POWr Social Media Icons

Wednesday, March 12, 2014

http://commons.wikimedia.org/wiki/File:Fichchee-_The_New_Year_of_Sidama-_The_Sidama_people_celebrate_the_festival_en_mass_in_their_sacred_place_called_Gudumale_which_is_located_on_the_beautiful_city_of_Hawassa-_2013-12-18_17-37.jpg
በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ዉስጥ ከሚገኙ አስራ ሶስት ዞኖች መካከል እጅግ በርካታ የሆነ የህዝብ ቁጥር ያለዉ የሲዳማ ዞን ነዉ።
በያዝነዉ አመት በተደረገ የጥናት መረጃ የሲዳማ ዞን 3.2 ሚሊዮን ህዝብ መያዙ ተነግሮአል። የለቱ የባህል ጥንቅራችን የሲዳማ ብሄረሰብ ባህላዊ ገጽታዎችን ይቃኛል።
በደቡብ ኢትዮጽያ በይርጋለም ከተማ ነዋሪ የሆነዉ ጋዜጠኛ ቦጋለ ጥላሁን የረጅም ግዜ አድማጫችን ብቻ ሳይሆን ተሳታፊም ነዉ። በኢትዮጽያ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችን አቅፎ በሚገኘዉ በደቡብ ዞን አጓጓጊ የሆኑ የተፈጥሮ መስቦችን አሉት የሚለን ጋዜጠኛ ቦጋለ ከአዲስ አበባ 320 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘዉ በይርጋለም ከተማ ነዋሪ ሲሆን ስለ ሲዳማ ብሄረሰብ ባህል በተለይም ሆሪ ተብሎ ስለሚታወቀዉ ያላገቡ የሲዳማ ልጃገረዶች የዘፈን ዉዝዋዜ፤ ስለ ቋንቋዉ፣ ስለ ሰርግ፣ እንዲሁም ሌሎች የባህል ገጽታዎች ያጫዉተናል። በሌላ በኩል በሲዳማ ዞን ባህልና እስፖርት ማዕከል ድምጻዊ የሆነችዉ ትብለጽ ተከስተ በሲዳማ ቋንቋ በምታዜመዉ ዘመናዊ ሙዚቃዋ በአካባቢዉ ተወዳጅነትን ማትረፍዋ ነገርላታል። የሲዳማ ዞን የተፈጥሮ መስቦች ያሉበት በቱሪስቶች የሚወደድ ድንቅ የተፈጥሮ ጸጋ ያለዉም አካባቢ ነዉ መረሃ ግብሩን ያድምጡ


ሪፖርተር ጋዜጣ 12March2014 -

 መጋቢት 3, 2006 ዓ.ም.


-የፓርላማ አባላት ከሕገ መንግሥቱ ጋር እንዲጣጣም ጠይቀዋል
የአገሪቱ ፕሬዚዳንትን ለሕግ ታራሚዎች ይቅርታ የማድረግ ሥልጣን የሚቀንስ አዲስ ‹‹የይቅርታ አሰጣጥና አፈጻጸም ሥነ ሥርዓት›› ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማው ቀረበ፡፡ አንዳንድ የፓርላማው አባላት ረቂቅ አዋጁ ከሕገ መንግሥቱ ጋር ይቃረናል በማለት እንዲስተካከል ጠይቀዋል፡፡

የፕሬዚዳንቱን ሥልጣንና ተግባር የሚዘረዝረው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 71 (7) ‹‹ፕሬዚዳንቱ በሕግ መሠረት ይቅርታ ያደርጋል›› በማለት ይደነግጋል፡፡
በ1996 ዓ.ም. የወጣው በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ የሚገኘው የይቅርታ ሥነ ሥርዓት አዋጅም በሕገ መንግሥቱ ለፕሬዚዳንቱ የተሰጠውን ይቅርታ የማድረግ ሥልጣን ያጠናክረዋል፡፡ በዚህ አዋጅ መሠረት ፕሬዚዳንቱ የይቅርታ ቦርድ የውሳኔ ሐሳብን መሠረት በማድረግ፣ እንዲሁም በውሳኔ ሐሳቡ ላይ የቀረቡ መረጃዎችን ፕሬዚዳንቱ በራሱ መመዘን ለሕግ ታራሚዎች ይቅርታ እንዲያደርግ ወይም እንዲከለክል ሥልጣን ይሰጠዋል፡፡ የፕሬዚዳንቱን ይቅርታ ያገኘ ታራሚ በሕጉ መሠረት የተጣለበትን ጥሶ የተገኘ ከሆነ በይቅርታ ቦርዱ የውሳኔ ሐሳብ አቅራቢነት ፕሬዚዳንቱ የሰጠውን ይቅርታ የማንሳት መብት በዚሁ በሥራ ላይ ባለው አዋጅ ለፕሬዚዳንቱ ተሰጥቷል፡፡ 
ባለፈው ማክሰኞ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ግን፣ ‹‹ፕሬዚዳንቱ የይቅርታ ቦርድን የውሳኔ ሐሳብ መሠረት በማድረግ ይቅርታ ይሰጣል፤›› ሲል በረቂቁ ክፍል ሁለት አንቀጽ 4 (1) ላይ አስቀምጧል፡፡ በማከልም ቦርዱ ለፕሬዚዳንቱ የሚልከው የውሳኔ ሐሳብ ይቅርታ የተወሰነላቸውን ታራሚዎች በመተለከተ ብቻ ነው፡፡
 በቦርዱ ውሳኔ አቅራቢነት ፕሬዚዳንቱ ቀደም ሲል የሚሰጠውን ይቅርታ የመሰረዝ መብት አሁን በሥራ ላይ ባለው አዋጅ ቢኖረውም፣ ለፓርላማው የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ግን በፕሬዚዳንቱ የተሰጠ ይቅርታ ተጥሶ ወይም የተጭበረበረ መሆኑ ሲረጋገጥ ቦርዱ ያለፕሬዚዳንቱ ውሳኔ በራሱ እንዲሰረዝ ያደርጋል ይላል፡፡ ‹‹ቦርዱ ይቅርታ የሚሰጣቸውን ሰዎች ብቻ ለይቶ ለፕሬዚዳንቱ ስለሚያቀርብ ፕሬዚዳንቱም በቦርዱ የውሳኔ ሐሳብ መሠረት ብቻ ይቅርታ ስለሚሰጡ የይቅርታ መሰረዝን በተመለከተ ወደ ፕሬዚዳንቱ የውሳኔ ሐሳብ ማቅረብ ተገቢነት የለውም፤›› በማለት ከረቂቅ አዋጁ ጋር የተያያዘው ማብራሪያ ያስረዳል፡፡
የተሰጠ ይቅርታ ዋጋ የሚያጣባቸው ምክንያቶች ሁለት መሆናቸውን፣ እነዚህም የተሰጠው ይቅርታ በተጭበረበረ ማስረጃ ላይ የተመሠረተ እንደሆነና ይቅርታው ሲሰጥ የተቀመጠው ቅድመ ሁኔታ ከተጣሰ የሚሉ ምክንያቶች ናቸው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ለፕሬዚዳንቱ የሚሰጠውን ለታራሚዎች ይቅርታ የማድረግ ኃላፊነት ይጋፋል በማለት አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት ረቂቅ አዋጁ መስተካከል እንደሚገባው ጠይቀዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ በቦርዱ ውሳኔ ይቅርታ ይሰጣሉ በማለት ረቂቅ አዋጁ ያስቀምጣል፡፡ ነገር ግን ፕሬዚዳንቱ ባይቀበሉትስ? ይህ ማለት ውሳኔው ያለቀው እታች ነው ማለት ነው በማለት የረቂቅ አዋጁን ድንጋጌ ተችተዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ የሰጠውን ይቅርታ ቦርዱ ያለፕሬዚዳንቱ እውቅና ማንሳት እንደሚችል የሚገልጽ ድንጋጌ መካተቱ ተገቢ አለመሆኑን አባላቱ ገልጸዋል፡፡
 ከዚህ በተጨማሪም የፕሬዚዳንቱ ይቅርታ የመስጠት ሥልጣን እንዳስፈላጊነቱ አግባብ ላለው የክልል መንግሥት አካል በውክልና መስጠትና የይቅርታ ጥያቄዎችን የሚመረምረው ቦርድም በተመሳሳይ በክልል ለሚቋቋሙ ቦርዶች ውክልና ሊሰጥ እንደሚችል በረቂቅ አዋጁ ተካቷል፡፡ ረቂቅ አዋጁ በሥራ ላይ ካለው አዋጅ በተለየ ሁኔታ ይቅርታን የሚያስከለክሉ ወንጀሎችን ይዘረዝራል፡፡ ሙስና፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ግብረ ሰዶም፣ ሽብርተኝነት፣ አደገኛ ዕፅ ማምረት፣ ማዘዋወር፣ ይዞ መገኘት ወይም መጠቀም፣ በመሠረተ ልማት አውታሮች ላይ የሚፈጸም ወንጀል፣ በሴቶችና በሕፃናት ላይ የሚፈጸም የጠለፋና የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ይህ ቢሆንም መንግሥት የይቅርታ ዓላማን ያሳካል ብሎ ካመነበት በረቂቅ አዋጁ ይቅርታን የሚያስከለክሉ ወንጀሎች ምክንያት ሆነው ሊቀርቡ እንደማይችሉ ረቂቅ አዋጁ ይደነግጋል፡፡
 በተጨማሪ መንግሥት በሚያወጣው ደንብ መሠረት በሚዘረዘሩ ሌሎች ወንጀሎች ይቅርታ የማይጠየቅባቸው ሊኖሩ እንደሚችሉ ያስቀምጣል፡፡ የፓርላማው አንዳንድ አባላት ከላይ የተጠቀሰውን ድንጋጌ፣ ረቂቅ አዋጁ ይቅርታ የሚከለከልባቸውን ወንጀሎች መዘርዘር ከጀመረ በኋላ ሌሎች ወንጀሎች ደግሞ በሚወጣ ደንብ እንዲዘረዘሩ ማለቱ ግራ እንደሚያጋባቸው፣ የወንጀል ዓይነቶቹን  ሙሉ በሙሉ መዘርዘር ወይም ይቅርታ የሚያስከለክልባቸውን መርህ ብቻ ማስቀመጥ ነው በማለት እንዲስተካከል ጠይቀዋል፡፡
ረቂቅ አዋጁ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕግ አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ ለሚመራው የፓርላማው የሕግ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር ዕይታ ተመርቷል፡፡ 

ኮከቤ የማነ የፊኛ ካንሰር እንዳለበት ያወቀው ከአሥር ዓመታት በፊት ነበር፡፡ ህመሙን ካወቀ በኋላ ከሌሎች የካንሰር ሕመምተኞች ሰምቶ ሕመሜን ቢያስታግስልኝ በማለት ወደ ሳቅ ትምህርት ቤት ይቀላቀላል፡፡
በወቅቱ ሞትን እስከመመኘት ድረስ በበሽታ ይሰቃይ እንደነበር ይናገራል፡፡ ኮከቤ የኬሞቴራፒ ሕክምና ይፈጥርበት የነበረውን ሕመም ለመቋቋምና ስቃዩን ለማስታገስ ከረዱት ዋነኛው ሳቅ እንደሆነ ይገልጻል፡፡  
የካንሰር ሕክምናን አብረውት ይከታተሉ ከነበሩት መካከል ብዙዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ ተመልክቷል፡፡ በአካል የሚያውቃቸው ሲያልፉ ከማየቱም በላይ ሕይወቱ አደጋ ላይ በወደቀበት ወቅት ራሱን መሳቅ አስተምሯል፡፡ ኮከቤ ወደኋላ በትዝታ እየቆዘመ ‹‹ዕድለኛ ነኝ›› ይላል፡፡ 
ዛሬ የ45 ዓመት ጐልማሳ ነው፤ ባለትዳርና የልጆች አባትም ነው፡፡ በቤተ መንግሥት ውስጥ የሜዳ ቴኒስ አጫዋች የሆነው ኮከቤ ‹‹የእኔ ደስተኛ መሆን ለቤተሰቦቼም ተርፏል፤ ማታ ቤት እስክገባ ይቸኩላሉ፡፡ ምንም ችግር ቢኖር በሳቅ እናሳልፈዋለን፤›› ይላል፡፡ ደስተኛ መሆኑን የሚገልጸው ኮከቤ ልጆቹ እሱን በማየት ሲስቁ ማየት ያስደስተዋል፡፡ 
በዓለም የድንቅ ነገሮች መዝገብ ላይ ለሦስት ሰዓት ከስድስት ደቂቃ ያለማቋረጥ በመሳቅ ሪከርድ የጨበጠና ‹‹የዓለም የሳቅ ንጉሥ›› የሚል መጠሪያ ያገኘው በላቸው ግርማ፣ ኮከቤን ለመሰሉና ሌሎች የሳቅ ትምህርት ቤት ካቋቋመ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በእነዚህ ዓመታት ወደ ትምህርት በመሔድ ስለ ሳቅ፣ አሳሳቅንና በሌሎች ተያያዥ ትምህርቶች ለአንድ ወር ሠልጥነው የወጡ ተማሪዎች አሉ፡፡ በአፍሪካ ባሉ አገሮች ጅማሮዎች ቢኖሩም በኢትዮጵያ የሚገኘው ትምህርት ቤት የቆየና ግንባር ቀደም እንደሆነ የተለያዩ ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡ 
በላቸው ስለሳቅ ትምህርት ቤት ሲናገር በዓለም ላይ ባሉ የተለያዩ ሀገሮች ሳቅን እንደ አማራጭ ሕክምና መስጫ ለመጠቀም ምርምር ያደረጉ ሰዎችን መነሻ እንዳደረገ ይገልጻል፡፡ በሕፃናት፣ ካንሰርና ኤችአይቪን በመሰሉ በሽታዎች በተጠቁ፣ በጐዳና ተዳዳሪዎች፣ በቤተሰብ እንዲሁም ሌሎች የማኅበረሰቡ አካላት ላይ የጀመረውን የሳቅ ሕክምና  ትልቅ ግምት የሚሰጠው እንደሆነ ይናገራል፡፡ 
ከዓመታት በፊት የቀድሞ ባለቤቱን በኤችአይቪ ኤድስ ያጣውና ቤቱ በእሳት የወደመበት በላቸው ሳቂታና ደስተኛ መሆንን ያለፈ ሐዘንን ከመርሳትና ከይቅር ባይነት መንፈስ ጋር ያያይዘዋል፡፡ በሳቅ ጤነኛና ደስተኛ፣ ከሰዎቸ ጋር ያለ ግንኙነትንም ሰላማዊ ማድረግ እንደሚቻልም ያምናል፡፡ 
ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከሰውነት የደም ዝውውር፣ ከስሜት ህዋሳት፣ የማስታወስ ችሎታ፣ አተነፋፈስ፣ የአካል እንቅስቃሴ፣ እይታና ማዳመጥ ጋር ባለው ተዛማጅነት ለሰው ልጅ መሳቅ ጠቀሜታው የጐላ ነው፡፡ በላቸውም ‹‹ብዙ በተሳቀ ቀን የመማር፣ መሥራት፣ ማሰብ ችሎታ አብሮ ያድጋል›› ይላል፡፡ 
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የካንሰር ስፔሻሊስት የሆኑትን ዶክተር ቦጋለ ሰለሞንን ከካንሰር ሕክምና ጋር በተያያዘ ስለ ሳቅ ሕክምና አዎንታዊ ተፅዕኖ የሚያውቁት አለመኖሩን ገልጸውልናል፡፡  
ሔዋን መላኩ ጊዜውን በትክክል ባታስታውስም ከዓመታት በፊት ደስታ ከሕይወቷ የጠፋ መሆኑን ትናገራለች፡፡ ለባለቤቷና ለልጆቿ ደስታ የሚሰጣቸው ነገር ለሷ ትርጉም አልባ ስለሚሆንባት አንዳች ክፍተት ተፈጥሯል፡፡ ለችግሯ እንደ አማራጭ የወሰደችው ልጆቿን ትምህርት ቤት ስታመላልስ ወዳየችው የሳቅ ትምህርት ቤት ጎራ ማለት ነበር፡፡ 
ሔዋን እንደምትገልጸው ስለሳቅ ከተማረች በኋላ ከቤተሰቧ ጋር ያላት ሕይወት ተለውጧል፡፡ ‹‹የመሳቅ ትርጉም ስለማይገባኝ ልጄ ስትስቅ ምን የሚያስቅ ነገር አለ? ብዬ እጠይቅ ነበር፡፡ ከቤት ውጪ፣ ለምሳሌ ታክሲ ውስጥ ብዙ ሰው ይጋጫል፤ ዛሬ ዛሬ እኔ በቻልኩት መጠን ነገሮችን ስቄ በማለፍ ጥሩ ስሜት ለመፍጠር እሞክራለሁ፤›› የምትለው ሔዋን መሳቅ ስታበዛ አንዳንዶች ጤናዋን እንደሚጠራጠሩ ትገልጻለች፡፡ ከማንኛውም ሰው ጋር ብትሆን ከሳቅ እንደማትቆጠብ የምትናገረው ሔዋን ከባለቤቷ ጋር ያላት ግንኙነት መለወጡንም ትናገራለች፡፡ 
እውን ሰዎች ከሳቅ ጋር በተያያዘ በአዕምሮአቸው፣ በአስተሳሰባቸውና ከሰዎች ጋር ባላቸው ግንኙነት የሚመጣ ለውጥ ስለመኖሩ የሥነ ልቦና ባለሙያ የሆነችውን ሐና አምሃን አነጋግረናል፡፡ ሐና እንደገለጸችው በበርካታ ሀገሮች ላይ የሳቅ ሕክምና (laughter therapy) ከተሰጠ ከሥነ ልቦና ጋር ለሚያያዙ አንዳንድ ችግሮች በተወሰነ ደረጃ መፍትሔ ይሰጣል፡፡ 
ሐና ‹‹ሁሉም ዓይነት ሳቅ የደስታ ምንጭ ነው ማለት ባይቻልም ሰዎች ሲደሰቱ ፈገግ ማለታቸውና መሳቃቸው አይቀርም፡፡ ያለምክንያት በመሳቅ ብቻ ደስታን ወደ ሕይወት ማምጣት ይቻላል ባይባልም የሰው ልጅ ሲስቅ በአዕምሮው የሚነቃቁ ሕዋሳት ስላሉ ደስታ ይፈጠራል፤›› ትላለች፡፡ 
እንደ ሐና ገለጻ የሥራ ባህርያቸው ሆኖ ሁሉንም ሰው በፈገግታ የሚቀበሉ ሰዎች ሁልጊዜ ደስተኛ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ከሁሉም ዓይነት ሳቅ ከእውነተኛ ደስታ የመነጨ ሳቅ የተሻለ ነው፡፡ ሳቅ አንድ ሰው ከሌሎች ሰዎች ጋር ባለው ግንኙነት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አለው፡፡ ፈገግ እንኳን ሲል የማታይ ሰው ቢስቅ በአካባቢው ባሉ ሰዎች ቀለል ያለ ስሜት ይፈጥርና ቀና የሆነ አመለካከት እንዲኖራቸውና ግንኙነታቸው እንዲያድግ ሲረዳ ይታያል፡፡ 
ሐና ‹‹አንድ ሰው ራስን እስከማጥፋት ድረስ የሚያደርስ የሥነ ልቦና ቀውስ ውስጥ ቢሆን ሙሉ በሙሉ በሳቅ ይፈወሳል ማለት ሳይሆን፣ ሳቅ የሚፈጥረው ደስታ የሰው ልጅ ስለ ራሱና አካባቢው ያለውን አመለካከት አቃንቶ ከውጥረት ሊያወጣ ይችላል፤›› ትላለች፡፡     
ቃል ኪዳን ጀምበሬ የተወለደችው ጅማ ነው፤ በጳውሎስ ሆስፒታል ውስጥ የቢሮ ረዳት ናት፡፡ ለሕክምና የሚሄዱ ሰዎችን ካርድ ከማውጣት አንስቶ ሌላም እርዳታ መስጠት ከጀመረች ሦስት ዓመት አስቆጥራለች፡፡ ቃል ኪዳን ከልጅነቷ ጀምሮ ሳቂታና ተጫዋች ብትሆንም የሳቅ ትምህርት ቤት ገብታለች፡፡ 
መሳቅ ለበርካታ በሽታዎች መድኃኒት እንደሆነ የምታምነው ቃልኪዳን ከቀሪው ተማሪዎች በተለየ ሳቂታ በመሆኗ ‹‹አምባሳደር›› የሚል ማዕረግ ያገኘችው ቃልኪዳን ሳቅ በሥራ ቦታዋ ለመታከም የሚመጡ ሕመምተኞችን እንደምትረዳበት ትናገራለች፡፡ ምጥ የያዛቸው ሴቶች ከባድ ሕመም ውስጥ ያሉ ታካሚዎች ወይም ሌሎችን በፈገግታ ትቀበላቸዋለች፡፡ ሕመምተኞችን ባትፈውሳቸውም ጥሩ ስሜት እንዲሰማቸው ለማድረግ ሳቋን እንደምትጠቀምበትም ትናገራለች፡፡ 
በእርግጥ በርካቶች ‹‹ሳቅ የደስታ ምንጭ ነው፤›› እና ሌላም አባባልን እያጣቀሱ ሳቅን ከደስታ ጋር አያይዘው ሲስቁ አልያም ለመሳቅ ሲሞክሩ ይታያሉ፡፡ በሌላ በኩል ደስታ የሚሰጠው ሳቅ ሳይሆን የሰው ልጅ የእውነት የሚስቀው ደስተኛ ሲሆን ነው የሚሉም አሉ፡፡ ‹‹ብዙ ስሜቴን በሳቅ የማሳልፍ ቢሆንም አላዝንም ማለት አይደለም›› የምትለው ቃልኪዳን በተለይ እናቷን እንዲሁም ልጇን በሞት ያጣችበትን ጊዜ አስታውሳለች፡፡
የሦስት ልጆች እናት የሆነችው ቃልኪዳን ልጆቿ አጥፍተው ተናዳባቸው እንኳን በሳቅ ያለፈችበት ጊዜ ቢኖርም ‹‹የማምንበትን ነገር የሚነኩ›› የምትላቸው ጉዳዮች ላይ ኮስታራ እንደምትሆን ትገልጻለች፡፡ ሁሉን በሳቅ የምታልፍ መሆኗን በማየት የሚያስከፋ ነገር አድርገው እንኳን ስቃ እንድታልፍ የሚጠብቁ ሰዎችም ያጋጥሟታል፡፡ በዚህም ዛሬ ላይ ሆና ‹‹ያንን ስቄ ማለፍ አልነበረብኝም፤›› የምትላቸው አጋጣሚዎችም አሏት፡፡ 
በሳቅ ትምህርት ቤት የሚሰጠው ትምህርት ለአንድ ወር የሚቆይ ሲሆን ንድፈ ሐሳብና ተግባርን ያጠቃልላል፡፡ ተማሪዎች ስለሳቅ ምንነት የሳቅ ዓይነቶችና ጠቀሜታ ተምረው ወደ ተግባር ሲገቡ በነፃነት እንዲስቁ በተለያዩ የአካል እንቅስቃሴዎች ይታገዛሉ፡፡ 
የሳቅ ትምህርት ቤት ውስጥ ያገኘናቸው ተማሪዎች ‹‹ተፈስሀ ተሀስየ እሰየ›› የሚሉት ቃላት የሳቅ ትርጓሜ ናቸው ይላሉ ቃላቱን ሲደጋግሙም ይሰማሉ፡፡ ተማሪዎቹ ጐንበስ ቀና እያሉ ከመሬት ላይ እየተንከባለሉ ያለማቋረጥ ሲስቁ በአካባቢው ተገኝቶ የሚመለከታቸውን ሰው ፈገግ ያሰኛሉ፡፡ ብዙዎቹ ተማሪዎች ‹‹ሳቅ ከሰው ወደ ሰው ይጋባል›› ይላሉ፡፡ 
ትምህርቱን ካጠናቀቁ በኋላ ሙያቸው ለሌሎች የሕክምና እርዳታ ከመስጠት ጋር የተገናኘ ተማሪዎችና በሳቃቸው ለየት ያሉ የሚባሉት ፕሮፌሽናል የሳቅ ባለሙያ ሆነው ይመረቃሉ፡፡ ቀሪዎቹም ራሳቸውንና አካባቢያቸውን በተማሩት ትምህርት የተሻለ ያደርጋሉ በሚል እምነት የሳቅ ተመራቂ ይሆናሉ፡፡    
ሪፖርተር ጋዜጣ 12March2014 -
 መጋቢት 3, 2006 ዓ.ም.