አንድነትና መድረክ ተለያዩ

ላለፉት ስድስት ዓመታት ገደማ ያህል በጋራ ለመሥራት ተስማምተው የተቃውሞ ጐራው ላይ በጋራ ሲሠሩ የነበሩት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) እና አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) የነበራቸውን አብሮ የመሥራት ስምምነት አቋርጠው ተለያዩ፡፡ 
ሁለቱ ፓርቲዎች የቀድሞው የአንድነት ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው ሰጥተውታል በተባለው አስተያየት የተነሳ እሰጥ አገባ ውስጥ መግባታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ አስተያየቱን አንድነት ያስተባብል በሚል ከመድረክ የቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ለፓርቲዎቹ መለያየት ከፍተኛውን ድርሻ መውሰዱን የሁለቱ ፓርቲዎች ባለድርሻ አካላት መግለጻቸውን መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡ 
ከሁለት ሳምንታት በፊት ዳግም የመድረክ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ለአንድነት እስከ ኅዳር 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ ገደብ መስጠታቸውን መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡ 
በዚህም መሠረት አንድነት ለመድረክ ኅዳር 11 ቀን 2007 ዓ.ም. በጻፈው የመልስ ደብዳቤ፣ ከመድረክ አባልነት መውጣቱን ገልጾ መጻፉን የመድረክ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጥላሁን እንደሻው ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡
የአንድነት ብሔራዊ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አበበ አካሉ በበኩላቸው፣ ‹‹ከመድረክ ጋር በይፋ ተለያይተናል፤ ፊርማችንን ቀደናል፤›› በማለት ከመድረክ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ማቋረጣቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ለሁለቱም የፓርቲ አመራሮች ምርጫ በተቃረበበት ወቅት እንዲህ ዓይነት ውሳኔ መውሰድ አጠቃላይ ሰላማዊ ትግሉን አይጐዳውም ወይ የሚል ጥያቄ ሪፖርተር አቅርቦ ነበር፡፡ የሁለቱም ፓርቲ አመራሮች ጉዳት ማስከተሉን ተቀብለው ነገር ግን ከአቅም በላይ በመሆኑ መለያየት መፍትሔ እንደሆነ አስረግጠው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በዚህ ረገድም ‹‹ይሄ እኮ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ የተቃውሞ ፓርቲዎች የጋራ ትብብር አለመኖር፤ ውህደት አለመኖር የኢትዮጵያን ሕዝብ ትግል ይጐዳዋል፡፡ ይህንን እናውቀዋለን፡፡ ነገር ግን ትግሉን እየጐዳው ቢሆንም አብሮ የማይሄድና የማይሆን ነገር ሲታይ አብረህ መቀጠል አትችልም፡፡ መለያየት አለብህ፤›› በማለት ልዩነቱ በመስፋቱ መለያየቱ የግድ እንደሆነ አቶ አበበ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
‹‹እንዲህ ዓይነት ውሳኔዎች ትግሉን እንደሚጐዳ ይታወቃል፤›› በማለት የገለጹት አቶ ጥላሁን በበኩላቸው፣ ‹‹የተቃውሞ ጐራውን ለመጉዳት የተነሱና የተመኙ ሰዎች የሠሩት ሥራ ጠቅላላ አንድነትና መድረክን ወደ መለያየት ወስዷል፤›› በማለት ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የሁለቱም ፓርቲ አመራሮች ወደፊት ስለሚያደርጉት የትግል አቅጣጫ የየራሳቸውን ዕቅድ ማዘጋጀታቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ‹‹እኛ ቀድሞውኑ በአፍራሽ መልኩ የመጣውን እንዴት እንደምንቋቋምና እንዴት ትግላችንን በዚህ ጉዳት ምክንያት ሳይዳከም ሊቀጥል እንደሚችል የራሳችንን ሥራ ስንሠራ ስለቆየን ይህን ጉዳይ አሁን እንደ አዲስ አናየውም፡፡ በእኛ በኩል የራሳችንን ትግል በተጠናከረ ሁኔታ እንቀጥልበታለን፤›› በማለት አቶ ጥላሁን ቀጣይ ሥራቸውን ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ አቶ አበበ በበኩላቸው፣ ‹‹መድረክ አንካሳ ነው ያደረገን፡፡ ነገር ግን አንካሳ ሆነን ከምንቀጥል ባለን ነገር ሮጠን ምርጫውን እኛ ባለን መዋቅር ብንጋፈጠው የተሻለ ውጤት እናገኛለን፤›› በማለት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር