከቆጮ የተሰራ ባህላዊ ምግብ “በሻፌታ” /ከሸክላ በተሰራ ባህላዊ ገበታ/ ቀርቦ በወተት በጋራ የመመገብ ሥርዓት የሚካዳሄድ ሲሆን አመጋገቡ የሚጀምረው በአካባቢ ከሚገኝ አንጋፋ ወይም ጪሜሳ /ብቁ አረጋዊ ቤት/ በመገኘት ገበታው ከቀረበ በኋላ ለቡራኬው ሁሉም እጁን በገበታው ትይዩ በመዘርጋት “ፍቼ ከዘመን ዘመን አድርሽን” በማለት አንጋፋው የሚሰነዝረውን ቡራኬ ቃል በጋራ በማስተጋባት አመጋገቡ ይጀምራል፡፡ ለመመገቢያ በቅድሚያ ለሁሉም በእሳት ሙቀት ተለብልቦ የለሰለሰ ኮባ ስለሚታደል አንጋፋው በኮባው ከገበታው በመጨበጥ ከጀመረ በኋላ በጋራ የመመገቡ ሂደት ይጀምራል፡፡ በፍቼ እለት በየቤቱ የሚቀርበው ገበታ ውስጥ ሥጋ አይካተትም፡፡ የዚህ አይነተኛው ምክንያት ከብቱም በሰላም ከዘመን ዘመን መሸጋገር ስላለበትና ሲዳማ ለከብት ከፍተኛ ግምት ያለው በመሆኑ ነው፡፡ቀደም ሲል ታርዶ ሲበላ የተረፈ ሥጋ እቤት ውስጥ ካለ በእለቱ ሥጋው ከቤት ውጪ እንያዲያድር ይደረጋል፡፡ አባወራ /የቤቱ ባለቤት /በፍቼ እለት ከቤቱና ከቤተሰቡ ተለይቶ ሌላጋ አያድርም፡፡ በዚህ እለት በየደጁ ከእርጥብ እንጨት “ሁሉቃ” የተሰኘ መሹለኪያ ተዘጋጅቶ አስቀድሞ አባወራው በሁሉቃው ውስጥ ከሾለከ በኋላ ቤተሰቡንና ከብቱን ያሾልካል ይህም በሰላም ከዘመን ዘመን የመሸጋገር ተምሳሌት ነው፡፡የጨንበላላ /የፍቼ ማግስት/ አከባበር

“ጫንበላላ” በፍቼ ማግስት በእለተ ቃዋለንካ  የሚከበር ሲሆን የፍቼ እለት በጋራ በተበላበት “ሻፌታ” /ባህላዊ ገበታ/ ውሃ ተሞልቶ ጠዋት ላይ አባወራውና ቤተሰቡ በውሃው ፊታቸውን በማስነካት እና ከዚሁ ጋር የቀረበውን ቅቤ አባወራው እየቆነጠረ የራሱን እና የቤተሰቡን አናት በማስነካት ወደ አዲሱ ዘመን የመሸጋገር ተምሳሌት ይከናወናል፡፡ የ“ጨንበላላ” እለት መሬት የማረስ እንጨት የመስበር የመሳሰለውን ተግባር ስለማይከናወን ለማገዶም ቢሆን አስፈላጊው እንጨት አስቀድሞ ይዘጋጃል፡፡ በዕለቱ አባወራው ከብቶቹን ማለፊያ “ካሎ” /የግጦሽ ሳር/ ውስጥ አሰማርቶ ለከብቱ ቦሌ ነስንሶ እያበላ ከብቱን አጥግቦ ያውላል፡፡ በዚህ ዕለት ልጆች ተሰባስበው በየቤቱ በመሄድ “አይዴ ጨምባላላ” እንኳን አደረሳችሁ ሲሉ የቤቱ ባለቤቶች ምላሹን “ኢሌ ኢሌ” ከዘመን ዘመን ያድርሳችሁ በማለት ልጆቹን አጥግበው ያበሏቸዋል፡፡ አናታቸውን ቅቤ ይቀቧቸዋል፡፡ በዚህ ዕለት ልጆችንም ሆነ ከብትን በአርጩሜ መምታት ነውርና አይደረጌ ነው፡፡ፍቼ ፋሎ

“ፍቼ ፋሎ” የፍቼን በዓል በጋራ በባህላዊ አደባባይ በድምቀት የማክበር ሥነ-ሥርዓት ነው፡፡ ስለሆነም በአመዛኙ የፍቼ ዕለተ ቀን በተከበረ በሶስተኛው ቀን አሊያም አንደአካባቢው በተመረጡ ቀጣይ ቀናት “ፈቺ ፋሎ” ወይም /ሻሻጋ/ በባህላዊ አደባባይ በጋራ ይከበራል፡፡አደባባዩ “ጉዱማሌ” ይባላል፡፡ “ጉዱማሌ” የፍቼ በአል በጋራ የሚከበርበትና እንዲሁም በሌላ ጊዜ የጎሳ መሪዎችና “ጭሜሳዎች” /ብቁ አረጋውያን/ ልዩ ልዩ ባህላዊ ስርዓት የሚያከናውኑበት የተከበረ ባህላዊ ስፍራ ነው፡፡ ህብረተሰብ በአሉን ለማክበር በጎሳ በጎሳ በመሆን በተለያየ ባህላዊ ጭፈራና ባህላዊ አልባሳት አጊጠው ወደ “ጉዱማሌ” ይጓዛሉ፡፡ ሁሉም በጋራ በየጎሳው ወደ “ጉዱማሌ” ከገቡ በኋላ የባህላዊው ሃይማኖት አባቶችና የጎሳ መሪዎች እንደ ማህበራዊ ደረጃቸው በየተራ ንግግር ያደርጋሉ፣ ይመርቃሉ፣ ባሮጌው ዘመንና በአዲሱ ዘመን ላይ ያተኮሩ መልእክቶች ያስተላልፋሉ፡፡ በጎው እንዲጎለብት አስከፊው እንዳይደገም ምክር አዘል መልዕክት ያስተላልፋሉ፤ ዘመኑ የሰላም፣ የብልጽግና የልማት ይሆን ዘንድ ቃል ቡራኬ ያደርሳሉ፡፡

(የሲዳማ ዞን ማስታወቂያና ባህል መምሪያ በ2001 ዓ.ም ካሳተመው ፍቼ መጽሄት የተወሰደ፡፡)
ምንጭ፦http://tubamegazine.blogspot.com/2012/08/fichchaa-2001.html
PROFILE
ሲዳማ ቡና 

ሙሉ ስም ፡ ሲዳማ ቡና ስፖርት ክለብ 
ምስረታ ፡ 1999
ስታዲየም ፡  ይርጋለም ስታዲየም ሀዋሳ ስታዲየም
የክለቡ የወቅቱ አሰልጣኝ ፡ ታረቀኝ አሰፋ  ዳኜ

ክለቡ ያገኛቸው ክብሮች ፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሊግ ሻምፒዮን 2001
ሲዳማ ቡና በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግ እየተሳተፈ ያለ ክለብ ነው፡፡ ክለቡ ከተመሰረተ ጥቂት አመታት ብቻ ቢቆጠሩም በብሔራዊ ሊግ ሻምፒዮን ሆኗል፡፡ በፕሚየርሊጉም ጥሩ ተፎካካሪ እየሆነ ይገኛል፡፡

ምስረታ 

ሲዳማ ቡና ስፖርት ክለብ የተመሰረተው በ 1999 ዓ/ም ነበር በደቡብ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና ላይ ሲዳማ ዞንን በመወከል ሥስት ክለቦች ይሳተፋሉ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ዳራ ከነማ ነበር፡፡ ዳራ በውድድሩ ለፍፃሜ በመድረስ ውጤታማ ይሆናል፡፡ ይህም ክልሉን በመወከል ሀዋሳ ላይ ወደተካሄደው የኢትዮጵያ የክልል ክለቦች ሻምፒዮና ከተሳተፉ አራት ቡድኖች አንዱ ለመሆን አበቃው፡፡ በዚህ ውድድር ቀዳሚዎቹን አራት ደረጃዎች የሚይዙ ቡድኖች ወደ ብሔራዊ ሊግ ሲያልፉ ዳራም ሦስተኛ ደረጃን አግኝቶ ስለነበር ብሔራዊ ሊጉን ተቀላቀለ፡፡ እናም ዳራ ከተማን ብቻ ይወክል የነበረው ክለብ መላውን የሲዳማ ዞንን እንዲወከል በማሰብ ሲዳማ የሚለውን ስያሜ አገኘ፡፡

ሲዳማ ቡና በብሔራዊ ሊግ
ሲዳማ ቡና ሁለት አመት በብሔራዊ ሊግ አሳልፏል፡፡ በመጀመሪያው አመት ቆይታው በ 2000 አራተኛ ደረጃን ይዞ ነው ያጠናቀቀው፡፡ በሁለተኛው አመት 2001 ውድድሩ በሁለት ምድብ ተከፍሎ ሲካሔድ በምድብ ሁለት የነበረው ሲዳማ በመጨረሻው ጨዋታ ከአየር ሀይል ጋር ያለ ግብ በመለያየት ከምድቡ ከሜታ አቦ ቢራ ቀጥሎ ሁለተኛ ደረጃን አግኝቷል፡፡ በዚህ ጨዋታ ቢሸነፍ ኖሮ ይህን ደረጃ አያገኝም፡፡ በቀጣይ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ለማለፍ ከየምድባቸው የመጀመሪያዎቹን ሁለት ደረጃዎች የያዙ አራት ቡድኖች  መካከል የአንድ ዙር ውድድር ተደረገ፡፡ ሻሸመኔ ከነማ፤ ደደቢትንና ሜታአቦ ቢራን በማሸነፍ ዘጠኝ ነጥብ የሰበሰበው ሲዳማ ቡና የብሔራዊ ሊግ ሻምፒዮን በመሆን ዓመቱን አጠናቀቀ፡፡ አጥቂውን ሰዳት የሱፍንና አሰልጣኙን ታረቀኝ አሰፋን በኮከብነት አስመርጧል፡፡

ሲዳማ ቡና በፕሪሚየር ሊግ
ሲዳማ ቡና ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈበት የ 2002 ፕሪሚየር ሊግ እንደመጀመሪያው ጥሩ ሊባል የሚችል ውጤት አስመዝግቧል፡፡ ከሻምፒዮኑ ቅ/ጊዮርጊስ ጋር በመጀመሪያው ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ አቻ መለያየቱ መከላከያን በይርጋለም ላይ 4 ለ 2 ማሸነፍ ከጠንካራ ክለቦች ጋር ያሳየውን ፉክክር ያመለክታል፡፡

የሲዳማ ቡና መሰረት
ሲዳማ ቡና ከሌሎች ክለቦች በተለየ ሁኔታ የፋይናንስ ምንጪን የዞኑን ህዝብ በማድረግ ይታወቃል፡፡ በአለም እውቅና በተሰጠው ቡና ስም የተሰየመው ይኸው ክለብ በዞኑ ህብረተሰብ ከፍተኛ የፋይናንስ ድጋፍ ይደረግለታል፡፡ ክለቡን በበላይነት የሚመራው የሲዳማ ዞን  ስፖርት ምክር ቤት ሲሆን  ክለቡ ሙሉ በሙሉ የሚንቀሳቀሰው ከሕብረተሰቡ በሚሰበሰብ ገንዘብ ነው፡፡ ከአርሶ አደሩ ጀምሮ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል አመታዊ መዋጮ ያደርጋል፡፡ በየአመቱ በሚካሔድ የገቢ ማሰባሰቢያም ውጤታማ ሆኗል፡፡ በ 2001 የብሔራዊ ሊግ ዋንጫ ማንሳቱን ተከትሎ ባደረገው የገቢ ማሰባሰቢያ ከ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ማሰባሰቡ ለዚህ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናም ሲዳማ ቡና በዚህ ረገድ ያለው ልምድ ለሌሎች ክለቦችም በአርአያነቱ የሚጠቀስ ነው፡፡
ምንጭ፦http://www.ethiofootball.com/team/profile.php?teamid=36
ሀዋሳ መጋቢት 5/2006 በሃዋሳ ከተማ የላቀ እንቅስቃሴ ላበረከቱ ሴቶችና በትምህርታቸው ጥሩ ውጤት ላስመዘገቡ ሴት ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት ተሰጠ፡፡
በኢትዮጵያ ለ38ኛ ጊዜ የተከበረውን  የሴቶች ቀን ምክንያት በማድረግ በተደረገው ሽልማት በሁሉም የትምህርት ደረጃ በትምህርታቸው የላቀ ውጤት ላመጡ 31 ሴት ተማሪዎች ለትምህርታቸው አጋዥ የሆኑ መጽሓፍት ተበርክቶላቸዋል።
በሃዋሳ ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች በመጀመሪያው መንፈቀ ዓመት ለሴት ተማሪዎች ልዩ የትምህርት ድጋፍ  ያደረጉ  ሞዴል ሴት መምህራን በከተማው ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች  ጉዳይ ጽሕፈት ቤት የተዘጋጀላቸውን የምስክር ወረቀትና የገንዘብ ሽልማት ተቀብለዋል።
በከተማው በተለያዩ የልማት ቡድን በመደራጀት ውጤታማ የሆኑ 16 የልማት ቡድኖችም የተዘጋጀላቸውን ሽልማት ተረክበዋል፡፡
በቅርቡ በተጀመረው የከተማ ጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም በስምንቱም ክፍለ ከተሞች አበረታች ውጤት ያስመዘገቡ ስምንት ጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችም ተሸላሚዎች ሆነዋል፡፡
ከተሸላሚ ተማሪዎች መካከል ተማሪ ዝናሽ ዘንባባና ተማሪ አብጊያ ብርሃኑ በሰጡት አስተያየት ሴቶች ባለፉት ስርዓት ከነበረው ጭቆናና አድሎአዊ አሰራር ተላቀው በልማትና በመልካም አስተዳደር እኩል ተጠቃሚነታቸው መረጋገጡ እጅግ ያኮራናል ብለዋል፡፡
የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ  ጉዳይ መምሪያ  ኃላፊ ወይዘሮ ገነት ገረመው  እንደተናገሩት በከተማው የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ  አቅም ለማሻሻል የብድር አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በርካታ ሴቶች በማህበር ተደራጅተውና ሃብት አፍርተው ወደ ባለሃብትነት መሸጋገራቸውንና ለብዙዎች የስራ እድል መፍጠራቸውንም ተናግረዋል፡፡
ምንጭ፦ኢዜኣ