የፀረ ሙስና ኮሚሽን በቡና ወጪ ንግድ ችግሮች ላይ ያካሄደው ጥናት መጠናቀቁ ተሰማ

የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በቡና የወጪ ንግድ ላይ በተፈጠሩ ችግሮች ዙሪያ ሲያካሂድ የቆየውን ጥናት ማጠናቀቁን ምንጮች ገለጹ፡፡
ኮሚሽኑ ሕገወጥ ሥራ ሠርተዋል ባላቸው ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጋር እየተነጋገረ መሆኑ ታውቋል፡፡
የፀረ ሙስና ኮሚሽን ረዘም ያለ ጊዜ ወስዶ ሲያካሂድ የቆየው ምርመራዊ ጥናት ተጠያቂ የሚሆኑትን እንደለየ የሚናገሩት ምንጮች፣ በቀጣይነት መወሰድ ባለበት ሕጋዊ ወይም አስተዳደራዊ ዕርምጃ ላይ በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ ውይይት እየተካሄደ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ወዶ አጦ፣ ጥናቱ እየተካሄደ መሆኑን ነገር ግን ገና አለመጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡
የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ምንጮች ግን ኮሚሽኑ በንግድ ሚኒስቴርና በቡና ላኪዎች ላይ ትኩረት አድርጎ ሲያካሂድ የቆየውን ጥናት ማጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡ ጥናቱ ትኩረት ካደረገባቸው ጉዳዮች መካከል ንግድ ሚኒስቴር በቡና ላኪዎች ላይ በቂ ክትትልና ቁጥጥር አለማድረጉ፣ የተሟላ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት አለመኖሩ፣ በሁሉም ድርጅቶች ላይ ወቅቱን የጠበቀ የቡና ክምችት ቆጠራ አለመካሄዱ፣ ለውጭ ገበያ የተዘጋጀን ቡና ኤክስፖርት በማያደርጉ  ነጋዴዎች ላይ ዕርምጃ አለመወሰዱ፣ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በሚሸጥ የቡና ገለፈት ላይ ተገቢውን ቁጥጥርና ክትትል አለመደረጉ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ከዚህ በላይ ጐልቶ የታየው ችግር ደግሞ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ሳይሰጥ ቡናን ወደ ውጭ አገር ኤክስፖርት ማድረግ ነው፡፡
ብሔራዊ ባንክ ወደ ውጭ ለሚላክ ቡና የሚሰጠው ፈቃድ አለ፡፡ ይህ ፈቃድ ካልተገኘም ቡና ወደ ውጭ መላክ የተከለከለ ነው፡፡ ነገር ግን የተወሰኑ ነጋዴዎች ይህ ፈቃድ ሳይኖራቸው፣ ፈቃድ እንዳላቸው በማስመሰል በአሥር ሺሕ ቶን የሚቆጠር ቡና ወደ ውጭ መላካቸውና ገንዘቡም የት እንደገባ እንደማይታወቅ ኮሚሽኑ ባካሄደው ጥናት ተመልክቷል፡፡
በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ኮሚሽኑ ባካሄደው ዝርዝር ጥናት ችግሩን ፈጥረዋል ተብለው የተጠረጠሩ አካላቶችን እንደለየ ምንጮች ይናገራሉ፡፡ ከዚህም በላይ ለውጭ ገበያ የተዘጋጀን ቡና ለአገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ አገሪቱ ማግኘት ያለባትን የውጭ ምንዛሪ አሳጥተዋል የተባሉ የቡና ነጋዴዎች ላይ ጥናቱ አነጣጥሯል፡፡ 
ከዚህ ቀደም በትክክለኛ መንገድ ሥራችንን እየሠራን ነው የሚሉ ነጋዴዎች በዚህ ጉዳይ ላይ በተደጋጋሚ ቅሬታ ሲያነሱ ነበር፡፡ ቅሬታው የሚቀርብለት ንግድ ሚኒስቴር አስፈላጊውን ዕርምጃ አይወስድም የሚሉ ትችቶች ሲቀርቡበትም እንደነበር ይታወቃል፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር