ነዳጅ ቀነሰ… ትራንስፖርትስ?

በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ እየቀነሰ ነው፡፡ ካለፉት ሦስት ወራት ወዲህ የታየው የዋጋ ቅናሽ ያልተጠበቀ ነው ተብሏል፡፡ በአሜሪካ መሪነት ኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) ከተባለው ጽንፈኛ ቡድን ጋር እየተደረገ ያለው ፍልሚያ፣ የነዳጅ ዋጋን ያንራል ተብሎ ቢጠበቅም እውነታው ግን የተገላቢጦች ሆኗል፡፡
ከአይኤስ ጋር የሚደረገው ፍልሚያ የዓለም የነዳጅ ዋጋን ያንራል በማለት ከተለያዩ አቅጣጫዎች የተነሰነዘሩ ትንታኔዎች በግምት ቀርተዋል፡፡ አንቱ የተባሉ የኢኮኖሚ ባለሙያዎችና ተቋማት የነዳጅ ዋጋ ይሰቀላል በማለት ሰፊ ትንታኔ የሰጡትም ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ መንገድ ያጋጠሙ ክስተቶችን በመተራስ መሆኑ ይነገራል፡፡ በተለይ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ከወራት በፊት ይፋ እንዳደረገው፣ ከአይኤስ ጋር የሚደረገው ፍልሚያ በዚሁ ከቀጠለ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ አይቀሬ መሆኑን ነበር፡፡ ነገር ግን እንደተገመተው ሳይሆን የነዳጅ ዋጋ ያልተጠበቀ ቅናሽ አሳየና የብዙዎች ግምት እንዳይሰምር አደረገ፡፡
የነዳጅ ዋጋ ሊጨምር ይችላል ሲባል ሊቀንስ የቻለው ደግሞ አሜሪካ ከፍተኛ ነዳጅ በማምረት ወደ ገበያው ማስገባትዋ ስለመሆኑ አንዳንድ መረጃዎች ያለመክታሉ፡፡ ከአይኤስ ጋር በሚደረገው ፍልሚያ ምርታቸውን ይቀንሳሉ የተባሉ አንዳንድ ነዳጅ አምራች አገሮች እንደተጠበቀው ሳይቀንሱ በመቅረታቸውና አሜሪካ ባልተጠበቀ መንገድ ምርቷን መጨመሯ ለነዳጅ ዋጋ መውረድ አንኳር ምክንያት ሆነው ይቀርባሉ፡፡ 
የነዳጅ ገበያ ተለዋዋጭ ባህሪይ ያለው ነው፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት የታየው ቅናሽ እስከመቼ ይቀጥል ይሆን? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ቢያስቸግርም፣  ሰሞናዊው የነዳጅ ዋጋ ቅናሽ በተለይ ለነዳጅ ግዥ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለሚያወጡ አገሮች መጠነኛ እፎይታ የሰጠ ነው፡፡ የነዳጅ ዋጋ መጨመርና መቀነስ በየትኛውም አገር ኢኮኖሚ ውስጥ የሚፈጥረው አሉታዊና አውንታዊ ተፅዕኖ ቀላል ባለመሆኑ፣ ከጥቂት ወራት ወዲህ ዋጋው መቀነሱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን አበራክቷል ማለት ይቻላል፡፡ 
ወቅታዊውን የዓለም የነዳጅ ዋጋ ከአገራችን አንፃር ስንመለከት ግን ነገሩ ብዥታን ይፈጥራል፡፡ የነዳጅ ዋጋ በዓለም ገበያ እየቀነሰ ነው መባል ከጀመረበት ጊዜ ወዲህ በአገር ውስጥም የነዳጅ ዋጋ ይቀንሳል የሚል እምነት በማሳደሩ፣ የነዳጅ የችርቻሮ ዋጋ ለምን አይቀንስም እየተባለ ሲጠየቅም ነበር፡፡ የዓለምን ዋጋ ሁኔታ እያየ የሦስት ወሩን አማካይ በመውሰድ የነዳጅ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋዎችን ይፋ ማድረግ የሚጠበቅበት የመንግሥት መሥሪያ ቤት፣ የነዳጅ ዋጋ ስለቀነሰ የአገር ውስጥ የመሸጫ ዋጋ ላይ ቅናሽ ማድረጉን ዘግይቶ ያሳወቀው ግን ባለፈው ሳምንት ነው፡፡ የተወሰነ ማስተካከያ መደረጉም መልካም ነው፡፡
ባለፈው ሳምንት የተደረገው የዋጋ ማስተካከያ በእግርጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ በቀነሰበት ልክ ወይም በተመጣጣኝ የዋጋ ልክ ቅናሽ ተደርጓል ወይ የሚለው ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ ባለፈው ሳምንት አንድ ሊትር ናፍጣ የዘጠና ሳንቲም ቅናሽ ተደርጎበት 18.09 ብር እንዲሸጥ ተወስኗል፡፡ ቤንዚንም ቅናሽ ተደርጎበት የአንድ ሊትር የመሸጫ ዋጋ ወደ 19.95 ብር ወርዶ እየተሸጠ ነው፡፡
የዋጋ ማስተካከያው ከጥቅምት 29 እስከ ኅዳር 30 የሚቆይ ነው፡፡ የዋጋ ቅናሹን ተከትሎ ብዙ የሚጠበቁ ነገሮች አሉ፡፡ የትራንስፖርት ዋጋን በምሳሌነት እንውሰድ፡፡ እንደሚታወቀው የነዳጅ ዋጋ ቀነሰ ሲባል የትራንስፖርት ታሪፍም ተስተካክሎ እንደሚቀንስ ይጠበቃል፡፡ ከዚህ ቀደም በነዳጅ ጨመረ ሰበብ ዋጋቸው የናሩ ምርቶችና አገልግሎቶች ሊቀንሱ ይገባል ነበር፡፡ ነገር ግን የሰሞኑን የነዳጅ ዋጋ ቅናሽ ተከትሎ የትራንስፖርት ዋጋ አልተስተካከለም፡፡ የሸቀጦች ዋጋም ለውጥ አልታየበትም፡፡  የሸቀጦች ዋጋ ከዚህ በኋላ ባሉት ቀናት ሊቀንስ ይችላል ተብሎ ሊታሰብ ይችላል፡፡ ነገር ግን የትራንስፖርት ዋጋ አለመስተካከሉ አስገራሚ ነው፡፡  
በቀደሙት ልምዶች የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ሲደረግ፣ የሸቀጥና የአገልግሎ ዋጋዎች ተከትለው ይጨምራሉ፡፡ የነዳጅ መቀነስ ሲሰማ ጭማሪ ለማድረግ የሚታየውን ያህል ጥድፊያ በቅናሹ ላይ አይታይም፡፡ ይህ በተደጋጋሚ ስንመለከት የቆየነው ቢሆንም ከሰሞናዊው የነዳጅ ዋጋ ቅናሽ ጋር ተያይዞ የትራንስፖርት ዋጋ ያለመቀነሱ ነገር ግራ ማጋባቱ አልቀረም፡፡ 
የነዳጅ ዋጋ ቅናሹን ተከትሎ በተለቀቀው የሕዝብ ማስታወቂያ ላይ፣ የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያ መደረጉን እንጂ ይህንን ተከትሎ የትራንስፖርት አገልግሎት ታሪፍ ምን ያህል እንደተደረገ የሚገልጽ ነገር የለም፡፡ ከዚህ ቀደም የነበሩ ልምዶች እንደሚያሳዩን ግን ከነዳጅ ዋጋ ጭማሪም ሆነ ቅናሽ ጎን ለጎን የትራንስፖርት ታሪፍ አብሮ ይገለጽ ነበር፡፡ አሁን ለምን እንዳልተደረገ መንግሥት ማብራሪያ ሊሰጥበት ይገባል፡፡ የተደረገውን የዋጋ ቅናሽ የትራንስፖርት ታሪፍን ለማስተካከል ብቁ አይደለም ከተባለም ከነምክንያቱ ቢገለጽ አይከፋም፡፡ በነዳጅ ዋጋ ጨመረ ሰበብ ዋጋ የሚጨምርበት ሸማችና ተገልጋይ ነዳጅ ሲቀንስ ሊቀነስለት አይገባም ወይ? የሚለው ጥያቄ መልስ ያሻዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር