POWr Social Media Icons

Tuesday, January 14, 2014

ሃዋሳ ጥር 6/2006 በሲዳማ ዞን  ባለፉት ስድስት ወራት ከ1ሚሊዮን  ለሚበልጡ የቤት እንስሳት የተለያዩ በሽታዎች  መከላከያ ክትባትና ህክምና መሰጠቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ ።
በመምሪያው የግብርና ልማት እቅድ ኦፊሰር አቶ ደርቤ በትራ ዛሬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች ያለውን የእንስሳት ሃብት በዘመናዊ መንገድ በማርባት አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥረት እየተደረገ ነው ።
አርሶ አደሮቹ ከእንስሳት ሃብቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በጤና አጠባበቅ ረገድ መንግስት በሰጠው ትኩረት ለ692 ሺህ057 እንስሳት የተለያዩ በሽታ መከላከያ ክትባት፣ ለ429ሺህ 586ቱ ደግሞ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን አስታውቀዋል ።
ለቤት እንስሳቱ የበሽታ መከላከያ ክትባቱና ህክምናው የተሰጠው የእንስሳት ህክምና ባለሙያዎች ከቦታ ቦታ በመዘዋወርና በእንስሳት ጤና ከላዎች በመገኘት መሆኑን ተናግረዋል ።
የህክምና አገልግሎቱ የእንስሳት ሰውነት በማቁሰል ለሞት የሚዳርጉ የጎሮርሳ፣ የጉርብርብ፣የአባጎርባና አባሰንጋ፣ የሰንባ በሽታን ለመቆጣጠር  የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል ፡፡
መምሪያው በዚህ አመት  156 ሺህ 700 የዳልጋ ከብቶች፣ ፍየሎችና በጎች በማድለብና በማሞከት  ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘት መቻሉን አቶ በትራ ተናግረዋል፡፡
በቻይና ዋና ከተማ ቤጂንግ የሚገኘው የስታር ባክስ ኬሪ ማዕከል ለቡና መገኛዋ ኢትዮጵያ ክብር የቡና ቀመሳ ሥነ ሥርዓት አካሄደ፡፡
እንደ ዋልታ ዘገባ፣ ስታር ባክስ የኢትዮጵያ ቡና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ የሚያደርገው ጥረት በኢትዮጵያ ኤምባሲ አንድ የሥራ ኃላፊ ምሥጋና ቀርቦለታል፡፡ በቻይና የስታር ባክስ ኩባንያ ባለሥልጣን ስለኢትዮጵያ የተፈጥሮ ቡና ጣዕም መልካምነት በሥነ ሥርዓቱ ላይ መግለጻቸው ታውቋል፡፡ ስታር ባክስ ለዓለም ገበያ ከሚያቀርባቸው የተፈጥሮ ቡናዎች ልዩ ጣዕም ያላቸው የሊሙና የሲዳማ ቡና እንደሚገኙበት ዘገባው አስረድቷል፡፡